‹‹ሀገራዊ የሆኑ ፕሮጀክቶች በዞናቸው በመሠራት ላይ በመሆናቸው ቀጣዩ ጊዜ ብዙ ተስፋ የሚሰነቅበት ነው››- አቶ ዳዊት ገበየሁ የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ

የንጉስ ሃላላ ምድር ዳውሮ፣ በምዕራብ ደቡብ ክልል ከሚገኙ ዞኖች ውስጥ አንዱ ነው። ዞኑ፣ በርከት ያለ የድንጋይ ከሰልን ጨምሮ ሌላ ማዕድን የሚገኝበት ሲሆን፣ በግብርናው ዘርፍ ደግሞ የተለያየ ምርት ለማምረት የሚያስችል ሰፊ መሬት ባለቤትም ነው። በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት የተሰራው የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክትአካል የሆነው እና በንጉሥ ሀላላ ስም የተገነባው የሃላላ ኬላ ሪዞርት የሚገኘው በዚሁ ዞን ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ የቱሪስት ፍሰትንም እያስተናገደ ይገኛል።

ስለ ዞኑ አጠቃላይ ገጽታ እንዲሁም የኢንቨስትመንት ልማትና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የጋዜጠኞች ቡድን በቅርቡ ወደስፍራው ባቀናበት ወቅት ከዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ከአቶ ዳዊት ገበየሁ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል። መልካም ንባብ።

አዲስ ዘመን፡- ዳውሮ በምዕራብ ኢትዮጵያ ከተካለሉ ዞኖች ውስጥ አንዱ ነው፤ በአሁኑ ወቅት በዞኑ እየተካሔደ ስላለው እንቅስቃሴ ቢገልጹልን?

አቶ ዳዊት፡- የዳውሮ ዞን ቅርብ ጊዜ ከተዋቀሩ የአዲሱ የደቡብ ምዕራብ ዞኖቹ መካከል አንዱ ነው። በዚህ መነሻ በዞኑ በርካታ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እንዲሁም የኢኮኖሚ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። ከዚህ አንጻር ውጤቶችም በመመዝገብ ላይ ናቸው። የሕዝብ የመልማት ጥያቄዎች ከለውጡ ወዲህ ምላሽ እያገኙ በመሆናቸው በተሻለ ሒደት ላይ እንገኛለን።

እንደሚታወቀው ቀደም ባለው አወቃቀር ዞኑ የነበረው በደቡብ ክልል ውስጥ ነው። በዚያን ጊዜ የእኛን ዞን ጨምሮ ሌሎች ዞኖችም የአስፓልት መንገድ የሚባል አልነበራቸውም። ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ከለውጡ ወዲህ የተጀመሩ የአስፓልት መንገዶችን ማጤን ይቻላል። በወላይታ በኩል ያለው አንዱ ማሳያ ሊሆን የሚችል ነው። ከዚያም አልፎ በክላስተር የመደራጀት ጥያቄም መመለስ የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ለዚህም ማሳያው እንደክልል ሲታይ የማኅበራዊ ክላስተር ያለው በዞናችን ውስጥ ነውና ይህም መልካም የሚባል አሰራር ነው።

በተለይ ደግሞ እኩል ከመልማት አንጻር የፍትሃዊነት ጥያቄዎች እየተመለሱልን ይገኛሉ። በርካታ ኢንቨስተሮችም ወደዞናችን እየገቡ ነው። በተለይም ሀገራዊ የሆኑ ፕሮጀክቶች በዞናቸው በመሰራት ላይ በመሆናቸውም ቀጣዩ ጊዜ ብዙ ተስፋ የሚሰነቅበት ነው ለማለት እወዳላሁ።

አዲስ ዘመን፡- ከማህበራዊ ጉዳይ አኳያ ምን የተሰሩ ስራዎች አሉ?

