መርካቶ ያበቀላት ጠንካራ ሰራተኛ

የመርካቶ ስም ሲነሳ ዋና መጠቅለያዋ ሆኖ የሚያገለግለን “አራዳነት” የሚለው ቃል ነው። አንዳንዶች “የመርካቶ ልጅ ቀልጣፋና ጨላጣ ነው!” ይሉታል። ሌሎች ደግሞ የመርካቶ ልጅ “ቢዝነስ ሁሌም በእጁ ነው” ለማለት ሲሹ፤ “የመርካቶ ልጅ ጦሙን አያድርም” ይላሉ።

አንዳንዶች ደግሞ ፍጥነቱና አዋቂነቱ እያስደመማቸው፤ “የመርካቶ ልጅ ከጨበጥክ በኋላ የእጅህን ጣቶች መጉደል አለመጉደላቸውን ቁጠር” ይላሉ። በሥልጡንነቱና በዕውቀቱ እንዲሁም በልምዱ የሚኮሩት ደግሞ፤ የመርካቶ ልጅ ቱሪስትና ፒስኮር ከለየ የቆየ፣ “ጨውና አሞሌ፣ ወመንቴና አለሌ ገና ዱሮ አንጥሮ ያየ”፣ የዕውቀት ሰው ነው እያሉ፣ በእርግጠኝነት ይናገራሉ።

የመርካቶ ልጅ፤ ንግድን ከሕይወቱ ጋር ያዋሃደና ልምዱን ለነገ ማዋል የሚችል፣ አወንታዊ ልዕልና ያለው የተግባር ሰው ነው፤ ብለው የሚናገሩ አያሌ ናቸው። ጣሊያን “መርካቶ እንዲጂኖ” የሚለን፤ ሠፊውን የምስራቅ አፍሪቃ ገበያ የራሱ የሆነ ልዩ ባህሪ ያለው ነው ሲለን ነው። ሌሎች ፈረንጆች “The indigenous Mer­kato” እንደሚሉት መሆኑ ነው።

መርካቶ ከምስራቅ አፍሪካ አንደኛ ሰፊ ገበያ ነው። የመርካቶ ትልቁ አዳራሽ፤ በበላይ ተክሉ ኬክ ቤት፣ በዋንዛ ካፍቴሪያ፣ በዋርካ ካፍቴሪያና በሰሜን ሻይ ቤት፣ እንዲሁም ወደ አራተኛ ሲል ባለው በምስራች ሆቴል እና በበርካታ ልብስ ሱቆች የተከበበና የታጀበ ነው።

ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ስለ መርካቶ ያነሳሁት መርካቶ ተወልዳ ያደገች፤ በባልትና ውጤቶች ንግድ የተሰማራች፤ በንግዱም ዓለም ገብታ ስኬታማ የሆነች እውነትም የመርካቶ ልጅ የምታስብልን ፈጣን የንግድ ሰው የሆነች ሴትን ላስተዋውቃችሁ ስለወደድኩ ነው። መልካም ቆይታ።

ገነት ብርሃኑ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው መርካቶ አውቶብስ ተራ አካባቢ ሲሆን አሁን አዲስ አበባ ሳሪስ አካባቢ ትኖራለች። ባለ ትዳርና የሶሰት ልጆች እናት ስትሆን ልጆቿን አሳድጋ የእሷን እርዳታ መፈለግ ባቆሙበት ወቅት ነበር ሁልጊዜ የምትመኘውን የባልትና ሰራን ለመስራት የተነሳችው።

“ባልትና ስራን የመረጥኩት የውስጥ ፍላጎት ስላለኝ ነው” የምትለው ወይዘሮ ገነት ሰው የውስጥን ፍላጎት አዳምጦ ሲሰራ ስኬታማ ይሆናል ብላ እንደምታስብ ትናገራለች።

