የምሥራቅዋ ንግሥት እየተባለች የምትወደሰው ድሬዳዋ ከኢትዮጵያ ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች አንዷ መሆኗ ይታወቃል። ከባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት መጀመር ታሪክ ጋርም ተያይዞ ስሟ ይነሳል። እስከ ጅቡቲ የተዘረጋው የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ሲጀምር በከተማዋ ውስጥ የተቋቋመው የኢትዮጵያና የጅቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት የከተማዋን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ ያነቃቃ እንደነበር አይዘነጋም። ይህም የንግድ እንቅስቃሴ ማዕከል እንድትሆን አስችሏታል።
በንግድ እንቅስቃሴ መታወቋ ደግሞ ከተለያየ የኢትዮጵያ ክፍል ወደ ከተማዋ የሚሄደው ሰው እንዲጨምር አድርጓል። ከድሬዋ እየሸመቱ ወደአካባቢያቸው ወስደው የሚሸጡ ሰዎች ጥቂት አልነበሩም።
ድሬደዋ አስተዳደር እንዲህ በተለያየ ታሪክ እንደምትታወቀው ሁሉ፤ በከተማዋ በከፍተኛ ሁኔታ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር እንዳለባትም አብዝቶ ይነሳል። በቧንቧ መስመር ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳትም ከፍተኛ ወጪ በማስከተል ተጨማሪ ተግዳሮት ሆኗል። አካባቢው ላይ እየተስተዋለ ያለውን ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትም ሆነ፣ ከፍተኛ ወጪ እያስከተለ ያለው በቧንቧ መስመር ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመፍታት ምን እየተሰራ ነው? ስንል ጥያቄ እቅርበናል።
በዚሁ ዙሪያ በድሬደዋ አስተዳደር የውሃ አቅርቦትና ስርጭት ዳይሬክተር ኢንጂነር ረመዳን ሙሳ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተውናል፤ መልካም ንባብ።
አዲስዘመን፤ የድሬደዋ አስተዳደር የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር እንዴት ይገለጻል? አሁን ላይ ያለው የውሃ ሽፋን ምን ያህል ነው?
ኢንጂነር ረመዳን፤ የውሃ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ነው። የተፋሰስ ልማት ሥራ በተጠናከረ ሁኔታ ካልተሰራ ችግሩ እየተባባሰ መሄዱ አይቀርም። ቀደም ባሉት ጊዜያቶች ሁለት መቶና ሶስት መቶ ሜትር ተቆፍሮ ውሃ ይገኝ ነበር። አሁን ላይ እስከ አምስት መቶ ሜትር ድረስ ጥልቀት መቆፈር ይጠበቃል። ይሄ በጣም ኣሳሳቢ ነው።
በአሁኑ ጊዜ ለሐረር ውሃ እየቀረበ ያለው ከድሬደዋ አስተዳደር ነው። ሐረርን የገጠማት ችግር ድሬደዋ አስተዳደርን እንዳይገጥማት ምን ማድረግ አለብን የሚለው መታሰብ አለበት። እየታየ ያለውን ችግር ታሳቢ ያደረገ የጥናት ሥራዎች ተጀምረዋል። አሁን ላይ ሥራዎች እየተሰሩ ያሉት ያሉንን የውሃ መገኛዎችን በአግባቡ በመያዝ ተደራሽነቱንም ፍትሀዊ ለማድረግ ነው ጥረት እየተደረገ ያለው።
