‹‹አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ›› ለሰው ልጅ ስጋት ወይስ ተስፋ?

በአማርኛ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም ሰው ሰራሽ ማሰላሰል ወይም ሰው ሰራሽ ሰው የሚመስል የማሽን ሥራ ሊባል ይችላል። ሆኖም ግን በምሁራን ሲባል የተሰማ የአማርኛ አቻ ስላልተለመደ ሁሉም ሰው በሚጠራበት ‹‹አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ›› ስሙ እንቀጥላለን። አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማለት በአጭሩ የሰው ልጅ የሚሰራውን ሥራ በማሽን መሥራት ማለት ነው። በቅርቡ በተጀመረው ደግሞ ማሰብና ማሰላሰልን ጨምሮ የሰውን ልጅ አዕምሮ የሚተካ ሰው መሳይ ማሽን ማለት ነው።

በዚህ ጉዳይ ላይ የታሪክ እና የማህበረሰብ ጥናት (ሶሽዮሎጂ) ተመራማሪዎች ስጋታቸውን እየገለጹ ናቸው። ከታሪክ ተመራማሪዎች አንዱ የሆነው የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪው ዩቫል ኖህ ሄራሪ ‹‹የነገው ታሪክ (Brief History of Tomorrow) የሚል ባለ 264 ገጽ መጽሐፍ አለው። ሰውየው በብዙ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እየተጋበዘ ስለሰው ልጅ ቀጣይ ዕጣ ፋንታ ማብራሪያ ይሰጣል። በዚህ መጽሐፉ ግን በዝርዝር ያስረዳል። ይሄው ተመራማሪ ‹‹21 ትምህርቶች ለ21ኛው ክፍለ ዘመን (21 Lessons For The 21st Cenrury)›› በሚለው መጽሐፉ ስለአሁኑ ዘመን የቴክኖሎጂ ተግዳሮቶች ስጋቱን ይገልጻል። አሁን ያለው የዲጂታሉ ዓለም የሰውን ልጅ ሰብዓዊነት ይለውጣል ይላል። አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሰውን ልጅ የበላይነት እንደሚቀማ እና ዓለምን በቁጥጥሩ ሥር እንደሚያደርግ ይተነብያል፤ ምልክቶችም ታይተዋል ይላል። ሊያስከትሉ የሚችሉትን ችግርም በአገራችን ልማድ ‹‹ጥንቆላ›› በሚባለው አይነት ይናገራል። ምናልባትም የሰው ልጅ ከዛሬ 50 ዓመታት በኋላ ሞትን ሊያሸንፍ ይችላል ብሎ ይናገራል።

የተመራማሪዎችን ስጋት ይዘን ነባራዊ ሁኔታውን ልብ እንበል። አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ምንድነው? አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አሁን ላይ የረቀቀ ስለሆነ፣ የሰውን ልጅ አስቦ የመሥራት ሚና የሚወጣበት ደረጃ ላይ ስለደረሰ እንጂ ቴክኖሎጂው ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ (1900) ጀምሮ እንደሆነ ይነገርለታል። ይሄውም የማሽን ቴክኖሎጂ ሥራዎች ሁሉ አሁን ባለበት ደረጃ ባይሆንም የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ውጤት ነበሩ ማለት ነው። የሰው ልጅ በአዕምሮው ውጤት የቁጥር ቀመሮችን ሠራ። የሒሳብ ስሌቶችን (መደመር፣ መቀነስ፣ ማባዛትና ማካፈል) በአዕምሮው እያሰበ ይቀምር ነበር። በኋላ ግን የማሰቢያ ማሽን መጣ። ትልልቅ ቁጥሮችን በፍጥነት ማስላት አስቻለው ማለት ነው። የሰውን ልጅ ሥራ አቀለለ ማለት ነው።

በድሮው ጊዜ በድንጋይ ላይ ይጻፍ ነበር፤ ቀጥሎ በብራና ይጻፍ ነበር፤ ቀጥሎ ወረቀት ሲመጣ ሥራ አቀለለ። ቀጥሎ አሁን የምንጠቀምበት ኮምፒውተር መጣ። አሁን ደግሞ የኮምፒውተር ቁልፎችን (ኪቦርድ) መቀጥቀጥ ሳያስፈልግ እየነገሩት ብቻ የሚጽፍ መተግበሪያ በአንዳንድ ተጠቃሚዎች ዘንድ አለ። ይህ ሁሉ ደረጃው ይለያይ እንጂ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አይነት ነው። የሰውን ልጅ ሥራ ተክተው የሚሰሩ ናቸው። ድንጋዩም፣ ወረቀቱም፣ ኮምፒተሩም የሰውን ልጅ ሃሳብ ለማስተላለፍ ሲያገለግሉ የነበሩ ናቸው። አድካሚ ሥራዎችን ያቀለሉ ናቸው።

በእነዚህ ሁሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ግን አንድ ሀቅ አለ። ሁሉንም የሚቆጣጠራቸው የሰው ልጅ ነው። አሁን ያለውን የኮምፒውተር ሁኔታ እንደ ማሳያ ብንወስድ፤ ኮምፒውተር ያልሰጠነውን ነገር አይሰራም። ያላዘዝነውን ነገር አያንቀሳቅስም። ሁሉንም ሥራዎች የሚያሰራው የሰው ልጅ ነው።