ለቤተሰቦቿ ሶሰተኛ ልጅ ስትሆን ወላጆቿ ከወለዷቸው ሶስት ልጆች በጠጨማሪ የቤተሰብ ልጆች ቤት ሞልተው ያሳድጉ ነበር። ወላጆቿ ቤት እንግዳ የማይጠፋበት የእንግዳ ተቀባዮች ቤት ነበር። ቤቱ የበርካቶች ማረፊያ፤ የብዙዎች ሕይወት ማደላደያ፤ መሸጋገሪያ የሆነ ቤት ውስጥ እንዳደገች ትናገራለች። እንዲህ በደግነት የተሞላ ቤት ውስጥ ያደገችው ሴት እራሷም በዛ የቤተሰብ ስርዓት እየተመራች ኑሮዋን እየመራች መሆኑን ታብራራለች።

“ልጆቼ አድገው ትምህርት ቤት ሲገቡ ነው የወጣሁት። ልጅ ድሪያለሁ የመጨረሻ ልጄ አስር ዓመቱ እያለ ነው ሰራ የገባሁት ቁጭ ማለት አልፈለኩም። ከእራሴ አልፌ ለሌሎች የስራ እድል ልፈጥር ብዬ ነው። “ብላለች።

በዚህ ሁኔታ ያደገችው ሴት የእራሷን ቤት መስርታ በመልካም የእናትነት ሰርዓት ልጆቿን አሳድጋለች። ልጆቿ እራሳቸውን ማስተዳደር በሚችሉበት እድሜ የእራሷን ስራ የምትሰራበትን ሀሳብ ይዛ ተነሳች።

የንግድ መነሻ ካፒታል

የባልትና ውጤትን እያዘጋጁ ለገበያ ማቅረብ የሚለውን ሀሳቧን እውን ለማድረግ መነሻ ካፒታል ማፈላለግ ጀመረች። ከጥቃቅንና አነስተኛ ለስራ የሚሆን ሶስት መቶ ሺ ብር ብድር ያገኘችው ይች ሴት በተለያየ ጊዜ በወሰደችው ስልጠና መሰረት በግል የሚተዳደር የባልትና ውጤቶች ማምረቻ አቋቋመች። የግለሰብ ነጋዴ የሚተዳደር የንግድ ቤት በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት የምትናገረው ወይዘሮ ገነት ከጥቅሞቹም መካከል የድርጅቱ ባለቤት በድርጅቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ብቸኛ ውሳኔ ሰጭ የሆነበት ነው። የግል ድርጅቶች አብዛኛውን ጊዜ ብዙ ካፒታልና ሙያዊ የሆነ እውቀት የማይጠይቁ ሥራዎች ላይ ሰዎች በቀላሉ የንግድ ፈቃድ አውጥተው የራሳቸውን የንግድ ሥራ የሚመሰርቱበት አደረጃጀት መሆኑም ሌላው ጥቅም ነው ትላለች። በመሆኑም ስትደራጅ ለብቻዋ ተበድራ ለመስራት መምረጧን ትናገራለች።

በአንድ ግለሰብ የሚመሰረቱ የንግድ ድርጅቶች ከዚህ ቀጥሎ የተመለከቱት ጥቅሞች ይኖሩታል የምትለው ወይዘሮ ገነት በዚህ መልኩ ዝርዝር ሁኔታውን አስቀምጣለች። በግለሰብ የሚቋቋም ንግድ በቀላሉ የሚመሰረት መሆኑ ማለትም የዚህ አይነት የንግድ ድርጅት ለመመስረት ከሌሎች ሰዎች ጋር መሻረክ፣ የጋራ ስምምነት ላይ መድረስ ወዘተ. የማይጠይቅና ሙሉ በሙሉ በግለሰቡ ውሳኔ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ሂደቱን ቀላል የያደርገዋል። አንድ ግለሰብ በፈለገው ሙያ፣ በፈለገው ጊዜና ቦታ ንግዱን የመመስረት ሙሉ ነፃነት አለው።

