“የሕዳሴ ግድባችን ታዳሽ ኃይል በመሆኑ ቀጣይነት ላለው የኢኮኖሚ እድገት መሠረት ነው” ብርሃኑ ደኑ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በንግድ ሥራ ኮሌጅ የኢኮኖሚክስ መምህር

ዛሬ የመሠረተ ድንጋይ ከተቀመጠለት 13ኛ ዓመቱን ደፍኗል – ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ፈተናን በመጋፈጥ የዘለቀ ቢሆንም፤ በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፎ ወደ ፍጻሜው መቃረብ ችሏል። ይህ የሆነው ግን በኢትዮጵያውያኑ ብርታትና ጥንካሬ እንዲሁም መንግሥት አይተኬ ሚናውን በአግባቡ መወጣት በመቻሉ ነው። የኢትዮጵያውያኑ ማንነት እና ታሪክ የሆነው የሕዳሴ ግድብ፣ ሊጠናቀቅ የወራት ያህል ጊዜ ብቻ ቀርተውታል። በቅርቡ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት እንዳስታወቀውም የግድቡ ግንባታ አፈጻጸም በአማካይ 95 በመቶ ደርሷል። የግድቡ አጠቃላይ የሲቪል ሥራው ደግሞ 98 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ መከናወኑም ተጠቅሷል።

ይህ ወደ ፍጻሜው የተንደረደረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረሱ የኢትዮጵያን መንግሥት እና የዜጎቿን ቁርጠኝነት የሚያመላክት ነው። ግብጽን ጨምሮ ምዕራባውያኑም ሆኑ ሌሎች አካላትም ሆኑ ተቋማት በዚህ ግድብ ያልወረወሩት የተንኮል ጠጠር አልነበረም። ከማስፈራራት እስከ ማስጠንቀቂያ፤ ከማሸማቀቅ እስከ ማጭበርበር ድረስ ትልልቅ ናቸው የሚባሉ ሀገራት ጭምር በኢትዮጵያ ላይ ያደረሱት ደባ ታሪክ ሆኖ በትውልድ አዕምሮ ተመዝግቧል።

ይሁንና ኢትዮጵያ በዚህ የሕዳሴ ግድብ ያስመዘገበችው ድል በብዙ ጉዳዮቿ ላይ ጨክኖ መጨረስን ብቻ ሳይሆን በቀጣይም ተመሳሳይ ቁርጠኝነትን ማሳየት የምትችል መሆኗንም ጭምር ነው።

ብዙዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ምንም እንኳ ኢትዮጵያ በፈለገቻቸው በቁርጥ ቀን አብረዋት ለመሆን ፈጣኖች ባይሆኑም ከኢትዮጵያ ጥንካሬ እና የ“ይቻላል” መንፈስ ብዙ የሚማሩበት ዕድል እንደሆነ ይታወቃል። የግድቡ መጠናቀቅ ስኬቱ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የእነርሱም ጭምር እንደሆነም የተረዱ ይመስላል።

አዲስ ዘመንም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለትን 13ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ግድቡ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ምንድን ነው? ሲል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በንግድ ሥራ ኮሌጅ የኢኮኖሚክስ መምህር ከሆኑት ከብርሃኑ ደኑ (ዶ/ር) ጋር ልዩ እትሙን አስመልክቶ ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አጠናቅሮ አቅርቦታል። መልካም ንባብ ተመኘንላችሁ።

አዲስ ዘመን፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በሰባት ወር ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል፤ ይህን እንዴት ያዩታል? ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውስ እንደምን ይገለጻል?

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- በመጀመሪያ ደረጃ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ብዙ ውጣ ውረድን አልፎ የተጋረጡበትንም ፈተናዎች ተሻግሮ ወደ ምረቃ ምዕራፍ መሸጋገር መቻሉ ከምንም በላይ ትልቅ ስኬት ነው። ብዙዎች ይህ ግድብ እውን እንዳይሆን በብዙ ጥረው የነበረ መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም።

ይህ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለምረቃ መቃረቡ አንድ ትልቅ ስኬት ሆኖ ሳለ፤ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እና ያንን በአግባቡ መጠቀም መቻል ደግሞ ለኢኮኖሚው ከፍተኛ የሆነ ጠቀሜታ ያለው ነው። ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምናያቸው የበለጸጉ ሀገሮች ሁሉ በከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል የተደራጁ ናቸው። ምርቶቻቸውንም በዚሁ ባላቸው የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመርቱና ለተደራሻቸውም የሚከፋፍሉ ናቸው።

በርግጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የተለያየ የኃይል ምንጭ ነው። ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ የሚመረጠውና እና ለብክለትም የማያጋልጥ ከውሃ የሚገኝ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዓይነት ሲሆን፣ ጠቀሜታውም ዘርፈ ብዙ ነው። ከዚህ አንጻር አንደኛው ለኢኮኖሚ የሚጠቅመውን የአካባቢ ጥበቃ የሚመለከት ነው። እንዲህም ሲባል አየሩንም ከብክለት የሚከላከል እና ነፃ የሚያደርግ መሆኑ ነው።

ሁለተኛው ደግሞ እንደሚታወቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ታዳሽ ነው። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኃይል አቅርቦቱ ታዳሽ ኃይል እንዲሆን የሚበረታታበት ጊዜ ነው። ከዚህ አንጻር ሲታይ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚፈልገው ውሃ ነው፤ ውሃ ደግሞ ከዝናብ ይገኛል፤ ሁሌም ቢሆን ዝናብ ይዘንባል። ግድቡ ያለምንም ችግር መልሶ መሙላት ይችላልና ታዳሽነቱ በዚሁ መልኩ የሚቀጥል ይሆናል።

ስለዚህ እንደሌሎች ለምሳሌ እንደ ነዳጅ ማውጣት ዓይነት የኃይል አማራጭን ብንመለከት በሂደት እያለቀ የሚሄድ የኃይል ምንጭ ነው። ከዚህ የተነሳ ሀብቱ የሚያልቅ በመሆኑ ወደፊት ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን ትልቅ ጥያቄ የሚያስነሳም ጭምር ነው። ይህ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዓይነት ታዳሽ ኃይል ለወደፊቱ የኢኮኖሚ ቀጣይነት ዓይነተኛ የኃይል ምንጭ ነው። በአጭሩ የሕዳሴ ግድባችን ታዳሽ ኃይል በመሆኑ ቀጣይነት ላለው የኢኮኖሚ እድገት መሠረት ነው።

ይህ ብቻም ሳይሆን የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ የሚያሻሽልና ቀጣይነት እንዲኖረው ከማድረግ አንጻር አስተዋጽኦው ከፍ ያለ ነው። ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያውያኑ ጥንካሬ የተገነባው እና ሊጠናቀቅ ጫፍ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ለዘመናት ወደኋላ ቀርቶ የነበረውን የኢኮኖሚ እድገት እና ግስጋሴ ወደፊት ለማስፈንጠር ሚናው የጎላ ነው። ሀገሪቷ ልታድግ የምትችልበትን፣ ምርታማነት የሚጨምርበትን፣ በከፍተኛ ደረጃ የሥራ እድል የሚከፈትበትንም እድል የሚፈጠር ነው።

አዲስ ዘመን፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ አንዱ ጠቀሜታው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ነው፤ ከዚህ አንጻር የሕዝብን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል የሚቻለው እንዴት ነው?

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- የኢኮኖሚ እድገት እና ጠቀሜታ ማለት አንደኛ የሕዝብን ኑሮ የሚያሻሽል እንደ ማለት ነው፡። የሕዝብ ኑሮ ማሻሻል ሲባል ደግሞ የሥራ እድልን መክፈት ነው። የሥራ እድል ተከፈተ ማለት ደግሞ የገቢ ምንጭ ተገኘ እንደማለት ነው። ገቢን ከፍ ለማድረግ ዋነኛው መሠረት የሆነው ምርታማነትን መጨመር እና ማበራከት ነው።

በኢኮኖሚ ሴክተሮች ወይም በሁሉም ክፍለ ኢኮኖሚዎች ማለትም በአገልግሎት መስጫ፣ በኢንዱስትሪ እና በግብርናው ዘርፍ ላይ ሁሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ዛሬ ዛሬ በከፍተኛ ደረጃ አስፈላጊ ነው። ዘርፎቹም በተሳለጠ ሁኔታ ቀጣይነት እንዲኖራቸው ኃይል ከፍ ያለ ፋይዳ ያለው ነው።

ከዚህ ጎን ለጎን ቀጣይነት ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት መቻል ፋብሪካዎች የሚያመርቷቸውን የምርት ዓይነቶች በተገቢው መንገድ ማምረት እንዲችሉ ያደርጋል። በየኢንዱስትሪው እና በየፋብሪካው ያሉ ማሽኖች የምንጠቀምባቸው በኤሌክትሪክ ኃይል ነው። ስለዚህም እነዚህ ሁሉ ቀጣይነት ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል አገኙ ማለት በጣም ከፍተኛ የሆነ ምርታማነትን ማምጣት ያስችላቸዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እና ሥራ እየተስፋፋ ሲሄድ ብዙ የሥራ ዕድል ያገኛሉ። እንዲህም ሲባል ኢኮኖሚው እያደገ ሲሄድ በርካታ ሰዎች ሥራ አጥ ተብለው ከተፈረጁበት ቋት ውስጥ መውጣት ይችላሉ። የተፈጠረው የኢኮኖሚ መስክ በራሱ በርካታ ሰዎችን ፈላጊ ይሆናል።

