‹‹ተመካክረን ሀገራችንን ካለችበት ችግር ውስጥ እናውጣ የሚል ትልቅ ቁርጠኝነት ሕዝቡ ዘንድ አለ›› – አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር)የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

ሀገራዊ ምክክር ስር የሰደዱ ሀገራዊ አለመግባባቶችን፣ ግጭቶችን ለመፍታት ጥቅም ላይ የሚውል አንድ ዓይነት የግጭት መፍቻ ዘዴ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ድርድር (negotiation) የተለያየ ጥቅምና ፍላጎት የሚወክሉ አካላት በሰጥቶ መቀበል መርህ ልዩነቶቻቸውን የሚፈቱበት ዘዴ ነው።

ሌላው እርቅ (reconciliation) ሲሆን የደረሰ በደል ላይ ጥልቅ ውይይት ማድረግና በመተማመን ይቅር በመባባል ስምምነትን ማስፈኛ ዘዴ ነው። የማስማማት (mediation) የግጭት መፍቻ ዘዴ በሶስተኛ ወገን አማካኝነት ልዩነትን ለማስወገድ ጥቅም ላይ የሚውል ነው።

ከግጭት መፍቻ ዘዴዎች መካከል አንዱ የሆነውን ሀገራዊ ምክክር (national dialogue) ለማድረግ እንዲቻል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ አፅድቆ ወደ ሥራ ከገባ ከሁለት ዓመታት በላይ ተቆጥሯል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ምን ዓይነት ተግባራትን አከናውኗል? በውጤት ደረጃስ ያለበትና አሁን እየሠራ ያለውን ሥራ በተመለከተ ከኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር አምባዬ ኦጋቶ ጋር ቆይታን አድርገናል ።

አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የምክክር ዓይነት ምን የተለየ ገጽታ አለው?

ዶክተር አምባዬ፡- የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ተግባራዊ ያደረገው ዘዴ አካታች ሀገራዊ ምክክርን ሲሆን ሀገራዊ ምክክር በሀገራችን ወቅታዊና ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ተመራጭ ግጭት መፍቻ ዘዴ ነው። ሀገራዊ ምክክር አንድ ወጥ ሃሳብ እና አንድ ወገን ብቻውን የሚመክርበት ሳይሆን በየአጀንዳው የተለያዩ ሃሳቦች፣ ጥቅሞች፣ ፍላጎቶችና መብቶች የሚወከሉበትና ምክክር የሚደረግበት፣ እነዚህን ሃሳቦች የሚያንጸባርቁ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚወከሉበት ብዝሀነት ያለው መድረክ ስለመሆኑም ተደጋግሞ ይነሳል።

በዚህም በሀገራችን የሚስተዋሉ መሠረታዊ ችግሮችን እና ልዩነቶችን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ በማምጣት፣ የተለያዩ ጥቅሞችና የህብረተሰብ ክፍሎች በሚሳተፉበት ምክክር የጋራ መፍትሔ ለማምጣት የተመረጠና ጥቅም ላይ የሚውል ዘዴ ሆኖ እየተተገበረ ነው።

የሀገራዊ ምክክር ጥቅም በዋናነት ግጭትን ለማስወገድ ፣ የፖለቲካና ዴሞክራሲ ሽግግርን ለማሳለጥ የሚጠቅም ነው። በተለይም ግጭቶችን ለመከላከል፣ ለማስተዳደር እና ለመፍታት ዓይነተኛ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል። በዓለም አቀፍ ደረጃም በበርካታ ሀገራት በተለያዩ ጊዜያት በተለያየ መነሻ ምክንያቶች ሀገራዊ ምክክሮችን አካሂደዋል። የተወሰኑት የተሳካላቸው ሲሆን በተወሰኑት የሚፈለገውን ግብ ሳያሳካ ቀርቷል።

