ዓመታዊ የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ክለቦች ሻምፒዮና መካሄድ ከጀመረ አምስት ቀናትን ያስቆጠረ ሲሆን በነገው ዕለት ፍጻሜውን የሚያገኝ ይሆናል። ውድድሩ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ፣ በትንሿ ሁለገብ ስታዲየምና በሱሉልታ፣ በሁለት ዲቪዚዮኖች ተከፍሎና አዲስ ስያሜያን በመያዝ በርካታ ክለቦችን እያፎካከረ ይገኛል።
ጆርካ ሁነት አዘጋጅ ለውድድሩ ከ 1 ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ ለአሸናፊ አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት እንደሚበረከትላቸው ታውቋል። ሻምፒዮናው መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም መካሄድ የጀመረ ሲሆን በክለብ አትሌቶች መካከል ከፍ ያሉ ፉክክሮችን እያስተናገደ ነገ በድምቅት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ባለፉት አምስት ቀናት በተካሄዱ የማጣሪያና የፍጻሜ ውድድሮች የተለያዩ ውጤቶች ተመዝግበዋል። ከአጭር ርቀት እስከ ረጅም ርቀትና የሜዳ ተግባራት ውድድሮችን አካቶ የሚካሄደው ይህ ሻምፒዮና በየዘርፉ ብዙ አትሌቶችን እያፎካከረ ይገኛል። የተወሰኑት የሜዳ ተግባራት ውድድሮች በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየምና በሱሉልታ እየተካሄዱ ሲሆን የሩጫና የተቀሩት ተግባራት በወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሜዳ ላይ እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በአንደኛና በሁለተኛ ዲቪዚዮን ተከፍሎ እየተካሄደ በሚገኘው ውድድር ክለቦች በርካታ አትሌቶች አሰልፈው ውድድራቸውን እያከናወኑ ናቸው። በአንደኛ ዲቪዚዮን 7 ክለቦችና በሁለተኛ ዲቪዚዮን 9 ክለቦች በአጠቃላይ 16 ክለቦች በውድድሩ እየተሳተፉ ይገኛሉ። በሁለቱም ዲቪዚዮኖች 600 ሴትና ወንድ አትሌቶች እየተካፈሉ ነው። የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ አትሌቶችም በአንደኛ ዲቪዚዮን ተካተው ውድድራቸውን እያከነወኑ እንደሆነ ተጠቅሷል።
ውድድሩ በአንደኛ ዲቪዚዮን ወንዶች 5 ሺ ሜትር ፍጻሜ የተጀመረ ሲሆን ዘነበ አየለ ከፌዴራል ማረሚያ፣ ግዛቸው ሙሴ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ባቲ ቦራ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ተከታትለው በመግባት ቀዳሚዎቹን ደረጃዎች ይዘው አጠናቀዋል። ውድድሩ ባለፈው ማክሰኞ ሲቀጥል በ 2ኛ ዲቪዚዮን ወንዶችና ሴቶች 400 ሜትር፣ ርዝመት ዝላይ ወንዶችና ሴቶች፣ በ1ኛ ዲቪዚዮን ሴቶች 10 ሺ ሜትር፣ 100 ሜትር ሴቶችና ወንዶች፣ 400 ሜትር ሴቶች ርዝመት ዝላይ ወንዶች የፍጻሜ ውድድሮች ተደርገዋል።
