ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ስለማስመሰል ተናግሯል። ከጥንት የግሪክ ፈላስፎች አንዱ የሆነው ፕሌቶ 35 ያህል ድርሳናት አሉት፤ ከእነዚህ ውስጥ 33ቱ ማስመሰል ላይ ጦርነት ያወጀባቸው ናቸው። በተለይም ‹‹ለመሆን እንጂ ለማስመሰል አንሰራም›› የሚለውን ጠቃሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
ሌላው መሸፈን(ገመና) የሚለው ነው። በግሪክ ‹‹አሌሲያ›› የሚባል ቃል አለ፤ ‹‹አሌሲያ›› ማለት ከመሸፈን መዝለል ወይም እውነቱን ማሳወቅ ማለት ነው። እኔ ተማሪዎቼን ሳስተምር ባርኔጣዬን በማውለቅ ፀጉሬን አሳያቸው ነበር፤ ይሄው አሁን እውነቱ ወጣ እላቸዋለሁ። እኔ ባርኔ ጣዬን የማደርገው መላጣ ለመሸፈን አይደለም፤ በሰው ፊት ‹‹ስቴቲክስ›› የሚ ባል ነገር አለ፤ ግልጥልጥ ብሎ መሄድ ጥሩ አይደለም።
ዛሬ ‹‹መፍትሔው ኢትዮጵያዊነት ነው›› በሚለው ሀሳብ ላይ እንድናገር ነው የተጠየቅኩት። ስናገር የኢፌዴሪን ሕገ መንግስት አንድ ገጽ ከሩቧን ወይም መግቢያዋን ይዛመዳሉ ወይስ ይገዳደራሉ? በሚል የመጀመሪያውን አቀርባለሁ።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መግቢያ ላይ አራት ነገሮች ነው የምይዘው። አንደኛው፤ ሲጀመር እን ዲያው እንደመግቢያ የሚሆነን መንደ ርደሪያ ነው። ህገ መንግስት በሁለት ወገን የሚጠነሰስ ውል ነው። የእኛው ህገ መንግስት በብሄሮች፣ በብሄረሰቦችና ህዝቦች፤ በእነዚህ በሦስቱ እና በመንግሥት መካከል የተደረገ ውል ነው። አንቀጽ 33 ላይ ዜግነት የሚባል ቃል አለ። ዜግነት ሁልጊዜ የሚነሳው እንደ ውጭ ጉዳይ ነው።
አንደኛው፤ ‹‹ኢትዮጵያዊ ዜጋ የውጭ ዜጋ ቢያገባ ዜግነቱን አያጣም›› ይላል። ሁለተኛው፤ ‹‹ማንኛውም ዜጋ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን የመለወጥ መብት አለው›› ይላል። ሦስተኛ፤ የኢትዮጵያ ዜግነት ለውጭ አገር ሰዎች ሊሰጥ ይችላል ይላል። እነዚህን ይበል እንጂ ‹‹ዜግነት እንዲህ ነው፣ የዜግነት ባህሪ እንዲህ ነው›› አይልም። ዜግነትን እንደ ውጭ ፖሊሲ ከግንኙነት ጋር ብቻ ነው የሚገልጸው።
‹‹መጪው የጋራ ዕድላችን መመስረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረም እና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበል›› ይላል። ‹‹ከታሪክ የወረስነውን›› የምትለዋን ወሰድኩ። ይሄ ማለት የሚታረም ታሪክ እና የማይታረም ታሪክ፣ የሚታረም ባህል የማይታረም ባህል፣ የሚታረም የብሄሮች ታሪክ፣ የማይታረም የብሄሮች ታሪክ ብሎ ይለየዋል ማለት ነው።እንግዲህ የሚ ታረመውና የማይታረመው የቱ እንደ ሆነ አይታወቅም።
‹‹ኢትዮጵያ አገራችን የራሳችን አኩሪ ባህል ያለን፣ የየራሳችን መልክዓ ምድር የነበረን፣ ያለን ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በተለያየ መስኮችና የግንኙነት ደረጃዎች ተሳስበን አብረን የኖርን…›› ይላል። እዚህ ላይ የወሰድኩት ነገር ‹‹የየራሳችን አኩሪ ባህልና መልክዓ ምድር›› የሚለውን ነው። እያንዳንዱ ብሔር የሚለይበት ተፈጥሯዊ አካል ወይም ፀባይ አለው ማለት ነው። ‹‹ትክክለኛ ወይም ተቀባይነት ያለው መንግሥት በዚህ ተፈጥሯዊ በሆነው ብሄር ላይ ተመስርቶ ሲቋቋም ነው›› ይላል። ከትርጓሜ አንፃር ይሄ የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦች የማሳ ተምሳሌት ያደረገ ነው። የበቆሎ ማሳ፣ የገብስ ማሳ፣ የስንዴ ማሳ እንደማለት ነው።እነዚህ ግንኙነት የላቸውም፤ ገበሬው ነው ሰብስቦ የሚያገናኛቸው።ሁሉም የተለዩ ከሆኑ እንዴት ነው እንዲህ ማድረግ የሚቻለው? በማሳ ተምሳሌት ሊሰራ አይችልም።