የሀገራዊ ምክክር አላማዎች መሠረታዊ የሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶችን በማጥበብ መግባባትን ለመፍጠር፣ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከልና ከመንግሥት ጋር ያለን ግንኙነት ለማሻሻል፣ መተማመንን ለማጎልበት፣ የመነጋገር የፖለቲካ ባህልን ለማስፈን ፣ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት፣ ጠንካራና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት በጋራ ለመገንባት፣ ልዩነቶችን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለመፍታት፣ የዴሞክራሲና የፖለቲካ ሽግግር ለማስቻል፣ ልማትን ለማፋጠን የሚጠቀሱ ናቸው።

በተጨማሪም የሀገራዊ ምክክር አላማ መሠረታዊ አለመግባባቶች፣ ልዩነቶችና ግጭቶች ምን እንደሆኑና መሠረታዊ ምክንያታቸውን መለየት እና በእነዚህ ላይ ልዩነቶችን በምክንያታዊ፣ በሰለጠነ፣ በመቻቻል መንገድ የጋራ መግባባቶች ላይ ለመድረስ እና የግጭቶቹ መንስኤ የሆኑ ልዩነቶችን ለማጥበብ ካልሆነም በልዩነቶች ላይ በመስማማት በሃሳብ ለመለያየት ብሎም ይህን የሃሳብ ልዩነት በዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊና ህጋዊ መንገድ መፍታት የሚቻልበትን ዘዴ በጋራ በመቀየስ ለመግባባት የጋራ ጥረት የሚደረግበት መድረክ ነው።

ሀገራዊ ምክክር ዓላማን ለማሳካት ምክክሩ ሊከተላቸው የሚገቡ መርሆች እንዳሉት በግልጽ የተቀመጠ ሲሆን በዚህም መሠረት አካታችነት፣ ግልፅነት፣ ተአማኒነት፣ መቻቻልና እና መከባበር፣ ምክንያታዊነት፣ የምክረ ሃሳቦች ተግባራዊነት እና አውድ ተኮርነት፣ ገለልተኛ አመቻች፣ የአጀንዳ ጥልቀትና አግባብነት፣ ዴሞክራሲያዊነት፣ የሕግ የበላይነት ይጠቀሳሉ። ከዚህ አንፃር ኮሚሽኑ ተሳታፊዎች በቅን ልቦና እንዲሳተፉ እና ፍትሀዊነት መርሆችን ሊያካትት ይችላል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት በቅድመ ዝግጅት፣ በዝግጅትና በትግበራ ምዕራፍ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑም የሚታወቅ ነው።

ኮሚሽኑ ተሳታፊዎች የተወከሉበትን የማኅበረሰብ ክፍል አውድ በተመለከተ በቂ ግንዛቤ ያዳበሩ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ላይ ሲሆን ለዚህም ገለልተኛ ተቋማትና አጋሮችን በማሳተፍ በርካታ ሥራዎችንም እያከናወነ ይገኛል። ወደፊትም ብዙ ተግባራትን እንደሚከናውን ይጠበቃል።

በአሁኑ ሰዓት ተሳታፊዎች የሀገራዊ ምክክር ምንነትና አስፈላጊነት እንዲሁም የአመራረጥ ሂደቱን በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ማብራሪያ እየተደረገላቸው ነው።

ለምሳሌ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረኮች ላይ የሚሳተፉ ተወካዮች የውክልና ሂደት በዚህ ባሳለፍነው ሳምንት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ኮሚሽኑ አሳውቋል። በ12 ዞኖች ከሚገኙ 97 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች 9ሺ3መቶ የሚሆኑ ዜጎች ተሳታፊ ሆነዋል።

በቀጣይ በሚካሄዱ የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረኮች ላይ ከ1ሺ 5መቶ የማያንሱ ተወካዮች በክልል ደረጃ በሚካሄዱ የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረኮች ላይ የክልሉን ነዋሪ ወክለው ይሳተፋሉ ተብሎም ይጠበቃል።

በተመሳሳይ በአማራ ክልልም ማስቀጠል በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ውይይት ተደርጓል።

