የበለፀገ ምግብ ለማኅበረሰብ ጤና

ምግብ ከመሰረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎቶች ውስጥ አንዱ ነው። ያለምግብ የሰው ልጅ ጥቂት ቀናት ሊሰነበት ይችላል እንጂ ሟች ነው። ምግብ ሲባል ግን እንደው በደፈናው የሚረባውንም የማይረባውንም ጨምሮ አይደለም። ከምግብም በላይ ምግብ አለ። የስነ ምግብ ባለሞያዎች እንደሚሉት ከሆነ ትክክለኛ ምግብ የሚባለው ለጤና ተስማሚ፣ ሰውነትን ሊገነባና በሽታ ሊከላከል የሚችል ብሎም በልዩ ልዩ ንጥረ ነገሮች የዳበረ ነው።

ምግብ ከምግብነት ባሻገር የሰው ልጅ ጤና ተጠብቆ እንዲዘልቅ የሚያስችል በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተደርጎ ይሰራበታል። ይህ ማለት ሰዎች ለጤና ተስማሚ የሆኑ ምግቦችን እንዲመገቡ ቁጥጥር ከሚያደርገው የመንግስት አካል ጀምሮ ምግብን አምርተው ለተጠቃሚው እስከሚያደርሱት ድረስ ጠንካራ ስራ ይሰራበታል። እንዲህ በተናበበ መልኩ በምግብ ላይ ልዩ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ሀገራት ደግሞ የዜጎቻቸው ጤና ማስጠበቅ ችለዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ገና በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ለምግብ የሚሰጠው ትኩረት አናሳ ስለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ። በነዚህ ሀገራት ዜጎች በአብዛኛው የሚመገቧቸው ምግቦች በንጥረ ነገር የዳበሩ አይደሉም። ይልቁንም በአብዛኛው በፋብሪካ የተቀነባበሩና የምግብ ይዘታቸው ያለቀለት ምግቦችን ነው የሚመገቡት። ተፈጥሯዊ ምግቦችን የመመገብ ዝንባሌ ቢኖራቸውም ለምግብ ግብአትነት የሚውሉ ምርቶች በውስጣቸው የያዙትን ጠቃሚ ንጥረ ነገር አስቀድመው ስለሚያወጧቸው የተሟላ ምግብ ተመገቡ ለማለት አይቻልም።

በኢትዮጵያም ስንዴ፣ ገብስና ሌሎችንም አዝርት ፈትጎ የመመገብ ዝንባሌ ይታያል። ይህም ጠቃሚ የምግብ ንጥረ ነገሮችን ባለመመገብ ምክንያት በተለያዩ በሽታዎች የመጠቃትና የመቀንጨር ችግሮች ይታያሉ። በቫይታሚንና ሚኒራሎች የበለፀጉ ምግቦችን ባለመመገብ ምክንያት ተማሪዎች በትምህርት ቤት ዝቅተኛ ውጤት ማምጣት፣ ካደጉ በኋላም ምርታማ ያለመሆንና ሌሎችም ተያያዥነት ያላቸው ችግሮች ይገጥሟቸዋል። ይህ ደግሞ በሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የራሱ ተፅእኖ ይኖረዋል።

ለዚህም ነው መንግስት በምግብና በስርዓተ ምግብ ዙሪያ ትኩረት አድርጎ በመስራት ላይ ያለው። የምግብና የስርዓተ ምግብ ፖሊሲም ፀድቆ ወደ ስራ ከገባ ሰንብቷል። በርግጥ በምግብና በስርዓተ ምግብ ላይ ያለው ችግር አሁንም በግልፅ የሚታይ ቢሆንም አበረታች ጅምር ስራዎች በመንግስትና በምግብ ዙሪያ በሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

