ድንበርተኞቹ

እኛ ኢትዮጵያውያን የመሬትና የድንበር ጉዳይን የሕልውና ጥያቄ አድርገን እንወስደዋለን። ለነገሩ አያት ቅድመ አያቶቻችን እፍኝ አፈር ተዘግና ከሀገራችን እንዳትወጣ ሲሉ አይደል ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረጉት። ይህ ጉዳይ ወደ ግለሰቦችም ወርዶ ደም አቃብቷል፡፡

ጎረቤታሞቹ በፍቅር ሲኖሩባት ከነበረች ሰፈራቸው አንዱ በሞት አንዱ በእስር እስኪለዩ ድረስ፤ ያጋጫቸው ከላይ ያነሳሁት የመሬት ጉዳይ እሰኪነሳ ድረስ፤ በሠላም ይኖሩ ነበር፡፡ የኋላ ኋላ ግን ድንበርተኞች ድንበሬን ገፋህ አልገፋሀ በሚል የከፋ ፀብ ውስጥ ገብተዋል። ይህ የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ምክንያት የተነሳው ፀብ ስር ሰዶ ነፍስ እስከመጥፋት አድርሷል የሚለን ከአዲስ አበባ ፖሊስ የተዘጋ መዝገብ ያገኘነው መረጃ ነው።

እርቅን ያልወደደ ከሰይጣን የተዋደደ እንዲሉ አበው እርቅን ጠልተው ቂምን ሰንቀው የሰነበቱት፤ ለሽማግሌ ለያዥ ለገናዥ ያቃቱትን የእነዚህን ሁለት ሰዎች ታሪክ አነሆ ብለናል። መልካም ቆይታ።

የዋሁ ቂመኛ

ጨዋታ የሚወድ ፈገግታ ከፊቱ የማይጠፋ ሰው ነበረ። ነገሮችን ቀለል አደርጎ የመመልከት ተሰጥዖ ያለው ከሁሉ ጋር በሰላም የመኖርን መርሕ የሚከተል አይነት ሰው ነው። ሩህሩህና ለጋስ የሆነው ይህ ሰው ደግነት መለያውም ነበር። ደግነት ሳያንሰው፤ የአንደበቱ ልስላሴ የበርካቶችን ልብ የሚገዛው ይህ ሰው በፀብ ከመጡበት ግን ሰይጣን ራሱ የሚቀናበት እልኸኛ ነበር። አንዴ ነገር ከጀመረ ዳር ሳያደርስ ማቆም የማይወድ ሁለት መልክ ያለው ይህ ግለሰብ የዋህነቱን የሚፈታተን ጉዳይ ገጥሞታል።

ከእንግዳ ተቀባይ ጎረቤቱ ጋር በሠላም፤ በመከባበር ሲኖር የቆየው ይህ ሰው አጥር በጋራ ለማጠር ከተነሱበት ቀን አንስቶ ነገር ሆዱ ገብታል። መሬቷ ከስልሳ ሳንቲ ሜትር ባትበልጥም መደፈሩ መናቁ አያንገበግበው የሚወደውን ጎረቤቱን በክፉ መመለከት ከጀመረ ሰነባብቷል።

ቀን ቀንን ሲጨምር ጥላቸው እየባሰበት ሲሄድ የቅርቡ ሰዎች ነገሩን ትተው በሠላማዊ መንገድ ችግራቸውን እንዲፈቱ ቢለምኗቸውም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው የማይበርድ ጠብ ውስጥ ገብቷል። ይህ ፀብ ስር ሰዶ የሕይወት ዋጋን እስከሚያስከፈል ድረስ ይህ ቂመኛው ሰው ሲወጣና ሲገባ ባላንጣውን በአይነቁራኛ ሲመለከት ቆየቷል።

ባለ ከዘራው

ተግባቢ ነው፤ እንኳን ሰው ወፍ ያለምዳል የሚባል አይነት ሰው። በእድሩም በማኅበራዊ ሕይወትም ዋነኛ ተሳታፊ በሰፈሩ የታወቀ ግለሰብ ነበረ። አንድ ሰው ጎረቤቱ አዲስ ገዝቶ ሲገባ በተለመደው እንግዳ ተቀባይነቱ ተቀብሎ አካባቢውን አላምዶታል።

ቤቱን ሠርቶ እስኪያጠናቅቅ ያለውን የግንባታ መርጃ እቃ ከማበደር አንስቶ በሀሳብም በጉልበትም ሲያግዝ ቆይቷል። ሰው መጋበዝ ማብላት የሚወደው ይህ ሰው ጎረቤቱ ቤቱን ሠርቶ እስኪያጠናቅቅ ድረስ በተመቸው ቀን ሁሉ ምሳ እያሠራ ቡና እያስፈላ ከነሠራተኞቹ ሲንከባከብ ቆይቷል።