በአዲስ አበባ በተዘጋጀው ሀገር አቀፍ መድረክ ለአጀንዳ አሰባሰብ የሚረዱ ግብዓቶች ተገኝተዋል።

የአጀንዳ ማሰባሰቢያና ለምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ ተወካዮችን የመምረጫ ሥርዓት ላይ ግብዓት ለማሰባሰብ የተዘጋጀው ሀገር አቀፍ መድረክም ነበር። በመድረኩ 250 የሚሆኑ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ከመንግሥት፣ ከተለያዩ ማህበራት፣ ከሚዲያና ኪነጥበብ እንዲሁም ሌሎች ዘርፎች ላይ ያሉ አካላት ተሳታፊ እንዲሆኑበትም ተደርጓል።

በአጀንዳ ማሰባሰቡ ሂደት ላይ እገዛ የሚያደርጉ አወያዮችን ማለትም በዩኒቨርሲቲ በመምህርነት እያገለገሉ ያሉ ፤ የማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል ያልሆኑ ፤ ዩኒቨርሲቲው በሚገኝበት ክልል ቋንቋና በአማርኛ ቋንቋ ክህሎት ያላቸው ፤ ለኮሚሽኑ የሚያስፈልገውን የሥራ ጊዜ መስጠት የሚችሉ፤ በኮሚሽኑ የተዘጋጀውን የሞደሬተሮች መመሪያ የሚያከብሩ፤ መሆናቸው ግምት ውስጥ ገብቶ የተለዩ ናቸው።

የተወካዮች ልየታ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ተደራሽነትን ለማስፋት የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው። ከባቢያዊና ሀገር አቀፍ ሚዲያዎችን በመጠቀም መረጃዎች ተደራሽ እንዲሆኑ እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው።

ሚዲያዎች በዜና መልክ መረጃዎችን ከመስጠት በተጨማሪ ግንዛቤ የሚስጨብጡና የተለዩ ሃሳቦች የተንሸራሸረባቸው ሰፋፊ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ ጥረትም እያደረጉ ነው።

አዲስ ዘመን ፦ የኮሚሽኑ አሁናዊ ቁመና ምን ይመስላል ? የትኛው የዝግጅት ምዕራፍ ላይ ነውስ ማለት ይቻላል?

ዶክተር አምባዬ ፦ ኮሚሽኑ በአዋጅ ተቋቁሞ ሥልጣንና ኃላፊነቱ ተደንግጎ ከተሰጠው ቀንና ጊዜ አንስቶ በርካታ ሥራዎችን በተለያዩ አካባቢዎች ላይ አከናውኗል፤ ከዚህ አንጻርም የኮሚሽኑ ሥራ አንድ ቦታ ላይ የቆመና በዚህን ቦታና ጊዜ ይህንን ሰርቷል ብሎ ለመናገር የሚያመቹ አይደሉም። በመሆኑም በዚህ ምዕራፍ ይህንን ሰርተናልና ወደቀጣዩ እንሄዳለን ማለት ሳይሆን ሁልጊዜም ቢሆን ወደፊትም ወደኋላም እየሄድን የምንሰራቸው ሥራዎች ብዙ ናቸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እንግዲህ አሁን ላይ ዋና ሥራችን አድርገን ያለነው አጀንዳን የማሰባሰብ ሥራ በተለያዩ ክልሎችና ወረዳዎች ላይ ነው። ይህም ከሞላ ጎደል በሁሉም ክልሎች ለማካሄድ ተሞክሯል። በነገራችን ላይ ትግራይና አማራ ክልልን አያካትትም። ነገር ግን በሌሎች ክልሎች ላይ እየሄድን የሠራነው የአጀንዳ ቀረጻ ሥራ ውጤታማ ነበር ማለት ከመቻሉም በላይ አሁን ላይ ደግሞ ወደማገባደዱ ደረጃ ላይ ደርሰናል።

ኦሮሚያ ላይም በሚቀጥለው ሳምንት ሰርተን እናጠናቅቃለን ፤ ሶማሌ ክልል ላይ የኮሌራ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ካልሆነ በቀር ሁሉንም ለማዳረስ ተሞክሯል ፤ ደቡብም በተመሳሳይ ጥሩ ሥራ እየተሠራበት ያለ አካባቢ ነው።

