‹‹የሀገራችንን ሰላምና እድገት የምናስጠብቀው የአብሮነት እሴቶቻችንን ስናስቀጥል ነው›› – ሃጂ ሙስጠፋ ናስር የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚ እና የሰላምና ክልሎች ዲያስፖራ ዘርፍ ኃላፊ

ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና የተለያዩ እምነት ተከታዮች ተከባብረውና ተቻችለው የሚኖሩባት ሃገር ናት:: በተለይም ሁሉም በየእምነቱ ሌሎችን በማክበርና በመደገፍም ረገድ ያለው እሴት ከሌላው ዓለም በተለየ ደምቆ የሚታይበት ነው:: በዚህ ረገድ ቤተእምነቶች የጎላ ሚና እንዳላቸው ይታመናል:: ዘንድሮ ለ1445ኛ ጊዜ ለአንድ ወራት ያህል በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ሲካሄድ በቆየው የረመዳን ፆምም ይኸው የመረዳዳትና የመከባበር መልካም እሴት እንደሁልጊዜው ጎልቶ የታየበት ወር ነው::

አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም በዓሉን በማስመልከትና እነዚህ ነባር እሴቶች መቀጠል በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚ እና የሰላም ክልሎችና ዲያስፖራ ዘርፍ ኃላፊ ሃጂ ሙስጠፋን አናግሯል::

አዲስ ዘመን፡- በቅድሚያ ለ14445ኛ ኢድ በዓል እንኳን አደረስዎ እያልን፤ በዚህ አጋጣሚ ለመላው ሙስሊም ማኅበረሰብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላልፉና ውይይታችንን እንጀምር?

ሃጂ ሙስጠፋ፡- እኔም በቅድሚያ መልዕክቴን እንዳስተላልፍ እድሉን ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ፤ ለመላው ሕዝበ ሙስሊም ለረመዳን ፆምና ዘንድሮ ለ1ሺ445ኛ ጊዜ በድምቀት እየተከበረ ላለው የኢድ አልፈጥር በዓል አላህ እንኳን በሰላም አደረሳችሁ ማለት እወዳለሁ:: በዓሉ የሰላም፣ የደስታ፣ የመከባበር፣ የብልፅግና እንዲሆንልን እመኛለሁ:: በዓሉን ስናከብር ዘካ በማውጣት፣ ድሆችን በመደገፍ፣ ደካሞችን በመዘየር፣ የተራቡትን በማብላት፣ የታረዙትን በማልበስ ልናከበር ይገባል:: በሸሪያችን ሱበኸን አላህ ወታላህ ያዘዙን ተግባር በመፈፀም በዓሉን ማሳለፍ አለብን::

ይህንን በዓል ስናከብርና ስንደሰት በጎረቤት የሚኖሩ ማንኛውም አይነት ተከታዮች ልዩነት ሳንፈጥር መላው የሰው ልጆችን ሁሉ እንድንረዳና እንድናስብ ፈጣሪያችን ያዘናል:: ስለዚህ ደካሞችን የጎሳም ሆነ የሃይማኖት ልዩነት ሳንፈጥር በመደገፍ፤ ታመው ሆስፒታል የቀሩትን በመጠየቅ፤ ወህኒ ቤት ያሉትንና አስታዋሽ የሌላቸውን በመደገፍ በዓሉን እንድናሳልፍ በአላህ ስም ጥሪ አደርጋለሁ::

በዓል ሲባል ለ30 ቀን የፆምና ፆማችን ተቀባይነት እንዲኖረው ዱአ (ፀሎት) እያደረግን አላህን የምንማፀንበት እንጂ ጨፍረን አልያም ዘለን የምናሳልፈው አይደለም:: በእስልምና አስተምህሮ እንዳውም ምንም አይነት ለደስታ ሲባል መጠጥ መጠጣት ፈፅሞ የተከለከለ ነው:: በልምድ የምናዘጋጃቸው እንደ ቃሪቦና ኬኔቶ መጠጦች ሳይቀሩ ሰውን ወደሌላ መስመር ይከታሉ ተብሎ ስለሚታሰብ ለእኛ ለሙስሊሞች አይፈቀድልንም:: ከእነዚህ ነገሮች ራሳችን ማቀብ ይገባናል::

