‹‹ በአጭር ጊዜያት ውስጥ በክልሉ አንጻራዊ ሰላም ማስፈን ችለናል››አቶ እንዳሻው ጣሰው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳደር

በቀድሞ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ስር ከነበሩና በቅርቡ ራሳቸውን ችለው ከወጡ ክልሎች መካከል የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አንዱ ነው። ክልሉ ከተመሠረተበት ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ ያሉትን የልማት አቅሞች በመጠቀም የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን እያከናወነ ነው።

በዋናነትም በተቀናጀ ግብርና ልማት ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት እያገኘ ነው። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የጋዜጠኞች ቡድንም በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የግብርና ልማት ሥራዎችን የመስክ ምልከታ አድርጓል፤ በእነዚህ የልማት ሥራዎች ዙሪያ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ከአቶ እንደሻው ጣሰው ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል። እንደሚከተለው ይቀርባል።

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ በአዲስ መልክ ሲደራጅ ቅድሚያ ሰጥቶ ያከናወናቸው ሥራዎች ምን እንደነበሩ ይጥቀሱልንና ውይይታችንን እንጀምር?

አቶ እንዳሻው፡- እንደሚታወሰው ከስድስት ወራት በፊት ማለትም ነሐሴ 12 ምክር ቤቱ ተሰብስቦ የክልሉን መመስረቻ አዋጅና ሌሎች ተያያዥ አዋጆችን ካፀደቀ በኋላ ነሐሴ 13 ቀን በይፋ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ተመስርቷል። በወቅቱ ከነበረን ዋና ዋና ሥራዎች መካከል የአመራር ማደራጀት ሥራ አንዱ ነው፤ ሰባት ዞኖችና ሶስት ልዩ ወረዳዎች በማደራጀትም ወደ ሥራ ገብተናል።

ከአደረጃጀቱ በኋላ በክልሉ ውስጥ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ስለአሉ ይህንኑ ባካተተ መልኩ ነው ወደ ሥራ የገባነው ። ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ አመራሮችን መለየት፣ ማደራጀት፣ ወደ ሥራ ማስገባት ትንሽ ጊዜ የሚወስድ ሥራ ነበር። ነገር ግን በአጭር ጊዜ አመራር የማደራጀት ሥራ ተሰርቷል። ጠቅላላው አመራር ከክልል ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ ከ4 ሺ 500 ይደርሳል።

ሌላው ክልላችን ከ120 ሺ በላይ ሲቪል ሠራተኞች አሉት፤ እነዚህን ሠራተኞች በተሟላ መልኩ ወደ ሥራ ማስገባት የመጀመሪያ ወራት ሥራችን ነበር። ሌላው የዚህ ክልል አደረጃጀት ሰባት ክላስተሮች አሉት። የመጀመሪያው ሆሳዕና ነው፤ ሆሳዕና የፕሬዚዳንቱ መቀመጫ ነው። ሌሎች ከዚያ ጋር ተያያዥነት ያላቸው መሥሪያ ቤቶችም እዚያ አሉ።

ቡታጀራ የኢኮኖሚ ክላስተር ይባላል፤ ኢንቨስትመንት፣ ንግድና የመሳሰሉት ተቋማት መቀመጫ እዚያ ነው። ወልቂጤ የመሠረተ ልማት፣ ምክር ቤቶችና የመሳሰሉት ተቋማት የሚገኙበት ነው። አራተኛው ሃላባ ሲሆን ከፍትሕና ከፍትሕ ሥርዓት ጋር የተያያዙ ክላስተሮች ያሉበት ነው።

ግብርና እና ከግብርና ጋር የተያያዙ ክላስተሮች መቀመጫ ደግሞ ዱራሜ ከተማ ነው። ሌላው ወራቤ ከተማ ሲሆን ማህበራዊ ክላስተርና ሌሎች መሥሪያ ቤቶች ይገኙበታል። እነዚህን ሰባት ክላስተሮች አደራጅቶ ሥራ ማስጀመር የመጀመሪያው ሥራችን ነበር። እጅግ በጣም ፈታኝ ቢሆንም ሥራውን ማሳካት ችለናል።

እነዚህን ከሠራን በኋላ ክልሉን ወደ ማስተዋወቅ ሥራ ጥቅምት 17/2016 ዓ.ም ገባን። በዚህም የሌሎች ክልሉች ርዕሰ መስተዳደሮች፣ ከፍተኛ ባለስልጣናትና ሌሎች የክልሉ ተወላጆች እንዲሁም የሠራዊት አባላት ባሉበት እጅግ በጣም በደመቀ ሁኔታ የክልሉን የሥራ መጀመሪያ ማብሰሪያ በሆሳዕና ከተማ አከናውነናል። ከዚያ በኋላ የሕዝብ መድረክ ወደ ማዘጋጀት ገባን ።

የሕዝብ መድረክ ማከናወን ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት አዲስ ክልል እንደመሆኑ እቅድ ለማቀድ ከሕዝብ ሃሳብ መሰብሰብ የግድ ስለሚል ነው። በመሆኑም አስቀድሜ ባልኳቸው ሰባት ዞኖችና ሶስት ልዩ ወረዳዎች ትልልቅ መድረኮች አከናውነናል። እሱን መሠረት አድርገን የመጀመሪያ የመቶ ቀን እቅድ አዘጋጅተናል። የመቶ ቀን እቅዱንም ውጤታማ በሆነ መንገድ ፈጽመናል። በመቀጠልም ሁለተኛውን ዙር የመቶ ቀን እቅድ አዘጋጅተን ይህም ውጤታማ በሆነ መንገድ አጠናቀናል።

አስቀድሜ እንደገለፅኩት በዚህ ክልል በርካታ ሥራዎች ያሉ ቢሆንም ስድስት ለሚሆኑት ዘርፎች ቅድሚያ ሰጥተን በመተግበር ላይ እንገኛለን። የመጀመሪያው የፀጥታና ሰላም ሥራ ነው። የክልሉን ግብርና ልማት ማሳደግና የገቢ አቅም ከፍ ማድረግ ሌሎቹ ትኩረት የተሰጣቸው ሥራዎች ናቸው። ትምህርት፣ ጤና እንዲሁም የሥራ እድል ፈጠራ ሥራዎች ሌሎቹ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እየተከናወኑ ያሉ የልማት መስኮች ናቸው። በኋላ ላይ ገምግመን ያስገባነው የገበያ ልማትና ኢንቨስትመንት ሥራዎችም ተጠቃሾች ናቸው።

እነዚህ እንዳሉ ሆነው በየእለቱ በግብረ ኃይል የሚመራው የመሠረተ ልማት አውታር ሥራ ከዚሁ ጋር የሚካተት ነው። በዚህ ውስጥ መብራት፣ ውሃ፣ የከተማና የገጠር መንገድ ሥራ አለ፤ እንዲሁም እኛ ባናስተዳድረውም የቴሌኮም መሠረተ ልማት ዝርጋታም እንዲሁ በእቅድ ተይዘው እየተከናወኑ ካሉ ሥራዎች መካከል ነው።

አዲስ ዘመን፡- የክልሉን ሰላም ከማስጠበቅ አኳያ የተሠሩ ሥራዎች ምን ያህል ውጤታማ ናቸው?

