ከፈረሳው በስተጀርባ የደራው ገበያ

አዱ ገነት ፈርሳ እየተሠራች ስለመሆኗ እየተመለከትን ነው። ከመሐል እምብርቷ፣ አራዳ ተነስቶ በአራቱም አቅጣጫ እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ በመሄድ ላይ ያለውን የኮሪደር ልማትና ሂደቱን እለት በእለት እየተከታተልን እንገኛለን። በ”ነብስ ይማር” የተለየናት እናት ፒያሳ ሙሉ ለሙሉ ትፍረስ እንጂ ከበፊቱ ባልተናነሰ የከፍተኛ ሕዝብ ቁጥር መናኸሪያነቷን ገና አላቆመችም። ያላትን መስጠቷን ገና “እምቢኝ”፣ “አጉራህ ጠናኝ” አላለችም። የባሕርይ ነውና፣ ያው እንደ ልማዷ ያላትን ሁሉ “እንካችሁ” በማለት ላይ ስለመሆኗ እላይዋ ላይ የሚርመሰመሰው “ማዕድን ፈላጊ” (ቆፋሪም ካለ እንደዛው) በሙሉ ምስክር ነው።

አንድ ፈራሽ አካል ባለበት ሁሉ፤ ከአስፈራሽ፣ አፍራሽ፣ ፍራሽና ፍርስራሽ ቀጥሎ ማን በስፍራው እንደሚገኝ እኛ ልምድ ያለን የከተማ ነዋሪዎች አሳምረን የምናውቀው ጉዳይ ነው። “ጭስ ካለ እሳት አለ” እንደሚባለው ሁሉ፤ ፍራሽና ፍርስራሽ ካለ ማን እዛ እንዳለ ይታወቃል። ለምን እዛ እንዳለም ይታወቃል። የዛሬው ትዝብታችንም ያው የሚታወቀውን እንደገና የማሳወቅ ጉዳይ ሆኖ፣ ልዩነቱ የአሁኑ ፈራሽ፣ አስፈራሽ፣ አፍራሽ እና ፍራሽ ብቻ ሳይሆኑ እነዛ፣ ገና የመጀመሪያዋ ምስማር ከመዶሻና ፋስ ጋር ስትገናኝና ቆርቆሮው “ቋ” ማለት ሲጀምር “ከች በኮረኮንች” ስለሚሉቱ ሰፋ አድርገን መሄዳችን ነው።

እንደምንመለከተው አዲስ አበባ በኮሪደር ልማቱ መሀሏ ባዶ እየሆነ ነው። መሐሏ ባዶ የመደረግ፣ መሆኗን ጉዳይ በተመለከተ ያለው የሕዝብ አስተያየት የዛኑ ያህል ዥንጉርጉር ቢሆንም፣ ለፒያሳ ልጆችና ወዳጆች ግን ሀዘኑ ስለ መበርታቱ በማህበራዊ ሚዲያዎች ያለ እረፍት የሚሄዱት ልዩ ልዩ አስተያየቶች እና አስያየቶች ናቸው። “ታሪክ ወደመ” የሚለው እንዳለ ሆኖ “ሊያልፍላት ነው” የሚለውም በመልስ ምት እየሄደ ይገኛል። ይህ ወደ ፊት የምናየው ሆኖ ለዛሬው ከፈረሳው በስተጀርባ ወደ ደራው ገበያ እንመለስ።

ብዙዎቻችን ከግንባታ ሥራዎች ጋር ያሉትን (መሐንዲስ፣ አናጢ፣ ግንበኛ፣ ሾፌር ወዘተ) ነው ትኩረት ሰጥተን፤ ልብ ብለን የምናያቸው። ልክ ነው። በአንድ (መልሶም ይሁን ሌላ) ግንባታ ወቅት ዋናዎቹ አክተሮች እነሱ ናቸው። በመሆኑም የቅድሚያ ትኩረቶቻችንን ቢያገኙ የሚገርም ሊሆን አይችልም። ነገር ግን፣ ከእነሱ ባልተናነሰ ትኩረቶቻችንን ሊስቡ የሚገቡ ብዙ አካላት እያሉ አንዳቸውንም ልብ አለማለታችን ነው ችግሩ። አዎ፣ ብዙ አሉ። ብዙ ቢኖሩም ለዛሬ “ማዕድን ፈላጊዎቹ” ላይ አተኩረን ትንሽ እንወያያለን።

ስሙ (ፖታሽ፣ ብረት፣ ወርቅ ∙ ∙ ∙) ይለያይ እንጂ ተቆፍሮ የሚወጣ ሁሉ ማዕድን ነው፤ የተቀበረ ካልሆነ በስተቀር። ለምሳሌ ካሮት “ቫይታሚን ኤ” እንደ ሆነው ሁሉ፤ የከርሰ ምድር ውሃም ማዕድን ነው ማለታችን ነው። ለጊዜው ፒያሳም ሆነ ሌሎች የፈረሱና እየፈረሱ ያሉ፣ ምዕተ ዓመትን የተሻገሩ ሰፈሮች በውስጣቸው ምን ምን አይነት ማዕድናት እንዳሉ ለጊዜው ባናውቅም፤ ከመፍረሳቸው በፊት ያለ/የሌለውን ይመረምር ዘንድ ተቋቁሞ አስፈላጊውን ምርመራ ያደረገ አካል (ጥምር ኮሚቴ) ካለ (ኖሮ ከሆነ) ወደ ፊት በሪፖርቱ የሚያሰማን ሆኖ፤ ለዛሬው ግን ከተፈጥሮ ማዕድናት ባልተናነሰ በፍርስራሽ ቦታዎች እየተፈለጉ ያሉ ማዕድናት ብዛታቸው የትየለሌ፤ አይነታቸው ከሰማይ ኮኮብ፣ ከምድር አሸዋ የሚበልጥ ሆኖ ይታያል።