ለውሃ እጥረቱ ሌላው ተግዳሮት እየሆነ ያለው፤ ካልሼም ባይካርቦኔት ወይንም ጨው ነው። ይሄ ጨው የውሃ መተላለፊያዎችን ቧንቧ በመዝጋት ጉዳት እያስከተለ ነው። በዚህ የተነሳ ውሃ ማዳረስ የማይቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል። መስመሮቹ በጨው ስለሚበሉ አንዳንዴ መስመሩ ተሰብሮ በመፍሰስ ብክነት ያጋጥማል። እንዲህ ያለው ችግር ሲያጋጥም ሐረር ላይም እጥረቱ በተመሳሳይ ይከሰታል። ምንጫችን አንድ በመሆኑ ችግሩ ይሰፋል። የጨው ክምችቱ እየጨመረ ሲሄድ በስርጭቱ ላይ የአንድ ቀን ልዩነት እንዲፈጠር ያደርጋል።
ችግሩ በቀላሉ የሚነገር አይደለም። ከውሃ እጥረቱ በላይ በጨው ምክንያት የሚስተጓጎለው እየበለጠ ችግር እየሆነ ነው። በጨው ምክንያት አስተዳደሩ ለከፍተኛ ወጭ እየተዳረገ ነው። በየዓመቱ ቢያንስ ወደ 20ኪሎ ሜትር የውሃ ማስተላለፊያ መሥመር ይቀየራል።
በአጠቃላይ ተቋሙ እየሰጠ ባለው ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት የተጠቃሚውን ፍላጎት አሟልቷል ብሎ አያምንም። በተቀመጠው ዲዛይን ሙሉ ለሙሉ እያቀረብን አይደለም። ክፍተት አለ። ከንግድ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ወደ ከተማዋ የሚመጣው ሰው ቁጥር ከፍተኛ ነው። የሰው ፍሰቱም ያለውን ውሃ ስለሚሻማ ለእጥረቱ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አለው። አቅርቦትና ፍላጎትን ለማጣጣም ባይቻልም አሁን ላይ እንደመፍትሄ ተወስዶ እየተሰራ ያለው በፈረቃ አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ ነው።
አሁን ባለው መረጃ የድርጅቱ ደንበኞች ወደ 49ሺ ይሆናሉ። አገልግሎቱም ተደራሽ እየሆነ ያለው ለዘጠኝ የከተማ ቀበሌና በመካከል ላይ ለሚያልፉ የገጠር ቀበሌዎች ነው። እነዚህ ከተቋሙ ጋር ውል ገብተው ወርሃዊ ክፍያ እየከፈሉ የሚጠቀሙና ተቋሙም በደንበኝነት የያዛቸው እንጂ አገልግሎቱን ከሚያገኙት በመግዛትና በተለያየ መንገድ የሚጠቀመው ተገልጋይ ቁጥር ከፍተኛ ነው። በቤተሰብ በአማካይ በሚወሰድ ስሌት እንኳን እስከ 300ሺ ሰው አገልግሎት እንደሚፈልግ ይገመታል።
ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ያለውን መረጃ ብንወስድ እንኳን ከነፃ ንግድ ቀጣና እና ከተለያዩ ነገሮች ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ወደ ድሬደዋ ፈልሷል። እነዚህ ሁሉ የተጠቃሚውን ቁጥር የሚጨምሩ በመሆናቸው ትክክለኛውን መረጃ ለመስጠት ያስቸግራል።
በከተማዋ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችም የራሳቸውን ጉድጓድ በመቆፈር የሚጠቀሙ ቢሆኑም፤ ከቀጥታ መስመር አገልግሎት ይፈልጋሉ። የከተማ አስተዳደሩ ኢንዱስትሪ መንደር ለሚባሉት ግን ተደራሽ እየሆነ ያለው በሥራ ላይ ባለው ፕሮጀክት ነው።
የድሬደዋ አስተዳደርን ከሌሎች አካባቢዎች ለየት የሚያደርገው፤ የከተማና የገጠር ወረዳዎች አሏት። ይህ ተቋም በአብዛኛው አገልግሎት እየሰጠ ያለው ከተማ ውስጥ ቢሆንም ውሃ በሚገኝባቸው የገጠር አካባቢዎችም ተደራሽ ያደርጋል። አገልግሎቱ የሚሰጥባቸውን አካባቢዎች በጥናት በመለየት ክለሳ ለማድረግ ሥራ ተጀምሯል።
አዲስዘመን፤ -ታዲያ ችሩን ለማስወገድ ምን ታስቧል ?
