– ክልሉ በሌማት ትሩፋትም ውጤታማ እየሆነ ነው
ቦንጋ፡- በክልሉ በበጀት ዓመቱ 889 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ገለጹ። ክልሉ በሌማት ትሩፋትም አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን አስታውቋል።
የቢሮ ኃላፊው አቶ ማስረሻ በላቸው በተለይ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በክልሉ ባሉ ሶስት ሺ 886 የችግኝ ጣቢያዎች አማካኝነት ሀገር በቀልና የውጭ ዝርያ ያላቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች ያካተተ የዘር ዝግጅት ተደርጓል።
ኃላፊው እንዳሉት ችግኞቹ የሚተከሉት በሚያዝያና ሐምሌ ወር ላይ ጀምሮ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ዝግጅቱ በቅርቡ በግምገማ ወደ 26 ሚሊዮን ችግኞች ዝግጅት ተደርጓል። ይህም በየቀኑ ይጨምራል። አሁን ላይ 40 ሚሊዮን የደንና ጥምር ደን 71 ሚሊዮን የቡና ችግኞች ለሚያዝያና ሐምሌ ተከላ ዝግጅት ተደርጓል። የተለያዩ የደን ዝርያ ያላቸው ሁለት መቶ 60 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ችግኞች በግብርናው ዘርፍ ይተከላሉ።
በሌላ በኩል የሌማት ትሩፋት ስራው ከክልል ምስረታው ጋር አብሮ መጀመሩን የገለጹት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በክልሉ እንደ ሀገር የተያዘው የሌማት ትሩፋት በወተት፣ በዶሮ ስጋ፣በማርና በአሳ ላይ እየተሰራ መሆኑንና ይህም ውጤት እያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል።
ክልሉ ካለው አቅም አንጻር በቀይ ስጋ ድለባ ተጨምሮ በአምስት ዘርፎች የሌማት ትሩፋት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ በአራት ዓመት የሚከናወን ሥራ በወተት 504 የሚሆኑ መንደሮችን በመለየት አንድ መቶ 22 የወተት መንደሮችን በመለየት 14 ሺ 400 የሚሆኑ የወተት ላም አርቢዎችን በማደራጀት ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል።
እንደ አቶ ማስረሻ ገለጻ፤ በወተት መንደሮች ዝርያን ማሻሻልና የመኖ ልማትን በስፋት በመስራት ከአራት ዓመት በኋላ በመንደር ውስጥ ያለውን የወተት ምርት ከፍ ለማድረግ እየተሰራ ነው። በዚህ ዓመት ብቻ 18 ሺ 209 የሚሆኑ የውጭ ደም ያላቸው ላሞችን በማዳቀል ወደ ስድስት ሺ 256 የሚሆኑ ጥጃዎች ተገኝተዋል። 86 ሺ የሚሆኑ ጊደሮች ወደ መንደሮች እንዲሰራጩ ተደርጓል።
የወተቱ ምርት ሊያድግ የሚችለው በመኖ ላይ ለውጥ በማምጣት ነው ያሉት አቶ ማስረሻ፤ ሀገረሰብ ላሞች ቢሆኑም ጥሩ ከተመገቡ ጥሩ ወተት ሊሰጡ ስለሚችሉ 55 ሺ ኩንታል በላይ የሚሆን መኖ ተሰራጭቷል። አሁን ባለው ሁኔታ በወተት ምርት ሁለት መቶ 22 ነጥብ 15 ሚሊዮን ሊትር ወተት ማምረት ተችሏል ብለዋል።
የዶሮ እርባታ በ703 መንደሮች ላይ በአራት ዓመት ውስጥ እንደሚከናወን የጠቆሙት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በዚህ ዓመት በ218 መንደሮች 21 ሺ የሚሆኑ አርቢዎችን በማደራጀት ወደመንደሮቹ ገብተዋል። አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን የአንድ ቀን ጫጩት ለማሰራጨት ታቅዶ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን የሚሆን የአንድ ቀን ጫጩትና አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የሚሆን ቄብና ኮክኔ ተሰራጭቷል ብለዋል።
ሁለት ሺ 507 ቶን የሚሆን መኖ በእነዚህ መንደሮች ላይ ተሰራጭቷል። በግማሽ ዓመቱ አንድ መቶ 31 ሚሊዮን እንቁላል ለማግኘት ታቅዶ ባለፉት ስድስት ወራት 113 ነጥብ 49 ሚሊዮን እንቁላል መሰብሰብ ተችሏል። ይህም የእቅዱን 86 በመቶ ገደማ ነው። የዶሮ ስጋ ወደ 2 ሺ 24 ነጥብ 5 ቶን ሲሆን፤ ይህም የእቅዱን 89 በመቶ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
ሞገስ ተስፋና ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም