ሠላም ልጆችዬ እንዴት ናችሁ? ደህና እንደሆናችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። በትምህርታችሁም ጥሩ ውጤት ለማምጣት በጣም እየጣራችሁ እንደሆነ ጥርጥር የለኝም።
መቼም ልጆችዬ መልካም የሚባሉ ነገሮችን ለመማር ብዙ አማራጮች እንዳሉ ታውቃላችሁ አይደል? ጎበዞች። ለዛሬ አንድ ጥሩ መልዕክት ያለው ታሪክ እናቀርብላችኋለን። ርዕሱ ንቦችና ዝንቦች ይሰኛል። የጻፉት ደግሞ ንጉሥ አየለ ተካ ይባላሉ ። ሙሉውን ታሪክ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
ሰዎች የንቦችን ኅብረት ጥበብና ሠራተኝነት የሰሙ ሁለት ዝንቦች በንቦች ቅናት አደረባቸው። አንድ ቀን እንደ አጋጣሚ ሁለት ዝንቦች ጎን ለጎን በጫካ ውስጥ ሲበሩ በርቀት ሁለት ንቦች በዝግታ ሲበሩ አይተው በፍጥነት ደረሱባቸው። ወዲያው ከዝንቦቹ አንዱ ወደ ንቦቹ ጠጋ አለና “እንደምን ዋላችሁ?” ብሎ ሰላምታ አቀረብላቸው። ንቦቹም በትሕትና ለሰላምታው መልስ ሰጡ።
“እባካችሁ የምናማክራችሁ ጉዳይ ስላለን አንድ ጊዜ እዚች ዛፍ ቅርንጫፍ ላይ አረፍ ብለን እንወያይ?” ብላ ከፊት በኩል ያለችው ዝንብ ንቦቹን ጠየቀቻቸው። ንቦቹም “አይ ቆሞ ለማውራት እንኳ ጊዜ የለንም። እንቸኩላለን። ግን ችግራችሁ ምንድን ነው? እስቲ ንገሩን “ የሚል መልስ ሰጡ። ወዲያው በንቦቹ መጣደፍ ውስጥ ውስጡን የተናደደችው አንዷ ዝንብ ወደፊት ቀረብ አለችና “መቼም ጉዳያችንን በዚህ በነፋስ ውስጥ መናገሩ ምስጢር መበተን ነው። ቢሆንም እናንተ ከቸኮላችሁብን ምን ይደረግ እንከተላችኋለን” አለች።
“ምን ሆናችሁ? ምን በደል ደረሰባችሁ? እስቲ ንገሩን ግዴለም?” አለች አንዷ ንብ። ከፊት በኩል የሚበረው ዝንብ ብስጭትጭት ብሎ “እኛ ዝንቦች ስንባል ያልደረሰብን ምን በደል አለ? ሰዎች እቤታቸው በገባን ወይም ዕቃቸው ላይ ባረፍን ቁጥር ያባርሩናል። በነፍሳት መግደያ አየሩን እየበከሉት ሳናስበው ይጨርሱናል። በዚህ አይነት እስካሁን ያለቀው የዝንብ ዘር ስፍር ቁጥር የለውም። ስንት ታላላቅና ደፋር የሆኑ ዝንቦች እንደ ቅጠል ረገፉ! ስንት የዝንብ ቆነጃጅት ያለ ርህራሄ ታፍነው ተገደሉ! ሌላው ቢቀር አዛውንት እንኳ ጭራ እያወናጨፉ ሽባ አድርገው ያስቀሯቸው ስንት የዝንብ እመቤቶች አሉ! ከዚህ የከፋ ምን በደል አለ!” ብሎ እንባ እየተናነቀው ተናገረ።
ወዲያው ሌላው ዝንብም ከተል አድርጎ “እኔ እኮ የምለው ሰዎች እኛን ለምን ጠሉን? “ጥዝ” እያልን ስለምንበር እረብሽናቸው ነው እንዳንል እንዲያውም የናንተ ድምፅ ከእኛ ያይላል። በዚህ ላይ እኛ እንደ እናንተ አንናደፍ። ሰዎች ግን ምን እንደታያቸው አናውቅም። ሁሌ እናንተን እያደነቁ እኛን ብቻ ያጠቁናል። የሚነፋብን የነፍሳት መግደያ መርዝ ገና ከሩቅ ሲሸተን “ኡሁ ኡሁ “ ያስብለናል። ከዚያም ያቃጥለንና እንሞታለን። እናንተን ግን ቢበዛ ጢስ ነው የሚያጥኗችሁ። ይህንን የሚያደርጉትም ለጊዜው ቀፎአችሁን እንድትለቁላቸው ነው እንጂ ሊገድሏችሁ ብለው አይደለም። ማራችሁን ቆርጠው ጢሱን ሲያጠፉት ምንም ሳትሆኑ ወደ ቀፏችሁ እንደገና በሠላም ትመለሳላችሁ…” በማለት ምሬቱን ለንቦቹ ገለጸ።