በዓል ነው ብለን እየጨፈርንና እየዘለልን እንድናሳልፍ ሳይሆን ጾምና ፀሎታችን እንዲሁም ስራችን በፈጣሪ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል ብለን ከአምላክ ጋር የምንነጋገርበት፤ የምናስብበት፤ ሌሎችን በመደገፍ የምናከብርበት ነው:: ሙስሊሙ ሕብረተሰብ ራሱ ብቻ ከመደሰት ይልቅ አንድ ጉርሻ ለማግኘት ጭንቅ ውስጥ ያለውን የሰው ልጅ እያሰበ እየደገፈ በዓሉን ማሳለፍ አለበት::

በዚህ አጋጣሚ ላነሳው የምወደው ጉዳይ በሀገራችን የነበረው አንዳንድ አላስፈላጊ ግጭቶች፤ የሰው ሕይወት ያለፉባቸው ሁኔታዎች ነበሩ፤ ይህ ሁኔታ አሁንም እንዳይደገም ሙስሊሙ ሕብረተሰብ ዱአ (ፀሎት) ማድረግ አለበት:: አላህ ለሀገራችን ሰላም እንዲሰፍን ፤ ለህዝባችንም መረጋጋት እንዲሰጥ፤ በሀገራችን የነበረውን የኑሮ ውድነት አላህ ወደኋላ መልሶ ዘመኑ የጥጋብ፣ አርሶአደሩ የለፋበት ማሳ ለምልሞና ምርቱን የሚሰበስበት፤ ሁሉም በየዘርፉ ሰርቶ እርካታ የሚያገኝበት ዘመን አላህ እንዲያደርግልን እመኛለሁ::

የሀገራችን ሰላምና እድገት እንዲቀጥል፤ ግጭቶችን አላህ እንዲያበርዳቸው፤ የሰውን ሕይወት የሚነጥቁ ሰዎች አደብ እንዲገዙ ፈጣሪ ልቦና እንዲሰጣቸው መላው ሙስሊም ዱአውን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል እላለሁ::

አዲስ ዘመን፡- ወደኋላ ልመልሶትና የ30 ቀናት የረመዳን ፆምን ሕዝበ ሙስሊሙ ምን በማከናወን እንዳሳለፈ ያስታውሱን?

ሃጂ ሙስጠፋ፡- ባለፈው አንድ ወር ሙሉ መላው የእስልምና እምነት ተከታይ ቅዱስ ቁርዓን እንደሚያዘው በየመስኪዱ ተራዊ ሶላት በመስገድ፤ ዱአ በማድረግና ዘካ በመስጠት ነው ያሳለፈው:: በመላው ሃገሪቱ በሚባል ደረጃ ከአንዳንድ አካባቢዎች በስተቀር ፆሙም ሆነ የሶላት መርሃግብሩ በሰላም ነው ያለፈው:: እርግጥ አልፎ አልፎ አለመግባባቶች ነበሩ፤ ይሁንና ረመዳን ከገባ በኋላ ሁሉም ተቻችሎ ፆሙን እየፆመ፤ ሶላቱን እየሰገደ ነው የቆየው:: በተለይ ኦሮሚያ ክልልና አዲስ አባባ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ጥቂት የሚባሉ አለመግባቶች አጋጥሞ ነበር፤ ሆኖም በሰላማዊ መንገድ እንዲያልቅ ስራ እየተሰራ ነው::

በአጠቃላይ ሕዝበ ሙስሊሙ ማንኛውም አይነት ግጭት ትቶ ወደ እርቅና መረጋጋት እንዲገባ ተደርጓል:: ዘካ የሚሰጡም ባለሃብቶች ለድሆች መንገድ ላይ አስፈጥረው፤ ድሆችን እያበሉ እስካሁን በስኬት ነው የደረስነው:: ከዚህም በኋላ ቢሆን በረመዳን የታየው መልካምነት እንደሚቀጥል ባለሙሉ ተስፋ ነኝ:: ኢን ሻላህ ! እስከአሁን የነበረው ጥቃቅን አለመግባባቶችና ልዩነቶች ወደፊትም በመቻቻል ይቀጥላል ብዬ አምናለሁ::

አዲስ ዘመን፡- በእስልምና አስተምህሮ ኢድ ማለት ምን ማለት ነው? በእለቱስ ምን ምን ተግባራት ይፈፀማሉ?