አቶ እንዳሻው፡– በዚህም ረገድ ፀጥታ ላይ የተሠራው ሥራ ተጠቃሽ ነው። ክልሉ ሲመሰረት እንደአሸን የፈሉ የማህበራዊ ድረ-ገፆች ነበሩ። አንዳንዶቹ እጅግ በጣም ቀና የሆነ መልዕክት የሚያስተላልፉ ናቸው። አብዛኞቹ ግን ክልሉን እንዳይረጋጋ የሚያደርጉ ነበሩ። የተቋቋመው ክልል በብሔር ብሔረሰቦች መፈቃደድ ላይ የተመሠረተ ቢሆንም አንዱን ማወደስ፤ ሌላውን ማንቋሸሽ ፤ በአመራሮች መካከልም መከፋፈል እንዲኖር ለማድረግ እንዲሁም ሌሎች ፀብ ቀስቃሽ የሆኑ ነገሮችንና በአጠቃላይ የጥላቻ ንግግር አዘል መልዕክቶች የሚተላለፍባቸው ነበሩ።

እነሱን ሥርዓት ለማስያዝ ትልቅ ሥራ ተሰርቷል። ሁለተኛው ይሄን ተከትሎ በተሳሳተ መንገድ ለመሰለፍ የሚሞክሩ ወጣቶች ነበሩ ፤ አንዳንድ ቦታ መንገድ ለመዝጋት ሞክረው ነበር። ሕግ የማስከበር ሥራ ሲሠራ ደግሞ ሶስት መንገዶች ናቸው ያሉት፤ የመጀመሪያው ማስተማር ነው። በማስተማር ሰዎች እንዲመለሱ ለማድረግ ተሞክሯል፤ ሁለተኛው ውይይት ነው፤ በማወያየት ችግር ውስጥ የገቡ ሰዎች ከችግሩ እንዲወጡ ምክር የመስጠት ሥራ ተሰርቷል። የመጨረሻው ሕግ ማስከበር ነው፤ እነዚህን ሶስት ሥራዎች ተራ በተራ በመጠቀም የክልሉን አጠቃላይ ፀጥታ በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ ችለናል።

በክልላችን የሸኔ እንቅስቃሴ ያሉባቸው ቦታዎች አሉ፤ ለምሳሌ ወደ አዲስ አበባ መውጫችን ከወልቂጤ ወሊሶን ተሻግረን ቱሉ ቦሎ አካባቢ የተወሰነ ችግር ተፈጥሮ ነበር፤ አሁን ያለንበት ደረጃ ጥሩ ነው። አሁን ተሽከርካሪዎች እንደልብ ይንቀሳቀሳሉ፤ ሸቀጥ ከዚያ ወደዚህ፤ ከዚህ ወደዚያ ይመላለሳል። በነገራችን ላይ ይሄ መስመር እስከ ጋምቤላ ድረስ የሚዘልቅ የገበያ መስመር ነው። ይሄ መስመር አሁን ላይ ነፃ ቀጠና ነው።

ሁለተኛው ከቡታጀራ- ጥያ- ሌመን መንገድ አንድ ጊዜ ችግር ተፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል። ሕዝቡን አነቃንቀን፤ ሠራዊቱን አደራጅተን ከኦሮሚያ ፖሊስና ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን ይሄም መስመር ነፃ ሆኗል። ሶስተኛው ከቡታጀራ ወደ ዝዋይ የሚወስደው መንገድ የተወሰነ የሸኔና የአካባቢ ሽፍታም  ጭምር የሚንቀሳቀስበት ነበር፤ ይህንንም ለማረጋጋት ተሞክሯል።

ከዚህ ባሻገር በሕዝቦች መካከል የሚስተዋሉ አንዳንድ ግጭቶች ነበሩ፤ ለምሳሌ በመስቃን ቤተ-ጉራጌ እና ማረቆ መካከል ግጭት ነበር፤ እነዚህ ሕዝቦች ለረጅም ዓመታት አብረው የኖሩ ናቸው፤ ለወደፊቱም አብረው የሚኖሩ ናቸው። አንዳንድ በመሃል በገቡ አካላት ምክንያት ለበርካታ ጊዜ ግጭቶች ይከሰቱ ነበር። ይሄ በአሁኑ ሰዓት በእርቅ ተቋጭቷል።

ለግጭቶች ምንጭ የሆኑ ወንጀለኞች በሕግ ቁጥጥር ስር ሆነው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ነው።

እነዚህን የመሳሰሉ ችግሮች አሁን ላይ ወደ ቦታችው ተመልሰዋል፤ ረግበዋል። በክልላችን ፍፁም የሆነ ሰላም አለ እንኳን ባይባልም አንፃሪያዊ ሰላም ግን ሰፍኗል። አስቀድሜ ለጠቀስኳቸው የልማት ሥራዎች ስኬት ሰላም ወሳኝ በመሆኑ በሰላም ጉዳይ ላይ ተረባብረን እሰራን ነው ።

በሁለተኛ ደረጃ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ የራሱን ሰላም ብቻ ሳይሆን የጎረቤቶቹን ሰላም ማስጠበቅ መቻል አለበት። እኛ ሰላም ስንሆን፤ ጎረቤት ክልሎች ሰላም ሲሆኑ ተያይዘን እናድጋለን፤ ኢትዮጵያ ሀገራችንም ሰላሟ የተረጋገጠ ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- በተቀናጀ የግብርና ልማት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ምን ይመስላሉ ?

አቶ እንዳሻው፡- በክልሉ ካለው ጠባብ መሬት አንጻር የግብርና ሥራ ለዚህ አካባቢ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው። ከ7 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በክልሉ ይኖራል። ሰብሰብ ያለ አካባቢ ስለሆነ የግብርና መሬቶችን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል። በዚህ መሠረት 2016 ላይ በተቀናጀ የግብርና ልማት ሥራዎች ላይ በጣም ተረባርበናል። የመጀመሪያው ሥራችን የነበሩት የአካባቢን ፀጋ መለየት ነው፤ ምን ዓይነት ግብርና ላይ ብንሳተፍ ውጤታማ እንሆናለን? በሚል በደንብ ተለይቶ፤ እቅድ ወጥቶለት ስምሪት ተሰጥቷል።

በሁሉም አካባቢ ያሉን የውሃ አማራጮች ክረምትና በጋ ብቻ ሳይሆን በልግንም ሆነ መኸርንም መጠቀም እንድንችልና ሁሉንም ወሮች የሥራ ጊዜ በማድረግ መሬታችን ዕረፍት ሳይኖረው እየተሠራ ነው። የበጋ ሥራ ስንጨርስ ሌሎቹ ይቀጥላሉ። ለምሳሌ ሃላባ ውስጥ ሲምቢጣ የሚባል አካባቢ ያለ ማህበረሰብ ከ20 ዓመታት በላይ በሴፍትኔት ድጋፍ ነው የቆየው፤ አሁን በትራክተር ያርሳል።