የዘመኑ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አደገኛነት እዚህ ላይ ነው እንግዲህ! የአሁኑ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሰውን ልጅ የበላይነት እየቀማ ነው። አሳቢው እሱ ሆኖ፤ የሰው ልጅ ግዑዝ ሊሆን ነው ማለት ነው። ይህን ደግሞ በቀላሉ በምንጠቀማቸው መተግበሪያዎች ማየት እንችላለን። ሥራ ስላቀለሉን በራሳችን አስበን መሥራት የሚገባንን ነገር ሁሉ በመተግበሪያ እንሰራዋለን ማለት ነው። ይህ እየረቀቀ እና አይነቱ እየጨመረ ሲመጣ የሰው ልጅ ማሰብ የሚባል ነገር ያቆማል ማለት ነው። ያኔ ጥቂቶች ተመራማሪዎች በሚሰሩት ቴክኖሎጂ የዓለም ሕዝብ ሁሉ ግዑዝ ሊሆን ይችላል ማለት ነው። በተለይም የምርምሩ አካል ያልሆኑት የታዳጊ አገራት ዜጎች ከሰውነት ወደ ዕቃነት ይቀየራሉ ማለት ነው። ያቺኑም ትንሿን ማሰባቸውን በማሽን ተክተው ግዑዝ ነገር ሆነው ይቀራሉ ማለት ነው።

ዛሬ ላይ ሁሉንም ነገር በሰው ሰራሽ ማሰብ (AI) መሥራት ይቻል ይሆናል። ለምሳሌ፤ የካፌ አስተናጋጅ ሮቦት ሊሆን ይችላል። የትኛውንም ያዘዙትን ነገር ሳያዛባ ሊያመጣ ይችላል። ሥራዎች ሁሉ በዚሁ በሰው ሰራሽ ማሰብ (AI) ሊሰሩ ይችላሉ። ግን ይሄ ሮቦት ትክክለኛውን ሰዋዊ ስሜት ይሰጣል? የሰው ልጅ ውበት የሆኑትን መሳቅ፣ መጫወትና መናደድም ቢሆን ሊያስገኝ ይችላል? ማህበራዊ ሕይወት ሲቋረጥ የሰው ልጅ ዕጣ ፋንታ ምን ይሆናል? የፈጠራ ሃሳቦች ከምን ሊገኙ ይችላሉ? ዓለም የሆነ ቦታ ላይ እንዳትቋረጥ አያሰጋም ወይ?

ይህን ሳስብ አንዳንድ ጊዜ በሃይማኖታዊና ልማዳዊ መንገድ የሚነገረው ‹‹የኖህ ዘመን›› እየተባለ የሚነገረው የጥፋት ዘመን ትዝ ይለኛል። ምናልባት ዓለም የሆነ ቦታ ላይ ቆማ፤ እንደገና ከዜሮ ልትጀምር ይሆን? የሚል ቀልድ መሰል ሀሳብ እንድናስብ ያደርጋል። ሰዋዊ የሆነው የሰው ልጅ ስሜት ከጠፋ ማሽን ብቻውን ግዑዝ ነው።

እንደ ዩቫል ኖህ ሄራሪ ያሉ የሰው ልጅ ታሪክ ተማራማሪዎች ያስቀመጡት ትንቢት ሊደርስ የሚችልበት ነባራዊ ሁኔታ አለ። አንድ የማይታመን የሚመስል ትንቢቱን እናንሳ። ምናልባትም ከ50 ዓመታት በኋላ የሰው ልጅ ሞትን ሊያሸንፍ ይችላል፤ ዕድሜውን እንደ ሞባይል ባትሪ ‹‹ቻርጅ›› እያስደረገ ሊቆይ ይችላል ይላል። በመለኮታዊ መንገድ አማኝ በሆነ ማህበረሰብ ውስጥ ይህ የማይዋጥ ነገር ነው። ዳሩ ግን እስከ አሁን ከሆኑ ነገሮች በመነሳት ይህን መገመት ደግሞ ቀላል ነው። ለምሳሌ ከዛሬ 100 ዓመታት በፊት አሁን ያለው የህክምና ደረጃ አልነበረም። የሰው ልጅ በቀላል በሽታዎች ይሞት ነበር። እንደ አሁኑ ያልተወለደ ሕጻን ጾታ ማወቅ አይቻልም ነበር። ስለዚህ ከዛሬ 50 እና 100 ዓመታት በኋላ የሰውን ልጅ ሕዋሶች እንደገና በማደስ ዕድሜን ማራዘም አይቻልም ብሎ ማሰብ አይቻልም።

ይህ የቴክኖሎጂ ዕድገት የሰውን ልጅ ጥበብ እና ዕድገት የሚያሳይ ሆኖ ሳለ፤ ችግሩ ግን አሁን አሁን ደግሞ አደጋ እየተጋረጠበት ነው። የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ የማሰብ ስሜት የሚያጠፋ ሊሆን ነው። በተለይም በታዳጊ ሀገራት ዜጎች የቴክኖሎጂው ጥገኛ ስለሚሆኑ ምንም ነገር በራሳቸው ማሰብ የማይችሉበትን ሁኔታ እየፈጠረ ነው ማለት ነው። የጥቂቶች የረቀቀ ዕውቀት የብዙዎችን ተፈጥሯዊ አዕምሮ ይቀማል ማለት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ለታዳጊ ሀገራት የሥራ ዕድል በማሳጣትም ሌላ አሉታዊ ድርሻ ይኖረዋል።

በአጠቃላይ ሰው ሰራሽ ማሰብ (AI) ለሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ስሜት አደጋ ሊሆን ይችላል!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You