አቶ ዳዊት፡- ከማኅበራዊ ጉዳይ አኳያ አንዱ የማኅበራዊ ሴክተር ባህልና ቱሪዝም ነው። በአካባቢያችን በርካታ የቱሪስት መስህቦች አሉ። ከእነዚህ የቱሪስት መስህቦች ውስጥ ለአብነት ያህል ለመጥቀስ የሃላላ ኬላውን ጨምሮ የጨበራ ጩርጩራ ፓርክ እንዲሁም ዋሾዎች፣ ፍል ውሃዎች፣ ፏፏቴዎችና ሌሎች ታዋቂ የሆኑ የሃይማኖት ተቋማትም ጭምር የሚገኙበት ነው።

ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትራችን ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነው የታላቁ ንጉስ ሃላላ ኬላ ሎጅ አንዱ ሲሆን፣ ይህም ሎጅ በ2015 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ተመርቆ ወደሙሉ ትግበራ ውስጥ መግባት የቻለ ነው። እውነት ለመናገር ዞናችን በበጀት እጥረት ውስጥ በመሆኑ ትልቅ ቀውስ ውስጥ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን ከሃላላ ሎጅ በየወሩ ከሁለት እስከ ሶስት ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት ችለናል።

ይህንን ገቢ በዞናችን ውስጥ ያለው የሎማ ወረዳ የሚያገኘው ሲሆን፣ ዞኑ ለሎማ ወረዳ በየወሩ የሚያስተላልፈውን ወጪ የሚሰጠው በጀት ከሃላላ ኬላ ሎጅ የሚያገኘውን ገቢ በመቁረጥ ነው። ከዚህ የተነሳ የሎማ ወረዳ የነበረበትና በየወሩ የሚከፍለው እዳ እየተቀነሰ መምጣት ችሏል ማለት ነው።

እንደሚታወቀው የንጉስ ሃላላ ካብ የቆየ ነው፤ የድንጋይ ካብ ነው፤ እኛም ለዘመናት በአጠገቡ ስንመላለስ ቆይተናል። ይሁንና በወቅቱም ምንም አይነት ትርጉም አልሰጠነውም። ነገር ግን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን አንድ ጊዜ በመጡበት አጋጣሚ ቦታውን ካስተዋሉ በኋላ ስፍራው ከዚያ ቀጥሎ የሆነው የቱሪስት መስህብ ነው።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ከሃላላ ኬላ የገበታ ለሀገር አካል ሆኖ እስከ ዋካ ኢሰራ የአስፓልት መንገድ መስራት ጭምር ሊታቀድ ችሏል። በአሁኑ ወቅት ግምት ሁሉ የወጣለት ሲሆን፣ በቅርቡም ለመስራት የሚያስችል ሒደት ላይ ይገኛል። ስለዚህ እነዚህን መሰል ስራዎች ስናጤን ጉዳዩም ሆነ ሀብቱ ቀደም ሲል የነበረ፤ ነገር ግን እኛ ማጤን ያልቻልነው ነው። ስለዚህ በጠቅላይ ሚኒስትራችን አማካይነት እንደ ሀገር ታቅዶ የሚሠራ ታላቅ ሥራ ነው።

በእርግጥ ለዚህ ዓመት ብቻ የእፎይታ ጊዜ ተብሎ በአካባቢው ማለትም ሎጁን የሚያስተዳድሩ ባለሀብቶች የአንድ ዓመት ጊዜ ተሰጥቷቸዋል እንጂ ከዚህ በኋላ ለሚመጡት ዓመታት የተሻለ ገቢ ማግኘት ይቻላል ብዬ አስባለሁ።

ሌላው አስቀድሜ እንደጠቀስኩት የማኅበራዊ ክላስተር ያለው በዞናችን እንደመሆኑ የክልሉ ጤና ቢሮ፣ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እና ትምህርት ቢሮ ያለው በዞናችን ዋና ከተማ ተርጫ ነው።