ማረስ ብቻ ሳይሆን ምርታቸው ተርተርፎ የሚያወጣላቸው አጥተዋል። ቲማቲም እዚያ አካባቢ አሁን ስድስት ብር ነው የሚሸጠው። ሽንኩርትም እንዲሁም በከፍተኛ መጠን ተመርቶ ገዢ እየፈለገ ነው ያለው። በመሆኑም የክልሉ መንግሥት ተረባርቦ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው እያደረገ ነው።

በአካባቢው ስንዴን ጨምሮ ፤ ድንች እና ሌሎች የጓሮ አትክልቶች በተሟላ ሁኔታ እየተመረተ ነው። አሁን ላይ የሲምቢጣ ሕዝብ ራሱን ችሎ ሌሎች ቀበሌዎችንም መርዳት ጀምሯል። ከዚህ ቀደም ግን ውሃን በአግባቡ የማይጠቀሙ ሕዝቦች ነበሩ። አሁን ላይ ግን ከወራጅ ውሀ በተጨማሪ በየአካባቢው አምስት ሜትር ጉድጓድ በመቆፈር በሚገኝ ውሀ በመስኖ እያለማ ነው።

ሌላው ባልተለመደ ሁኔታ አትክልትን በክላስተር የማልማት ሥራ በክልላችን ተጀምሯል። ክልላዊ በሆነው 30-40-30 ኢንሼቲቭ ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበ ነው። ይህም ማለት መርሃ ግብሩ ለሶስት ዓመታት የሚተገበር ሲሆን በመጀመሪያው ሰላሳ፤ በሁለተኛው ዓመት 40 እንዲሁም በመጨረሻው ዓመት 30 የፍራፍሬ ችግኝ በመትከል እያንዳንዱ አርሶ አደር 100 የፍራፍሬ ዛፍ እንዲኖረው ለማድረግ የታለመ ነው።

በዚህም ከሶስተኛው ዓመት በኋላ እያንዳንዱ የክልሉ አርሶ አደር ቤተሰቡን የሚያስተዳድርበት አስተማማኝ የገቢ ምንጭ ይኖረዋል የሚል እሳብ አለን ። በአሁኑ ወቅት ይህ መርሃ ግብር በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደና ተስፋ ሰጭ ሆኗል። በሌላ በኩል እንሰት የክልላችን ዋና ምርት ነው፤ ቆጮ፣ ቡላ፣ አምቾ ሆኖ ለምግብነት ከመዋሉም ባሻገር ተረፈ ምርቱ ቃጫ ሆኖ ቤት ይሰራበታል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ድርቅ የመቋቋም አቅም ስላለው እንሰትን የማስፋፋት ሥራ ለመስራት ታስቦ እየተሰራ ነው ። በዚህ መሀል የእንሰት በሽታ ተከስቶ ስለነበር በቅድሚያ በሽታን ለመከላከልና ለመግታት ሥራ ጥኩረት ሰጥተን ለመንቀሳቀስ ተገደናል ።

ብዙ ባህር ዛፍ የተተከለባቸውን ቦታዎችን በሌላ ፍራፍሬ የመተካት ሥራ በስፋት እየተከናወነ ነው። ባህር ዛፍ በባህሪው ብዙ ውሃ ይጠቀማል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለማደግም ምንም ጥረት አይፈልግም፤ የሰነፍ ሥራ ነው። ሥራን አያበረታታም። በመሆኑም አርሶ አደሩን እያሳመንን በባህር ዛፍ ፋንታ ፍራፍሬ እንዲተክሉ እያደረግን ነው። ለምሳሌ ስልጤ ዞን ስልጢ ወረዳ ላይ ከሶስት ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ መጠን የነበረውን ባህር ዛፍ ወደ ሙዝ፣ አቦካዶና የተለያዩ ፍራፍሬዎች እየተቀየሩ ነው ያሉት። አንዳንዶቹ አርሶ አደሮች ምርትታቸውን ወደ ውጭ መላክ ጀምረዋል።

ሌላው የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርታማነትን የማሳደግ ሥራ በስፋት እየተከናወነ ነው። በተለይ የማዳበሪያ ሥርጭት ችግር ነበረበት፤ ይህ ብቻ ሳይሆን የማዳበሪያ ገንዘብ በአግባቡ አይሰበሰብም ነበር። በዚህ ዓመት አጠቃላይ ጥናት ካደረግን በኋላ የማዳበሪያ ሥርጭት ሥርዓት ባለው ሁኔታ አርሶ አደሩ ጋር እንዲደርስ እየተሠራ ነው።

በአጠቃላይ የግብርና ልማት ሥራችን ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ በጣም በተቀናጀ መንገድ እየተከናወነ ነው። ይህ በመከናወኑ ከተገኙ ውጤቶች መካከል ለአብነት ብጠቅስ ሽንኩርት በእኛው ክልል ከ140 እስከ 180 ብር ይሸጥ ነበር፤ አሁን የሽንኩርት ዋጋ ወደ 50 ብር ወርዷል፤ ገና ከዚያ በታችም ይወርዳል።

ቲማቲምም እስከ 100 ብር ተሽጧል፤ አሁን ላይ ሸማቹ ከ15 እስከ 20 ብር ያገኛል። ስለዚህ ምርታማነት ጨምረናል ማለት ነው። በተጨማሪም 93 የእሁድ ገበያዎችን ከፍተናል፤ ይሄ ግን በቂ ስላልሆነ የእሁድ ገበያዎችን የማጠናከር ሥራ በስፋት የምንሄድበት ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- የገበያ ትስስር ጉዳይ አሁንም በአርሶ አደሩ እንደ ችግር የሚነሳ ጉዳይ ነው። በተለይ የወተት ምርት በስፋት በክልሉ ቢመረትም፤ በአካባቢያቸው አግሮ ኢንዱስትሪ ባለመኖሩ ከዚህ በላይ ማምረት ስጋት ሆኖባቸዋል። ይህንን ችግር በመፍታት ረገድ የክልሉ መንግሥት ምን ዓይነት ጥረት እያደረገ ነው?