ቤቱ ተሠርቶ አልቆ ዙሪያው መታጠር እስኪጀምር ድረስ በጥሩ የወዳጀነት ሰሜት ሁለት ዓመታትን አሳልፈዋል። ልክ አጥሩ መታጠር ሲጀምርና የጋራ ድንበራቸው ላይ ሲደርስ ያለመግባባት ይፈጠራል። ሁለቱም የየራሳቸው ትክክልን ይዘው ቢነሱም እልኻቸው በትክክል ተነጋግረው እንዲግባቡ አላደረጋቸውም ነበር።

በቀላሉ ሊፈቱት የሚችሉትን ችግር በሁለቱም እልኸኝነት የተነሳ መቋጫው መጠፋፋት ሊሆን በቅተዋል። ተነጋገረው ቢስማሙ ለሁለት ተካፍለው ሊጠቀሙበት የሚችሉት መሬት ቢሆነም መነጋገር ባለመፈለጋቸው ምክንያት አንዱን ለሞት አንዱን ለአስር ያበቃ ፀብ አድርገውት አልፈዋል።

ድንበርተኞቹ

በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 አንቆርጫ ዳንሴ ሰፈር ተብሎ ከሚጠራው ሰፈር ቀድሞ የገባው ያሬድ ሰለሞን የተባለው ሰው ነበር። ቦታ ገዝቶ ቤት ሠርቶ መኖር ከጀመረ ከሁለት ዓመታት በኋላ ጉታ ከበደ የተባለ ሰው በቀኝ በኩል ቦታ ገዝቶ ይገባል። በወቅቱ ያሬድ የተባለው ሰው ማከፋያ አጥር ሳይሠራ በመቆየቱና የተነሳ አዲስ የገባውም ሰው ብዙም ሳይጨነቅ የገዛው ቦታ ላይ ግንባታውን ማከናወን ይጀም ራል።

ቀድሞ የገባው ጎረቤቱን በጥሩ ሁኔታ ተቀብሎ ቤቱን ሠርቶ ቤተሰቡን እስኪያስገባ ድረስ በፍቅርና በመተጋገዝ ቆዩ። ግንባታው ተጠናቆ ዙሪያው ታጠሮ ከአቶ ያሬድ ጋር የሚያዋስነው አጥር ለማጠር ተነጋገሩ። የጋራ አጥራቸው በመሆኑም ሁለቱም በጋራ መሠረት አውጥተው የየራሳቸውን ብሎኬት ሊደረድሩ ተስማምተው ለሥራ የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ በሙሉ አቀረቡ።

ቦታው ተለክቶ ሲባጎ ሊዘረጋ ሲል ግን ቀድሞ የገዛው ሰው ̋የኔ ቦታ እዛ ድረስ ነው ̋ ሲል። ይሄኛው ደግሞ ̋እኔ የገዛሁት ቦታው እዚህ ድረስ ነው ̋ በማለት ክርክር ይገጠሙና ሽማግሌ መካከላቸው ገብቶ እንዲዳኛቸው በማለት የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው ሥራውን ያስቆማሉ።

በሽማግሌም ሆነ በተለያዩ መንገዶች ተስማምተው መልካም ጉርብትናቸው እንዲቀጥል በርካታ ጥረቶች ቢደረጉም ተስማምተው ጉዳያቸውን በሠላም ከመጨረስ ይልቅ ፀብን ምርጫቸው አድርገው ሁለቱም በየፊናቸው ይዛዛቱ ጀመር።

የነበረው መከባበርና ፍቅር ጠፍቶ አንዱ ሌላውን ሊያጠፋ የሚዝት ከመዛትም አልፎ አሳቻ ቦታና ጊዜን የሚጠብቅ ሆነ። አጥሩም እንደ ነገሩ በመወታተፉ የተነሳ በወጡ በገቡ ቁጥር ንዴታቸው እየጨመረ በክፉ በመተያየት ለመጠፋፋት መፈላለግ ጀመሩ።

ቀን ደርሶ ተነጋግረው ችግራቸውን ከመፍታት ይልቅ ዱላ መሰናዘርን የመረጠው ያሬድ የተባለው ሰው ሌላውን ድንበረተኛውን ለመግደል አስቦ ሰኔ 19 ቀን 2014 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ሲሆን በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 አንቆርጫ ዳንሴ ሰፈር ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ጉታ ከበደን በነበራቸው ጸብ ምክንያት ቂም በመያዝ ለፀብ ይጋበዛል።

አንድ አንድ ሲባባሉ የቆዩት ሰዎች የያሬድ ንዴት ከፍ በማለቱ የተነሳ በያዘው ከዘራ ዱላ ከኋላ ጭንቅላቱን ደጋግሞ በመምታት ኮብልስቶን ንጣፍ ላይ እንዲወድቅ በማድረግ የራስ ቅሉ አጥንት እንዲሰበር በማድረጉ ጎረቤትዬው ሕይወቱን እንዲያጣ ያደረገው ሲሆን እሱም ማረፊያው እስር ቤት እንዲሆን አድርጎታል።