ኢንጂነር ረመዳን፤– በተለይ የጨው ክምችቱ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር እየሰራን ነው። በአካባቢያችን ያሉት ዩኒቨርሲቲዎች ድሬደዋና ሐረማያ ናቸው። እነርሱም በግላቸው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንደተጠበቀ ሆኖ በቅንጅት ሆነን የምንሰራቸው ሥራዎችም አሉ።
አንዳንዴ ግን ችግሮችን የምንፈታበት መንገድ ከአቅም በላይ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ አለ። የጥናት ሥራ ከሆነ በዚህ በኩል ችግር የለም። በተለያየ ጊዜ ጥናት ተደርጓል። ለምሳሌ ጨውን ለማከም ጥናት ሊካሄድ ይችላል። ወደ ትግበራ ለመቀየር ደግሞ ከፍተኛ መጠን ያለው በጀት ይፈልጋል። ይሄን ለማሟላት ደግሞ አቅም ይጠይቃል።
ችግሮች ከታወቁ መፍትሄ ስለማይጠፋ ችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋርም ሆነ ከአንዳንድ ባለድርሻ አካላት ጋር ሥራዎችን መሥራት አልተቋረጠም። በአማካሪ ድርጅቶች የጥናት ሥራም ጎን ለጎን ማካሄድ ያስፈለገውም መፍትሄ ለማምጣት ነው። ድሬደዋ ለሚቀጥሉት ዓመታት ውሃ ከየት ነው የምታገኘው? ከተገኘስ በኋላ ምንድነው የምናደርገው ? የሚለውን ነው ጥናቱ የሚዳስሰው።
አዲስ ዘመን፤ -አሁን ላይ በቀን ምን ያህል ሜትሪክ ኩዩብ ንጹ የመጠጥ ውሃ ለተጠቃሚው እየቀረበ ነው?
ኢንጂነር ረመዳን፤- በርግጥ አንዳንዴ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት መቆራረጥ በራሱ የሚያሳድረው ተጽእኖም አለ። አቅርቦቱን በመመዝገብ ነው የጀመርነው። በሶስት ሳይቶች (አቅጣጫዎች) ላይ ለመከታተል በተደረገው ጥረት በቀን ከሰባት ሺ እስከ ስምንት ሺ እንዲሁም ከአምስት ሺ እስከ ስድስት ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ የማምረት አቅም ያላቸው ዞኖች መኖራቸው ተረጋግጧል።
እነዚህ በክትትል የተረጋገጡ ናቸው። ሌሎች ታሳቢ ያልተደረጉ ጉድጓዶች ግን አሉ። የእሳት አደጋን ለመከላከል የሚውል የውሃ መጠንን ጭምር ማወቅ ያስፈልጋል። በአጠቃላይ የተሟላ መረጃ ከተሰበሰበ በኋላ በቀን ምን ያህል ሜትሪክ ውሃ መንጭቶ ጥቅም ላይ እንደሚውል ማወቅ ይቻላል። በወር ውስጥ ግን እስከ አንድ ሚሊየን ሜትር ኪዩቢክ ውሃ ይመረታል። ታሳቢ ያልተደረጉት ሲጨመሩ ግን ቁጥሩ ከፍ ይላል።
አዲስ ዘመን፤ ከመሠረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት ጋር በመናበብ ያለመሥራት እንደ ችግር ይነሳል፤ ይህን ችግር ለማስወገድ ምን እየሰራችሁ ነው ?
