
ወልቂጤ፡– ጢያ ትክል ድንጋይን የሃገሪቱ ሁነኛ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው አስታወቁ። ከግል ባለሃብቶች ጋር በመተባበር ሌሎችንም በክልሉ የሚገኙ የተፈጥሮ ሃብቶችና የማይዳሰሱ ቅርሶችን ለማስተዋወቅና የክልሉን የገቢ አቅም ከፍ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ እንዳሻው ጣሰው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ ክልሉ ከየም ሳጃ ጀምሮ እስከ ጢያ ድረስ እንዲሁም በሌሎችም የክልሉ አካባቢዎች ሰፊ የተፈጥሮና የማይዳሰሱ ሃብቶች ይገኛሉ። ይሁንና እነዚህን ሃብቶች የቱሪዝም መዳረሻ ከማድረግ አኳያ እስካሁን የተሠሩት ሥራዎች እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም። ይህም በተለይም የክልሉ ሕዝብ የዘመናት ቁጭት ሆኖ ቆይቷል። በመሆኑም የክልሉ መንግሥት በተለይም የጢያ ትክል ድንጋይ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በመገንባት ለሃገሪቱ ሁነኛ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ርብርብ እያደረገ ነው።
‹‹ወደ ከንባታ ብንሄድ 777 የሚባለው ተራራማ ስፍራ፤ ስልጤ ላይ ያሉ ሐይቆች፣ ሁለቱ ጉራጌዎች አካባቢ ደግሞ ዘቢዳር አለ፤ የም ብንሄድ እጅግ የሚያምር ሥነምሕዳር አለ፤ ከጉራጌ ዞን እስከ ወላይታ የሚዘልቁ ሰንሰለታማ ተራሮች ራሳቸው ሌላው የክልላችን መስሕብ ናቸው። እነዚህን በሙሉ ስናይ ሥራ አልተሠራም ብሎ ኅብረተሰቡ ቢቆጭ ተገቢ ነው። አሁን ግን ቁጭቱን ወደ ሥራ ለመተግበር ገብተናል›› በማለት አብራርተዋል።
በዋናነትም የክልሉ መንግሥት የጢያ ትክል ድንጋይን ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልፀው፤ ‹‹ለዚህም ሥራ ይውል ዘንድ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የመደመር መጽሐፍ ተሽጦ እንድንሠራበት አበርክተውልናል›› ሲሉ አስታውሰዋል።
ክልሉ በአዲስ መልክ ከተደራጀ በኋላ ጢያ ትክል ድንጋይ የዓለም ቅርስ ጭምር እንደመሆኑ ይህንን የሚመጥኑ ሁለት ዓይነት ዲዛይኖች መሠራታቸውን አመልክተው፤ ‹‹አንዱ ዲዛይን ባሕላዊ ነገሩን የሚያሳይ ሲሆን፤ ሌላው ዘመናዊ ነገሩ ምን ሊሆን እንደሚችል የሚያሳይ ነው። በመቀጠልም ሁለቱን ዲዛይኖች ወደ አንድ የማምጣት ሥራ ተሠርቷል›› በማለት አብራርተዋል።
ይህንን ዲዛይን መሠረት በማድረግ ለቅርስ ለሚመለከተው የመንግሥት አካልና፤ ዩኔስኮም ሃሳብ ሊሰጥበት ስለሚገባ ቦርድ መቋቁሙንም ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት የክልሉ መንግሥት ሥራ ለማስጀመርና መሠረተ ድንጋይ ለማስቀመጥ ዝግጅት ላይ መሆኑን አመልክተዋል። ‹‹አሁን ያለን መርሆ ‘የማናስጨርሰውን ሥራ አናስጀምርም’ የሚል ነው›› ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ በመሆኑም ሥራ ከመጀመሩ በፊት የፋይናንስ አቅም ከየት ይመጣል? የሚሉትን ነገሮች መልስ መስጠት ይገባል ተብሎ እየተሠራ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የጥያ ትክል ድንጋይን በተሻለ መንገድ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የተሠራው ዲዛይን ቱሪስቱን የሚስብ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም በርካታ ባለሃብቶች፤ ኤምባሲዎችና ዓለምአቀፍ ሰዎችም የሚሳተፉበት መሆኑን አመልክተዋል።
በተመሳሳይም ሌሎችንም የቱሪዝም መዳረሻዎች ለማስፋት ጥናት እየተደረገ መሆኑን አቶ እንዳሻው ጠቁመው፤ ‹‹በተለይም ከባለሃብቶች ጋር በጋራ የሚሠሩ ሥራዎችን እየለየን ነው። እሱ ብቻ ሳይሆን ከነሐሴ እስከ ጥቅምት ወር ድረስ የማይዳሰሱ እንደ መስቀል፣ ያሆዴ በዓልና መሰል ባሕላዊ ክዋኔዎች ራሳቸውን ችለው የቱሪዝም መስሕብ እንዲሆኑ የሚያደርግ ዝግጅት እያደረግን ነው ያለነው›› ብለዋል። ይህም ከሚቀጥለው ዓመት ወዲህ ወደሥራ የሚገባበት መሆኑን ነው የጠቀሱት።
ማሕሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 28 ቀን 2016 ዓ.ም