ሃጂ ሙስጠፋ፡– በእርግጥ ይሄንን ጥያቄ ከእኔ ይልቅ ኡላማዎች ቢመልሱት የተሻለ ነው፤ ሆኖም እንደ አንድ የሃይማኖት አባት እንደምረዳው፤ ለ30 ቀናት ስናካሂድ የነበረውን ፆም የምንጨርስበት፣ ያለንን ነገር ሸሪያችን እንደሚያዘውም በድሆች በማካፈል ነው የምናከብረው:: በሸሪያችን እንደተደነገገውም አራት አራት እፍኝ ካለን በማካፈል፤ አልያም ወደ ገንዘብ ተለውጦ ይከፈላል:: አንድ ወር ሙሉ የፆምንበትን ምንዳ ከፈጣሪ የምናገኝበትና ለዚያም ምህረቱን የምንጠይቅበት፤ በሕብረት ወጥተን ያለፈውን ፆም ወራት ለፈፀምናቸው መልካም ተግባራት ከፈጣሪ ብድራቱን የምንቀበልበትና ዱአ የምናደርግበት ቀን ነው::

ኢድ አልፈጥርን የተለየ የሚያደርገው ነገር 30 ቀን ፆም ተፅሞ፣ ከፈጣሪ ምህረቱን ጠይቆ፣ ስራዬ ከፈጣሪ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል ብሎ ሁሉም የሚያምንበት ቀን ነው:: ለዚያም ማረጋገጫ የሚሆንበትና የመጨረሻ ወይም የመቋጫ ሶላት የሚሰገድበት እለት ነው:: ከዚያ አኳያ ሁሉም አደባባይ ወጥቶ ይህም ማለት የፆመ ብቻ ሳይሆን በወሊድና በሕመም ምክንያት ያልፆመች እናት ሳትቀር ወጥታ በዓሉን ትታደማለች:: በሌላ አገላለፅ በዚያ እለት ሕዝቡ ከእስር እንደተለቀቀ አልያም ከችግር እንደወጣ እንደሚደሰት ሁሉ ወንጀላችን ሁሉ በፈጣሪ ተምሮልናል፣ አላህ ምህረት አድርጎልናል፤ ከማንኛውም ኩነኔ ነፃ ወጥተናል ብለን የምናምንበት ልዩ በዓል ነው:: ለዚህም በፀፀት ታውባ የምናደርግበት ነው::

አዲስ ዘመን፡- ኢድ በኢትዮጵያ የተለየ የሚባል ማህበራዊ እሴቶች እንዳለው ይነጋራል፤ እነዚህ እሴቶች ምንድን እንደሆኑ ቢያብራሩልን?

ሃጂ ሙስጠፋ፡- የኢድ ማኅበራዊ እሴት የሚባሉት ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን በሚያከብርበት ጊዜ ለታረዘው የሚያለብስበት፣ በአካባቢው የሚገኙ ድሆችን የሚያበላበት፣ ካለው የሚያካፍልበት ከመሆኑም ባሻገር በእለቱ ዘር፣ ቀለም እንዲሁም ሃይማኖት ባለየ መልኩ ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር ተጠርቶ የመብላትና በዓሉን በጋራ የሚያከብርበት መሆኑ ነው:: በዓሉን ለማክበር ያሰናዳናቸውን ምግብና መጠጦች በጋራ የሚቋደስበት መሆኑ የተለየ ያደርገዋል::

ሌላው ደግሞ የተጣላ የሚታረቅበት፣ በየቤቱ ያሉ ደካሞችን ሄዶ መዘየሩ፣ ትላልቅ አዛውንቶችን መጠየቁ ሁሉ የኢድ እሴት ነው:: በነገራችን በኢድ የሚከናወኑ ተግባራት ሁሉ ክርስቲያንና እስላም ተብለው የሚፈፀሙ አይደሉም:: የተቸገረውን መጠየቅና መስጠት ነው ዋናው መርሆ:: ሁሉንም መርዳትና ማገዝ፤ ተጠራርቶ አብሮ መብላትም እሴታችን ነው::

ከዚህ ጋር ተያይዞ እኔ በተወለድኩበት ሀዋሳ አካባቢ በኢድ እለት እኛ አደባባይ በዓሉን ለማክበር ስንሄድ ክርስቲያኖች መስኪድና ቤታችንን የመጠበቅ ልምድ አለ:: እንደአጋጣሚ ሆኖ የእኔ ቤት መስኪድ አጠገብ እንደመሆኑ ከመስኪዱ ጥበቆች ጭምር በዓሉን ለመታደም ሲሄዱ እስከምንመጣ ድረስ ንብረታችንን የሚጠብቁ አጠገባችን ያሉ የሌላ እምነት ተከታዮች ናቸው::