ቀደም ሲል የተርጫ ከተማ አሁን የተላበሰውን አይነት ገጽታ አልነበረውም፤ በአሁኑ ወቅት በከተማችን በርካታ ለውጦች አሉ። በክልል ደረጃ ያሉ ቢሮዎችም ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው። ከዚህ በኋላም ለተሻለ እድገት በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን።

ከትምህርት ሴክተርም አንጻር ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አሉ። ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ያለው ተማሪ በአካባቢው (ዳውሮኛ) ቋንቋ መማር አለበት በሚል እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። ለዚህም ስኬታማነት የመጽሐፍ ሕትመቶችን ለማከናወን ሕዝቡን በማነቃነቅ ላይ እንገኛለን። ከዚህ አኳያ ለዚህ የመጽሐፍ ሕትመት ሲባል ብቻ የራሱ አካውንት ተከፍቶ ገንዘብ እየተሰበሰበ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ጨረታው አልቆ ወደ ሕትመት ውስጥ የተገባበት ደረጃ ላይ መድረስ ተችሏል። እንዲያም ሆኖ የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ አንጻር በአግባቡ ሊሰራባቸው የተገቡ ጉዳዮች መኖራቸው ሳይዘነጋ ማለት ነው።

ለምሳሌ በተለይ ዩኒቨርሲቲ የመግባት ምጣኔው በጣም ዝቅተኛ ነው። ከዚህ አንጻር ከትምህርት ጥራት ጋር ተያይዞ የሚታዩ ጉድለቶች ላይ በደንብ መስራት አለብን ወደሚለው ድምዳሜ መጥተናል። በርካታ ተማሪዎችን ዩኒቨርሲቲ ማስገባት ነበረብን። አሁን ባለው ሁኔታ እንደ ሀገር ተይዞ እየተሰራ ያለው ሥራ በጣም ጥሩ ሥራ ነው ማለት ይቻላል። ትምህርት እንደ ሀገር ተወዳዳሪ የሆነን ዜጋ ከማፍራት አንጻር አጽንዖት ተሰጥቶት እየተሰራበት ያለ ሥራ በመሆኑ ትልቅ ጉዳይ ነው። እሱን እንዳንቃለን፤ በዚያ ልክ ግን እየሰራን ነን ወይ? ተማሪውን በጥራት እያፈራን ነን ወይ? የሚለው ነገር የእኛ የቤት ሥራ ይሆናል ብዬ አምናለሁ።

አዲስ ዘመን፡- የትምህርት ጥራትን ለማምጣት ታችኛው ደረጃ ላይ መስራት ግድ ይላልና በአጸደ ሕፃናት አካባቢ ምን እየተሰራ ነው?

አቶ ዳዊት፡- ጥያቄው ትክክልና ተገቢም ነው፤ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችም አሉ። በእርግጥ ከአጸደ ሕፃናት ጋር በተያያዘ ከተማ አካባቢ ብዙም ችግር የለውም። ከተማ አካባቢ የግል ትምህርት ቤቶች አሉ። ትምህርት መስጫ ማዕከላቱ በዞን ከተማም ሆነ በወረዳ ከተማዎችም ውስጥ ይገኛሉ። ይህ ልምድ በገጠር ከተሞችም እየተስፋፋ ነው። መንግሥትም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ስለሆነ በዛ ልክ በተለይ እስከ ስድስት ዓመት ላሉ ልጆች ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ ረገድ እየተሰራ ነው።

ተማሪዎች አንደኛ ክፍል እስከሚገቡ ድረስ በጣም ትኩረት ሰጥተን መስራት አለብን በሚል ታቅደው እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አሉ። እንዲያም ሆኖ ሰፊ ጉድለት እንዳለውም በመረዳታችን በቀጣይ ሰፊ ሥራ እንዳለብን አምነን በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን።

አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር አቀፍ በግብርናው ዘርፍ እየተሰራ ያለ በርከት ያለ ሥራ እንዳለ ይታወቃል፤ ከዚያ አኳያ እንደ ዞን በተለይ ከመስኖ ስንዴ ጋር ተያይዞ ምን እየተሰራ ነው?