ኢንጂነር ረመዳን፤ በቅንጅት እየተናበቡ መሥራት ለመሠረተ ልማት ሥራ ወሳኝ ነው። በቅንጅት ሲሰራ የሀብት ብክነትን ያስቀራል። ይህን ታሳቢ በማድረግ በአዳዲስ ፕሮጀክት ሥራዎች ላይ ለመተግበር ጥረት ተደርጓል። በነባር ፕሮጀክቶች ላይ ግን አሁንም መቅረፍ አልተቻለም። የውሃ መስመር በተዘረጋበት ላይ የአስፓልት ሥራ ይሰራል። የኮብል ስቶን ንጣፍ የሌላቸው አካባቢዎች ላይ አዲስ ሥራ ይሰራል። እነዚህ አካባቢዎች የውሃ መሥመር የተዘረጋባቸው ስለሆኑ የውሃ መስመር ፍንዳታ ሲያጋጥም እንደ ገና መጠገን ወይም አዲስ መስራት ያስፈልጋል።
ይሄ ከፍተኛ የሆነ የሀብት ብክነት ያስከትላል። አሁን ላይ ግን መሠረተ ልማቱን የሚያከናውኑ ተቋማት ለባለ ድርሻ አካላት ቀድሞ በማሳወቅ ችግሩን ለመቀነስ ጥረት እየተደረገ ነው።
ቀድሞ እንዲያውቁት ሳይደረግ ወደ ሥራ አይገባም። ሁሉም በዘፈቀደ የየራሱን ሥራ ለመሥራት አይነሳም። ይሄ ትልቅ መሻሻል ነው። እንደ አስተዳደርም መሠረተ ልማትን የሚያቀናጅ እንዲሁም ሁሉም ዓመታዊ እቅዳቸውን በፊርማ የሚያሳውቁበት የአሰራር ሥርዓት ተዘርግቷል። የተዘረጋውን የአሰራር ሥርዓት አጠናክሮ መቀጠል ከተቻለ ችግሮች ቀስ በቀስ እየተቀረፉና ትክክለኛውንም መሥመር እየያዙ ይሄዳሉ።
አሁን ላይ በውሃ መሠረተ ልማት በብዛት እየተቆፈረ ያለው ከካልሼም ባይካርቦኔት ወይንም ከጨው ጋር በተያያዘ ችግር ነው። ምክንያቱም ጥገና ካልተደረገ የውሃ ብከነት ይከሰታል። ተጠቃሚዎችም ተገቢውን አገልግሎት አያገኙም።
አዲስ ዘመን፤ ማኅበረሰቡ ለመጠጥና ለተለያየ አገልግሎት ተመሳሳይ የሆነ ውሃ ከመጠቀም ቢቆጠብ ብክነትን መቀነስና በበቂ ሁኔታም ማግኘት እንደሚቻል የውሃ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ምክረሀሳብ ይሰጣሉ። እዚህ ላይ የተሰራ ሥራ ካለ እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ ሥራ ላይ የተከናወነ ተግባር ካለ ቢገልጹልን ?
ኢንጂነር ረመዳን፤ ከብክነት አንጻር ሁለት ነገሮችን ማየት ይቻላል። አንዱ ሕዝቡ አውቆ የሚያባክነው ነው። ሌላው ከእውቀት ማነስ የሚፈጠረው ነው። ለመጠጥ ሊውል የሚችል ውሃ ለመኪና እጥበትና ለተለያዩ አገልግሎቶች ሲውል ይስተዋላል።እነዚህን ክፍተቶች በመልሶ መጠቀም መፍታት ይቻላል። መልሰን ጥቅም ላይ ልናውላቸው የሚችሉ ሀብቶችን በቸልታ እያለፍናቸው በመሆኑ ነው እንዲህ ያሉ ክፍተቶች የተፈጠሩት።
በተለያየ ምክንያት በሚያጋጥም ብልሽት አላግባብ ውሃ ሲፈስ አይቶ የማለፍ ሁኔታም ሌላው ችግር ነው። ይሄ ተቆርቋሪነት አለመኖርን ያሳያል። ለሚመለከተው አካል መረጃ ሰጥቶ ብክነትን መታደግ ሲቻል በምንቸገረኝና በቸልተኝነት ይታለፋል። ዞሮ ዞሮ ግን ጉዳቱ የተገልጋዩ ነው። የውሃ እጥረቱን የበለጠ እንደሚያባብሰው መገንዘብ ያስፈልጋል።
አንድ ሰው በቀን እስከ 80ሊትር ውሃ መጠቀም እንዳለበት የውሃ ፖሊሲ ይገልጻል። አሁን ባለው መወቅታዊ መረጃ ግን አንድ ሰው መጠቀም ካለበት የውሃ መጠን በላይ እየተጠቀመ ነው። ይሄም አኗኗሩ ያመጣው ለውጥና የከተማ ማደግ ነው። የመፀዳጃ ቤት አጠቃቀም በመቀየሩ ቆሻሻውን ለማውረድ ውሃ ይለቀቃል። የሚለቀቀው የውሃ መጠን ደግሞ ከፍተኛ ነው።
ከደንበኞች ጋር በዓመት ሁለቴ የምንገናኝበትን ፎረም አዘጋጅተናል። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ግንኙነቱ ወደ ሶስቴ ሊሆን ይችላል። ደንበኞች በአሰራር ላይ ሀሳብ አስተያየት እንዲሰጡ የሥራ አፈጻፀምና እቅድ ይቀርባል። በተጨማሪም ከእነርሱ የሚጠበቀውን ግዴታና ኃላፊነት የማስገንዘብና የተሟላ መረጃ እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራ ይሰራል።
