ከትናንት በስቲያ በተለያዩ የዓለም ከተሞች በርካታ የጎዳና ላይ ውድድሮች ሲከናወኑ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለይም በሁለት ታላላቅ የማራቶን ውድድሮች ድል ቀንቷቸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን አሸናፊ ከሆኑባቸው ውድድሮች መካከል አንዱ የፓሪስ ማራቶን ሲሆን ሌላኛው የዴጉ ማራቶን ነው፡፡
ከወራት በኋላ ትልቁን የስፖርት መድረክ ኦሊምፒክ በምታስተናግደው የፓሪስ ጎዳናዎች ዓመታዊው የፓሪስ ማራቶን ከትናንት በስቲያ ሲካሄድ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታ አሸናፊ መሆን ችለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በርካታ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ባሸነፉበት የፓሪስ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታ በበላይነት ሲያጠናቅቁም ከአምስት ዓመት ወዲህ የመጀመሪያ ሆኗል፡፡
የመጀመሪያ የማራቶን ውድድራን ያደረገችው አትሌት መስታወት ፍቅር ርቀቱን በ02:20፡ 45 በማጠናቀቅ የሴቶቹን ውድድር ስታሸንፍ፣ በተመሳሳይ በወንዶች ሙሉጌታ ኡማ 02፡05፡33 ሰዓት በመግባት ውድድሩን በቀዳሚነት አሸንፏል፡፡
ጠንካራ ፉክክር በታየበት የወንዶች ውድድር አትሌት ሙሉጌታ ከኬንያውያን አትሌቶች ጋር ብርቱ ፉክክር በማድረግ በአስራ አምስት ሰከንዶች ልዩነት ነው ለድል የበቃው፡፡ የገባበት ሰዓትም በርቀቱ የራሱ ምርጥ ሆኖ ተመዝግቧል፡ ኢትዮጵያዊውን አትሌት ተከትሎ ኬንያውያኑ ቲተስ ኪፕሩቶ በ2:05:48 ሰዓት ሁለተኛና ኤሊሻ ሮቲች በ2:06:54 ሰዓት ሦስተኛ በመሆን አጠናቀዋል፡፡ ሦስተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ሮቲች 2021 ላይ የውድድሩን ክብረወሰን የጨበጠ አትሌት እንደመሆኑ የዘንድሮውን ውድድር የማሸነፍ ትልቅ ግምት ተሰጥቶት ነበር፡፡
በሴቶች መካከል በተካሄደው ፉክክር በርቀቱ ከዚህ ቀደም ስማ የማይታወቀው አትሌት መስታወት ፍቅር ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረገችውን ውድድር በ2:20:45 ሰዓት በድል ተወጥታለች፡፡ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት እናትነሽ አላምረው ደግሞ በ2:20:47 ሰዓት የሁለተኛነቱን ደረጃ በመያዝ ውድድሩን ፈፅማለች፡፡ ኬንያዊቷ የረጅም ርቀት የዓለምና የኦሊምፒክ ቻምፒዮን አትሌት ቪቪያን ቼርዮት ወደ ማራቶን ፊቷን ካዞረች ወዲህ የተለያዩ ድሎችን ብታስመዘግብም በዘንድሮው የፓሪስ ማራቶን በሦስት ሰከንድ ልዩነት ተከታትለው ለገቡትን አዳዲስ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እጅ ሰጥታለች፡፡ ቼሪዮት ውድድሩን በሦስተኝነት ስትፈፅም 2:21:47 ሰዓት አስመዝግባለች፡፡
የ2016 ሪዮ ኦሊምፒክ የ5ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊና የአራት ጊዜ የዓለም ቻምፒዮና ቼሪዮት ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የማራቶን ውድድር እንደ ማድረጓና 40 ዓመት ላይ እንደመገኘቷ ያስመዘገበችው ውጤት የሚያስከፋ አይደለም፡፡
በሳምንቱ መጨረሻ ተጠባቂ የሆነው ሌላኛው ትልቅ የማራቶን ውድድር በደቡብ ኮሪያ ዴጉ የተካሄደው ሲሆን ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሩቲ አጋ የውድድሩን ክብረወሰን በማሻሻል አሸንፋለች። በወንዶች ግን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ደረጃ ውስጥ መግባት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ በተሰጠው የዴጉ ማራቶን አትሌት ሩቲ አጋ የውድድሩን የቀድሞ ክብረወሰን በ48 ሰከንድ በማሻሻል በ2፡21፡08 ሰዓት ማጠናቀቅ ችላለች፡፡ እሷን ተከትለውም ኬንያውያኑ አንጌላ ቱናይ በ2፡21፡ 32 እንዲሁም ኤቫሊን ቺርቺር በ2፡22፡12 ሰዓት ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ፈፅመዋል፡፡ የውድድሩ የቀድሞ ክብረወሰን 2፡ 21፡56 ሲሆን 2022 ላይ በኤርትራዊቷ አትሌት ናዝሬት ወልዱ ተይዞ እንደቆየ ይታወሳል፡፡
በተመሳሳይ እለት በበርሊን በተካሄደው የግማሽ ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሴቶቹን ፉክክር አንደኛና ሁለተኛ ሆነው ማጠናቀቅ ችለዋል። አትሌት ሙላት ተክሌ የሃያ አንድ ኪሎ ሜትር ፉክክሩን በ66፡53 በማጠናቀቅ ቀዳሚ ስትሆን ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ዘራይ ፍታው በ67፡22 በማጠናቀቅ ሁለተኛ ሆናለች፡፡ በዚሁ ውድድር በወንዶች መካከል የተካሄደውን ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አቋርጠው ወጥተዋል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1/2016 ዓ.ም