አቶ ዳዊት፡– እንደሚታወቀው የሀገራችን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ግብርና ነው። ለሀገር ውስጥ ምርት እድገት (GDP) ያለው አስተዋጽኦም በጣም ከፍተኛ ነው። ለጊዜው እኛ ትኩረት አድርገን እየሰራን ያለነው በበጋ መስኖ ስንዴ እና በተፋሰስ ልማት ላይ ነው። ምናልባት አሁን ካለው ሁኔታ አንጻር የተለየ ቢሆንም፤ ቀደም ሲል ሃሳቡ ሲመጣ በ2015 ዓ.ም አሁን የበጋ ስንዴ የሚባለው “ስንዴ በበጋ እንዴት ይመረታል?!” የሚል እሳቤ ነበር።

ይህ ተነሳሽነት የጠቅላይ ሚኒስትራችን ነው። ይሁንና “እንዴት ይቻላል? እንዴትስ ይታሰባል?” የሚል አተያይ ነበር። ይህ አስተሳሰብ በእኛ በአመራሩም ውስጥ የነበረ ነው። እውነት ለመናገር ጉዳዩ ከገባን በኋላ የመጡ ለውጦች አሉ። በ2015 በጀት ዓመት ላይ የእኛ እቅድ አራት ሺ 152 ሔክታር መሬት ላይ ማልማት ነው።

ይህን የ2015 በጀት ዓመት ውጤት ካየን በኋላ ለ2016 ደግሞ እቅድ ይዘናል፤ ይኸውም ያቀድነው ወደ ሶስት ሺ 445 ሔክታር መሬታ ላይ ማልማት ነው። እስካሁን ድረስ ወደ 900 ሔክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል። በእርግጥ ይህን ቁጥር ከእቅዱ አንጻር ስናየው ዝቅተኛ ነው። ይሁንና በፍጥነት እየተሰራ ይገኛል።

የግብርና ግብዓት ድጋፍን በሚመለከት የምርጥ ዘር አቅርቦት ወደ 296 ኩንታል ቀርቧል። ሌላውን ደግሞ ከአንዱ አርሶ አደር ወደሌላው አርሶ አደር በማዘዋወር ዘር እየተዘራ ይገኛል። እንደ ሀገርም የተያዘውን እቅድ ስናይ ከራሳችን ፍጆታ አልፈን ወደውጭ ሀገርም ኤክስፖርት ለማድረግ ይቻላል። ለምሳሌ በዞናችን ጌና ወረዳ ያለውን የበጋ መስኖ ስንዴ ማየት ይቻላል። በዚያ አካባቢ በጥሩ ሁኔታ መንቀሳቀስ ችለናል ማለት ይቻላል።

ሌላው ተፋሰስ ላይ የሚሰራ ሥራ ሲሆን ይህም በዞን ደረጃ ንቅናቄ ተደርጎ እየሄድንበት ያለ ተግባር ነው። ወደ ሥራ የተገባውም ከአጠቃላይ ሕዝብም 33 በመቶ በተፋሰሱ ሥራ ይሳተፋል በሚል በመለየት ነው።

አዲስ ዘመን፡- የመንገድ ዝርጋታ ፕሮጀክት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

አቶ ዳዊት፡- ትልቁ ነገር በአካባቢያችን የጸጥታ ችግር የሚባል ነገር አለመኖሩ ነው። ከዚህ አንጻር ቱሪስቶችን መሳብ ይቻላል። ለዚህም ደግሞ የቱሪስት መስህቦች አሉን። ነገር ግን ከመሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ ያለው ነገር ሲፈትነን ይሰተዋላል። አንዱ ጥያቄያችን የመንገድ ችግር ነው። ለምሳሌ ከሃላላ ኬላ እስከ ዋካ ያለው አስፓልት የታቀደው በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ነው። ብዙ ነገሩ አልቋል። ከዚህ ውጪ ያሉትን ምን ማድረግ አለብን? የሚለው ነገር ለምሳሌ የማኅበራዊ ትስስር ገጽን ብንወስድ በእሱ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል።