እነሱም በዓላቸውን ሊያከብሩ ወደ ቤተክርስቲያን ሲሄዱ እኛም በተራ ቤታቸውን እንጠብቃለን:: በፆም ወቅትም በአካባቢያችን ካሉ ክርስቲያኖች ጋር ነው አብረን የምናፈጥረው:: በየቤቱ ሾርባና ብስኩት እንልክላቸዋለን:: ይሄ አይነቱ ነባር እሴትና አብሮነት በሁሉም አካባቢ ሊስፋፋና ሊቀጥል ነው የሚገባው:: ይህንን ማድረግ ማለት የግል እምነታችን የሚነካ አይደለም፤ ግን የሀገራችንን ሰላምና እድገት የምናስጠብቀው የአብሮነት እሴቶቻችንን ስናስቀጥል ነው::

እኔ በቅርቡ ልጄን ስድር ለክርስቲያኖች በሬ ገዝቼ አርጂያለሁ፤ ይህንን በማድረጌ በአካባቢዬ ላሉ የሌላ እምነት ተከታዮች ያለኝን ከበሬታ አንፀባረኩበት እንጂ ምንም የሚጎዳ ነገር አልሆነብኝም:: በመሆኑም አብሮ የመብላትና የመካፈል፤ የመከባበር ባህላችንን ሁላችንም ልንጠብቀው ይገባል የሚል እምነት ነው ያለኝ:: ኢድም ስናከብር ክርስቲያን ወገኖቻችን በፈቀዱት ያክል አስጠግተን ማካፈልና ማገዝ ይገባል:: ሃይማኖታችንም የሚያዘን በመሆኑ ሁላችንም ኃላፊነታችን ልንወጣ ይገባል ባይ ነኝ::

አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ በሆኑ ምክንያቶች በርካታ ዜጎች ተፈናቅለዋል፤ ቀያቸውን ለቀው ለችግርና ለእንግልት ተዳርገዋል፤ እነዚህን ወገኖች በመደገፍ አኳያ የሕዝበ ሙስሊሙ ሚና ምን መሆን አለበት ይላሉ?

ሃጂ ሙስጠፋ፡- እንደተባለው በሀገራችን በተለይም ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ጥቂት የማይባል ሕብረተሰብ በግጭትና በድርቅ ምክንያት ተፈናቅሏል፤ ለስደትም ተዳርጓል:: ከዚህ አኳያ ሕዝበ ሙስሊሙ ሃብቱንና ንብረቱን እንዲሁም ጉልበቱን ሳይሰስት ለሃገር ጉዳይ አውሏል:: ለተፈናቀሉት ዱቄት በማዋጣት፣ ከብት በመስጠት የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል::

እንደማንኛውም ዜጋ ሙስሊሙ ከፍተኛ ተሳትፎ አድርጓል:: ለአብነት መጥቀስ ካስፈለገ በሰሜኑ ጦርነት ለተፈናቀሉ በርካታ ዜጎች፣ በሱማሌ፣ በደቡብና በሌሎችም የሀገራችን ክፍሎች ቀያቸውን ለቀው በእንግልት ላይ ለሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ ድጋፍ አድርጓል:: ስለዚህ የሙስሊሙ ተሳትፎ በየትኛውም ቦታ ላይ ቀላል የሚባል አይደለም::

በነገራችን ላይ ለተፈናቃዮች ማብላት፣ ማልበስና ማስጠጋት የሸሪያ ሕጋችን ትዕዛዝ ነው፤ በመሆኑም በየቦታው ያለው የሙስሊም ሕብረተሰብ ሃብት በማሰባሰብ፤ ሰውን በማስተባበር ረገድ ወደኋላ ያለበት ጊዜ የለም፤ በዘንድሮ ረመዳንም ብዙ የድጋፍ ስራዎች ተሰርቷል፤ ወደፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው::

አዲስ ዘመን፡- ከፆምና ከበዓላት ባሻገር የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህሉ በምን መልኩ መቀጠል አለበት ብለው ያምናሉ?

