የቡና ቅምሻ ውድድሩን ለተሻለ ገበያ

ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትልቅ ሥፍራ ያለው ቡና በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የብዙ ሚሊዮኖች መተዳደሪያ በመሆን ይጠቀሳል። በተለይ በውጭ ምንዛሬ ግኝት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይታወቃል። ይህንንም ታሳቢ በማድረግ የቡና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ሀገር ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ መሆን እንድትችል ከታች ከልማቱ ጀምሮ በአዘገጃጀትና በኤክስፖርት ንግዱ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጥረቶች ሲደረጉ ይስተዋላል።

የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ብሎም ጥራት ያለው ምርት ለዓለም ገበያ በማቅረብ የተሻለ ገበያ ለማግኘት ከሚደረጉ ጥረቶች መካከል በቡናው ዘርፍ የሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ውድድሮችና ሁነቶች ይጠቀሳሉ።

ዓለም አቀፍ የቡና ውድድር የኢትዮጵያን ቡና በዓለም ገበያ ለማስተዋወቅና የተሻለ ገበያ ለማግኘት ያለው አስተዋጽኦ ትልቅ ነው። ቡናው ተወዳዳሪ ሆኖ በተሻለ ዋጋ ለዓለም ገበያ ሲቀርብ አርሶ አደሩ ከሚያገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባለፈ ተነሳሽነቱን በእጥፍ ያሳድገዋል። ይህ ከለውጥ ለአርሶ አደሩ ከሚያስገኘው ፋይዳ አልፎ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ትርጉም ያለው ውጤት ማምጣት እንደሚያስችል በመጥቀስ ሊበረታታ እንደሚገባው ብዙዎች ይስማማሉ።

ከሰሞኑም ‹‹ኦርጋኒክ ፌር ትሬድ›› የተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት የቡና ቅምሻ ውድድር አካሂዷል። ውድድሩ በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን፤ እአአ የ2024 የቡና ቅምሻ ውድድርም በቅርቡ ለአራተኛ ጊዜ ተካሂዷል። ኦርጋኒክ ፌር ትሬድ ሰርትፍኬሽን ያላቸው ማህበራት፣ ዩኒየኖችና የግል ቡና አምራቾች በየዓመቱ የሚወዳደሩበት የቡና ቅምሻ ውድድር ሲሆን፣ ለአምራቹ፣ በቡና ሥራ ውስጥ ለሚሳተፉና ለሀገርም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚያበረክት በመድረኩ ተጠቁሟል።

ከሀገሪቱ የተለያዩ ቡና አምራች አካባቢዎች የተውጣጡ ማህበራት፣ ዩኒየኖችና አምራቾች በተሳተፉበት በዚህ ውድድር፣ ከምርጥ አስሩ የአንደኝነት ደረጃን የወሰደው ጉጂ ዞን፣ ኡራጋ ወረዳ፣ ላዮ ትራጋ አካባቢ የሚገኝ ማህበር ነው።

የማህበሩ ምክትል ማናጀር አቶ ተስፋዬ ዱቤ ‹‹ማህበሩ የአንደኝነት ደረጃን በማግኘቱ እጅግ ደስተኛ ነኝ›› ሲሉ ጠቅሰው፣ ማህበሩ ጥራት ላይ ትኩረት አድርጎ በመሥራቱ ለአሸናፊነት መብቃቱን አስታውቀዋል። ለገበያ የሚያቀርባቸው ቡናዎችም ጥራት ያላቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፣ አንደኛ ደረጃ ቡና፣ የተፈጥሮ ቡና እና የታጠበ ቡና ከአንደኛ እስከ አራተኛ ደረጃ ያሉትን የቡና ዓይነቶች ለገበያ እንደሚያቀርብ አስታውቀዋል።

‹‹ማህበሩ በተፈጥሮ የተገኘና ምንም ዓይነት ባዕድ ነገር ያልተደባለቀበትን ጥራት ያለውን ቡና በጥንቃቄ አዘጋጅቶ ማቅረብ በመቻሉ ተሸላሚ ሆኗል›› ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ ማህበሩ ከዚህ ቀደም ከአርሶ አደሩ የሰበሰበውን ቡና ለዩኒየን ያቀርብ እንደነበር አስታውሰዋል። ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ግን ራሱን ችሎ ለዓለም ገበያ እንዲሁም ለሀገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ ጀምሯል ብለዋል። ማህበሩ ራሱን ችሎ ኤክስፖርት ማድረግ በጀመረበት በአጭር ጊዜ ተሸላሚ መሆን መቻሉን ጠቅሰው፣ በሽልማቱ በእጅጉ እንደተደሰቱና አበረታች መሆኑን ተናግረዋል። በቀጣይም ጥራት ላይ ትኩረት በማድረግ የተሻለ ውጤት ለማምጣትና በውጤቱም አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን አበክሮ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