ማኅበራዊ ትስስር ገጽን በትክክል መጠቀም ከቻልን ጠቀሜታው በጣም ጉልህ ነው። በማኅበራዊ ትስስር ገጽ ቅስቀሳ ብቻ ሕዝቡ ገንዘብ አዋጥቶ በ2015 ዓ.ም 96 ኪሎ ሜትር መንገድ መስራት ተችሏል። ይህ ወደ ገንዘብ ሲቀየር ወደ 23 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር ነው። ለምሳሌ ዲሳ ወረዳ፣ ዛባ ወረዳ ቶጫ ወረዳ እንዲሁም ማልጋ ወረዳ ላይ የመንገድ ሥራ ተሰርቷል። በመንገድ ስራው የተሳተፈው ዳውሮ ወይም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ሰው ብቻ አይደለም። ለአብነት ማንሳት ካስፈለገ ከውጭ ሀገር ለመንገድ ሥራ በሚል ገንዘብ የላኩ አሉ። የበጀት እጥረቱም ስላለ የመንግሥትን እጅ ብቻ የምንጠብቅ ከሆነ ጉዳዩን ከባድ ያደርገዋል በሚል በዚህ መልኩ ለመንቀሳቀስ ሞክረን ጥሩ ውጤትም አግኝተንበታል።

ይህ ሥራ በመንገድ ሥራ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ሳይሆን በጤናም ሆነ ትምህርት ቤት ግንባታ ላይ የሚንጸባረቅ ነው። ለምሳሌ ጌና ወረዳ ላይ እኔ ራሴ በማህበራዊ ትስስር ገጼ ላይ መነቃቃት እንዲፈጠር አድርጌያለሁ። በአሁኑ ወቅት በቦታው የትምህርት ቤት ግንባታ በመካሄድ ላይ ይገኛል። እንዲህ ሲባል ከመንግሥት ምንም አይነት ገንዘብ ሳናወጣ ማለት ነው።

ማሪ መንሳ ወረዳ ላይ ደግሞ ከሰሞኑን ቅስቀሳ ተደርጎ በርካታ ሚሊዮን ብር በመሰብሰብ ላይ ነው። ትልቁ ችግራችን የመንገድ ችግር ነው። ይህን ችግር ደግሞ መፍታት ያለብን ሕዝቡን በማስተባበር ነው።

በለውጡ ጊዜ ትልቁ ጥያቄ የነበረው የመንገድ ጥያቄ ነው። ይኸውም አንዱ በፌዴራል መንግሥት ምላሽ የተሰጠው እና ትልቁ ጥያቄ የነበረው ወልድሃኔ-ዱራሜ-ዱርጊ የሚባለው በጣም አጭር መንገድ አለ፤ እሱ መንገድ ጅማሬ ላይ ይገኛል። ይህ መንገድ አጭር ይሁን እንጂ ደቡብ ምዕራብን ከየትኛውም አካባቢ ማገናኘት የሚችል መንገድ ነው። የታርጫ-ኦሙናዳ መንገድ ደግሞ ሥራ ከጀመረ ቆየት ብሏል። የዱራሜ-ዱርጊ በዚያ በከንባታ በኩል ጥሩ እየተሰራ ይገኛል።