‹‹ጥቅማችንን፣ መብታችንን፣ ነፃነታ ችንን በጋራ እና በተደጋጋፊነት ለማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ…›› ይላል። እዚህም ላይ ‹‹አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ›› የሚለውን እወስዳለሁ። አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ አገር አይደ ለም። ይሄ በአንድ የኢኮኖሚ ማዕከል ላይ ያለ ነው፤ አገር ግን ከዚህ በላይ ነው።
ከሽማግሌዎቹ አሁን በሕይወት ከሌሉት ትልልቅ ሰዎች ክቡር አቶ ሀዲስ አለማየሁ የዛሬ 25 ዓመት ገደማ ኢትዮጵያዊነት ማህበርን ከጓደኞቻቸው ጋር ሲያቋቁሙ ደጃዝማች ዘውዴ ገብረ ሥላሴ ነበሩ፣ ክቡር ቢትወደድ ዘውዴ ገብረሕይወት ነበሩ።ስለማህበሩ ዓላማ ከተናገሩት አንዳንድ ነገሮች ልውሰድ።
‹‹ሥዩመ እግዚአብሔር›› ይላሉ። የኢትዮጵያ ህዝብ የአገሩ፣ የራሱ፣ የታሪኩ፣ የባህሉ፣ የኑሮ ሥርዓቱ፣ የሥልጣኔው፣ የመብቱ፣ የግዴታው፣ የሥልጣኑ ሁሉ ባለቤት እሱ ራሱ መሆኑን፤ እግዚአብሔር የእነዚህ ሁሉ ባለቤት መሆኑን፤ እግዚ አብሔር ሥልጣን የሰጠው ለገዥው የኢትዮጵያ ህዝብ እንጂ ለገዥዎች አለመ ሆኑን ማስረዳትና ማስተማር ይገባል ብለዋል።
‹‹ሥዩመ እግዚአብሔር›› የሚ ለውን ሀሳብ ይወስዳሉ፤ ሥዩመ እግዚ አብሔር ማለት ግን ንጉሠ ነገሥቱ ወይም ንግሥቲቷ አይደሉም። ህዝቡን ነው ያሉት። ሃይማኖታዊ ነገሩን ተቀብለው እግዚአብሔር ግን ለህዝቡ እንጂ ለገዥዎች እንዳልሰጠ ይናገራሉ። የኢትዮጵያ ህዝብ በአገሩ ላይ ማንኛውንም መብት እግዚአብሔር ነው የሰጠው ይላሉ።
ሊቁ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ ስለማ ህበረሰቡ ያላቸውን አመለካከት ሲገልጹ የኢትዮጵያ ህዝብ፤ ነፃነት፣ አን ድነት እና ልዩነት ያለው ህዝብ ነው ይላሉ። አሁን እየጮህን ያለነው ነፃነትና አንድነት አካባቢ ችግር አለ እያልን ነው። ልዩነቱ በሰፊው አለ፤ በእሱ በኩል ምንም ችግር የለም። ሊቁ ኪዳነወልድ ክፍሌ ንግግራቸውን ሲቀጥሉም፤ በዚህ ስም የምትታወቅና የተከበርንባት የነፃነት እመ ቤት ኢትዮጵያ በአንድነቷ ለዘለዓለም ትኑ ር ይላሉ።
ይሄ ‹‹ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር›› የሚባል ነገር ላይ ከአንዳንድ ሰዎች ጋር ክርክር ገጥሜ አልተወደደልኝም። እስኪ ዛሬ ላብራራው።
ዝክረ ነገር ላይ ትልቁ ጸሐፊ ማህተመሥላሴ ጣሊያን እንደወጣ ‹‹ኢትዮጵያ በነፃነቷ ለዘለዓለም ትኑር!›› ይላሉ። ምክንያቱም ጣሊያን እያለ የነፃነት ማጣት ጉዳት ታይቷል። ለዚህም ነው ‹‹ነፃነቷን›› የሚል ነገር ያነሳሉ።እነ ሀዲስ አለማየሁ ኢህአዴግ አዲስ አበባ ሲገባ አንድ ነቷ ፈተና ላይ ስለወደቀ ‹‹ኢትዮጵያ በአንድነቷ ለዘለዓለም ትኑር›› ይሉ ነበር። ይህን ሲሉ የሆነ የሚታገሉት ነገር ስላላቸው ነው እንጂ እንዲሁ ዝም ብሎ በሬዲዮ ተመቸኝ ብሎ ‹‹ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!›› አይባልም። የሆነ ማሳያ ነገር ከሌለው ትርጉም አይኖረውም።