የአካባቢው አርሶ አደር በስፋት ደረጃ አንድ ቡና እንደሚያመርት የጠቀሱት አቶ ተስፋዬ፤ የብድር አቅርቦት አለማግኘት እንዲሁም ከአካባቢው ቡናውን ለማውጣት የመንገድ ችግር ስለመኖሩም ጠቁመዋል። ይህም ቡናውን በወቅቱ ለገበያ እንዳይደርስ በማድረግ ችግር እየፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል። ይሁንና ማህበሩ በእነዚህና መሰል ችግሮች እየተፈተነ ጥራት ያለው ደረጃ አንድ ቡና ለዓለም ገበያ እያቀረበ ነው። በቀጣይም እነዚህን ችግሮች መፍታት ከተቻለ በተሻለ ጥራት ከፍተኛ መጠን ያለውን ቡና ለዓለም ገበያ ማቅረብ ይቻላል ብለዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ማህበሩ አንድ ሺ 905 አርሶ አደሮችን ያቀፈ ሲሆን፣ 72 ሚሊዮን ብር የሚገመት ቋሚ ንብረትም ማፍራት ችሏል፤ በበጀት ዓመቱ በያዘው ዕቅድ ደረጃ አንድ ቡና ስድስት ኮንቴይነር፣ ደረጃ አራት ቡና ሰባት ኮንቴይነር እና ሁለት ኮንቴይነር የታጠበ ቡና በጥራት አዘጋጅቶ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየሠራ ነው።

የሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ያገኘው የኦሮሚያ ቡና ገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒየን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ምትኩ በቀለ፣ ዩኒየኑ በማሸነፉ የተሰማቸውን ደስታ ሲገልጹ፤ በባለፈው ዓመት ውድድር ምርጥ አስር ውስጥ ቢገባም አሸናፊ መሆን አልቻሉም ነበር ሲሉ አስታውሰው፣ ችግሮቹን በመለየት ታች አርሶ አደሮች ዘንድ ወርዶ በተለይም በሁለት ማህበራት ላይ በባለሙያ የታገዘ ሥራ መሥራቱን ተናግረዋል።

በዩኒየኑ ውስጥ በሚገኙ ባንኮ ሚጪጫና ደመዳሙ በሚባሉ ማህበራት ላይ ትኩረት በማድረግ ጠንካራ ሥራ በመሥራቱም በውድድሩ የሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ማግኘት እንደቻለ አቶ ምትኩ አስታውቀዋል። ይህም ዩኒየኑ ቡናውን ለዓለም ገበያ ማቅረብ የሚችልበትን ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርለትና የተሻለ የገበያ አማራጭ የሚሰጠው መሆኑን ተናግረዋል። ለዚህ ውጤት ያበቃው በዩኒየን ደረጃ የጥራት ቁጥጥር የሚባሉ ብቁ ባለሙያዎችን በማደራጀት አርሶ አደሩ ቡናን ከማምረት ጀምሮ ዩኒየኑ ጋ እስኪያደርስ ድረስ የክትትል ሥራ መሠራቱ መሆኑን አስታውቀዋል።

ሌላው አርሶ አደሩ ለጥራት መሥራት ማለት ምን ማለት ነው በሚለው ላይ የደረሰው ቡና በጥራት እንዲለቀም ከቡና ግብይት ጋር በተያያዘ ስልጠና እንደሚሰጥ ገልጸው፤ በዚህም ቡናው በተሻለ ዋጋ ተሸጦ ለአርሶ አደሩ የተሻለ ውጤት እንዲያመጣ ይሠራል ነው ያሉት።

እሳቸው እንዳሉት፤ ቡናው በውድድሩ ያገኘው ደረጃ ለዓለም ገበያ ሲተዋወቅ ተመራጭ ይሆናል። በመመረጡም የተሻለ ገበያ ከማግኘት ባለፈ ተጨማሪ 20 እና 30 ሳንቲም የሚያገኝበት ሁኔታም ተፈጥሯል። ይህም የበለጠ ለመሥራት የሚያበረታታ ነው። በቀጣይም እነዚህ ማህበራት ተጠናክረው የሚሰሩበትና ሌሎች ማህበራትም ወደዚህ ደረጃ የሚመጡበት ሁኔታ ይፈጠራል በማለት ውድድሩ በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት መሆኑን አመላክተዋል።