አምና ከፍ ያለ የመልካም አስተዳደር ችግር ነበር። ይህም መነሻው የታርጫ-ዋካ መንገድ ነው። መንገዱ በመዘጋቱ ወላዶች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በአሁኑ ወቅት የተያዘው በፌዴራል መንግሥት ሲሆን፣ ግንባታውም በመጠናቀቅ ላይ ነው። በመሆኑም የመንገድ ችግሮች እየተፈቱ ናቸው ማለት ይቻላል።

ሕዝቡን በማነቃነቅ የተሰሩ ስራዎች አሉ። መንግሥትም በተመሳሳይ እየሰራው ያለ ነገር አለ። ከታርጫ ወደ ጭዳ የሚወስደው መንገድ አስፓልት ነበር። አጋጣሚ ሆኖ የመንገድ ስራውን የያዙ ኮንትራክተሮቹ ባለመቻላቸው እንደገና ጨረታ ወጥቶ ወደ ሥራ እየተገባ ይገኛል። በሌላ በኩል ደግሞ ትልቅ የመልካም አስተዳደር ችግር የታየበት ነው ተብሎ የሚጠቀሰው ከታርጫ ወደ ጅማ የሚወስደው መንገድ ነው። ወደ ዴዶ አካባቢ ደግሞ ጥሩ የሚባል ጅማሮ አለ ማለት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- በዞኑ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ ምን ይመስላል? ለኢንቨስተሮች ምንስ ምቹ ሁኔታ አለ?

አቶ ዳዊት፡- ኢንቨስትመንት ለኢኮኖሚ ያለው ፋይዳ ከግብርናው አይተናነስም ማለት ይቻላል። ኢንቨስትመንት ከሌለ እድገት የለም። ማደግ የሚባል ነገር አይታሰብም። ስለዚህ በገጠርም በከተማም ኢንቨስተሮችን መሳብ የግድ ነው።

በእኛ ዘንድ በከተማም ሆነ በገጠር ሰፊ የሆነ መሬት አለ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ኢንቨስተሮችም እየመጡ ናቸው።

እንደሚታወቀው ከአንድ ወረዳ አርሶ አደሩ የሚከፍለው ግብር አለ። ይህንን የክፍያ መጠን ግን አንድ ኢንቨስተር ብቻውን ይከፍለዋል። ስለዚህ ኢንቨስተሮችን መሳብ ብንችል እና ምቹ ሁኔታን ብናመቻች በአንድ ወረዳ ውስጥ ያሉ ሁሉም አርሶ አደሮች የሚከፍሉትን ግብር አንድ ኢንቨስተር መክፈል ይችላልና ፋይዳው ላቅ ያለ ነው።

በቅርቡ የጀማመርናቸው ስራዎች አሉ። እውነት ለመናገር ግን ኢንቨስተሩም እኛም ዘንድ ማነቆዎች አሉ። በአሁኑ ወቅት በገጠር ግብርና የተሳተፉና ሥራ ላይ ያሉ 32 ኢንቨስተሮች አሁን ሥራ ላይ ያሉ ናቸው። ዘጠኝ ኢንቨስተሮች ደግሞ በከተማው ሥራ ላይ ናቸው። ስራው ያለው በተለያየ ደረጃ ላይ ነው። በውሉ መሰረት በአራትና አምስት ዓመት ሰርተው የማይጨርሱም አሉ። በጥቅሉ የከተማ እና የገጠሩን ኢንቨስተሮች ብናስተውል በሥራ ላይ ያሉ 41 ናቸው። በአብዛኛውም የተሰማሩበት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ግንባታ፣ ጥምር ግብርና በተለይ በቡና እና በፍራፍሬ ዘርፍም ጭምር ነው። ሰሞኑን ከአሜሪካ የመጣች አንዲት ኢንቨስተር በአቦካዶ ላይ ብቻ ለመስራት ተዘጋጅታለች።

