አዲስ አበባ፡- የብሔሮች፣ ብሕረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ህዝቡ ዕርስ በዕርሱ እንዲተዋወቅና ባህሉንም እንዲያስተዋውቅ ዕድል መፍጠሩን አንድ ጥናት አመለከተ፡፡በየዓመቱ በተመሳሳይ ሰነድ ላይ እየተመሰረተና አንድ አይነት ውይይት እየተደረገ ሲከበር የቆየበት መንገድም አከባበሩን አሰልቺ ማድረጉን ይሄው ጥናት ጠቁሟል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለተከታታይ 12 ዓመታት የተከበረውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል አከባበር ላይ የተካሄደውን ጥናት አስመልክተው በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ጥናቱ የበዓሉ መከበር መልካም ውጤት እንዳለው ያመለከተ ሲሆን ፣ ተግዳሮቶችም እንደነበሩበት ጠቁሟል፡፡
የቀኑ መከበር በብዙዎች ዘንድ የማይታወቁ ብሔረሰቦች እና ባህላቸው እንዲሁም ማንነታቸው በሌሎች ዘንድ እንዲታወቅ ማድረጉን ጥናቱ ማመልከቱን የሚናገሩት አፈ ጉባኤዋ፣ ‹‹የጋራ እሴቶቻችንን ከማዳበርና የአገራችንን መልካም ገፅታ ከመገንባት አኳያም የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል›› ብለዋል፡፡ በመተማመን ላይ የተመሰረተ አንድነት እንዲኖር ማስቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡
አፈ ጉባኤዋ እንዳሉት፤ በዓሉን አስመልክተው ይዘጋጁ የነበሩት ሲምፖዚየሞችና የፓናል ውይይቶችም በሔገ መንግሥቱና በፌዴራል ሥርዓቱ ላይ የተሻለ ግንዛቤ እንዲፈጠር ማስቻላቸውን ጥናቱ የጠቆመ ሲሆን፣ ይህ በመሆኑ በዓሉ በባለቤትነት ስሜት እንዲከበር ማድረጉንም አመልክቷል፡፡
በዚህ መሰረት በዓሉ ከዓመት ዓመት በተሻለ ሁኔታ ሲከበር መቆየቱን፣ የህዝቡም ተሳትፎ የዚያኑ ያህል እያደገ መምጣቱን ከጥናቱ መረዳት መቻሉን ጠቅሰው፣ በመሆኑም የኢትዮጵያን አንድነት ከማጠናከር አኳያ የራሱን ድርሻ ተጫውቷል ማለት እንደሚቻልም አብራርተዋል፡፡
‹‹ ከዚህ በመነሳት በጥናቱ የበዓሉ መከበር መቆም እንደሌለበት፤ ክፍተት ናቸው የተባሉትን በመሙላት፣ አዳዲሶችንም በማካተት በዓሉን ማስቀጠል ይገባል የሚል አስተያየት ተንፀባርቋል›› ያሉት ወይዘሮ ኬሪያ፣ በሁሉም ክልሎች ማለት በሚያስችል ሁኔታ የልማት ሥራዎች መሠራታቸውን፣ ሁሉም የመንግሥት ተቋማት በዓሉን በባለቤትነት ከማክበርና ትኩረት ሰጥቶ ከመዝለቅ አንፃርም የተሻለ እንቅስቃሴ እያሳዩ መምጣታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዓሉ በየዓመቱ በተመሳሳይ ሰነድና አቀራረብ ሲከበር መቆየቱ፣ ይህም አካባበሩን አሰልቺ እንዳደረገው ጥናቱ ማሳየቱን አፈ ጉባኤዋ ጠቅሰዋል፡፡ ውይይት ለመጀመር ገና የፌዴራል ሥርዓት የሚለው ሐሳብ ሲነሳ ተሳታፊዎች ጥለው ይወጡ የነበረበትን ሁኔታም ጥናቱ በተግዳሮትነት ማስቀመጡን ገልፀዋል፡፡
አፈ ጉባኤዋ እንደገለፁት፤ በተለይ ባህልን፣ ታሪክንና ትውፊትን ለማስተዋወቅ በየዓመቱ በበዓሉ ላይ የሚገኙት የየብሔረሰቡ ተወካዮች ተመሳሳይ ናቸው፤ አመራሩም፣ የባህል ቡድኑም፣ የአገር ሽማግሌውም ሁሉም በየዓመቱ አንድ አይነት ናቸው፡፡ ታች ወርዶ የዳበረውን ባህል ከማምጣት አኳያ ክፍተት እንዳለ ጥናቱ አመላክቷል፡፡ የባህል መበረዝ ተግዳሮት ማጋጠሙንም ጠቁሟል፡፡
አስተናጋጁ ክልል በይድረስ ይድረስ ስሜት ዝግጅቱን እንደሚያደርግ ጥናቱ ማመልከቱን አፈ ጉባኤዋ ተናግረው፤ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የክልሉ ህዝብ አጣዳፊ ጥያቄ መሆናቸው በውል ሳይታወቁ ወደ ልማቱ ይገባ እንደነበርም መጠቆሙን አስረድተዋል፡፡
አፈ ጉባኤዋ ጥናቱን አስመልክተው እንዳሉት፤ በዚህም ሂደት ውስጥ አልፈው የተሠሩ ፕሮጀክቶች ጥራታቸው አጥጋቢ ሆኖ አልተገኘም፤ ተጀምረው ያልተጠናቀቁም አሉ፡፡ እንደ ምንም ከተጠናቀቁትም ወዲያውኑ የሚፈርሱ ሆነዋል፤ የፋይናንስና የጨረታ ሥርዓቱ በህጋዊ መንገድ አለመመራቱ ይህም ለብክነትና ለኪራይ ሰብሳቢነት በር መክፈቱን ጥናቱ ያመለከታቸው ችግሮች ናቸው፡፡
‹‹የበዓሉ ዕለት ብቻ ለመስተንግዶ በሚል በፌዴሬሽን ምክር ቤትና በአዘጋጁ ክልል የሚወጣ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር አግባብነት እንደሌለው በጥናቱ ተጠቁሟል›› ሲሉ አፈ ጉባኤ ኬሪያ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የብዙኃን መገናኛዎችም በዓሉን በተመለከተ የሚሳተፉት ባለቀ ሰዓት ነው፤ መገናኛ ብዙኃኑ የበዓሉን መልካም ገጽታ ለህዝቡ ከማዳረስ አኳያ ትልቅ ሚና ቢኖራቸውም፤ ክፍተት ነበረባቸው›› ሲሉ ጥናቱ መጠቁሙን አብራርተዋል፡፡
ሌላውና ትልቁ ጉዳይ በዓሉ ታላቅ አገራዊ በዓል ከመሆኑ አኳያ የረጅም ጊዜ ዕቅድና ስትራቴጂ የሌለው ሆኖ መታየቱም በጥናቱ የተገኘ ተግዳሮት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ዘንድሮ ለ13ኛ ጊዜ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስተናጋጅነት በብሔራዊ ደረጃ በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚከበር ይታወቃል፡፡ የበዓሉም መሪ ሐሳብ ‹‹በብዝሃነት የደመቀ ኢትዮጵያዊ አንድነት›› የሚል እንደሆነ ታውቋል፡፡
rüyada hindi yumurtası görmek