የኦሮሚያ ቡና ገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒየን ባገኘው ደረጃ አማካኝነት በቀጣይ ቺካጎ ላይ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የቡና ኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ ተሳታፊ ይሆናል ያሉት አቶ ምትኩ፤ ለዚህም ፌር ትሬድ አፍሪካ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል። በባዛርና ኤግዚቢሽኑም የኢትዮጵያን ቡና ከማስተዋወቅ ጎን ለጎን የአሸናፊነት ዋንጫው በራሱ የተሻለ የገበያ ዕድሎችን እንደሚፈጥር አስታውቀዋል፤ አዳዲስ የገበያ ትስስር የሚፈጥር መሆኑንም አመልክተዋል።

በኦርጋኒክ ፌር ትሬድ አፍሪካ የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ታደሰ ነጋሽ እንዳስታወቁት፡ ‹‹ፌር ትሬድ አፍሪካ ኮፊ ኮምፕቲሽን›› በመባል የሚታወቀው ይህ የቡና ጥራት ውድድር በቡና ቅምሻ ተወዳድረው ከተመረጡ 10 ቡና አምራች ማህበራት መካከል ሶስት ምርጦች የሚለዩበትና ለዓለም ገበያ የሚተዋወቁበትን ሂደት የተከተለ ነው። የውድድሩ ዋና ዓላማም የቡና ጥራትን ለማሳደግ፣ በዓለም አቀፍ ገበያ ትስስር ለመፍጠር እና አምራቾችና ማህበራትን ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ ያለመ ነው።

እሳቸው እንዳሉት፤ የቡና ቅምሻ ውድድሩ በቡና ምርት የኦርጋኒክ ፌር ትሬድ ሰርተፊኬት ያላቸው ዩኒየኖች፣ ማህበራት እና አምራቾች ምርታቸው እንዲያድግ፣ በጥራት እንዲያመርቱ እና የተሻለ የመሸጫ ዋጋ እንዲያገኙ ያስችላል። ውድድሩ በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን፤ የፌር ትሬድ አፍሪካ 2024 የቡና ቅምሻ ውድድር ኦርጋኒክ ፌር ትሬድ ሰርትፍኬሽን ያላቸው ማህበራት፣ ዩኒየኖች እና የግል ቡና አምራቾች ተሳትፈውበታል። በቡና ቅምሻ ተወዳድረው ከተመረጡ 10 ቡና አምራችና ማህበራት መካከልም ሶስት ተወዳዳሪዎች ተሸላሚ መሆን ችለዋል።

የቡና ቅምሻ ውድድሩም ዓለም አቀፍ እውቅና ባላቸው ዳኞች የተዳኘ ሲሆን፤ ከዳኞቹ መካከል አንዷ ብራዚላዊት ስትሆን፣ ሁለቱ የቡና ቀማሽ ዳኞች ኢትዮጵያውያን ናቸው። አንደኛ የወጣው ቡና አምራች ማህበር ቡናውን ለዓለም አቀፍ ገበያ በማስተዋወቅ የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝ ይደረጋል። ከዚህ ባለፈም በየዓመቱ በሚካሄድ ዓለም አቀፍ የቡና ኤግዚቢሽን ላይ የመሳተፍ ዕድል ይፈጠርለታል። ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዴንማርክ ኮፐንሀገን ላይ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የቡና ኤግዚቢሽን ላይ አሸናፊው ዩኒየን ተሳታፊ ይሆናል።

ውድድሩ ምርት ከተሰበሰበ በኋላ የሚካሄድ እንደመሆኑ ማህበራቱ ምርቶቻቸውን ለዓለም አቀፍ ተጠቃሚዎች የሚያስተዋውቁበትን ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ያሉት አቶ ታደሰ፤ የቡና ቅምሻ ውድድሩ ላለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት መካሄዱንም አስታውሰዋል። ውድድሩ ለቡና አምራቹ ጉልህ አበርክቶ ያለው ስለመሆኑ ሲያስረዱም፤ የውድድሩ ተሳታፊ የሚሆኑት በፌር ትሬድ የዕውቅና ሰርተፊኬት ያገኙ ቡና አምራች አርሶ አደሮችና ማህበራት መሆናቸውን ተናግረዋል። እነዚህ አርሶ አደሮች የፌር ትሬድ ሰርተፊኬት ያላቸው በመሆናቸው ብቻ በየዓመቱ በዓለም አቀፍ ገበያ ከሚሸጡበት የቡና ዋጋ ተጨማሪ በኪሎ የ20 ሳንቲም ጭማሪ የሚያገኙበት ዕድል ይፈጥራላቸዋል ብለዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ይህ ተጨማሪ ክፍያም ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል ነው፤ በተለይም አርሶ አደሩ አካባቢውን የሚያለማበትና የተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን የሚያከናውንበትም ይሆናል። አርሶ አደሩ በዚህ የጥራት ውድድር ምክንያት ከዓመት ዓመት ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና በተሻለ ዋጋ በመሸጥ ተጠቃሚ መሆን ችሏል። ቡና ገዢ ሀገራት ጥራት የሚፈልጉ በመሆናቸው ውድድሩን ይፈልጉታል። ለዚህም ውድድሩ ከተካሄደ በኋላ ከገዢ ሀገራት የሚመጡ ጥያቄዎች ማሳያዎች ናቸው።