የአካባቢ ጥበቃ ሥራን በተመለከተ፤ ምንም አያጠያይቅም የዛፍ ችግኞችን በመትከል የአካባቢ ሥነምህዳርን መጠበቅ ያስፈልጋል። መሥሪያቤታችን ከአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በጥምረት ሆኖ እየሰራ ይገኛል። በየዓመቱ በሚከናወነው የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃግብር የዛፍ ችግኝ መትከያ ቦታዎች እየተመረጡ እንዲተከል ይደረጋል።
የአካባቢ ጥበቃ ሥራም እንደ አጠቃላይ የውሃ መሠረተ ልማትን ለማሻሻል ተብሎ እየተደረገ ካለው የጥናት ሥራ ጋር ተካትቶ ይከናወናል። በጥናቱ እንዲመለስ ማድረግ ያስፈለገው የአካባቢ ጥበቃ ሥራው በተለየ ቦታ ላይ ትኩረት እንዲያገኝ ነው። ምክንያቱም የውሃ መገኛ ምንጩ ከድሬደዋ ከተማ ውጭ ቁልቢ አካባቢ ወይንም ሌላ አካባቢ ሊሆን ስለሚችል ነው።
አዲስዘመን፤ የውሃ ቆጣሪ ወይንም መሥመር ማግኘት አንዱ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ ይነሳል። ይህ ሁኔታ እናንተም አጋጥሟችሁ ከሆነ እንዴት እየፈታችሁት ነው?
ኢንጂነር ረመዳን፤ አዲስ ደንበኞች ጥያቄ ስላቀረቡ ብቻ አይስተናገዱም። ቀድመው የሚታዩ ነገሮች አሉ። አንዱ የተቋሙ የአቅም ሁኔታ ነው። ሌላው ደግሞ የቦታ ምቹነት ነው። ከኛ ሪዘርቫየር በላይ ወይንም ተደራሽ በማንሆንበት አካባቢ ጥያቄ ይቀርባል። ይሄን ጥያቄ ብናስተናግድና ደንበኛው ውሃ ማግኘት ባይችል መልሶ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ማንሳቱ አይቀርም። ስለዚህ የቦታ ምቹነት ወሳኝ ነው። ለሚያቀርቡት ጥያቄ መልስ ሳያገኙ የቀሩትም በአብዛኛው ምቹ ባልሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው።
ተቋሙ በሚችለው አቅም አዳዲስ ደንበኞችን እያስተናገደ ይገኛል። ይሁን እንጂ ከተቋሙ አቅም በላይ የሆኑ ችግሮች ሲኖሩ ደንበኞች ረዘም ላለ ጊዜ ሊጠብቁ ይችላሉ። የውሃ ቆጣሪ በግዥ ከውጭ ስለሚመጣ የግዥ አፈፃፀሙ ረዝም ያለ ጊዜ ይወስዳል።
እኛ በየዓመቱ ሶስት ሺ ደንበኞችን ለመቀበል ነው ያቀድነው። ሆኖም ግን የውሃ ቆጣሪው የግዥ መዘግየት በእቅዳችን መሠረት እንዳንፈጽም እያደረገን ነው። በተቻለ መጠን ግን እንዲገዛ የታዘዘው ግዥው ተፈጽሞ እንደደረሰን የደንበኞችን ጥያቄ እንመልሳለን። በያዝነው በጀት ዓመት በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ወደ 700 የሚሆኑ አዲስ ደንበኞችን ማስተናገድ ተችሏል። የተያዘው እቅድና አፈፃፀም የተመጣጠነ አይደለም።
ይህ ሊሆን የቻለው የውሃ ቆጣሪ አቅርቦት በበቂ ሁኔታ ባለመኖሩ ነው። ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የመጣው የደንበኞች ፍላጎትም ጫናው እንዲጨምር አድርጓል። የውሃ ቆጣሪ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ እንደመፍትሄ እየተወሰደ ያለው በሀገር ውስጥ ተመርቶ እንዲቀርብ በማድረግ ነው። መስሪያቤታችንም ይህንን በቦርድ አስወስኗል።
አዲስዘመን፤- አዳዲስ የፕሮጀክት ግንባታዎች ካሉና ለፕሮጀክት ግንባታው የተያዘውን ወጪ፣ መጠኑንም ጨምረው ቢገልጹልን ?