ይህ ትልቁ ሥራ በመሆኑ በተለይም በወረዳ ደረጃ የሚደረገውን ሥራ እየሰራንባቸው ባሉ ክልሎች ከ90 በመቶ በላይ በሆነ መልኩ ውጤታማ ነን ማለት ይቻላል። አማራ ክልል ላይ ለረጅም ጊዜያት ሥራዎች ተሰርተዋል፤ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ ላይ ባጋጠሙ ችግሮች ምክንያት በወረዳ ደረጃ ያሉትን ተሳታፊዎች ለመምረጥ አስቸጋሪ ሆኗል። ሠይህም ቢሆን ግን ሥራው እንዲቀጥል እያደረግን የክልሉ ነዋሪ ሆነው ለኮሚሽኑ ሥራ ተባባሪ የሆኑ አካላትን የመለየት ተግባርም እያከናወንን ነው።

በእዚህም በእስከ አሁኑ ሂደት ሰባት ወይም ስምንት አካላት ተገኝተው እነሱን የመለየት ሥራ እየተሠራ ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን እነዚህን ተባባሪ አካላት የሚያሰለጥኑልንን ሃያ ስድስት የዩኒቨርሲቲ መምህራኖችን (ፕሮፌሰሮችን) አሰልጥነናል። በመሆኑም አሁን ላይ ካለው የክልሉ መንግሥት እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር ላይ ከመሆናችንም በላይ የክልሉን የጸጥታ ሁኔታም እያረጋገጥን ሥራዎችን እየሠራን ነው። ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያት ደግሞ በየወረዳ ከተሞች ላይ ሰዎች ስለምናጓጉዙ ትራንስፖርት እንዲሁም አስፈላጊው ሎጂስቲክ እንዳለ ካረጋገጥን በኋላ መላክ ስለሚኖርብን ነው። ይህንን ሳናረጋግጥ መላካችንም በራሱ የችግር ምንጭ ሊሆን ስለሚችል በከፍተኛ ጥንቃቀቄ እየሠራን ነው።

በሌላ በኩልም በትግራይ ክልል በተለያዩ ደረጃዎች አመራሮችን እያገኘን ነበር። በተመሳሳይም ሌሎች የሲቪክ ማህበራትንም በማግኘት ስለሁኔታው እየተወያየን ቆይተናል በአሁኑ ወቅት እዛም ያለው ሁኔታ ቢሆን ተስፋ ሰጪ ከመሆኑም በላይ አንዳንድ ችግሮችም ሙሉ በሙሉ ከተቀረፉ በኋላ ኮሚሽኑ በአፋጣኝ ወደሥራ ይገባል። ኮሚሽኑ ይህንን ሥራ ሲሰራ ጎን ለጎንም የሚሰራቸው በርካታ ሥራዎች ያሉት በመሆኑ እነሱም በታሰበው ልክ እየተከናወኑ ነው።

አዲስ ዘመን ፦ ኮሚሽኑ በየክልሉ የተለየዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸውልናል፤ ከዚህ ጋር እንግዲህ አሁን ላይ አጀንዳ የማሰባሰቡ ሥራም የሚሠራበት ወቅት መሆኑ ይታወቃልና በዚህ ረገድ ሥራችሁ ምን ያህል ውጤታማ ነው ?

ዶክተር አምባዬ ፦ በአሁኑ ወቅት የተሳታፊዎች መረጣ እያደረግን ነው። እያደረግንም ብቻ ሳይሆን ወደማገባደዱ ደረጃ ላይ ደርሰናል። ይህ ደግሞ የኮሚሽኑ ትልቁ ሥራ ነው። በወረዳ ደረጃ ሀገራዊ ምክክሩ ላይ አጀንዳ የሚያቀርቡ የሚያቀብሉ ሰዎችን ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ውስጥ ያሉትን ለረጅም ጊዜ እያነጋገርን ነበር፤ ይህም የሥራው አካል ሆኖ አሁን ላይ ፍጻሜውን አግኝቷል።