ሃጂ ሙስጠፋ፡– አስቀድሜ እንደገለፅኩልሽ በሀገራችን በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ ምክንያቶች የተከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት እንደ አንድ የእምነት ተቋም በርካታ ስራዎችን ሰርተናል:: ለምሳሌ በሱማሌና አፋር ክልል አካባቢ የነበረውን ግጭት ለመፍታት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በጀት መድበን፤ መንግስትን ሳንጠይቅ የሃገር ሽማግሌዎችን አሰባስበን የማስታረቅ ሥራ ሰርተናል::

ይህንንም ያከናወነው ያለመንግስት ጣልቃ ገብነት ሲሆን ሁለቱንም ጎሳዎች ለማስታረቅና ወደመግባባት እንዲመጡ ሥራ ተጀምሯል:: በቅርቡ በሸራተን ሆቴል ጉባኤ ተካሂዷል፤ በቀጣይም ስርነቀል ለውጥ ለማምጣት እየተሰራ ነው ያለው:: ሌላው ከበዓላት ውጪ ተፈናቃዮችን ለመደገፍ እቅድ ይዘን የምንሰራው ስራ አለ፤ ይህ እንግዲህ በእርዳታ ልማት ዘርፍ የሚሰራ ነው:: እንደሃገር ግን መንግስት መድረስ ያልቻለባቸው አካባቢዎች ላይ እየተጠና ድጋፍ የማድረግ ስራ እንሰራለን::

አዲስ ዘመን፡- ሕዝበ ሙስሊሙ የሀገርን ሰላምና ልማት ከማስቀጠል አኳያ ምን አይነት አስተዋፅኦ ሊያበረክት ይገባል?

ሃጂ ሙስጠፋ፡– ከዚህ አኳያ እንደ አንድ ግለሰብም ሆነ ተቋምን ወክዬ ብናገር እስልምና አስተምህሮም ሆነ መርሆው ሠላም ነው:: ሙስሊሙም ራሱ የሰላም ተምሳሌት ወይም አምባሳደር ነው:: እስላም ማለት ራሱ ሰላም ማለት ነው:: አላህ ሱባን ወታአላ ከስሞቹ አንዱ ሰላም ነው:: የሚሰጠው፣ የሚነሳው፤ የሚሾመው፤ የሚሸልመው፤ የሚያድነው፣ የሚገለው እሱ ነው:: የሰላሙ ባለቤት እሱ ነው:: በሰላም ዙሪያ ሕዝበ ሙስሊሙ በሰላም ዙሪያ በጣም አጥብቆ ነው የሚሰራው:: እለት በእለት በምንሰግደው ሰላት ለሰላም ዱአ እናደርጋለን፤ ሰላምን የሚሰጠው አላህ ስለሆነ!::

ስለዚህ ሰላሙ የሃገሪቷ መንግስትን ተከትሎ መንግስትንም እየደገፈ፤ ዜጎቿ ላይ አላስፈላጊ ጫና እንዳይፈጥር መንግስትን በአቅማችን እየደገፍን፤ በመካከል የሚፈጠሩ አላስፈላጊ ድርጊቶች ካሉ ሕዝቡን እየገሰፅን ነው ያለነው:: መንግስት በሰላምና በልማት ረገድ ለሚሰራው ስራ እንደእስልምና ጉዳዮች ዘርፍ አቋቁሞ ጭምር እየሰራ ነው ያለው:: እስከ ክልል ድረስ የሰላም ዘርፉን አውርደን ራሱን ችሎ እየሰራ ነው:: እስከ ቀበሌ ድረስ ጭምር በመውረድ በእርቅና ሰላም ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን ነው የምንገኘው:: ይህም ተቋማችን ለሃገር እድገትና ሰላም መጠናከር እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚቀጥል ነው የሚሆነው::

አዲስ ዘመን፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ለዘመናት ሲጠይቅ የነበሩ ጉዳዮች ምላሽ እያገኙ ነው፤ ይህንን ጉዳይ እርሶ እንዴት ይመለከቱታል? በቀጣይስ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ጥያቄ በተሟላ መልኩ ምላሽ እንዲያገኙ ምን መሰራት አለበት ይላሉ?

ሃጂ ሙስጠፋ፡- የሙስሊሙ ሕብረተሰብ ጥያቄዎች ባለፉት መንግስታት የተወዘፉ ናቸው:: አንቺም እንዳነሳሽው በተለይም ከለውጡ ወዲህ የሙስሊሙ ሕብረተሰብ ጥያቄ የነበሩ ጉዳዮች እየተመለሱ መጥተዋል፤ አሁንም እየተመለሱ ናቸው:: በእርግጥ አንድ ልጅ ዛሬ ተወልዶ ዛሬ እንደማያድግ ሁሉ ጥያቄዎችም ደረጃ በደረጃ እየተመለሱ ነው፤ ይመለሳሉም የሚል እምነት አለን::

አንዳንድ ጊዜ በመንግስት ደረጃ የሚቀመጡ ሰዎች የግል እምነታቸውን ያከብራሉ፤ የሌላውን ደግሞ እንደቀልድ የሚያዩበት ሁኔታ ነበር:: ነገር ግን ይህ መንግስት የሕዝብ መንግስት እንደሆነ እያየን ነው::