በአነስተኛ ካፒታል ይመሰረታል መመስረቱም ሌላው መሆኑን የምታስረዳው ወይዘሮ ገነት የዚህ አይነት የንግድ ድርጅት ለመመስረት የሚያስፈልገውን የካፒታል መጠን የሚወስን ሕግ ባይኖርም ግለሰቡ የመረጠውን የንግድ ሥራ ማስኬድ እስከቻለ ድረስ አነስተኛ በሆነ ካፒታል ሊመሰረት ይችላል።

የንግድ ሥራው ብቸኛ ተጠቃሚ ባለቤቱ መሆኑን የምትናገረው ወይዘሮ ገነት የንግድ ሥራው የሚመራውና የሚተዳደረው በአንድ ግለሰብ እንደ መሆኑ በንግድ ሥራ እንቅስቃሴ የሚገኘውን ጥቅምም እንዲሁ ብቸኛ ተጠቃሚ ይሄው ግለሰብ ይሆናል ማለት ነው።

ድርጅቱን የመምራት ነፃነት የእሯሷ መሆኑን ጠቅሳ የንግድ ድርጅቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ማለትም ድርጅቱን የመምራት፣ የማስፋፋት ካልፈለገም ደግሞ የማፍረስ ወይም የመዝጋት፣ ሰራተኛ የመቅጠር ወይም የማሰናበት ውሳኔዎችን ያለማንም ጣልቃ ገብነት ባለቤቱ ብቻውን የመወሰን ሙሉ ነፃነት አለው ትላለች።

ሌላው የንግድ ሚስጥር ከመጠበቅ አኳያ የግል ድርጅት ጥቅም አለው። ማለትም አጠቃላይ የንግድ እንቅስቃሴው የሚመራው በአንድ ግለሰብ እንደ መሆኑ ለንግድ ስራው ጠቃሚ ናቸው የሚባሉና የሚስጥር መያዝ ያለባቸው ጉዳዮች በራሱ በባለቤቱ ብቻ የተያዙ በመሆናቸው ከራሱ ፈቃድ ውጭ በሆነ መንገድ ሊባክኑ አይችሉም ይህ ማለት ደግሞ ብራንድን በብቸኝነት ለመጠበቅ ልዩ ጥቅም አለው ብላለች።

ግብር ከመክፈል አኳያ የተሻለ ጥቅም አለው የምትለው ወይዘሮ ገነት በአንድ ግለሰብ የሚመራ የንግድ ድርጅት ግብር የሚከፍለው አንድ ጊዜ ብቻ በመሆኑ በግብር አከፋፈል ረገድ ተጠቃሚ ነው ትላለች።

የስራ ሂደትና ጥረት

ስራውን ስትጀምር ሶሰት ቋሚ ሰራተኞችን ይዛ መነሷቷን ትናገራለች። አሁን ላይ እንደ ጊዜውና ሁኔታው በኮንትራት የሚቀጠሩ ሰዎች መኖራቸውንና አሁን አምስት ቋሚ ሰራተኞች መኖራቸውን ታስረዳለች።

የኮንትራት ሰራተኞች የሚቀጠሩት ምርት በብዛት ሲታዘዝ ሲሆን ለእነዚህ ጊዚያዊ ሰራተኞች ከሶስት ሺህ እስከ አምስት ሺህ ብር ድረስ በወር የሚከፈል ይሆናል ብላለች። ለቋሚ ሰራተኞችም ተመሳሳይ አይነት የክፍያ ስርዓት ሲኖር ቋሚዎቹ ከመደበኛ የስራ ጊዜያቸው ውጪ የሰሩበትም የሚከፈላቸው መሆኑን ታብራራለች።

“ስራ ለመጀመር የተነሳሁት በራሴ ቦታ ላይ ነበር ” የምትለው ወይዘሮ ገነት የማምረቻም የመሸጫም ሱቅ እዛው መኖሪያ ቤቷ አካባቢ አድርጋ ከፍ ወዳለ ሰኬት ጉዞ ጀመረች። የባልትና ውጤቶቿን ቤቷ ባለው ሱቅ ከመሸጥ አልፋ በአላትን እየተከተሉ የሚዘጋጁ ባዛሮች ላይ ይዛ መውጣት ጀመረች።