ወይዘሮ ወገኔ ግርማ ‹‹ቴክኖ ሰርቭ›› በተሰኘና የገበሬዎችን አቅም በልዩ ልዩ መልኩ በመገንባት ጥራት ያለው የግብርና ምርቶችን እንዲያመርቱ በሚያደርግ ድርጅት ውስጥ ምክትል ካንትሪ ዳይሬክተር ሆነው ያገለግላሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፣ ድርጅቱ ስራውን በኢትዮጵያ ከጀመረ አስራ አምስት ዓመታትን አስቆጥሯል። ስራውን የጀመረው በቡና አቅርቦት ሰንሰለት ላይ የነበረ ሲሆን የገበሬውን አቅም በማሳደግ ጥራት ያለው ቡና አምርተው ለተጠቃሚው እንዲያደርሱ አድርጓል። በመቀጠል ደግሞ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ገበሬዎች ጥራት ያለው ምርት አምርተው ለተጠቃሚው እንዲያደርሱ የአቅም ማጎልበቻ ስራዎችን ሰርቷል።

በተጨማሪም በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ደረቅ ቆሻሻዎችን ሰብስቦ ዳግም ጥቅም የሚሰጡበትን ፕሮግራም በማመቻቸት በተለይ ወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል። በፕሮግራሙ እስካሁን ከ5 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሴቶችና ወጣቶች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ድርጅቱ የአቅም ማጎልበት ስራውን የሚያከናውነውም ቡና፣ አትክልትና ፍራፍሬ አብቃይ በሆኑ በሁሉም ክልልች በሚገኙ አካባቢዎች ላይ ነው። አብዛኛዎቹ ድርጅቱ የሚያከናውነው ስራዎችም በዩ ኤስ ኤድ፣ ዩ ኤስ ዲ ኤና ሌሎችም ይደግፉታል።

በምግብ ማቀነባበር ሂደት ደግሞ ድርጅቱ ለአምራቾች የተለያዩ ቴክኒካዊ ድጋፍ ይሰጣል። አምራቾች ድጋፉ ተደርጎላቸው ምን ደረጃ ላይ እንደደረሱ ያለውን ሂደትም ይከታተላል። ይህም ጤናማ የምግብ አመራረት ሂደት እንዲኖርና ዜጎች በንጥረ ነገር የበለፀጉ ምግቦችን እንዲመገቡ ያስችላል። በተዘዋዋሪ ደግሞ እነዚህን ምግቦች በመመገብ ጤናቸውን ለመጠበቅ ያስችላቸዋል።

በቀጣይም ድርጅቱ ለምግብነት የሚውሉ ምርቶች ጥራታቸውን በጠበቀ መልኩ ተመርተው ወደተጠቃሚው እንዲደርሱ ከአርሶ አደሩ ጀምሮ ምግብ አቀነባባሪዎች ድረስ ዘላቂነት ያለው የአቅም ግንባታና የቴክኒክ ድጋፍ ያደርጋል፤ እያደረገም ይገኛል። በተመሳሳይ አርሶ አደሮችና የምግብ ፋብሪካ ባለቤቶች የፋይናንስ ተደራሽነት ኖሯቸው የምግብ ጥራትና ይዘት ላይ እንዲሰሩ ከመንግስት ጋር ሆኖ ይሰራል።

በዚሁ ድርጅት ውስጥ የኒውትሪሽን የኢትዮጵያ ፕሮግራም ማናጀር ሆነው እየሰሩ ያሉት አቶ እያቄም አምሳሉ እንደሚናገሩት፣ በዱቄትና በምግብ ዘይት ውስጥ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች እንዲገቡ ኢትዮጵያ ለፋብሪካዎች ያወጣቸው መስፈርት (ስታንዳርድ) አለ። በዚሁ ስታንዳርድ መሰረት ድርጅቱ ፕሮግራም ዘርግቶ ለፋብሪካዎቹ የቴክኒክ አቅም ግንባታ ድጋፍ ያደርጋል፤ ስልጠናዎችንም ይሰጣል። ምግቡ ከበለፀገ በኋላ ደግሞ ምን ያህል ጠቃሚና ደረጃውን ያሟላ እንደሆነ የላብራቶሪ ፍተሻ ድጋፍ ያደርጋል። በሀገር ውስጥ ያሉ ላብራቶሪዎች የበለፀገውን ምግብ እንዲፈትሹ የአቅም ግንባታ ድጋፍ ይደረግላቸዋል። ከዚህ ባሻገር ድርጅቱ ከመንግስት ባለድርሻ አካላትና ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር ይሰራል።