ተነጋግሮ መፍታት ያልተቻው የመሬት ጉዳይ አንዱን አፈር ውስጥ ሲያስገባ ሌላው ከአፈር በላይ በፀፀት ከቤተሰቡ ተለይቶ እንዲኖር አደረገው።

አካባቢው የደረሱና የሆነውን የተመለከቱ ሰዎች ጉዳዩን ለፖሊስ በማመልከታቸው የተነሳ ፖሊስ በአካባቢው ደረሰ። ሟች ወድቆ ገዳይም በሰዎች ተይዞ ያዙኝ ልቀቁኝ ሲል ይደርሳሉ። አስከሬኑን ለምርመራ ወደ ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል ልከው ገዳዩን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራቸውን ጀመሩ።

የፖሊስ ምርመራ

ፖሊስ ጉዳዩን ከስር መሠረቱ ሲያጣራ መነሻቸው የድንበር ክርክር መሆኑን፤ ወዳጅ ዘመድ ጎረቤት በጉዳዩ ጣልቃ ሊገባ ቢሞከር እንኳን አሻፈረኝ ማለታቸውን፤ ከአንድ ዓመት በላይ በመጠላላት ሲተያዩ መቆየታቸውን ይረዳል። በእለቱም ገዳይ አልሞና አስቦ ሊያጠቃ የሚችልበትን ከዘራ ይዞ መውጣቱን የዓይን አማኞች ለፖሊስ አብራርተዋል።

እለቱ ጭቅጭቅ ያለ ዝናብ የሚዘንበበት ፀሐይ ያልታየበት ቀን ነበር። ሰኔ 19 ቀን 2014 ዓ.ም። ያን እለት ቤቱ ተኝቶ የዋለው ሟች ዝናቡ አረፍ ሲል እግሬን ላፍታታ ብሎ ይወጣል። በግምት ከቀኑ 7፡00 አካባቢ ነበር። የሟችን ከቤት መውጣት የተመለከተው ያሬድ ሰለሞን የተባለው ተከሳሽ ሟችን ለመግደል አስቦ ነበር ከቤቱ ተዘጋጅቶ የወጣው። ቦታው አንቆርጫ ዳንሴ ሰፈር ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ነበር።

ፖሊስ እንደሚለው ቀደም ሲል ከሟች ጉታ ከበደ ጋር በመሬት ጉዳይ በነበራቸው ፀብ ምክንያት ቂም በመያዝ በከዘራ ዱላ ከኋላ ጭንቅላቱን ደጋግሞ በመምታት ኮብልስቶን ንጣፍ ላይ እንዲወድቅ በማድረግ የራስ ቅሉ አጥንት እንዲሰበር በማድረጉ በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ሕይወቱ ያለፈ መሆኑን በመረጃዬ ደርሼበታለሁ ብሏል።

በምርመራውም መሠረት ገዳይ ሆን ብሎ አስቦ የሰው ነፍስ በማጥፋቱ የተነሳ በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 539/1/ሀ/ መሠረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት በከባድ ሰው መግደል ወንጀል ክስ እንዲቀርብበት ይደረጋል።

ፖሊስ የፎረንሲክ ምረመራውን፤ የተከሳሽን የእምነት ክህደት ቃል፤ የአይን እማኞችን ቃል በመቀበል ጉዳዩ በሕግ ፊት ትልቅ ቦታ እንዲሰጠው ያደርጋል ያለውን ማስረጃ በሙሉ አሟልቶ በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ይልካል።

የዐቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝር

በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግም የደረሰውን ማስረጃ በመመልከት በዚህ መልኩ የክስ ዝርዝሩን ያቀርባል።

ያሬድ ሰለሞን የተባለው ተከሳሽ ሰውን ለመግደል አስቦ ሰኔ 19 ቀን 2014 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ሲሆን በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 አንቆርጫ ዳንሴ ሰፈር ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ከሟች ጉታ ከበደ ጋር በመሬት ጉዳይ በነበራቸው ፀብ ምክንያት ቂም በመያዝ በከዘራ ዱላ ከኋላ ጭንቅላቱን ደጋግሞ በመምታት ኮብልስቶን ንጣፍ ላይ እንዲወድቅ በማድረግ የራስ ቅሉ አጥንት እንዲሰበር በማድረጉ በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ሕይወቱ ያለፈ በመሆኑ በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 539/1/ሀ/ መሠረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት በከባድ ሰው መግደል ወንጀል ተከሶ ብይን ይሰጥልኝ ሲል የጠይቃል።

ውሳኔ

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎትም በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶት ነበር።

ተከሳሽ የመከላከያ ምስክር አቅርቦ ያሰማ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ የቀረበበትን ክስ መከላከል ባለመቻሉ ምክንያት ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠትና የቅጣት ውሳኔ ለማሳለፍ ቀን ቆርጧል።

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት በዋለው ችሎት ላይ ተከሳሹን ጥፋተኛ በማለት በ14 ዓመት ከ3 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኗል፡፡

አስመረት ብስራት

 አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You