ይሁንና በስመ ኢንቨስተር የተቀመጡትንና ወደ ተግባር ያልገቡትን ገምግመናል። በዚህም መሰረት ስድስቱን ለይተን እንዲወጡ አድርገናል። እነዚህ አካላት መሬት ይወስዱና አጥረው የሚያስቀምጡ ናቸው። በመሆኑም አካሄዳቸውን ፈትሽን ገለል እንዲሉ አድርገናቸዋል። 41 ኢንቨስተሮች ናቸው ያልናቸውም እነዚህን ገምግመን ከለየን በኋላ ነው።

ከእነዚህ ውጪ አዲስ በቅርቡ ርክክብ የተደረገው ከሶስት ኢንቨስተሮች ጋር ነው። እነዚህ ሶስቱም ኢንቨስተሮች የሚሰሩት ገጠር ላይ ነው። ሌሎች ሶስት ኢንቨስተሮች ደግሞ በሒደት ላይ ይገኛሉ። የከተማው ደግሞ ዘጠኝ ተጨማሪ ፕሮጀክት ቀርቦ የመሬት ልየታ ላይ እንገኛለን። ከዚህ ውጪ ያለው ሌሎች ተጨማሪ ሶስት ኢንቨስተሮች እኛ ዘንድ ቀርበው የነበረ ሲሆን፣ ጉዳዩ በአሁኑ ወቅት ለክልል እንዲቀርብ ተደርጓል።

ሌላው ኢንቨስተሮች አካባቢ ያለውን ችግር ለመወያየት ሞክረናል። ጥቂት የማይባሉ መሬት ይወስዳሉ። ያለባቸው ችግር በጊዜ አልምተው አለመጨረስ ነው። ለምሳሌ አንድ ሺ ሔክታር መሬት ከወሰዱ “ሁለት እና ሶስት መቶ ሔክታር መሬት አልምቻለሁ፤ ሌላው ምቹ አይደለምና ተለዋጭ ይሰጠኝ” የሚሉ ሰበቦች ይበዛሉ። መሬት ከወሰዱ በኋላ ሶስት እና አራት ዓመት ቆይተው ምዝገባ የማያካሔዱ እንዲሁም የሥራ ግብር ሁሉ የማይከፍሉ አሉ። አንድ ኢንቨስተር መሬት ወስዶ አራት ዓመት ያህል ከቆየ በኋላ ምርቱ ማዕከላዊ ገበያ መቅረብ ይጠበቅበት ነበር። ነገር ግን እዚህ ላይ ክፍተት መግለጽ እወደዳለሁ። ቀስ አድርገው ለመውጣት የሚፈልጉትን ሰብሰብ አድርገን የመምከር እና የማስተካከል ሥራ መስራት ካልሆነ እግር በእግር ማሳደዱ ጠቀሜታ የለውም በሚል እየሰራን እንገኛለን።

ከዚህ በተቃራኒ በጥሩ ሁኔታ እያለሙ ያሉ ኢንቨስተሮች አሉ። ለምሳሌ ዲሳ፣ ጌሰራ ወረዳን መጥቀስ ይቻላል። በተመሳሳይ ተርጫ ዙሪም እንዲሁ ተጠቃሽ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ዞኑ ያለው የማዕድን ሀብት ምንድን ነው?

አቶ ዳዊት፡- በዞናችን የድንጋይ ከሰል ሀብት አለ። እኛ የምንከተለው መርህ ውጭ ሀገር የሚመረቱ ምርቶች በእኛ ሀገር ተመርተው እንዲተኩ ነው። ከዚህ አኳያ የውጭ ምንዛሬ ወጪን ከመቀነስ አንጻር ፋይዳው የላቀ ነው። በተለይ ከደቡብ አፍሪካ በከፍተኛ ወጪ የሚመጣውን የታጠበ የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ከማልማት አንጻር በሚል ታቅዶ እየተሰራ ነው።