ለሰዎች ጠቃሚና በምግቦች ውስጥ የሚገኙ ቫይታሚንና ሚኒራሎች አሉ። እነዚህ ቫይታሚኖችና ሚኒራሎች ሰዎች ጤናማ ሕይወት እንዲኖሩ ያስችላሉ። ለልጆች ደግሞ ጤናማና የዳበረ ሰውነት እንዲኖራቸው ይረዳሉ። ይሁንና በአሁኑ ግዜ ምግቦች በደምብ ስላልበለፀጉና እነዚህን ቫይታሚኖችንና ሚኒራሎችን ያሟሉ ስላልሆኑ ሕብረተሰቡ ከነዚህ ምግቦች ላይ የሚያገኘው ጥቅም ዝቅተኛ ነው። ለአብነትም ስንዴ ሲፈጭ ከላይ ያለውና አብዛኛውን ምግብ የያዘው ክፍል ስለሚወገድ የሚፈለገው የምግብ ንጥረ ነገር ለሰዎች አይደርስም።

ይህን ለመተካት የቫይታሚንና ሚኒራል ድብልቆች በምግብ ውስጥ እንዲገቡ የሚያስገድድ ስታንዳንርድ በመንግስት በኩል ወጥቷል። እነዚህን የቫይታሚንና ሚኒራል ድብልቆች በምግብ ውስጥ ለማስገባት ደግሞ እውቀቱ ያስፈልጋል። ስለዚህ መንግስት ባስቀመጠው ስታንዳርድ መሰረት ድርጅቱ የቴክኒክ ድጋፍ ያደርጋል።

በመንግስት በኩል በርካታ ጥናቶችና ምዘናዎች ተካሂደው በምግብ ውስጥ የጎደሉ ንጥረ ነገሮች ምን እንደሆኑና ይህን ተከትሎ ለምን በሽታዎች እንደመጡ ለማየት ተሞክሯል። እነዚህ የምግብ ንጥረነገሮችን በምግብ ውስጥ ማስገባቱ ለሕብረተሰቡ ጤና ወሳኝ እንደሆኑም ተረጋግጧል። በስታንዳርዱ መሰረት በምግቦቹ ውስጥ እነዚህን ጠቃሚ ንጥረነገሮች ለማስገባት አስፈላጊ ግብአቶች አሉ። እነዚህ ግብአቶች በምን ደረጃ ጥራቱን የጠበቀ ምግብ ማምረት እንደሚችሉ በስታንዳርዱ መሰረት ይፈተሻሉ።

ጠቃሚ የምግብ ንጥረ ነገሮች እጥረት እንደ ‹‹ስፓይና ቤፊዳ›› የተባሉና የአከርካሪ አጥንት የሚጎዱ በሽታዎችን እያስከተሉ ይገኛሉ። ይህ በሽታ ደግሞ በአብዛኛው እየጎዳ ያለው ሕፃናትን ነው። በተመሳሳይ መቀንጨርም የዚሁ የበለፀገ ምግብ እጥረት ውጤት ነው። እንደውም የበለፀጉ ምግቦችን አለመመገብ ወይም እጥረት መኖር ድብቁ ረሃብ ይሰኛል። ምክንያቱም ሰዎች ምግብ በልተው የጠገቡ ቢመስላቸውም የተመገቡት ምግብ በቂ ንጥረ ነገሮችን ባለመያዙ እንደተራቡ ስለሚቆጠር ነው። ስትንዳርዱ የወጣውና ይህ ምግብን የማበልፀግ ስራም የተጀመረው ይህን የድብቅ ረሃብ ችግር ለመቅረፍ ነው።