ኢንጂነር ረመዳን፤- ከዚህ ቀደም ከዓለም ባንክ በተገኘ ገንዘብ የተሰራው የውሃ ፕሮጀክት ለነዋሪውም ሆነ ለከተማ አስተዳደሩ ትልቅ እፎይታ የሰጠ መሆኑ ይታወሳል። ከዚህ ፕሮጀክት የተረፈ ወይንም ቀሪ ሥራ ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ቀጥሎበታል። በራስ አቅም መሰራት አለበት ብሎ በመነሳሳት ነው እየሰራ የሚገኘው።
ፕሮጀክቱ ወደ 18 ወራት የሚፈጅ ፕሮጀክት ሲሆን፤ በሚቀጥለው በጀት ዓመት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል። በገንዘብም ወደ አንድ ነጥብ ስድሰት ቢሊየን ብር የሚፈጅ ፕሮጀክት ነው። የዚህ ፕሮጀክት ሥራ ኢንደስትሪ ፓርኮችንም ታሳቢ ያደረገ ሲሆን፤ አጠቃላይ የከተማ አስተዳደሩን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ይፈታል የሚል እምነት የተጣለበት ነው።
አፈጻፀሙም አበረታች ነው። ከዚህ በኋላ ያለው ሥራ የመሥመር ዝርጋታ በመሆኑ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ይጠናቀቃል የሚል እምነት ነው ያለው። የፕሮጀክት ሥራው ከከተማ አስተዳደሩ ወጣ ባለ የገጠር ቀበሌ ውስጥ ነው እየተከናወነ ያለው።
አዲስ ዘመን፤ ከቆሻሻ ፍሳሽ አወጋገድ ጋር ተያይዞ ስላለው አገልግሎት፤አክለውም በሥራ ሂደት በጥንካሬና በክፍተት የሚጠቀሱትን ያንሱልንና በዚሁ ብናጠቃልል
ኢንጂነር ረመዳን፤ የውሃ፣ የቆሻሻ ፍሳሽ አገልግሎቶች ሁለቱም ትላልቅ ተቋማት ናቸው። ንጹህ የመጠጥ ውሃ ደንበኛው ጥያቄ እስኪያቀርብልን ድረስ ጠብቀን የምንሰራው ስራ አይደለም። ሁልጊዜ የኅብረተሰቡን ውሃ ፍላጎት ለማሟላት ጥረት ማድረግን ይጠይቃል። የሚያስተኛ ስራ አይደለም።
የቆሻሻ አወጋገዱም የራሱ የሆኑ ችግሮች ያሉበት ነው።ከቆሻሻ ፍሳሽ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥመን ችግር፤ አንዳንድ መፀዳጃ ቤቶች ሴፍቲ ታንክ ወይንም የቆሻሻ ማስወገጃ የሌላቸው አሉ። የአንዳንዶቹ ደግሞ የመድረቅ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። ይሄ ቆሻሻ ፍሳሹን ለማስወገድ ፈተና ነው የሚሆነው። የቆሻሻ መምጠጫ ወይንም ፓምፕ ላይ ጉዳት ያስከትላል።
በሌላም በኩል በአሰራር ላይም ክፍተቶች አሉ። የመምጠጫዎች የመሳብ አቅም በአግባቡ ሳይፈተሽ ለሥራ ሲወጣ አገልግሎቱ የተሟላ የማይሆንበት ሁኔታ አለ። ይሄም በተቋሙ አገልግሎት ላይ ችግር እያስከተለ በመሆኑ መታየት እንዳለበት ግንዛቤ ተይዟል። አንዳንዴ ደግሞ ጥያቄዎች ሲበዙ አገልግሎቱ የተቀላጠፈ የማይሆንበት ሁኔታ ይፈጠራል።