አቶ እንዳሻው፡- አርሶ አደሩ ከገበያ ትስስር ጋር ተያይዞ የሚያነሳው ችግር ትክክል ነው፤ ይሄ ችግር በክልላችን ሁለት ዓይነት መልክ ነው ያለው። ለምሳሌ ብዙ የዱቄት ፋብሪካዎች አሉ፤ ስንዴም በስፋት እየተመረተ ነው። ሆኖም ሁለቱን ማስተሳሰር ላይ ችግር አለ። እንደ ቲማቲም ያሉ ምርቶች አሁን ላይ በስፋት እየተመረቱ ቢሆኑም የዚያኑ ያህል ትስስሩ አልተጠናከረም። ወተትም እንደዚሁ ነው። የክልሉ መንግሥት ችግሩን ተገንዝቦ ግብረ ኃይል አቋቁሞ እየሠራበት ነው፤ ግን ደግሞ ፍጥነት ይፈልጋል። ምክንያቱም አንዳንዱ ምርት በዘገየ ቁጥር የሚበላሽና የሚባክን በመሆኑ ነው።

የወተት ምርት ጉዳይ በሁለት መንገድ መመለስ መቻል አለበት የሚል እምነት አለን፤ አንደኛው እንደተባለው ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን በየአካባቢው ማስፋፋት፤ በሁለተኛ ደረጃ ሥርጭቱን ማስፋፋት ይሻል። ሆኖም የሚያመርተው አካል ራሱ መሸጥ ብቻ ሳይሆን ተጠቃሚ ሊሆን ይገባል፤ ምክንያቱም የግብርና ልማታችን አንዱ አጀንዳ ህብረተሰባችን የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ ማድረግ በመሆኑ ነው።

አንዳንድ ቦታ ላይ ሰዎች በግለሰብ ደረጃ ሀብታም መሆን ጀምረዋል፤ የተለያዩ ምርቶችን ያመርታሉ፤ ግን ምርቱን አይጠቀሙበትም፤ የሰው ለውጥ ደግሞ የሚታየው መጀመሪያ እሱና ቤተሰቦቹ የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት ሲችል ነው። በአጠቃላይ ግን እንደ ክልል እየተሠራ ያለ ነገር አለ፤ ጥያቄያቸውም ትክክል ነው ብለን ነው የምንወስደው።

አዲስ ዘመን፡- የክልሉን የገቢ አቅም ፤ የትምህርት ጥራትና የጤና አገልግሎቱን በማሳደግ ረገድ ምን ያህል ለውጥ እየተመዘገበ ነው ?

አቶ እንዳሻው፡– ሌላው ጉዳይ የክልሉን የገቢ አቅም ማሳደግ ነው፤ ይሄ ክልል ጥሩ የሚባል የገቢ አቅም አለው፤ ግን እስከ ዛሬ እየሰበሰበ የነበረው ገቢ በቂ የሚባል አይደለም። አሁን በተጠናከረ መንገድ የገቢ አቅምን ማስፋት፤ ሥርዓት ማስያዝ፤ ሆቴሎች ሰው ለተስተናገደበት ነገር ትኬት እንዲቆርጡ ማድረግ፤ እነሱ የሚሰበስቡት 15 በመቶ ተጨማሪ እሴት ታክስ ጊዜውን ጠብቆ ለመንግሥት እንዲገባ ማድረግ እና የገቢ ሥርዓት ህጋዊነት የማላበስ ሥራዎች ተሰርተዋል። አምና በደቡብ ስር ሳለ ከነበረው ገቢ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መሻሻል ያሳያል።

በትምህርት በኩልም መሠራት የሚገባቸው በርካታ ሥራዎች እንዳሉ መገንዘብ ችለናል። አምና የስምንተኛ ክፍል ውጤት የዚህ ክልል 19 በመቶ ብቻ ነበር ያለፈው። 12ኛ ክፍል ደግሞ 2 ነጥብ ሰባት በመቶው ብቻ ነበር ያለፈው። ይሄ በጣም አሳፋሪ ውጤት ነው። የተማሪ ውጤት ማሻሻል ያስፈልጋል። ብዙ መምህራን አሉ፤ የመጻሕፍት አቅርቦት ጥሩ ነው፤ በአብዛኛው የቤተ ሙከራ አደረጃጀት ጥሩ የሚባል ነው፤ ስለዚህ ይሄ ባለበት የተማሪዎች ውጤት ለምንድን ነው የሚያሽቆለቁለው? ተብሎ ተገምግሟል።

ይህንን ለመለወጥ ወደ 10 ሺ የሚሆኑ መምህራንን በዋቸሞ፤ ወልቂጤና ወራቤ ዩኒቨርሲቲዎች አስገብተን አሰልጥነናል። ወደ 700 የሚሆኑ ርዕሰ መምህራንም አብረው ሰልጥነዋል። በእኛ ክልል ትምህርት የሚሰጥበት፤ ፈተና የሚዘጋጅበት መንገድ ሊፈተሽ ይገባል ተብሎ በዚህም ህብረተሰቡን በማሳተፍ ጥራቱን ሊያሻሽሉ የሚያስችሉ ሥራዎች ሰርተናል።

በጤና አገልግሎት ረገድም በዋናነት ሁለት ነገሮችን ለይተን እየሠራን ነው፤ አንዱ የጤና ኤክስቴንሽን ሲሆን ይህ የኤክስቴንሽን ሥራ ተዳክሞ ነበር። የጤና ነገር ማለቅ ያለበት ክልል ላይ ሳይሆን ቀበሌና መንደር ላይ ነው ብለን የጤና ኤክስቴንሽኑን የማጠናከር ሥራ ተሰርቷል።

በዚህም እንደወረርሽኝ የገቡ እንደ ኩፍኝና ኮሌራ የመሳሰሉ በሽታችን በአጭር ጊዜ ተቆጥረናቸዋል። ሌላው ጤና ላይ የጤና መድን ፈንድ አገልግሎትንም በከፍተኛ ደረጃ አጠናክረን እየሠራን ነው። ከዚህ ቀደም ወደ 800 ሺ አባል ነበረ፤ በዚህ ዓመት በምንሠራው ሥራ ወደ 600ሺ ሰው እንጨምራለን፤ በዓመቱ መጨረሻ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን የጤና ፈንድ ተጠቃሚዎችን እንፈጥራለን ብለን እናስባለን። በዚህ መንገድ ሥራው የሚሠራ ከሆነ የጤና አገልግሎታችን መሻሻል ይኖረዋል ብለን እናስባለን።

አዲስ ዘመን፡- ከሥራ እድል ፈጠራና ኢንቨስትመንትን ከማስፋፋት አኳያ የተከናወኑ ሥራዎችስ ምን ይመስላሉ?

አቶ እንደሻው፡- በቀጣይ ትኩረታችን የነበረው የሥራ እድል ፈጠራ ነው፤ የሥራ እድል ፈጠራ ከኢንቨስትመንት ጋር ይያያዛል፤ አሁን ያለበት ደረጃ ጥሩ ነው፤ ግን በምንጠብቀው ደረጃ አይደለም። በተለይ ሁለት አካላት የሥራ እድል ፈጠራ በወሳኝ መልኩ የሚጠብቁ አሉ። አንደኛው የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ጨርሰው የተቀመጡ አሉ፤ ምንም ይሁን ምን ለእነዚህ ተመራቂዎች የሥራ እድል መፍጠር መቻል አለብን። ሁለተኛው ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት አለ፤ በነገራችን ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ከተሜነት 28 በመቶ ደርሷል፤ ብዙ ሰው ወደ ከተማ የመምጣት ፍላጎት አለው።

በመሆኑም የሥራ እድል ፈጠራው እነዚህ አካላት ላይ ማተኮር እንዳለበት አምነን እየተንቀሳቀስን ነው። በገጠር በግብርና፤ በከተማ ደግሞ ጥቃቅንና አነስተኛ በደንብ ተደራጅተው እንዲሰሩ እየተደረገ ነው። በዚህም መሠረት በከብት ተዋፅኦ ልማት፣ በንብ ማነብና ዶሮ እርባታን የመሳሰሉ ብዙ አማራጮች ላይ  እንዲሰማሩ ጥረት እየተደረገ ነው ።

ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት የመጀመሪያ ሥራ ያደረግነው ለኢንቨስትመንት ፈቃድ የሚሰጥበትን መንገድ ማጥራት ነው። አዲሱ ክልል ከመቋቋሙ በፊት ወደ 140 የሚሆኑ ለኢንቨስትመንት የተሰጡ ቦታዎች ነበሩ። እኛ ስንመጣ መፅደቅ ስላልቻልን ኮሚቴ አቋቁመን እንደገና እንዲጠና ነው ያደረግነው።

ከእነዚህ ውስጥ 77ቱ የኢንቨስትመንት መስፈርቱን በማሟላታቸው አልፈዋል። 35ቱ እስከ 60 በመቶ መስፈርቱን አሟልተው የሚቀራቸው ነገር አለ፤ ቀሪው 40 በመቶ በሁለት ወር ውስጥ አሟልተው የ77ቱ አካል እንዲሆኑ ሥራ እየተሠራ ነው። 29 ለኢንቨስትመንት የተጠየቁ ፍቃዶች ግን ወንጀል አልያም ችግር ስላለባቸው አስቀርተናቸዋል።

ኢንቨስትመንት መጀመሪያ መጀመር ያለበት ከማጥራት ነው፤ ይሄንን ሥራ እየሠራን ኢንቨስተሮችን የማበረታት ፣ የንግዱን ማህበረሰብ የማወያየት፣ የንግድ ማህበረሰቡ ባለን አጠቃላይ አቅም ላይ ስምሪት እንዲያደርግ የመደገፍ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። ሲገመገም ትክክለኛ ሃዲድ (መስመር) ላይ መሆናችንን አረጋግጠናል። ግን ብዙ ይቀረናል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የንግድ ልውውጡን ሥርዓት ለማስያዝ እየሠራን ነው። በተለይ በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ ያሉ አሻጥሮችን ማስቀረት ይገባል፤ የተመረተ ምርት እንደልብ እንዲንቀሳቀስ መደረግ አለበት። ሌላው ኮንትሮባንድን መቆጣጠር፣ ኬላዎች መቀነስ፣ ስለዚህ ንግድ ላይ ምርት በደንብ ወደ ከተማ እንዲገባ መደረግ ይኖርበታል። የመሸጫ ቦታዎችን ማመቻቸት፣ የንግድ ሰንሰለቱን ማሳጠርና መሠረታዊ ሸቀጣሸቀጦች በሸማቾች ህብረት ሥራ ሱቆች እንዲሰራጩ ማድረግ ይጠበቃል። የተጀመሩ ሥራዎች አሉ፤ እነዚህን አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል።

አዲስ ዘመን፡- በክልሉ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ሥራዎች በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ?

አቶ እንዳሻው፡– በመሠረተ ልማት ረገድ የገጠርም ሆነ የከተማ መንገዶች በጀታችን በፈቀደ መጠን እየተሠሩ ነው ያሉት። ግን እንደዛም ሆኖ አንዳንዶች አምስትና ከዚያ በላይ ዓመታት የፈጁ አሉ፤ አሁን ያስቀመጥነው አቅጣጫ 95 በመቶ በላይ ያለቁትን ለይቶ መጨረስ ነው። አንዳንዱ መንገዱ ይሰራና ድልድይ የለውም። እሱን የማስተካከል ሥራ ተሰርቷል። ሆኖም ከህብረተሰቡ ፍላጎት አንፃር ግን የሚቀረን ብዙ ነገር አለ፤ እሱ ላይ ተረባርበን መሥራት ይገባናል።

ከዚሁ ጎን ለጎን የውሃ መሠረተ ልማትን የማስፋፋት ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ ነው። ከከርሰ ምድር የማውጣት፣ የማጎልበት፣ የማስጠናት፣ ሥራዎችን እያከናወንን ነው። ሰው አማራጭ ንፁህ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኝ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ጥሩ ናቸው ብለን ነው የምንወስደው። ለምሳሌ ወልቂጤ ከተማ በወር አንዴ ነበር ውሃ የሚያገኘው፤ አሁን ቀኑን አሳጥረነዋል። በአስር ቀንና ከዚያ በታች ውሃ ያገኛሉ። ከዚህ ቀደም ሆቴል ያደረ ሰው ውሃ የማያገኝበት ሁኔታ ነበር፤ አሁን ግን ቢያንስ በባልዲ የሚያገኝበት ሁኔታ አለ። አሁንም አቅም በፈቀደ መጠን የህብረተሰቡን ጥያቄ እንመልሳለን ብለን እናስባለን።

አዲስ ዘመን፡- የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በተለይ እንደ ወልቂጤ ያሉ ትልልቅ የክልሉ ከተሞች ላይ ለዓመታት የቆየ ችግር እንደሆነ ይታወቃል። በተለይ ለሆቴል ኢንዱስትሪው አለመስፋፋት እንደምክንያት ይጠቀሳል። የእርሶ አስተዳደር ይህንን ችግር ለመፍታት ምን ያህል ርቀት ተጉዟል?

አቶ እንደሻው፡- አስቀድሜ እንደገለፅኩት በስፋት እየተሠራባቸው ካሉ የልማት መስኮች መካከል የንፁህ መጠጥ ውሃ ሥራ አንዱ ነው፤ የዚያኑ ያህል ግን ፍላጎቱ በከፍተኛ መጠን እያደገ ነው። የውሃ ሥራ ደግሞ ከዲዛይን ጀምሮ ውሃ እስከ ማውጣት ድረስ ከፍተኛ በጀት ይፈልጋል። እኛ በዚህ ዓመት አዳዲስ ፕሮጀክቶችን አናስብም፤ ግን ደግሞ የተጀመሩትን ፍፃሜ እንዲያገኙ ድጋፍ እናደርጋለን ።

የዚያኑ ያህል ሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዮች አሉ። እኛ ከመምጣታችን በፊት የአንዳንድ ወረዳዎች ደመወዝ አልተከፈለም። ለአምስትና ስድስት ወራት መምህራን፤ የጤና ባለሙያዎች ደመወዝ አላገኙም። በመሆኑም ካፒታል ፕሮጀክት አቁመን ደመወዝ መክፈል ነው የጀመርነው። ስለዚህ ችግሩን እንዳለ ወስደን፤ ግን የሚቀድመው ማስቀደም አለብን።

ከወልቂጤና መሰል ከተሞች ላይ የተነሳው ጥያቄ ለዓመታት የቆየ መሆኑ ቢታወቅም እኔ ልመልስ የምችለው እኔ መሪ ከሆንኩበት ጊዜ ወዲህ ያለውን ነው። ከዚያ ወዲህ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ራሳቸው መጥተው ጥናቱን ካስጠኑ በኋላ የወልቂጤ ውሃ በልዩ ሁኔታ፤ እርሳቸው ብቻ ሳይሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትራችንም ሃሳብ በመሆኑ ይሄ ችግር በልዩ ሁኔታ መፈታት መቻል አለበት ተብሎ የጎደሉ እቃዎች መጥተው የወልቂጤ ነዋሪ ውሃ ያገኝበት ከነበረበት 30 ቀን ወደ አራት ቀን እያወረድን ነው ።