በዚህ ተጓዳኝ ስንሄድ ደግሞ በክልሎች ተቋማት አሉ። ለምሳሌ የሚዲያ፤ የሲቪክ ማህበረሰብ ፤ መንግሥት፤ የሃይማኖት ተቋማት፤ ወጣቶች ፤ የአካል ጉዳተኞች በጠቅላላው ከሃያ በላይ የሚሆኑ ተቋማቶች አሉ፤ እነዚህ ተቋማት ወክለዋቸው በክልል መድረኮች ላይ የሚሳተፉ አካላትን እንዲልኩ በደብዳቤ ጥሪ ተላልፎላቸዋል። በመሆኑም ከአማራና ትግራይ ክልል ውጭ ያሉት ተሳታፊዎቻቸው እነማን እንደሆኑ ዝርዝር አቅርበዋል።

በዚህም እያንዳንዱን (የመጡበትን ) ክልል ወክለው በሀገራዊና ክልላዊ የምክክር መድረክ ላይ አጀንዳን አምጥተው የሚመካከሩ አካላትን አሁን አግኝተናል ይህም የዝግጅት ሂደቱ አንዱ አካል ነው። አሁን ላይ ይህ አካሄድ በሚፈለገው ልክ ከሄደ በኋላ ቀጣዩን እንጀምራለን።

አዲስ ዘመን ፦ እዚህ ላይ ግን ዶክተር እንደው በዚህ ሂደት ላይ የሕዝቡን ስሜት እንዴት አያችሁት? ምን ታዘባችሁ?

ዶክተር አምባዬ ፦ አሁን የምናገረውም የተጠናቀረ መረጃ ባይሆንም እንኳን በእስከ አሁኑ ሂደት ከ90 ሺ በላይ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን አነጋግረናል። ይህ ደግሞ በምናዘጋጃቸው ትልልቅ ጉባኤዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በየትምህርት ክፍሉና በአነስተኛ ሁኔታ ተሰብስበን ያወራነውን ሁሉ ይጨምራል። እንግዲህ ከዚህ ተነስተን የሕዝቡ ስሜት ስንገልጸው በጣም የሚገርም ጉጉት እንዳለው ተረድተናል። ጉጉት ብቻም ሳይሆን በቶሎ ተመካክረን ተነጋግረን ሀገራችንን ካለችበት ችግር ውስጥ እናውጣ የሚልም ትልቅ ፍላጎትና ቁርጠኝነት ታይቷል።

በሌላ በኩልም በሄድንባቸው ክልሎችና ወረዳዎች ላይ ሕዝቡ ግጭትን ሙሉ በሙሉ ማስቆም አንችልም የሚል ስሜት ውስጥ ገብቶ የነበረ በመሆኑ አሁን ላይ ይህንን ችግር ለማስወገድ ዓይነተኛው መፍትሔ መነጋገር መሆኑን ሲረዳ ግን በቃ እንነጋገር ከሚለው አቋሙም በላይ መነጋገር ሀገራችንን ከችግር ለማውጣት ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገርም እንድትቀጥልልን ያደርገናል የሚል እምነት ጨብጧል። ሕዝቡ ያለው አማራጭ ንግግር ብቻ እንደሆነና እንደ ማህበረሰብም መጠንከር ካለብን በልዩነቶቻችን ዙሪያ ቁጭ ብለን መነጋገርና መወያየት ይኖርብናል በሚል ስሜት ውስጥ ሆኖ ነው የኮሚሽኑን ሥራም እየጠበቀ ያለው።

በመሆኑም ቶሎ በሉልን በጉጉት እየጠበቅን ነው፤ በመሳሪያ ችግሮቻችንን ልንፈታ አንችልም ፤ እንመካከር፤ አንነጋገር የሚል ድምጽን በየሄድንበት እየሰማን ነው።

