ማኅበረሰባዊ የለውጥ መሻቶች አንድን ማኅበረሰብ ወደ ቀጣይ የተሻለ የታሪክ ምዕራፍ አሻጋሪ ገፊ ምክንያቶች ስለመሆናቸው የተለያዩ የለውጥ ትርክቶች አመላካች ናቸው። የማኅበረሰብም ቀጣይ ብሩህ ዕጣ ፈንታ በአብዛኛው የሚወሰነው የለውጥ እሳቤዎች በማኅበረሰብ ውስጥ በሚኖራቸው ተቀባይነት እና ተጨባጭ ትግበራ ላይ እንደሆነ ይታመናል ።
የለውጥ ገፊ ምክንያቶች ከዚህም ባለፈ፤ አንድን ማኅበረሰብ እየተገዳደሩት ያሉ ፈተናዎች፤ ወደ ከፋ አደጋ ከመለወጣቸው በፊት፤ ለአደጋዎቹ ወቅትን የሚመጥን ምላሽ እንዲያገኙ የተሻለ እድል የሚፈጥሩ ናቸው፤ አዳዲስ አስተሳሰቦች በማኅበረሰብ ውስጥ ስፍራ አግኝተው ማኅበራዊ መሠረት እንዲኖራቸውም አዎንታዊ አስተዋፅዖቸውም ከፍ ያለ ነው።
ከዚህ በተጻራሪ ለውጥ እና የለውጥ መነቃቃቶች በጥንቃቄና በሰከነ መንፈስ፤ በጥበብ ካልተመሩ፤ በለውጥ ወቅት በሚፈጠሩ ግርግሮች ተጠልፈው የጥፋት ምንጭ መሆናቸው፤ ከለውጡ ብዙ በመጠበቅ ተስፈኛ የሆነውን ማኅበረሰብ ያልተጠበቀ አላስፈላጊ ዋጋ በማስከፈል የኋልዮሽ ጉዞ ውስጥ እንዲገባ ማድረጋቸው የማይቀር ነው።
በተለይም የለውጥ ጉዳይ የሞት ሽረት በሚሆንባቸው እንደኛ ዓይነት ማኅበረሰብ ውስጥ፤ ለውጥን ከፍ ባለ ጥንቃቄና የኃላፊነት መንፈስ መምራት ካልተቻለ፤ ሊያስከትል የሚችለው ጥፋት፤ ለሀገራቱ ሕዝቦች “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው የከፋ ነው። ማኅበራዊ ሕልውናቸውን አደጋ ውስ ጥ እንደሚጨምረውም ይታመናል።
በአንድ በኩል ለለውጡ ገፊ ምክንያቶች ፈጣን ምላሽ የሚፈልገው የማኅበረሰቡ መሻት፤ በሌላ በኩል በለውጡ ወቅት የሚፈጠሩ የተለያዩ ውጪያዊና ውስጣዊ ፍላጎቶች የሚፈጥሩት ግራ መጋባቶች ለውጡ ተፈጥሯዊ ጉዞውን እንዳይጓዝ ያደርጉታል። በብዙ መንገጫገጮች እና ፈተናዎች ውስጥ አልፎ እንዲሄድም ያስገድዱታል።
ለዚህ በዓረቡ ዓለም “በፀደይ አብዮት“ ስም ተጀምሮ የነበረው የዓረቡ ዓለም ሕዝቦች የለውጥ መሻት የፈጠረው መነቃቃት እና ያስከተለው ጥፋት የአደባባይ ሚስጥር ነው። የሕዝቡን የለውጥ መሻት ተከትለው የተፈጠሩ የተለያዩ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ፍላጎቶች የሀገራትን ሀገረ መንግሥታት በማፍረስ፤ እንደ ሀገር ያላቸውን ሕልውና ጥያቄ ውስጥ ከትተው አልፈዋል።
እነዚህን ፈተናዎችን ተሻግሮ ለውጡ ስኬታማ እንዲሆን ከሁሉም በላይ በለውጡ ኃይል ላይ ያለው ኃላፊነት ከፍያለ እንደሆነ ይታመናል። የለውጡን ገፊ ምክንያቶች በተጨባጭ አውቆ ምላሽ የሚያገኙበትን መንገድ ማፈላለግ፤ በዚህ መንገድ ውስጥ መላው ሕዝብ ተጓዥ ሆኖ የሚንቀሳቀስበትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ አስተውሎቶችን መፍጠር ይጠበቅበታል።
እነዚህ አስተውሎዎች መላው ሕዝብ የለውጡን ትሩፋቶች እጁን አጣምሮ ከመጠበቅ ወጥቶ የለውጡም፤ የትሩፋቶቹም ባለቤት የሚሆንበትን ዕድል የሚፈጥር፤ ለውጡ እንዳይቀለበስ ጠንካራ መሠረት እንዲኖረው፤ ቀጣይ ፍጥረታዊ ጉዞውንም ያለ ብዙ መንገጫገጭ ተጉዞ የማኅበረሰቡን የመለወጥ መሻት እውን ማድረግ የሚያስችል ነው።