አስቀድሜ እንደተናገርኩት አንዳንዱ ሆቴል የራሱን ጉድጓድ ቆፍሮ ውሃ አውጥቷል። ሌሎችም ሆቴሎች የየራሳቸውን ጉድጓድ ቆፍረው እንዲሰሩ ነው እየገፋፋናቸው ያለው። ችግሩ ግን ለመጠጥ ውሃ ተብሎ የሚመረተው ውሃ መኪና፤ ልብስ መሰል ነገሮች የሚታጠቡበት በእሱ ነው። ስለዚህ የተለያየ ውሃ ስለሌለ ለእጥረቱ እንደ አንድ ምክንያት የሚታይ ነው።

በሁለተኛ ደረጃ ውሃ ከምርቱ ቦታ ተነስቶ ተጠቃሚው ጋር እስከሚደርስ የሚባክንበት ሁኔታ አለ። በዓለም አቀፍ ጥናት መሠረት ስድስት በመቶው ሊባክን እንደሚችል ቢገመትም እኛ አካባቢ ግን የሚባክነው ውሃ 42 በመቶ እንደሚደርስ ነው የሚገመተው። ስለዚህ መንገድ ላይ የሚባክነውን መቆጣጠር ያስፈልጋል። በጥቅሉ ጥያቄው ትክክል ነው፤ ግን ደግሞ እየተፈታ ያለውን ነገር መውሰድ ያስፈልጋል።

ከመብራት ጋር ተያይዞ እኛ ባናስተዳድረውም የኃይል አቅርቦቱን የሚያስተዳድሩ አካትን የእኛ ግብረ-ኃይል አድርገናቸዋል። ዲስትሪክቶች የእኛ ግብረ ኃይል ናቸው፤ ችግር ሲያጋጥም ይነገራቸዋል፤ ለከተማዎች፣ ለኢንዱስትሪ መንደሮች፣ ለሆስፒታሎችና መሰል ተቋማት ባልተቋረጠ ሁኔታ ኃይል እንዲገኝ ባደረግነው ውይይት መሻሻሎች አሉ።

በአጠቃላይ እነዚህን ሥራዎች ይዘን እንዴት ነው ለህብረተሰቡ አገልግሎት የምንችለው? መልካም አስተዳደር ምን ይመስላል? ሰው አይጉላላም ወይ? አይመላለስም ወይ? የሚለውን ነገር ለመመለስ ጥረት ተደርጓል።

አዲስ ዘመን፡- ግን ደግሞ የኃይል መቆራረጥ ችግር በክልሉ በተደጋጋሚ የሚስተዋል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የኃይል አቅርቦት የሚሹ እንደ ዶሮ እርባታና መሰል የግብርና ሥራዎች ተግዳሮት እንደሆነባቸው ያነሳሉ። ወልቂጤ ከተማ የነበረው ዲስትሪክት መነሳቱም እንደ አንድ የቅሬታ ምንጭ ይነሳል፤ ይህንንስ ችግር ለመፍታት ምን እየተሠራ ነው?

አቶ እንደሻው፡- እውነት ነው የኃይል መቆራረጥ አለ፤ መቆራረጥ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ቦታ ላይ የሙከራ ሥርጭት እስኪመስል ድረስ መቆራረጡ ይደጋገማል። ግን ችግሩን ከለየን በኋላ ከመብራት ኃይል አመራሮች ጋር የጋራ ፎረም አቋቁመን በመፍትሄ ጉዳዮች ዙሪያ እንወያያለን፤ አሁን በአንፃራያዊ ሁኔታ ለውጥ አለ። ወልቂጤ መብራት ችግር ያለው ዲስትሪክት ስለሌለ አይደለም፤ ሌላ ጥያቄ ነው፤ እሱን ለብቻ ብናየው ነው የሚሻለው። መጠየቅ ያለበት ዲስትሪክቱ ይመለስልን ሳይሆን መብራት ይምጣልን ቢሆን ይመረጣል። ችግሩ ግን ተለይቷል።

አዲስ ዘመን፡- የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታትና ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ረገድ የተገኘ ውጤት ካለ ?

አቶ እንዳሻው፡- አንዳንድ ቦታዎች ላይ የመልካም አስተዳደር ችግር አሁንም ይስተዋላሉ። በተለይ የመሬት አስተዳደር አካባቢ ጎልቶ ይታያል፤ ለምሳሌ ከተሞች ላይ መሬት አስተዳደርን በተመለከተ ተከታታይ ቁጥጥር ይፈልጋል። መሬት ከሙስና ነፃ መሆን አለበት፣ ለዚህ ልዩ ልዩ ሞዳሊቲዎችን እየቀረጽነው ያለነው፤ እነዚህን አስተካክለን ለመሄድ እንሞክራለን፤ ሠራተኞችን አሰልጥነናል፤ በተቀመጠው መስፈርት መሠረት አገልግሎት እንዲሰጥ ተግባብተናል። ይህም ቢሆን ከሕዝቡ የሚመጡ አንዳንድ ቅሬታዎች አሉ።

ሰው አገልግሎት ለማግኘት መመላለስና መማለጃ መስጠት የለበትም፤ አንድ አንድ ቦታዎች ላይ ባየናቸው ምልክቶች ተመስርተን ርምጃ ወስደናል። በአጠቃላይ ክልላችን ባለው የስድስት ወራት እድሜ የአዲስ ክልል ባህሪ ሳይሆን የነባር ክልል ባህሪ ይዘን እየተንቀሳቀስን ያለነው ፤ የሕዝቡ ድጋፍ ጥሩ ነው፤ የምሁራንና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድጋፍ ጥሩ ነው። የወጣቶች አጠቃላይ ድጋፍ መልካም የሚባል ነው። ስለዚህ አመራሩም ሆነ ሕዝቡ የሚተጋገዝ ከሆነ በአጭር ጊዜ ወደ ጥሩ ደረጃ እናደርሳለን ብለን እናስባለን።

አዲስ ዘመን፡- ሆሳዕና ላይ ለመገንባት ታቅዶ የነበረው ኤርፖርት ምን ደረጃ ላይ ደርሷል ?