ባለፈው መንግስት ያልተፈቱ ችግሮች ተፈተዋል፤ ብዙ ጥያቄዎች ተመልሰዋል:: ይህ ማለት ግን ሁሉም ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል ማለት አይደለም፤ ግን ደግሞ ተራ በተራ መንግስት በሚመቸውና የሌላውን መብት በማይነካ መልኩ ጥያቄያችን ምላሽ እንዲያገኝ ያደርጋል የሚል እምነት አለኝ::

እንዳልኩሽ ሁሉም ጥያቄ መንግስት በአንድ ጀምበር ይመልሳል ብለን አንጠብቅም፤ ግን ጥያቄ እናቀርባለን፤ እንዲመለስልንም ከመንግስት ጎን እንሰራለን:: ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ ጥያቄዎችን ይፈታሉ ብለን እናምናለን ::

አዲስ ዘመን፡- ለሙስሊሙ ሕብረተሰብ ማስተላለፍ የሚወዱት ተጨማሪ መልዕክት ካለ ?

ሃጂ ሙስጠፋ፡- እኔ እንደ አንድ ሙስሊምና የሰላም ዘርፍ ኃላፊ የማስተላልፈው መልዕክት ለመላው ሰላም ወዳድ ሕዝቦች ነው፤ ሰላም ለኢትዮጵያ ሃገራችን፤ ሰላም ለአፍሪካ፤ ሰላም ለዓለም ሁሉ ሕዝብ እንዲሆን እመኛለሁ:: ሰላምን የሚፈልጉ ደግሞ የሰው ልጆች ብቻ ሳይሆኑ እንስሳትም ሆነ እፅዋቶች ጭምር ናቸው:: በየብስ፤ በአየርና በውሃ ውስጥ ያለ ፍጥረት ሁሉ ሰላም ይፈልጋል::

ሰላም ለፍጥረታት ሁሉ ነው:: ሠላምን የሚያጠፋ ደግሞ ራሱ ሰው ነው፤ በተለይ በመሳሪያ ኃይል ተደግፈው የሰው ሕይወት የሚያጠፋ ሁሉ አላህ ልቦና እንዲሰጣቸው ነው የምመኘው:: በሃገራችን በሰሜን፤ በደቡብ፤ በምዕራብና ምስራቅ ሁሉ ሰው ተገደለ ይባላል፤ ሆን ተብሎ ሰው እየታረደ ነው፤ እየተገደለ ነው፤ ገዳዮች ፈጣሪያቸውን እንዲፈሩ ጥሪ አቀርባለሁ፤ ገዳዮች ሰውን በመግደል እርካታ አያገኙም፤ እርካታ የሚሰጠው ሁሉንም አለመግባባቶች ወደ ውይይት በማምጣት ነው::

ወደ ጠረጴዛ፣ ዛፍ ስር ቁጭ ብሎ መፍታት የሚቻለውን ጉዳይ በጠመንጃ ኃይል ለመፍታት እየተደረገ የሰው ሕይወት እየጠፋ ነው ያለው:: ለሁሉም ልቦና እንዲሰጥ፣ በተለይ መሳሪያ የታጠቁ አከላት ለሰው ልጆች እንዲያዝኑ ጥሪ አቀርባለሁ:: መንግስትም ሆነ ተቃዋሚ ኃይሎች ለሕዝባቸው ራርተው አለመግባባትን ወደ ውይይት ሊያመጡ ይገባል::

ለግድያ የተስማማ የረዳ ያገዘ ሁሉ በፈጣሪ ዘንድ ይጠየቃል:: ስለዚህ ሕይወት የምታጠፉ ሰዎች የምትገድሉት የገዛ ወገናችሁን መሆኑን አውቃችሁ ከጥፋታችሁ ተመለሱ፤ ከፈጣሪ ቁጣ የሚያመልጥ ባለመኖሩ ለአውርቅ ልባቹን አዘጋጁ የሚል መልዕክት አለኝ:: ወደ ሰላምና መረጋጋት ተመለሱ እላለሁ፤ ለመላው ሙስሊም ሕብረተሰብ መልካም የኢድ አልፈጥር በዓል እንዲሆን እመኛለሁ፤ ኢድ ሙባረክ!::

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ::

ሃጂ ሙስጠፋ፡- እኔም አመሰግናለሁ::

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2/2016 ዓ.ም

Recommended For You