በመንግስት በተሰራ ጥናት ደግሞ በድብቅ ረሃብ ‹‹hidden hunger›› ምክንያት 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በዓመት መንግስት ያጣል። ይህ ገንዘብ ለብዙ ነገር መጠቀም ይቻል ነበር። ስለዚህ መቀንጨርና ሌሎችም ከበለፀጉ ምግቦች እጥረት ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ በሽታዎችን መከላከል የሚቻለው ምግቦችን በማበልፀግና ሰዎች ምግቦቹን በአግባቡ እንዲመገቡ በማድረግ ነው። ለዚህ ደግሞ የምግብ አመራረት ጥራቱና የማበልፀግ ሂደቱ በስታንዳርዱ መሰረት መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል። ስታንዳርዱ ተግባራዊ መሆን የጀመረ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ግን ተግባራዊ መሆን ይጠበቅበታል። ድርጅቱ በዚህ ረገድ ያለውን ስራ እየሰራ የሚገኘውም ክፍተቱን ለመሙላት ነው።

የኢትዮጵያ ምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማእከል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ በቀለ መኩሪያ በበኩላቸው እንደሚሉት በኢትዮጵያ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ችግር በስፋት ይታያል። ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት መቀንጨር በስፋት መታየት ደግሞ ለዚህ ችግር መኖር አንዱ ማሳያ ነው። የሕፃናት መቀንጨር በኢትዮጵያ 39 ከመቶ ደርሷል። ይህም በዋናነት የሚከሰተው በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ችግር ነው።

ከመቀንጨር ባለፈ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት የሚከሰቱ ሌሎች የጤና ችግሮችም አሉ። ለምሳሌ ኒውራል ቲዩብ ዲፌክት /የአከርካሪ አጥንት ጤና መታወክና የራስ ቅል መጠን መጨመር ችግር/ ገና በተወለዱ ሕፃናት ላይ በብዛት እየተከሰቱ መጥተዋል። ይህን ችግር ግን እናቶች በእርግዝና ወቅት ፎሊክ አሲድ በመውሰድ ማስወገድ ይችላሉ።

የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ችግር በጤና ላይ ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይም ከፍተኛ ተፅእኖ እያደረሰ ይገኛል። ከዚህ በፊት የተሰሩ ጥናቶች በተለይ ደግሞ cost of hunger በሚል የተሰራው ጥናት እንደሚጠቁመው ወደ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ሀገሪቱን በተመጣጠነ የምግብ እጥረት ምክንያት ያሳጣታል። የሀገሪቱን 16 ነጥብ 5 ከመቶ ዓመታዊ የተጣራ ገቢ/ጂ ዲ ፒ/ እንደሚያሳጣትም ነው ጥናቱ የሚያመለክተው። በዚህ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት በኢንዱስትሪ አካባቢዎች ምርታማነት ዝቅተኛ እንደሆነም ጥናቱ ያሳያል።

የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በጤናና በኢኮኖሚ መስክ የሚያደርሰው አሉታዊ ተፅእኖ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ በዚህ ላይ ሰፊ ስራ መስራት ያስልጋል። የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በጤናና በኢኮኖሚ ላይ እያስከተለ ያለው ችግር ለመቅረፍ በመንግስት በኩል የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። አንደኛው የምግብ ማበልፅግ ፕሮግራም ሲሆን ይኸው ፕሮግራም ተቀርፆ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስተባባሪነትና በማእከሉ የቴክኒክ አስተባባሪነት እየተሰራበት ይገኛል።

ዋና ስራ አስኪያጁ እንደሚያስረዱት ይህ የምግብ ማበልፀግ ፕሮግራም በሶስት የምግብ ምርቶች ላይ በዋናነት እየተሰራበት ይገኛል። የመጀመሪያው የምግብ ጨው ሲሆን በጨው ውስጥ አዮዲን እንዲጨመር ይደረጋል። ይህም ሕፃናት በእንቅርት፣ በአእምሮ እድገት ውስንነት፣ በሴቶች ላይ ደግሞ በፅንስ ላይ የሚፈጠር ችግርን ለመከላከል ይረዳል። በኢትዮጵያ ጨውን አዮዳይዝ አድርገውና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው ለገበያ የሚያቀርቡ በርካታ ጨው አምራች ፋብሪካዎች አሉ። በነዚህ ፋብሪካዎች አማካኝነት በአብዛኛው አዮዲን ያለበት ጨው ገበያ ላይ እየገባ ነው።