እዚህ ላይ መናገር የምፈልገው ነገር ቢኖር አሁን ላይ ብዙውን ነገር ጨርሰን በክልል ላይ የምናደርገውን የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ ላይ ደርሰናል። ከዚሁ ጎን ለጎንም ለሀገራዊው ምክክር ሂደት ተወካዮች የሚመረጡበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። በዚህም መሠረት በክልል ደረጃ ምክክር እናደርጋለን፤ እንዲሁም ተሰብስበን እያንዳንዱ ክልል የራሱን አጀንዳ አውጥቶ ተመካክሮ ሰላማችንን አንድነታችንን እየነሱን ያሉት አጀንዳዎቻችን እነዚህ ናቸው ብሎ በመመካከር ለሀገራዊ ምክክር የሚሆኑ ግብዓቶችን ያቀርባል።

ከዛም ደግሞ በሀገራዊ ምክክሩ ላይ ክልሎቻችውን ወክለው የሚመካከሩ አካላትን ጠቁመው መርጠውና አጸድቀው የሚሄዱበትን መድረክ እያዘጋጀን ነው።

አዲስ ዘመን፦ ይህ እንግዲህ በሀገር ውስጥ የምናደርገውና ዜጎች የሚያዋጡትን ሃሳብና አጀንዳ የምንቀምርበት ሂደት ነው ዳያስፖራውንስ በምን መልኩ ለማሳተፍ ነው የታሰበው?

ዶክተር አምባዬ፦ አዎ በዚህ ሀገራዊ ምክክር ላይ የዳያስፖራው ተሳትፎ በጣም ይፈለጋል ፤ ይፈለጋል ብቻም ሳይሆን አስፈላጊም ነው። ይህንን ከግንዛቤ በማስገባትም ሰሜን አሜሪካ ፤ ዌስትና ኢስት ኮስት፣ አውስትራሊያ ያሉትን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን እንዲሁም አፍሪካ ውስጥ በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ እንግሊዝና አውሮፓ ላይ የሚኖሩ ዜጎችን በሙሉ “በዙም ስብሰባ” አግኝተናቸዋል።

በዚህም በጣም ሰፊና ረጅም የሆነ ውይይትን አድርገናል። ይህ ሁሉ ነገር የሚያሳየው እንግዲህ የሀገራችንን ችግር የምንፈታው ስንመካከር አብረን ስንሆን ነው፤ ሃሳቦቻችንንም እናቀርባለን የሚል ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱም ሆኗል።

አዲስ ዘመን፦ ከሕዝባዊ ውይይት መድረኩ ውጭ ግን ግለሰቦችም ሊሆኑ ይችላሉ አልያም ተቋማት ብቻ ሃሳብ አለኝ ፤ አጀንዳ ይዣለሁ ያለ አካል ለእናንተ ሃሳቡን ማቅረብ የሚችልበት መንገድ ይኖር ይሆን ?

ዶክተር አምባዬ ፦ አዎ እስከ አሁን ድረስ በተለይም የተደራጁ ተቋማት አጀንዳዎቻችውን ቢሮ ድረስ ይዘው በመምጣት ስንቀበላቸው ነበር። ለምሳሌ በሴቶች ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች አንድ ላይ ሆነው ሴቶች በሀገራቸው ላይ ያላቸው አጀንዳ እነዚህ ናቸው ብለው ሰጥተውናል። በተመሳሳይ አካል ጉዳተኞች ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች ሃሳባቸውን ሰጥተውናል። አንዳንድ የሃይማኖት ተቋማትም አጀንዳዎቻችን እነዚህ ናቸው ብለው ሰጥተውናል። ይህ ብቻም አይደለም ግለሰቦችም አጀንዳችን ነው የሚሉትን የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎችን እየተጠቀሙ እንዲሁም በአካል ቢሮ ድረስ እየመጡ እየሰጡን ነው።

በጠቅላላው ለሀገር ውስጥም ይሁን ለውጭ አጋሮቻችን ምክክር የሰላም አማራጭ እንደሆነ እያቀረብን ነው ያለ ነው።

አዲስ ዘመን ፦ ብዙ ርቀቶችን እየሄዳችሁ እንደሆነ እንረዳለንና እንደው ሂደቱን ከስኬታማነት አንጻር ስንገመግመው የቱ ጋር ማስቀመጥ እንችላለን?