በየዓመቱ ውድድሩ ከተካሄደ በኋላ መረጃ በመያዝ ለገዢ ሀገራት ናሙና እንደሚላክ ጠቅሰው፣ የተላከውን ናሙና ተከትሎም የፍላጎት ጥያቄ ከገዢ ሀገራት ይመጣል ብለዋል። ቡና አምራች አርሶ አደሮች፣ ዩኒየኖችና ማህበራትም በጥያቄው መሠረት አንደኛ ደረጃ ቡና ወደ ውጭ ገበያ በመላክ መሸጥ ይችላሉ ሲሉ አብራርተዋል። አሸናፊው ቡና በመገናኛ ብዙኃን እንደሚተዋወቅ አመልክተው፣ በዚህም ሰፊ የገበያ ዕድል እንደሚያገኙና በውጭ ምንዛሪ ግኝትም ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ተናግረዋል።

እንደ አቶ ታደሰ ማብራሪያ፤ ቡና አምራች አርሶ አደሮች፣ ማህበራትና ዩኒየኖች የፌር ትሬድ አፍሪካ ሰርቲፋይድ መሆናቸው ከገበያ ትስስሩ ባለፈ የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ያግዛቸዋል፤ በፌር ትሬድ ሰርቲፋይድ የሆኑ አባላት በ10 ዩኒየኖች የተደራጁ 191 ማህበራትን ያሉት ሲሆን፣ በጠቅላላው 243 ሺህ 353 አርሶ አደሮችን ያቀፈ ነው።

አባላቱ የእርስ በእርስ የልምድ ልውውጥ በማድረግ የተለያዩ ተሞክሮዎችን ያገኛሉ። የኢትዮጵያ ቡና አምራቾች አርሶ አደር ሆነው ቡናን ከማምረት ጀምሮ ያመረቱትን ቡና ፕሮሰስ እንዲሁም ኤክስፖርት በማድረግ የተሻለ አደረጃጀት ያላቸው በመሆናቸው ከሌሎች ሀገራት ይለያሉ። ሌሎች ከዚህ ብዙ ሊማሩ ይገባል።

ከዚህ በተጨማሪም እሴት የተጨመረበትን ቡና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንደሚጠቅም የጠቀሱት አቶ ታደሰ፤ ‹‹በተለይም ሁለት ዩኒየኖች ቡናቸውን ቆልተውና ፈጭተው ለውጭ ገበያ እየላኩ ናቸው፤ ኤርፖርት ውስጥም እየሸጡ ይገኛሉ›› ሲሉ ጠቅሰዋል። ይህም በፌር ትሬድ አፍሪካ ሰርቲፋይድ እንደሚደረግ ተናግረው፣ በዓለም አቀፍ ገበያ ተቀባይነት አግኝቶ በተሻለ ዋጋ መሸጥ የሚችልበት ሁኔታ መፈጠሩንና የተለያዩ ሀገራትም እሴት የተጨመረበትን የኢትዮጵያን ቡና የመግዛት ፍላጎት እያሳዩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ፍላጎት ካሳዩ ሀገሮች መካከል ኢንዶኔዥያና ሞሮኮ እንደሚጠቀሱ ተናግረው፣ አንዳንድ ዩኒየኖች እሴት የተጨመረበትን ቡና ወደ ሀገራቱ ለመላክ እንቅስቃሴዎችን እንደ ጀመሩ አስታውቀዋል። ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር በሚፈጠር ግንኙነት የማስተዋወቅና የመሸጥ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና የተሻለ ገበያ እንደሚገኝም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ፌር ትሬድ አፍሪካ ቡና አምራች አርሶ አደሮች፣ ማህበራትና ዩኒየኖች ጥራት ያለው ቡና ማምረት እንዲችሉና ምርትና ምርታማነትን እንዲያሳድጉ ቴክኒካል የሆኑ ድጋፎችን እንደሚያደርግ የጠቀሱት አቶ ታደሰ፤ ዩኒየኖቹ ያሉበትን ደረጃ በማየት ስልጠናዎችን በመስጠት፣ በዓለም አቀፍ የቡና ሁነቶች ላይ መሳተፍ እንዲችሉ የማገናኘትና የተለያዩ ቡና ገዢ ሀገራት በሚመጡበት ጊዜም እንዲሁ የማገናኘት ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል። በተለይም ዱካውን የተከተለ ቡናን ለዓለም አቀፍ ገበያ ከማቅረብ አንጻር ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል ነው ያሉት።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You