አቶ እንዳሻው፡- ወደ አየር መንገድ ከመሄዳችን በፊት መሬቱ ላይ ብንጨርስ መልካም ነው። ከመንገድ መሠረተ ልማት ጋር ተያይዞ ከዓለም ገና ቡታጀራ፤ ከቡታጀራ -ሆሳዕና ፤ ከሆሳዕና- ወላይታ ሶዶ ከዚያም ወደ ጂንካ ሊገቡ የሚችሉ የመንገድ ዲዛይኖች አሉ። ክልሉ በተመሠረተ በሁለተኛው ወር ከመንገዶች ባለስልጣናት ጋር ሆሳዕና ላይ ውይይት አድርገን ነበር። አሁን ላይ የመንገድ ጨረታ እየወጣ ነው ያለው፤ እስከዚያ ድረስ ግን ጥገና እየተከናወነ ነው። ባለስልጣኑ በዚህ አጋጣሚ ሊመሰገን ይገባል ባይ ነኝ። ምክንያቱም ዋናውን ጨረታ አውጥቶ ግንባታው እስከሚጀመር ድረስ ህብረተሰቡ እንዳይንገላታ መጠገኑ የሚያስመሰግነው ነው።

እንዳነሳሽው በክልላችን አውሮፕላን ማረፊያ ያስፈልገናል። መኖር እንዳለበትም ተማምነናል። ጥናቱን የሚያደርጉ ቡድኖች ወደ ሆሳዕና ከተማ መጥተው ሶስት ቦታዎችን ለይዋል ፤ ዝርዝር ጥናትም እያደረጉ ነው። መቼ ነው የሚጀመረው? ምንድነው የሚሰራው? የሚለው ዝርዝር መረጃ ግን ከአቬሽን አላገኘንም። እንደተጀመረ ይፋ የምናደርገው ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- ቡኢ ላይ ለመገንባት ታቅዶ የነበረው አዳሪ ትምህርት ቤት ጉዳይስ ?

አቶ እንደሻው፡- ቡኢ ላይ ያለው አዳሪ ትምህርት ቤት የሚሠራው በግለሰቦች ነው፤ ውጭ ካሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያና እዚህ ሀገር ውስጥ ያሉ በጎ ፍቃደኞች ሥራ ለማስጀመር የሚያስችል ገንዘብ ተሰብስቦ ትምህርት ሚኒስቴር ገብቷል። በቅርብ ጊዜ ሠራው እንደሚጀመር ከትምህርት ሚኒስትሩ ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር በቅርቡ ውይይት አድርገናል።

የእነሱ ሃሳብ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ትምህርት ቤት ከተሠራ በኋላ በሚቀጥለው ዓመት የሆነ ነገር መጀመር አለበት የሚል ነው። በአጠቃላይ ግን የፕሮጀክቱ ባለቤት እኛ አይደለንም፤ አሁን በደረስንበት ንግግር ግን በቅርቡ ግንባታ እንደሚጀመር መረጃው አለን፤ ቦታው ተዘጋጅቷል፤ ለሁለተኛ ደረጃ የሚሆን እስከ 12 ሺ ካሬ ቦታ ተዘጋጅቷል።

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ በተፈጥሮም ሆነ ባህላዊ የቱሪዝም መስህብ ሀብት ባለቤት ቢሆንም ወደሌሎች ክልሎች የቱሪዝም መዳረሻ መንገድ ከመሆን በዘለለ ሰፋፊ የቱሪዝም ፕሮጀክቶች አለመከናወኑ እንደቅሬታ ይነሳል፤ በዚህ ረገድ ምን ታስቧል?

አቶ እንደሻው፡- ልክ ነው፤ ለምሳሌ ክልላችን ከየም ሳጃ አካባቢ እስከ ጥያ ድረስ ያለውን ቦታ ብቻ እንኳን ብንወስድ በርካታ የቱሪዝም መስህቦች ነው ያሉት። ለምሳሌ ወደ ከንባታ ብንሄድ 777 የሚባለው ተራራማ ስፍራ፤ ስልጤ ላይ ያሉ ሐይቆች፣ ሁለቱ ጉራጌዎች አካባቢ ደግሞ ዘቢዳር አለ፤ የም ብንሄድ እጅግ የሚያምር ሥነ ምህዳር አለ፤ ከጉራጌ ዞን እስከ ወላይታ የሚዘልቁ ሰንሰላታማ ተራሮች ራሳቸው ሌላው የክልላችን መስህብ ናቸው።

እነዚህን በሙሉ ስናይ ሥራ አልተሠራም ብሎ ህብረተሰቡ ቢቆጭ ተገቢ ነው። አሁን ግን ቁጭቱን ወደ ሥራ ለመቀየር እየተንቀሰቀስን ነው። ለምሳሌ ጥያ ትክል ድንጋይ ባለፈው የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን የመደመር መጽሐፍ ተሽጦ እንድንሰራበት አበርክተውልናል። በዚያን ጊዜ በነበረው የመጽሐፍ ሽያጭ የተወሰኑ ቃል የተገቡ ገንዘቦች እንዳሉ አስታውሳለሁ።

እኛ ከመጣን በኋላ የመጀመሪያ ያደረግነው ሥራ ጥያ ትክል ድንጋይ የዓለም ቅርስ ስለሆነ ሁለት ዓይነት ዲዛይን አሰርተናል። አንዱ ዲዛይን ባህላዊ ነገሩ የሚያሳይ ሲሆን ዘመናዊ ገጽታውንም ለማሳየት ተሞክሯል። በመቀጠልም ሁለቱን ዲዛይኖች ወደ አንድ የማምጣት ሥራ ተሰርቷል።

ይህንን ዲዛይን መሠረት በማድረግ ለቅርስ ለሚመለከተው፤ ዩኒስኮም ሃሳብ ሊሰጥበት ስለሚገባ ቦርድ ተቋቁሟል። ስለዚህ ሥራ ለማስጀመርና መሠረተ ድንጋይ ለማስቀመጥ ዝግጅት ላይ ነው ያለነው። አሁን ያለን መርሆ ‹‹የማናሰጨርሰውን ሥራ አናስጀምርም›› የሚል ነው። በመሆኑም ሥራ ከማስጀመራችን በፊት የፋይናንስ አቅማችን ከየት ይመጣል የሚሉትን ነገሮች መልሰን ነው ወደ ሥራ የምንገባው።

እንደ አጠቃላይ ግን የጥያ ትክል ድንጋይን በተሻለ መንገድ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የተሠራው ዲዛይን በጣም የሚያምር ነው፤ በርካታ ባለሀብቶች፤ ኤምባሲዎችና ዓለም አቀፍ ሰዎችም የሚሳተፉበት ነው የሚሆነው። ሌሎችንም የቱሪዝም መዳረሻዎች ለማስፋት ጥናት እያደረግን ነው፤ በተለይ ከባለሀብቶች ጋር በጋራ የሚሰሩ ሥራዎችን እየለየን ነው። እሱ ብቻ ሳይሆን ከነሐሴ እስከ ጥቅምት ወር ድረስ የማይዳሰሱ እንደ መስቀል፣ ያሆዴ በዓልና መሰል ባህላዊ ክዋኔዎች ራሳቸውን ችለው የቱሪዝም መስህብ እንዲሆኑ የሚያደርግ ዝግጅት እያደረግን ነው ያለነው፤ በቅርቡ ወደሥራ ይገባል።

አዲስ ዘመን፡- በርካታ ወጣቶች ሥራ ፍለጋ ወደ ከተማ ከሚፈልስባቸው አካባቢዎች መካከል ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፤ ወጣቱ በአካባቢው ሥራ ፈጥሮ እንዲሠራ ከማድረግ ረገድ ምን እየተሠራ ነው?