ዶክተር አምባዬ፦ ሂደቱ ስኬታማ ነው። በሥራው ላይም አካታች ነን ብለን ነው የተነሳነው። ሁሉም ባለድርሻ አካላት በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባቸዋል ስላልንም አሁን ላይ ትንሽ ጊዜ የወሰደ የመሰለው አካታችነትን ሙሉ በሙሉ መተግበር አለብን ብለን በመነሳታችን ነው።

በዚህ ሂደት ውስጥ ማንም ኢትዮጵያዊ አለኝ የሚለውን አጀንዳ ይዞ መምጣት ይችላል። ሀገራዊ ምክክር በየሳምንቱ ወይም በየዓመቱ የሚደረግ ነገር ባለመሆኑና ፋይዳውም ግዙፍ ስለሆነ በዚህ ሂደት ውስጥ እኛ አልተሳተፍንም፤ አልነበርንም፤ ውሳኔውም የእኛን ግሩፕ አላካተተም የሚል ችግር ውስጥ እንዳንገባ ሁሉንም አካላት ለማካተት እየሞከርን ነው። ለዚህ የሚያግዙንን የተለያዩ ጥሪዎችም እያደረግን ነው።

የሀገራችንን እድል እጣ ፋንታ መወሰን የምንችለው በመመካከር ነው። ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ደግሞ መድረኩን አዘጋጅቷል። የትኛውንም ቡድን አልያም ግለሰብ አያገልም። ችግሮቻችንን በምክክር መፍታት እንችላለን ብለን በሙሉ እምነት እየሠራን ነው። እንደ ሀገርም በተሰጠን የጊዜ ገደብ ውስጥ ሥራውን እናጠናቅቃለን ብለን እየሠራን ነው።

ይህም ቢሆን ግን አንዳንድ ልንቆጣጠራቸው የማንችላቸው ነገሮች እንዳሉም ይገባናል። ለምሳሌ በሰሜን በነበረው ጦርነት ምክንያት ትግራይ መሄድ አልቻልንም፤ ይህ መሬት ላይ ያለ እውነት ነው። በመሆኑም የተሰጠን የጊዜ ገደብ ሊያልቅ ነውና ክልሉ አይካተት ማለት አንችልም፤ በመሆኑም ሁሉም ሊያውቀው የሚገባው ነገር እኛ የምንቆጣጠረውን እንቆጣጠራለን ከአቅም በላይ የሆኑ ነገሮችን እንደ አመጣጣቸው እየፈተሸን እንሄዳለን።

አዲስ ዘመን ፦ የምክክሩ ሂደት በስኬት እንዲጠናቀቅ ከማን ምንም ይጠበቃል?

ዶክተር አምባዬ፦ ሁሉም ሥራዎች የጋራ ናቸው ብለን እናስባለን። ተቋሙ ብቻውን የሚሰራውም ሥራ አይደለም። ለዛም ነው ባለቤት እንሁን ብለን በተደጋጋሚ የምንናገረው፤ በመሆኑም እኛ ሂደቱን የምናሳልጥ አካላት ነን ፤ በመሆኑም እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል ጉዳዩ የእኔም ነው ማለት መቻል አለበት።

እኛስ እንደ ዜጋ ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን ምን እያደረግን ነው? መገናኛ ብዙሃን ምን እያደረጉ ነው? ባለቤት ሆነዋል ወይ? የሚለው ሁሉንም የሚመለከት ከመሆኑም በላይ ለምሳሌ ሀገሬ ከችግሯ የምትወጣው በመመካከር እንጂ በጠመንጃ አይደለም ብሎ መናገር ያለበት አካል ሚዲያ ነው። በመሆኑም ሁላችንም ለጉዳዩ ባለቤት እንሁን ያንን መሆን ስንችል ውጤትም አብሮነት ይመጣል ብዬ አምናለሁ።

አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።

ዶክተር አምባዬ፦ እኔም አመሰግናለሁ።

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 28 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You