ሁለተኛው ምርት የስንዴ ዱቄት ሲሆን የስንዴ ዱቄትን የሚያመርቱ ከ400 በላይ የሚሆኑ በርካታ ፋብሪካዎች በሀገር ውስጥ አሉ። ስንዴ ሲመረት በአብዛኛው ገለባው ተለይቶ ውስጡ ያለው ተፈጭቶ ለምግብት የሚውለው። አብዛኛው ንጥረ ነገር የሚገኘው ደግሞ በገለባው ላይ ነው። ከዚህ አንፃር ከስንዴው ገለባ የጠፋውን የምግብ ንጥረ ነገር መልሶ በመጨመርና የስንዴውን ዱቄት በማበልፀግ ለተጠቃሚዎች እንዲደርስ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። እንደ ሀገር አስገዳጅ ስታንዳርድ ፀድቆም ወደስራ ተገብቷል። በርካታ ስንዴ ዱቄት አምራች ኢንዱስትሪዎችም በተዘጋጀው ስታንዳርድ መሰረት ወደ ማበልፀግ ስራ እየገቡ ነው።

ሶስተኛው የምግብ ምርት ደግሞ ዘይት ነው። በኢትዮጵያ የምግብ ዘይት የሚያመርቱና ሙሉ ማጣሪያ ያላቸው ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች 34 ደርሰዋል። እነዚህ ኢንዱስትሪዎች ዘይትን ቫይታሚን ‹‹ኤ›› እና ‹‹ዲ›› እያበለፀጉ ማምረት ጀምረዋል። ከ34ቱ ከዘጠኝ በላይ የሚሆኑት በተከታታይ እያመረቱ ይገኛሉ። በቅርቡ ደግሞ ሁሉም ቫይታሚን ‹‹ኤ›› እና ‹‹ዲ›› ያለው ዘይት ማምረት ይጀምራሉ።

ስለዚህ በዚህ የምግብ ማበልፀግ ፕሮግራም የገበታ ጨው፣ የስንዴ ዱቄትና የምግብ ዘይት ናቸው ተመርጠው ስራ እየተሰራባቸው ያለው። እነዚህ የምግብ ምርቶች ተመርጠው እየተሰራባቸው ያለው ካላቸው ተደራሽነትና የተጠቃሜያቸው ብዛት ከፍተኛ ከመሆኑ አኳያ ነው። በቀጣይ ደግሞ እነዚህ ምርቶች በማየት በሌሎች የምግብ ምርቶች ማለትም ስኳር፣ ወተት፣ የበቆሎ ዱቄትና በመሳሰሉት ላይ የምግብ ማበልፀግ ስራ የሚሰራ ይሆናል።

ለዚህ የምግብ ማበልፀግ ፕሮግራም የተለያዩ ፖሊሲዎች ተቀርፀዋል። ከነዚህም ውስጥ የምግብና ስርአተ ምግብ ፖሊሲ በዋናነት የሚጠቀስ ሲሆን ፖሊሲው ፀድቆ ስራ ላይ ውሏል። በተመሳሳይ የምግብ ስትራቴጂም ፀድቆ ስራ ላይ ውሏል። የአምስት ዓመቱ የምግብ ማበልፀግ ስትራቴጂም ተዘጋጅቶ ስራ ላይ ውሏል። እነዚህን ሁሉ በመጠቀም የግሉም ሆነ የመንግስት ሴክተር መስሪያ ቤቱ በጋራ ሆኖ አሁን የሚታየውን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ችግር መፍታትና ሕብረተሰቡ የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ ማድረግ ይጠበቅበታል።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You