ፓርኪንሰን ልክ እንደ ስኳር በሽታ ሁሉ በኬሚካል እጥረት የሚከሰት የህመም አይነት ነው።የስኳር ህመም «ኢንሱሊን »በሚባል የኬሚካል እጥረት የሚከሰት ሲሆን ፓርኪንሰን ደግሞ «ዶፓሚን»በሚባል የኬሚካል እጥረት ይከሰታል። ይህን በሽታ ለየት የሚያደርገው ችግሩ በቀላል የምርመራ ዘዴ ተለይቶ አለመታወቁ ነው።
የስኳር ህመም መኖሩን ለማረጋገጥ ደምን መለካት ይቻላል። የፓርኪንሰን ህመምን ግን ማወቅ በልኬት ማወቅ የሚቻል አይሆንም።የፓርኪንሰን ህመምን ለማወቅ ያለው አማራጭ ምልክቶቹን ጠንቅቆ መለየት ብቻ ይሆናል።
የፓርኪንሰን ህመም ምልክቶች
የፓርኪንሰን ህመም የያዘው ሰው ብዙውን ጊዜ መንቀጥቀጥ ይስተዋልበታል።ሰውነቱን ጨምድዶ የመያዝ ስሜትና ሚዛኑን የመሳት ሁኔታም ይኖረዋል።አንዳንድ ጊዜ የፓርኪንሰን ተጠቂው በእረፍት ላይ በሚሆንበት ወቅት እጆቹና እግሮቹ ብቻ ተለይተው ሊንቀጠቀጡ ይችላሉ።እጆቹ ቡና ወይም ሌላ መሰል ነገሮችን ለመቀበል በሚዘጋጁበት ግዜ ደግሞ በድንገት መንቀጥቀጣቸውን ሊያቆሙ ይችላሉ።
የፓርኪንሰን ህመም ያለበት ሰው የሚንቀጠቀጠው በመዝናናት አልያም እረፍት ላይ በሚሆንበት ጊዜ ነው።መንቀጥቀጡ ደግሞ በአንድ ወይም በሁለት እጆቹ ላይ ሊሆን ይችላል።የሰውነቱ መገታተር የሚጀምረውም መንቀጥቀጥ በሚታይበት ጎን በኩል ያለው የእጅና እግር ጡንቻዎቹ ላይ ነው።ይህ ስሜት ብዙውን ግዜ ከሪህ ህመም ጋር ሊመሳሰል ይችላል።
የሪህና የፓርኪንሰን ህመም ልዩነት ሲታይም ሪህ እጅና እግርን በሚያዝናኑበት ጊዜ ህመሙ ሲያቆም ፓርኪንሰን ደግሞ በተመሳሳይ ስሜት ውስጥ ለውጥ የሚያመጣ አይሆንም። ፓርኪንሰን አካልን የማሳበጥ ምልክት የለውም።ምንጊዜም ግን ጡንቻ እንደተወጣጠረ የማስቅረት አይነት ስሜት ይኖረዋል።
ፓርኪንሰን እነማንን ያጠቃል?
በአብዛኛው ህመሙ \ ዕድሜያቸውከ 60 አመት በላይ የሆኑ ሰዎችን ያጠቃል።ነገርግን ከዚህ ዕድሜ በታች የሆኑ ሰዎችን ሊያጠቃ እንደሚችልም ጥናቶች ያረጋግጣሉ።ፓርኪንሰን በየትኛውም ሀገር የሚገኙ ወገኖችን በእኩል ደረጃ የሚያጠቃ ህመም ነው።ችግሩን ለማወቅ ከሁለት እሰከ አምስት ዓመት የሚፈጅ የምርመራ ሂደት ሊኖረውም ይችላል።
ህመሙ በምን ይከሰታል?
ፓርኪንሰን «ዶፓሚን » የሚባል ኬሚካልና « ስብስታንሺያ ኔግራ» ተብሎ የሚጠራው የአንጎላችን ክፍል እየቀነሰ ሲሄድ የሚከሰት ችግር ነው።ዶፓሚን ለምን እንደሚያልቅና ኬሚካሉም ስለምን እንደሚያልቅ የሚታወቅ ምክንያት ግን የለም።ከዚሁ ችግር ጋር ተያይዞ ግን የሚቀመጡ አንዳንድ መላ ምቶች ይናራሉ። ከነዚህም መሀል ፡- በጭንቅላት ላይ የሚከሰት ጉዳት፣የፋብሪካ ዝቃጮች ፣የጉድጓድ ውሀን አዘውትሮ መጠቀምና መሰል አጋጣሚዎች ለህመሙ እንደመነሻነት የሚቀመጡ ምሳሌዎች ናቸው።
የፓርኪንሰን ህመምና በሌሎች ላይ ያሉ ስጋቶች
ብዘውን ጊዜ ህመሙ ካለባቸው ሰዎች ጋር ቅርበት ያላቸው ሰዎች የፓርኪንሰን በሽታ ወደ እነሱ የሚተላለፍ መስሎ ሊሰማቸው ይችላል።ይሁን እንጂ በሽታው ከአንዱ ወደ ሌላው የሚተላለፍ ባለመሆኑ ስጋትም ሆነ የተለየ ጥንቃቄ የሚያሻው አይሆንም።
ምንጭ :-በፓርኪንሰን ላይ 100 ጥያቄዎችና መልሶች
አዲስ ዘመን ቅዳም ሰኔ 8/2011