ምርት እየበዛ ደንበኞቿ የባልትና ውጤቶቿን ጣእም እየለዩትና እየመረጡት ሲመጡ ቤቷ ካለው ሱቅ በተጨማሪ ብዙ ደንበኞች ወደምታገኝበት ቦታ ሱቅ ተከራይታ መስራት ጀመረች። ከአንድ የሰፈር ውስጥ ሱቅ ከፍ ወዳለ ደረጃ የተሸጋገረችው ይች ሴት በሞራል ለስኬት መታተር ጀመረች።

የባልትና ውጤቶች ሲባል ከበርበሬ አንስቶ ሽሮ፤ በሶ፤ ቅመማ ቅመም፤ የአጥሚት እህል፤ ቆሎ በስራው ከሚቀርቡት መካከል ሲሆን ማንም ሰው ጉልበት የሚጠይቀውን ይህን ጥራቱን የጠበቀ የባልትና ውጤቶች በቀላሉ ከሱቅ አንስቶ እንዲጠቀም ማድረጓን በኩራት ትናገራለች።

የገበያ ሁኔታ በየወቅቱ የሚለያይ መሆኑን የምትናገረው ወይዘሮ ገነት “በየወቅቱ የገበያውን ሁኔታ እየተከተሉ የሚመጡት የተለያዩ አይነት ፍላጎቶች እንደየ ፍላጎቶቹ እያመረትን እንሸጣለን ” ብላለች። ዋና የገበያ ጊዜ በዓላትን አስታኮ የሚከፈቱ ባዛሮች መሆናቸውን ተናግራ ብዛት ያለው ምርት በዚህ ወቅት እንደሚሸጥ አስረድታለች።

ስኬት

በሶስት መቶ ሺ ብር ብድር ስራ ለመጀመር የተነሳችው ይቺ ሴት አሁን ላይ ብድሯን መልሳ አምስት መቶ ሺ ብር ተቀማጭ ገንዘብ አላት። ከዛም በተጨማሪ የሚንቀሳቀስ ገንዘብና የመስሪያ ማሽኖች፤ የምርት ግብኣቶች፤ ተመርተው ያልተሸጡ ምርቶች ተጫማምሮበት የተሻለ የሚባል አቅም መፍጠሯን ትናገራለች።

“ገነት ባልትና ልዩነቱ ጥራቱ ነው ” የምትለው ወይዘሮ ገነት፤ ይህን በጥንቃቄና በጥራት የሚመረት የባልትና ወጤት በቀጣይ የታወቀ ብራንድ የማድረግ ሕልም እንዳላት ትናገራለች። በቀጣይ በጥራቱ የታወቀ የባልትና ብራንድን በመያዝ ሱፐር ማርኬቶች ውስጥ በመግባት አማራጭ ሆና ለመቅረብ እየሰራች መሆኑን ታብራራለች።

ባለቤቴ በስራው ላይ ድጋፍ ከሚሰጡኝ ሰዎች አንዱ ነው የምትለው ወይዘሮ ገነት፤ ግብኣት ከማቅረብ አንስቶ ሽያጭ ላይ በመሳተፍ ልጆቼም አብረው ይሰራሉ ትላለች።

በመጨረሻም

ሰዎች ስራ ከመጀመራቸው በፊት ውጤታማ እሆናለሁ ወይ? የነፍሴ ጥሪ ነው ወይ? የምወደውን ስራ ነው ወይስ የምሰራው ?የሚያጋጥሙኝን መሰናክሎች በስኬት እወጣዋለሁ ወይ? የሚለውን አስቦ ወደስራ መግባት ይኖርበታል። ሰው ስሜቱን ተከትሎ መስራት ከጀመረ ስኬት ደጁ ላይ መሆኑን ማመን አለበት ትለናለች። እኛም ሰው ከተሰማራ እንደየስሜቱ በዋለበት ሜዳ አይቀርም ማፍራቱ ብለን ተሰናበትናችሁ። ቸር ይግጠመን።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1/2016 ዓ.ም

Recommended For You