ለምሳሌ በዞናችን የሚገኘው የኢቲ ማዕድን ልማት ካፒታሉ ወደ አምስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ነው። እስካሁን ባለው ሁኔታ የፈጀው ወደ አራት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ነው። ጠቀሜታው ምንድን ነው የሚለው ሲፈተሽ የዚህ ፋብሪካ ሥራ በአንድ ወቅት 420 ጊዜያዊ እና ቋሚ ሰራተኛ ማሰራት ነበር። ጊዜያዊ ሆኖ ስራዎች ሲቆሙ መጨመር እና መቀነስ ሊታይበት ይችላሉ። በመሆኑም የሥራ እድል ከመፍጠር አንጻር ግን ፋይዳው ከፍ ያለ ነው። ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ 400 ቋሚ ሰራተኞችን የሚፈልግ ይሆናል። በሂደት ደግሞ በርካታ ወጣቶች የሥራ እድል የሚያገኙ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም።

በሌላ በኩል ደግሞ እንደዞን በተለይ ትኩረት እንዲደረግልን የምንፈልገው በገጠር ግብርና ላይ ነው። ምክንያቱም በዞናችን ያልተነካ ሰፊ መሬት አለ። ስለዚህ ባለሀብቶች ፍራፍሬ፣ አትክልትና መሰል ነገር ላይ ቢያመርቱ እነርሱም እኛም ተጠቃሚ እንሆናለን። ቦታውም ተርጫ ዙሪያ በመሆኑ ቅርብ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሱማሌ ላንድ ጋር ያደረገችውን ስምምነት በተመለከተ እርስዎ እንደ አንድ የዞን አስተዳዳሪ እና ኢትዮጵያዊ ያለዎ አተያይ ምን ይመስላል?

አቶ ዳዊት፡– እኛ ኢትዮጵያውያን ከዛሬ 30 ዓመት በፊት የባህር በር የነበረን ነን። ያጣነው ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ነው። በአሁኑ ወቅት የሀገራችን መንግሥት ወደዚህ ውሳኔ ሲገባ ብዙዎቻችን “እንዴት ይሆናል?” በሚል ውዥንብር ውስጥ ገብተን እንደነበር የሚታወስ ነው።

በብዙዎችም ዘንድ አንዳች የሚፈጠር መጥፎ ነገር እንዳለም ስጋት እንደነበር የሚታወቅ ቢሆንም፤ ያለ አንዳች ኮሽታ ነገሮች መስመር ይዘው ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሱማሌላንድ ጋር የባህር በር ልታገኝ የሚያስችላትን ሰነድ መፈራረም ችላለች። ይህ ትልቅ ነገር ነው። ኢትዮጵም የተከተለችው ሰላማዊ የሆነ መንገድን ነው። በወቅቱ የስምምነት ሰነድ በተፈረመበት ጊዜ በዞናችን በየወረዳው እና በተለይ ተርጫ ከተማ ላይ ሕዝቡ ለደስታ መግለጫ የድጋፍ ሰልፍ በዕለቱ ወጥቶ ወደቤቱ የገባው ከምሽቱ ሶስት ሰዓት አካባቢ ነው። ይህ የሚያሳየው በሕዝቡ ዘንድ ላቅ ያለ ፍላጎት መኖሩን ነው።

ፈጣሪ ፈቅዶ ይህ የባህር በር በእጃችን እንዲገባ እንሻለን፤ ለዚህ ደግሞ የሚከፈል የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁዎች ነን። የባህር በር ተጠቃሚ መሆን ከጀመርን ደግሞ አሁን ካለንበት በላይ በኢኮኖሚያችን ለማደግ ምቹ ሁኔታ ይፈጠርልናል።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።

አቶ ዳዊት፡- የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እየሰራ ያለውን ሥራ አደንቃለሁ። በራሳችሁ በጎ ፈቃድ በዞኑ ተንቀሳቅሳችሁ ለመጎብኘት ስለመጣችሁ በራሴና በዞኑ ነዋሪዎች ስም እጅግ አመሰግናለሁ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You