አቶ እንደሻው፡- በነገራችን ላይ ፍልሰቱ ባህላዊ አንድምታም አለው። ለምሳሌ የጉራጌን ማህበረሰብ ብንወስድ ፍልሰት የጀመረው ። ጥንታዊ መሠረት ያለው ነው። ጉራጌ በሁሉም አካባቢዎች ላይ ተንቀሳቅሶ መሥራት ባህሉም ጭምር ስለሆነ ነው። ከንባታና ሃድያ አካባቢ ያሉ ወጣቶች ደግሞ ወደ ደቡብ አፍሪካና መሰል የአፍሪካ ሀገሮች በስፋት የመሄድ ልምድ አላቸው።

አሁን ላይ ወጣቱ እንዳይሄድ መገደብ ሳይሆን ህጋዊ በሆነ መንገድ እንዲሄድ ማድረግ፤ በሚሄድበት አካባቢ ችግር እንዳያጋጥመው መከላከል፤ አስተምሮ መላክ ነው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው። የሌሎች ሀገራት የእድገት ተሞክሮ የሚያሳየው እንደዚሁ ነው። አሁን ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር እንደጀመረው ዓይነት ሥራ ማከናወን ያስፈልጋል። ወደ ውጭ ስንልካቸው እሴት ጨምረን መላክ አለብን። ይህንን ማድረጋችን ገቢ ያሳድጋል፤ ደህንነቱም ይጠበቃል።

ወደ ውጭ ከሚሰደደው በላይ የሚያሳስበን ዝም ብለው የተቀመጡ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ናቸው። እነዚህ ወጣቶችን መነሻ ገንዘብ ሰጥቶ ከሙያቸው ውጭም ቢሆን ሰርተው ሀብት እንዲያፈሩ ማድረግ ያስፈልጋል። ብድር፤ የመሥሪያ ቦታና የገበያ ትስስር በተመለከተ በጥቃቅንና አነስተኛ ለሚሰማሩ ወጣቶች የሚደረግ ድጋፍ አለ።

አዲስ ዘመን፡- ከቀቤና ጉራጌ ማህበረሰብ ጋር ተያይዞ አሁንም ድረስ ግጭቶች ይስተዋላሉ፤ ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ምን እየተሠራ ነው?

አቶ እንደሻው፡– የቀቤና ማህበረሰብ ራሱን የቻለ አንድ በክልላችን ያለ ብሔረሰብ ነው፤ ባለፈው ክልሉ ሲደራጅ ጉራጌ ዞን በአራት ቦታ ተከፍሏል። የማረቆና የቀቤና ልዩ ወረዳዎችና ለአስተዳደር እንዲመች ቡታጀራ አካባቢ ደግሞ ምስራቅ ጉራጌ ዞን ተብሎ ተደራጅቷል። ቀቤና አካባቢ የሚፈጠረው ፀብ የህብረተሰቡ አይደለም። ፀቡን እየቀሰቀሰም ሆነ እያስፋፋ ያለው ግማሹ አመራሩ ነው፤ ከፊሉ የተማረው ኃይል ነው፤ ሌላው ደግሞ ነጋዴ ነው።

ሁለቱ ሕዝቦች አብረው የኖሩ፤ የሚኖሩና የተዋለዱ ናቸው። አብረው መስጊድ የሚሰግዱ በጋራ ፈጣሪያቸውን የሚያመልኩ፤ ልጆቻቸው አብረው የሚማሩ ናቸው። ለወደፊትም አብረው ይቀጥላሉ። እኛ ብንመራቸውም ባንመራቸውም አብረው የሚኖሩ ሕዝቦች ናቸው። አሁን ሁለቱም ጋር ፤ ‹‹አንተ ትበልጣለህ፤ ሊላው ያንሳል›› እያሉ የሚያነሳሱ ፀሐፊዎች አሉ።

እኛ ከመጣን በኋላ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በሠራነው ሥራ አሁን ላይ መረጋጋት ተፈጥሯል። ግን እንደገና እንዲነሳ ፤ አንዱ በሌላው ላይ እንዲዘምት፤ ችግሮች እንዲፈጠሩ የሚያደርጉ አካላት አሉ። እነዚህ አካላት እርስበርስ ይተዋወቃሉ። ሆኖም ግን ሊሰመርበት የሚገባው በጉራጌና ቀቤና ሕዝቦች ምንም ዓይነት ችግር የሌለ መሆኑን ነው። ምክንያቱም ደግሞ ተጋብተው ቤተሰብ መስርተው የሚኖሩ ናቸው።

በቀጣይ ደግሞ የማካለል ሥራ ይሠራል። እዚህ ላለው የጉራጌ ሕዝብ ቅርቡ ቀቤና ነው፤ ለቀቤናም የሚደርሰው ጉራጌ ነው። በመሆኑም ሁለቱን ሕዝብ እያተራመሰ ያለው ከትርምሱ ጥቅም አገኛለሁ ብሎ የሚንቀሳቀስ አካል ነው።

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ ቀድሞ ከነበረበት ክልል ሲወጣ የነበረው የሀብት ድርሻ ምን ያህል በፍትሐዊ መንገድ ተካፍሏል ተብሎ ይታመናል?

አቶ እንዳሻው፡- በሀብት ክፍፍል በኩል እንደሚታወቀው ሲዳማም ሆነ ሌሎች ክልሎች ራሳቸውን ችለው ሲቋቋሙ ይዘው የወጡት የየራሳቸው ድርሻ አለ። ግን ዋነኛ ድርሻ የሚባለውንና ለሁለትና ለአራት የምንካፈላቸው ድርሻዎች አሉ። አንደኛው ድርሻ የሰው ኃይል ነው። እሱን ተከፋፍለን ጨርሰናል።

ሁለተኛው ሀብት የሚባለው ተሽከርካሪ፣ ሞተርና ኤሌክትሮኒክስ ነው፤ እሱንም ተከፋፍለን ጨርሰናል። ሌላው ሀብት በጋራ የሠራነው ሕንፃ ነው፤ ይህንንም የፌዴራል ሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ገብቶ ግምት እያወጣ ነው ያለው። ፍትሐዊ ነው፤ አይደለም የሚለው ገና ስላልተከፋፈልን መናገር አይቻልም።

ይህ ሲባል ግን ከሲዳማ ሕዝብ ጋር ያለን መልካም ግንኙነት በማያሻክር ሁኔታ የሚፈፀም እንደሆነ ከግንዛቤ መውሰድ ይገባል። ምክንያቱም ይህንን ሀገር የሚመራው አንድ ፓርቲ ነው። ሥራውን እየሠራው ያለው ያው አካል ነው። ስለዚህ ክፍፍሉ በጣም በጥንቃቄ የሚካሄድ ነው፤ ምክንያቱም ዝም ብሎ የባልና ሚስት ፍቺ መሆን የለበትም። ሕዝቡ መልሶ የሚገናኝ ነው። በመሆኑም እኛ ትኩረት የምንሰጠው የቀደመው መልካም ግንኙነታችን ተጠናክሮ በሚቀጥልባቸው ሁኔታዎች ላይ መሆኑን ከግምት ውስጥ ማስገባት ይገባል።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።

አቶ እንዳሻው፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን  መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You