ስለኢትዮጵያውያን ስናወራ፤ በኢት ዮጵያ ላይ የኖሩ እና ለኢትዮጵያ የኖሩ መካከል ልዩነት አለ። ብዙዎቻችን በኢት ዮጵያ ላይ የኖርን እንጂ ለኢትዮጵያ የኖርን አይደለንም። ለኢትዮጵያ የኖሩት በጎ ነገር ሰርተው ያለፉት መሪዎቿ፣ ለነፃነት የተዋደቁት አርበኞቿና ወታደሮቿ ናቸው። በዚህ አጋጣሚ በቅርቡ የተመረቀውን የጄኔራል መዕርድ ንጉሤን መጽሐፍ ማስታወስ እፈልጋለሁ። ለኢትዮጵያ የኖሩ መዓት ናቸው፤ ግን በቅርብ የወጣ እሱ ስለሆነ ለኢትዮጵያ ለኖሩ ምሳሌ ልጥቀስ ብየ ነው። መጽሐፉን ብታነቡት ብዙ ነገር ታገኙበታላችሁ። በሃይማኖትም፣ በስፖርትም፣ በየትኛውም ሙያ ያገለገሉትን ‹‹ለኢትዮጵያ የኖሩ›› ልንላቸው እንችላለን።
ኢትዮጵያ ከጠላቶቿ ብቻ ሳይሆን በጣም ከሚወዷትም መጠበቅ ያለባት አገር ናት። ‹‹እንዴት ሰው ከሚወደው ይጠበቃል›› ትሉኝ ይሆናል። ሚሶሎኒ እስላሞችን ይወዳል፤ አጥፍቷቸው ነው የወረደ፣ መንግስቱ ኃይለማርያም ኢትዮ ጵያን ይወዳል፤ ግን ምን እንዳደረገን እናውቃለን። ወጣቶች ‹‹መንጌ! መንጌ!›› ትላላችሁ፤ ስለማታውቁ ነው።
እስኪ ከቤተሰብ እንጀምር! አንድን ልጅ እኮ እናቱ ስለምትወደው ልታበላሸው ትችላለች።ከመውደድ ብዛት የጠየቃትን ሁሉ ስታደርግ ያ ልጅ እኮ ሊበላሽ ይችላል። እናም አንዳንድ ጊዜ አገር እንወ ድሻለን ከሚሏትም አላዋቂ ሳሚ ስለሚሆኑ መበላሸት ያጋጥማታል።ይሄን እንግዲህ ተመካከሩበት!
በብሄር፣ በጎሳ፣ በነገድ፤ የተለያየን ነን ቢባልም ቅሉ የሁሉም አሰባሳቢ ገበታ ግን ኢትዮጵያ ናት። ኢትዮጵያን አይተን እዚያ ገበታ ውስጥ እኛ አልገባንም፤ አልተካተትንም ማለት ይቻላል። ከዛሬ 45 ዓመት በፊት አሜሪካ ማለት ነጭ ብቻ ነበር። በኋላ በትግል ጥቁሮችም ገቡ። አሁን ደግሞ ሂስፓኒሾችም ገቡ፤ አገር እንደሰው እያደገ ይሄዳል። የዛሬ 45 ዓመት አዲስ አበባ ውስጥ ሦስት ብሄር ብቻ ነበር የማውቀው። አሁን ግን ከተማው ውስጥ ኢትዮጵያ ህብረብሄር ሆናለች። ይሄ የእድገት ምልክት ስለሆነ አይጠላም። ግን እኛ አልተካተትንምና ኢትዮጵያን እንገፈትራለን የሚለው አካሄድ አያዋጣም፤ ትክክልም አይደለም።
ኢትዮጵያዊነት ዝም ብሎ አንድ የኢኮኖሚ ማዕከል አይደለም። የህግ፣ የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚ፣ የሃይማኖት… ማህደር ናት። ኢትዮጵያ ሲባል የህዝብ ድምር ማለት አይደለም።በተለያየ ሁነት ውስጥ ሆኖ በአንድ የተደመረ ማለት ነው።
ስለእኛ ትውልድ ላውራችሁ። አንድ ወጣት የተናገረውን ነው የምነግራችሁ። ያ ትውልድ ድሮ አማራ አባቶቹን በል ቷል፤ አስበልቷል። አሁን ደግሞ እኛን ልጆቻቸውን ለማስበላት እየተጣደፈ ነው ካለኝ በኋላ ‹‹ዶክተር፤ ተጠያቂዎቹ የዘመን ሽንፍላዎች፣ ጊንጦቹ፣ እፉኝቶቹ እናንተ ናችሁ›› አለኝ። እናንተ ችግራችሁ የበታችነት ስሜት ነው አለ። ሩቅ ባልሆን ኖሮ ላገኝህ እፈልግ ነበር ብሎኛል፤ በእርግጥ እዚሁ ሰንጋ ተራ ተደብቆም ሊሆን ይችላል።
ዶክተር በድሉ ስም አንጠራም ብሏል፤ በእርግጥ ስም አለመጥራታችን በሽታ ነው፤ የከፋው በሽታ ግን በሌላ ሰው ስም መጠራት ነው። ያ ሰው መጨረሻ ላይ ምን አለኝ፤ ‹‹እኛ አብኖች›› አለኝ።እኔ አብንን በፍርሃት አይደለም የማውቀው። ‹‹እኛ አብኖች›› ሲል ግን በየት በየት አቆራርጦ እንደመጣ ገባኝ። በጨለማ ውስጥ ሆነው እንዲህ የሚናገሩ ሰዎች ወደ ብርሃን መውጣት አለባቸው!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 8/2011