ብረት፣ እንጨት፣ ቆርቆሮ፣ በር፣ መስኮት እና ፈራሹ አካባቢ ያፈራቸው ሁሉ በአፍራሽ ግብረ ኃይል መፍረሳቸውን ተከትሎ በተደራጁ ኃይላት ዘንድ እጅጉን ተፈላጊዎች ናቸው። በደላሎች ዐይን ስር የመውደቃቸውና በእነሱ ጆሮ ውስጥ የመጥለቃቸው ዕድል ከ100 በመቶ በላይ ሲሆን፤ ከዶዘርና ቡልዶዘር ቀጥሎ ወደ አካባቢው የሚተመው ኃይል በግብረ ኃይል እንጂ በነጠላ አንድ፣ ሁለት ∙ ∙ ∙ ተብሎ የሚቆጠር አይደለም።

በተለምዶ “ቆሬ ያለው” ከምንለው ኃይል ጀምሮ አካባቢው በ”ማዕድን ፈላጊዎች” ሲወረር ደቂቃ አይፈጅበትም። ማዳበሪያ ባዘሉ፤ መዶሻ ትከሻቸው ላይ ባጋደሙ፤ ማሰሪያ ገመድ ወገባቸው ላይ ሸብ ባደረጉ፤ ሌሎች በርካታ አይነት መፍቻዎችን በየ ጎና ጎናቸው በሸጎጡ ኃይላት በቁጥጥር ስር ሲውል ሊወስድ የሚችለው ጊዜ ቢኖር “አፍታ” ብቻ ነው።

እነዚህን ባሉበት ትተን ወደ ተደራጁት እንሂድ።

አራዳ ክፍለ ከተማ ጽሕፈት ቤትን ከፊቱ አድርጎ እየፈረሰ ያለን አካባቢ ለመመልከት ጎራ አልኩኝ። እዛ አካባቢ ይሄ ሁሉ ቤት መኖሩን ልብ ብየ አላቅም ነበር፡፡ ትርምሱ ሌላ ነው። እነዶዘርና ቡልዶዘር ሥራቸውን በሰዓቱ አጠናቅቀው የሄዱ ስለመሆናቸው ቦታው ላይ አለመኖራቸው ምስክር ነው። ወደ ትርምሱ ጠጋ ብየ መመልከት ምርጫዬ ሆነና ጠጋ አልኩ። ሠላማዊ ትርምሱ የጉድ ነው። በአይነት በአይነት የተደራጁ ግብረ ኃይላት በየተደራጁበት የሥራ መስክ (ቆርቆሮ ሰብሳቢው በቆርቆሮ፣ እንጨቱ በእንጨት፣ መስኮትና በሩም እንዳዛው፤ ነቃይና መንጋዩም በየቦታው) ያከማቹትን ለገበያ ምቹ በሆነ ስፍራ ላይ አድርገው ተቀምጠዋል። ገዥው ከያለበት መጥቷል። የተደራጁት ኃይላት ግንኙነታቸው ከደላላ እንጂ ከገዥ ጋር ባለ መሆኑ ፍልሚያውን የሚመሩ ደላሎች ናቸው። የእርስ በእርስ መወራረፉ እንዳለ ሆኖ “አንተ ሰውዬ እዚህ ምን አመጣህ፣ አንተ የራስህ ቦታ አለህ አይደለም?” የሚለውን ጨምሮ የደላሎች የእርስ በእርስ የገበያ ጦርነት በራሱ የሚናገረው እንዳለ ሆኖ፣ ከእነሱ ዝቅ ብሎና ጣራ ላይ ወጥቶ የሚያፈርሰውን ግብረ ኃይል ለተመለከተም ከፈረሳውም ሆነ አስፈራሽና አፍራሽ ባልተናነሰ በከፍተኛ ደረጃ የደራ ገበያ ስለ መኖሩ ማረጋገጫ ነው።

በዚሁ አካባቢ ተዘዋውሬ በምመለከትበት ወቅት ያገኘሁትና በጥቂቱም ቢሆን የሆድ የሆዱን (ከብርዱ ጀምሮ) ያጫወተኝ ወጣት እንደሚለው ከሆነ፣ ይህ እዚህ ጋ ከአስፈራሽና አፍራሽ ጎን በመሆን ፍርስራሾችን ለቅሞ፣ ሰብስቦና ለገበያ አቅርቦ ተጠቃሚ መሆን እንዲህ በቀላሉ የሚገኝ ነገር (እድል) አይደለም።

ወጣቱ እንደሚለው ከሆነ፣ በቅድሚያ በዓይነት መደራጀት የግድ ይሆናል። ከተደራጁ በኋላ ለአደራጀው መንግሥታዊ አካል ብር 7000 መክፈል ግዴታ ነው። ከዛ ባለ ፍቃድ መሆን ይከተላል። አሠራሩ ይህንን ይመስላል።

ይኸው ወጣት እንደሚለው ከሆነ ደላሎችም ዝም ብለው አይደለም እንደዚህ አይነት ወከባ የሚፈጥሩት፤ አሁን ለምሳሌ ይሄ (በእጁ እያሳየኝ) 15 ሺህ ብር ቢሸጥ ከእኛም ከገዥውም ብለው ሦስት አራት ሺህ ብር ያገኛሉ።

“አሁን ለምን ቆምክ፤ ለምን አትሰበስቡም?” ለሚለው ጥያቄም “ሰለቸን” የሚል መልስ ነበር የሰጠው።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 28 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You