በተለያዩ ምክንያቶች ከሚደረግ ፍልሰት ጋር በተያያዘ በከተሞች ከፍተኛ የሆነ የመኖሪያ ቤት እጥረት አጋጥሟል። በተለይም አዲስ አበባን ጨምሮ በክልል ዋና ከተሞች ችግሩ ነዋሪዎችን በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈታተነ ይገኛል። ችግሩም በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ዜጎች “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል።
ችግሩን ለመፍታት በየወቅቱ የተደረጉ ጥረቶች አንድም የችግሩን ስፋት እና ጥልቀት ያገናዘቡ እለመሆናቸው፤ ሁለተኛም፣ በተለያዩ አማራጮች የተደገፉ እና ዘላቂነት ባለው የልማት መስመር አለመጓዛቸው ችግሩ አሁን ላይ ገዝፎ ዜጎችን ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍሉ እያደረጋቸው ይገኛል።
በተለይም በአዲስ አበባ ያለው የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ካለው ፍላጎቶች ጋር አለመጣጣሙ፤ የቤት ኪራይ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲንር ከማድረግ ባለፈ፤ ተከራዮች ተከራይተው በሚኖሩት ቤት ውስጥ የሚኖራቸው ቆይታ በደላሎች በጎ ፈቃድና ያልተገባ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን አድርጎታል።
ይህም ተከራዩች እስከ ቤተሰቦቻቸው የተረጋጋ ሕይወት እንዳይመሩ ፈተና ከመሆን ባለፈ፤ በየጊዜው ከሚደረግ የኪራይ ጭማሪ ጋር በተያያዘ ከአቅማቸው በላይ ከገቢያቸው እስከ 70 ከመቶ የሚሆነውን ለቤት ኪራይ በማዋል፤ ለተጨማሪ የሕይወት ፈተና ተጋላጭ እንዲሆኑ፤ ጤናን ጨምሮ ሌሎች መሠረታዊ ፍላጎቶችን በማዛባት ዜጎችን ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች እየዳረገ ይገኛል።
ከችግሩ ግዝፈት የተነሳም አብዛኛው የመንግሥት ሠራተኛ እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች ከመሀል ከተሞች እየወጡ ወደ ከተሞች ዳርቻ ለመኖር ተገደዋል። ይህም በራሱ በከተሞች ካለው የትራንስፖርት እጥረት ጋር በተያያዘ ለተጨማሪ እንግልት ዳርጓቸዋል።
ችግሩን ለዘለቄታው ለመፍታት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ፣ የመንግሥትን፣ የነዋሪውንና የባለሀብቶችን ንቁ ተሳትፎ የሚፈልግ ነው። አሁንም ወደ ከተሞች ከሚደረግ ከፍተኛ ፍልሰት ጋር በተያያዘም ልዩ ትኩረት የሚሻ ብቻ ሳይሆን፣ ፈተናነቱንም በቀላሉ የምንሻገረው አይሆንም።
የጀመርነው ልማት በሁለንተናዊ መልኩ እየሰፋ ሲሄድ፣ የመኖሪያ ቤት የመሠረት ልማቶችን በስፋትና በጥራት መገንባት የሚያስችል ሀገራዊ የፋይናንስ አቅም ባለቤቶች ስንሆን ችግሩን ለዘለቄታው ልንሻገረው እንደምንችል ይታመናል። እንደ ሀገር ተስፋ የምናደርገውም ይህንኑ በእጃችን ያለውን መፍትሔ ነው።
እስከዛው ግን ከፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም ጋር በተያያዘ ከተፈጠረው ክፍተት ባለፈ፣ በቤት ኪራይ ዙሪያ በደላሎች ያልተገራ ስዕብና በተከራዮች ላይ እየተፈጠረ ያለውን ያልተገባ ችግር ለመቆጣጠር ሕግም የተከተለ የአሠራር ሥርዓት ማስፈን ተገቢ እንደሆነ ይታመናል።
ከዚህ አንጻር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመኖሪያ ቤት ኪራይ ላይ የሚስተዋለውን ኢ-ፍትሐዊ የዋጋ ጭማሪን በመቆጣጠር ጊዜያዊ መፍትሔ ይሰጣል ያለውን የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅን ማፅደቁ የሚበረታታ እና እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ፤ እንደ አንድ የመፍትሔ መንገድ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
አዋጁ በመኖሪያ ቤት ኪራይ ላይ የሚስተዋለውን የዋጋ አለመረጋጋት በመቆጣጠር በቤት አቅርቦት ላይ የሚስተዋለውን ችግር እንዲረጋጋ የሚያስችል፤ የአከራይና ተከራይ መብትን ሚዛናዊነት የሚጠብቅ፤ ሕጋዊነትን የሚያጸና፣ ግልጸኝነትን የሚያረጋግጥና ሥርዓቱን ከደላሎች ተጽእኖ የሚያላቅቅ እንደሚሆንም ይታመናል።
ከመኖሪያ ቤት ኪራይ ጋር በተያያዘ ለከፋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የተዳረጉ ዜጎችን፤ በተለይ በከተሞች አካባቢ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች አሁን ላይ ካሉበት የመሳቀቅ ሕይወት በተወሰነ መልኩ በመታደግ የተረጋጋ ሕይወት እንዲመሩ የሚያስችል ነው።
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 27 ቀን 2016 ዓ.ም