በዚህ በኩል ወደፊት ይስተካከላል ብለን የምንጠብቀው በዓለም ባንክ የተያዘው የፕሮጀክት እቅድ ነው። የዓለም ባንክ ከሳንቴሽን ጋር ተያይዞ የሚሰራው ፕሮጀክት ልክ እንደ ንጹህ መጠጥ ውሃ ፍሳሽ ቆሻሻም በመስመር እንዲወገድ ማስቻል ነው። የፕሮጀከት ሥራው ጥናት ተጠናቅቆ የጨረታ ሂደት ላይ ነው የሚገኘው። ሥራው በተያዘለት እቅድ ተጠናቅቆ ተግባራዊ ሲሆን፤ ንጹህ መጠጥ ውሃን ለማሰራጨት ግዴታ እንደሆነው ሁሉ የፍሳሽ ቆሻሻንም ለማስወገድ የሚሰጠው አገልግሎት ግዴታ ይሆናል ማለት ነው።
አንድ ቦታ አገልግሎቱ ቢቋረጥ ለምን ተቋረጠ ብሎ መፍትሄ መሰጠት አለበት። የንጹህ መጠጥ ውሃ አሰራር ሂደትን ተከትሎ ይከናወናል። ምክንያቱም አንድ ሰው ውሃ ሲጠቀም 60 እና 70 በመቶ ቆሻሻ ፍሳሽ ሆኖ ነው የሚወገደው። ስለዚህ ነው ትኩረት የተሰጠው። የግንባታ ሥራው በቅርቡ ይጀመራል።
በጥንካሬና በክፍተት እንደተቋም የማነሳው፤ በተለይ በጥንካሬ በኩል ተቋማችን እረፍት የሌለው ነው ማለት ይቻላል። ሰራተኞቻችን የእረፍት ቀን ሳይሉ ከሳምንት እስከ ሳምንት 24 ሰአት ሥራ ላይ ናቸው። ምክንያቱም ያለ ውሃ ምንም ነገር መሥራት ስለማይቻል።
በክፍተትና በተግዳሮት የማነሳው፤ ካልሼም ባይካርቦኔት ወጥንም የጨዋማነት ሁኔታ ትልቁ የተቋሙ ፈተና ነው ማለት ይቻላል። ተቋሙ ገቢ በማያገኝበት ነገር ላይ ነው እየሰራ ያለው። ጨው በሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ወጭ እያወጣ ነው። በኅብረተሰቡ ዘንድ ደግሞ ውሃን ሀብት አድርጎ ያለማየትና በብልሽትና በተለያየ ምክንያት ውሃ ሲፈስ በዝምታ ማለፉ እንደ ክፍተት የማነሳው ነው።
የድሬደዋ አስተዳደር የንጹ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለይቶ የውሃ አቅርቦት ሽፋንን ለማሳደግ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን በማገዝ ቁርጠኛ መሆኑን በተለያዩ ድጋፎቹ ማረጋገጥ ይቻላል። ውሃ ህይወት በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ በተለያየ መንገድ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል የሚል እምነት አለኝ።
በሌላ በኩል በግልም ሆነ በድርጅት ደረጃ በውሃ ዘርፍ ላይ እውቀቱ ላላቸውና ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙ አካላት የድሬዳዋን ውሃ አቅርቦት ችግር ለማቃለል የቻሉትን ሁሉ እገዛ እንዲያደርጉ እገዛ ማድረግ እፈልጋለሁ። እንዲህ ያለው ሀብት ያላቸው በአቅም ግንባታና በተለያየ መልኩ ተቋማዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል እገዛ ቢያደርጉልን ለውጥ ለማምጣት እያደረግን ያለውን እንቅስቃሴ የበለጠ ያጠናክርልናል ብዬ አምናለሁ።
አዲስዘመን፤ ለነበረን ቆይታ እጅግ በጣም እናመሰግናለን።
ኢንጂነር ረመዳን፤ እኔም አመሰግናለሁ።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2016 ዓ.ም