ከዚህ አንፃር የለውጥ ኃይሉም ሆነ፤ በለውጡ ጎራ ወደውና ፈቅደው ለውጡ በፈጠረው መነቃቃት የለውጥ ኃይል ሆነው የተሰለፉ ኃይሎች፤ ከሁሉም በላይ ለውጡ ሊያጋጥመው የሚችሉ ተገማች እና ተገማች ያልሆኑ ተግዳሮቶችን ቀድመው በማወቅ፤ በኅብረተሰብ ውስጥ ተገቢውን ግንዛቤ መፍጠር፤ በዚህም መላው ሕዝብ የለውጡ ኃይል ሆኖ እንዲሰለፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
በተለይም እንደኛ ባሉ ያደሩ የቤት ሥራዎች የለውጥ ዋነኛ ፈተና በሚሆኑበት ማኅበረሰብ ውስጥ፤ መቼም ቢሆን ጠላትነትን የፖለቲካ ዲስኩር አድርገው መጓዝ የሚፈልጉ ታሪካዊ ባላንጣዎች ባለበት ሁኔታ፤ የለውጥ ኃይሉ የሚያጋጥሙትን ችግሮች በስኬት ለመሻገር የማኅበረሰቡን የለውጥ ግንዛቤ ለሚያሰፉ ሥራዎች ቅድሚያ ሰጥቶ በተደራጀ መንገድ መሥራት፤ ለዚህ የሚሆን ዝግጁነትና ቁርጠኝነት መፍጠር ይጠበቅበታል።
ከዚህ አንጻር ላለፉት አምስት የለውጥ ዓመታት፤ የለውጥ ኃይሉ የለውጥ ፍላጎቶችን በመረዳት ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ፤ ሀገራዊ የለውጥ መሻቶች ተጨባጭ ተስፋ የሚሆኑበትን ስትራቴጂ ቀይሶ ተንቀሳቅሷል። ከዚህ ቀደሞ ከነበሩ ለውጦች የተሻለ ሀገራዊ ትሩፋት ይዞ እንዲመጣም፤ አዲስ የፖለቲካ ባሕል ለማስተዋወቅ ረጅም ርቀት ተጉዟል።
ችግሮችን በእርቅና በመደመር መንፈስ፤ ልዩነቶችን በንግግር እና በውይይት ለመፍታት የለውጡ ኃይል የሄደበት አዲስ የፖለቲካ መንገድ፤ ለውጡ በሕዝቡ ውስጥ በብዙ ተስፋ እንዲጠበቅ አድርጎታል። የዚያኑ ያህልም እንደ ሀገር ይዘነው ከመጣነው አሮጌ የፖለቲካ ባሕል /የሴራ ፖለቲካ/ አኳያ ለብዙ ፈተናዎች እንዲጋለጥ፤ ብዙ መንገጫገጮችን እንዲያስተናግድም አድርጎታል።
ለውጡ የፈጠረው ሀገራዊ መነቃቃት ያሳሰባቸው፤ ከትናንቶች ወጥተን ዛሬዎቻችንን የራሳችን እንዳናደርግ፤ ከዚያም አልፈን ነገዎቻችንን ተስፋ አድርገን እንዳንጓዝ የሚፈልጉ የውስጥና የውጪ ጠላቶቻችን ለውጡን እና የለውጥ ኃይል በብዙ ተፈታትነውታል።
ከፈተናው ክብደት የተነሳም አንዳንዶች ከቆሙበት ተንፏቀው ወደ ኋላ አፈግፍገዋል፤ ሌሎች በለውጡ በራሱ ላይ ጠላት ሆነው የሕዝባችንን የዘመናት በልማት የመለወጥ መሻት ለማደናቀፍ በአደባባይ ባልተገባ ባሕሪ፣ የጥፋት ሴራና ተልዕኮ ተሞልተው ታይተዋል።
የሀገርን ሕልውና ሳይቀር ፈተና ላይ በጣለው በዚህ የለውጥ ፈተና ውስጥ በተግባር ነጥረው የወጡት የለውጡ ኃይሎች፣ ሀገርን ከመበተን ስጋት ከመታደግ ባለፈ፤ ለውጡ በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲቆም አድርገዋል። ነገዎቻችን ብሩህ የሚሆኑበትን ሀገራዊ ዓውድ መፍጠር ችለዋል ።
ለውጡን እና የለውጡ የፈጠረውን ሀገራዊ መነቃቃቶች በጥንቃቄና በሰከነ መንፈስ፤ በጥበብ በመምራት፤ ለውጡ በለውጥ ወቅት በሚፈጠሩ ግርግሮች ተጠልፈው እንዳይወድቅ በማድረግ የለውጥ ኃይሉ ለሰጠው ታሪካዊ አመራር እውቅና ሊሰጠውና ሊበረታታ ይገባል!
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 4 ቀን 2016 ዓ.ም