በሻምፒዮናው የረቡዕ እለት ውሎም 1ኛ ዲቪዚዮን 10 ሺ ሜትር ወንዶች፣ ሱሉስ ዝላይ ሴቶች እና 2ኛ ዲቪዚዮን ወንዶች ዲስከስ ውርወራ የፍጻሜ ውድድሮች ተከናውነዋል። ከትላንት በስቲያ በተደረጉ 2ኛ ዲቪዚዮን 110 ሜትር ወንዶች፣ 100 ሜትር መሰናክል ሴቶች፣ 1ኛ ዲቪዚዮን 800 ሜትር ሴቶች፣ 100 ሜትር መሰናክል ሴቶች ውድድሮች ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። ትናንትና እንዲሁ በርካታ የሩጫና ሜዳ ተግባራት ውድድሮች ተከናውነው ተፈጽመዋል።
የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አትሌት መልካሙ ተገኝ፣ የውድድሩ ዋና ዓላማ ሀገርን የሚወክሉ አትሌቶችን መፍጠር፣ ክለብ የሌላቸውን አትሌቶች ወደ ክለብ ማምጣትና ውድድሩ ዓመታዊ በመሆኑ እንዳይቋረጥ አጠናክሮ ማስቀጠል መሆኑን ተናግሯል። በውድድሩ የሚሳተፉ አትሌቶች የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በሚያዘጋጀው ውድድሮች እንዲያልፉና ጠንካራና ሀገርን መወከል እንዲችሉ እንደሆነም አስረድቷል።
ፌዴሬሽኑ ውድድሩ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት መድረጉን ገልጾ፣ ከነዚህም መካከል ከሞሐ ለስላሳ መጠጦች ጋር የነበረው የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ጊዜ በመጠናቀቁ ውድድሩን በገንዘብ የሚደግፍ ተቋም ማግኘትና አብሮ መሥራት ነበር። በዚህም መሠረት ከጆርካ ሁነት አዘጋጅ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጋር ለመሥራት ውል ገብቶ የ5 ዓመት ስምምነት ተፈራርማል። በዚህም መሠረት ድርጅቱ ለውድድሩ ከ1.8 ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ ውድድሩ ስፖንሰር መደረጉ ተነግሯል። በተጨማሪም የተደረገው ቅደመ ዝግጅት ከክለቦች፤ ከባለድርሻ አካላት ጋር የነበረው ግንኙነት የተጠናከረና ስኬታማ መሆኑን ጨምሮ ገልጿል። የዘንድሮውን ውድድር ለየት የሚያደርገው በየዲቪዚዮኑ ለአሸናፊ አትሌቶች ሽልማት መዘጋጀቱን እንደሆነም ፕሬዚዳንቱ አስረድቷል።
በዚህም መሠረት በአንደኛ ዲቪዚዮን 1ኛ ሆነው የሚያጠናቅቁ አትሌቶች 3 ሺ ብር፣ 2ኛ የሚወጡ አትሌቶች 2ሺ፣ 3ኛ ለሚወጡ አትሌቶች 1 ሺ ብር ሽልማት ይበረከትላቸዋል። በሁለተኛ ዲቪዚን 1ኛ ለሚወጡ 2ሺ፣ 2ኛ ለሚወጡ 1 ሺ 500፣ 3ኛ 1 ሺ ብር የገንዘብ ሽልማት ይበረከታል። ከ100 ሜትር እስከ 10 ሺና የሜዳ ተግባራት በአጠቃላይ ከ100 በላይ አትሌቶች ይሸለማሉ።
ውድድሩ ዛሬም ቀጥሎ የሚካሄድ ሲሆን የእርምጃ ውድድርን ጨምሮ በርካታ የሩጫና የሜዳ ተግባራት ውድድሮች ፍጻሜና ግማሽ ፍጻሜ የሚካሄድ ይሆናል። በሁለቱም ዲቪዚዮኖች እርምጃ ውድድር 5ሺና 10ሺ፣ መዶሻ ውርወራ፣ ከፍታ ዝላይ፣ 200፣ 1 ሺ 500 ሜትር ፍጻሜ፤400 ሜትር መሰናክልና የዱላ ቅብብል ግማሽ ፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ። ውድድሩ ነገ ሲጠናቀቅ ከፍታ ዝላይ፣ 400 ሜትር መሰናክል፣ 5 ሺ፣ 3 ሺ ሜትር መሰናክል፣ 1 ሺ 500 ሜትር እና የዱላ ቅብብል ውድድሮችን ይካሄዳሉ።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 28 ቀን 2016 ዓ.ም