ከንቦቹ አንዷ ወደ ዝንቦቹ ዞር ብላ ሰዎች ለምን ይጠሉናል? ለምንስ ጥምድ አርገው ያዙን ነው የምትሉት አይደለም?” ስትል ጠየቀቻቸው። በዚህ ጊዜ ሁለቱም ዝንቦች “አዎ” በማለት ጮክ ባለ ድምፅ መልስ ሰጡ። “እንግዲያውስ ለምን እንደሚጠሏችሁ ማስረዳቱ ቀላል ነው። ለመሆኑ አሁን የምትመጡት ከየት ነው?” ብላ ንቢቱ ጠየቀች። አንዷ ዝንብ “እወዲያ ማዶ ካለው የቆሻሻ መጣያ “ ስትል መለሰች። “ከዚያስ በፊት የት ነበራችሁ?” ንቢቱ ድጋሚ ጠየቀች ። “ከዚያ በፊትም እታች አንድ የሞተ ከብት ነበረ እሱን ቀማምሰን ሳንጠግብ አሞራዎች አባርረውን ከመንደር አቅራቢያ መፀዳጃ ቤትም ጎራ ብለን ነበር…” ብላ ሁለተኛዋ ዝንብ በኩራት መንፈስ መለሰች።
“ታዲያ አሁን ወዴት ነው የምትሄዱት?” ንቢቱ አሁንም ጠየቀች። አሁንም ይኸው አብረን አይደል ወደላይኛው መንደር የምንሄደው? እያወቅሽ እንዴት ትጠይቂኛለሽ?” አለች ከፊት ያለችው ዝንብ። “ታዲያ ከቆሻሻ መጣያ ከጥንቡና ከሽንት ቤቱ ነካክታችሁ የያዛችሁት ቆሻሻ እላያችሁ ላይ ሆኖ እቤታቸው ድረስ ስትሄዱ እንዴት አይጠሏችሁ? እናንተ የምትውሉት ከመጥፎ ቦታ ነው። እኛ የምንውለው ግን ከጥሩ ቦታ ነው። እናንተን አጥቅተው እኛን ቢያደንቁ ያስከፋልን?” ብላ አንዷ ንብ ተናገረች።
ወዲያው ደግሞ አንዷ ዝንብ ቆጣ አለችና “እናንተ ከየት ነው የምትመጡት?” ስትል ንቦቹን ጠየቀቻቸው። “እኔ የምመጣው ከወንዝ ውሃ ቀድቼ እሷ እህቴ ደግሞ ለማር የሚሆን የጽጌረዳ አበባ ብናኝ ከአበቦች ላይ ቀስማ ነው” ስትል ንቢቱ መለሰች። “እንግዲያው እንደ እናንተ ጥሩ ነገር ካለበት ቦታ ብንውልና መልካም ብንሠራ ሰዎች ይወዱናል ማለት ነው?” ብላ ዝንቧ በድጋሚ ጠየቀች። “አዎ!” አሉ ንቦቹ በአንድነት። “ይህንን ባናደርግስ? ሌላ መፍትሔ የለውም ማለት ነው?” ዝንቦቹ ወደኋላ ቀረት ብለው ጠየቁ። ይኸን ጊዜ ንቦቹ “ይህን ባታደርጉማ የሰው ልጅ ጠላት ተብላችሁ እናንተን ይጨርሷችኋል።” ብለው ንቦቹ ፍጥነታቸውን ጨምረው ወደ ቀፏቸው በረሩ።
ልጆች ተረቱን ወደዳችሁት? እሺ ምን ተማራችሁ? ንጹሕ ቦታ መዋል ጥሩ እንደሆነ፣ ራስን ከሌሎች ጋር ማወዳደር እንደማይገባ፣ ቅናት መጥፎ እንደሆነ፣ ከንቦች ታታሪነትን፣ ጥሩ ቦታ ሲዋል ሰዎች እንደሚወዱን፣ ለወሬ እና ለአሉባልታ ጊዜ መስጠት እንደማይገባ እና ሌሎችም አላችሁ አይደል? በጣም ጎበዞች። ልጆችዬ በሚቀጥለው ሳምንት እናንተ የምትማሩበትን ነገር ለማቅረብ ቃል በመግባት እና በቸር እንድንገናኝ በመመኘት በዚሁ ተሰናበትን።
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 29 ቀን 2016 ዓ.ም