ይህ ማለት ተምረው ሥራ አጥተው የተቀመጡ ዜጎችን ወደ ሥራው መስክ እንዲገቡ የሚያደርግ ይሆናል። በርካቶች በሥራ መስክ ተሰማሩ ማለት ገቢ አደገ እንደ ማለት ነው። የግለሰብ ገቢ ሲያድግ የራሱ የግለሰቡን ገቢ ከማሻሻል አልፎ በሀገር ደረጃ የመንግሥት ገቢ ከፍ ለማድረግ የራሱ አስተዋጽኦ አለው። ምክንያቱም ዜጎች ሥራ አግኝተው መሥራት ሲጀምሩ ታክስ ከፋይ ይሆናሉ። ይህ ደግሞ ለመንግሥት ገቢ የሚያበረክተው የራሱ የሆነ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል። ዜጋውም ሀገርም ተጠቃሚ ሆኑ ማለት በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን እንቅስቃሴ የተያያዘ እንዲሆን ያደርገዋል ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፡- ከሥራ እድል ማስገኘት በተጨማሪ በሌላ በኩል ያለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውስ እንዴት ይገለጻል?

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- ጠቀሜታው ከሥራ ማስገኘት ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም፤ ምርት ማትረፍረፍ ወይም ምርት ማሳደግ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ፋይዳዎችም አሉት። እንደሚታወቀው ደግሞ በአሁኑ ወቅት የግብይትም ሆነ የሽያጭ ሥርዓታችን እንደቀደመው ዘመን ሆኖ የሚዘልቅ አይደለም። ዛሬ የምንጠቀምባቸው የግብይት ሥርዓቶች ለምሳሌ ዲጂታል (Digital) ገበያ እና ክፍያ ኤሌክትሪክ ከሌለ ፈጽሞ የሚታሰብ አይደለም። ከኤሌክትሪክ ኃይል ውጭ ምንም ማድረግ አይቻልም።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በከፍተኛ ደረጃ ኤሌክትሪክን ሳይቆራረጥ እና በተሳካ ሁኔታ ጥቅም ላይ የሚውል ኃይል ማምረቱ እና ማመንጨት መቻሉ ከፍተኛ የሆነ የግብይቱንም ሥርዓት ዘመናዊ የሚያደርግ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የክፍያ ሥርዓታችንንም የሚያዘምን ነው። በባንኮች ደረጃ የሒሳብ አያያዝ እና አገባብ ሪፖርት የማድረጉን ተግባር በተቀላጠፈ መንገድ እንዲካሔድ ያሉንን የዲጂታል (Digital) መስመሮችን ሁሉ ሳይቆራረጡ ሥራ ላይ እንዲውሉ የሚያስችል ነው ማለት ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በኢኮኖሚው መስክ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው። ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት በየጊዜው እየተቆራረጠ የሚያስቸግረውን የኤሌክትሪክ ኃይል ቀጣይነት እንዲኖረው ስለሚያደርግ በተለያየ የሥራ መስክ የተሰማራውን ሴክተር ሁሉ እፎይታ የሚሰጥ ይሆናል። ለምሳሌ በትምህርት ቤት አካባቢ እና በጤና ተቋማት አካባቢ በርካታ ማሽኖች ይኖራሉ። እነዚህ ሁሉ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚሹና በዚያው ኃይል የሚንቀሳቀሱ ናቸው። እነዚህ ትልልቅ እና በጤናውም፤ በትምህርቱም ዘርፍ ሰፊ አገልግሎት የሚሰጡ ሴክተሮችን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችለውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ወደሥራ መግባት እጅግ አስፈላጊው ጉዳይ ነው።

የአንድ ሀገር ዜጋ ጤና ተጠበቀ ማለት በኢኮኖሚው ዘርፍ ለሚሰራው ሥራም ሆነ ለኢኮኖሚው ደኅንነት ጠቃሚ ነው። ከዚህ አንጻር ኢኮኖሚው ከሁሉም ጋር የተያያዘ በመሆኑ የኢኮኖሚው ደኅንነት ተጠበቀ ማለት የብዙዎች ደኅንነት ተጠበቀ እንደማለትም ነው። ምክንያቱም ኢኮኖሚው ከትምህርት ሴክተሩም ጋር የተያያዘ ነው።

በቂ እና እጅግ በጣም የሚጠቅም የትምህርት ሥርዓትንም ለማካሔድ የኤሌክትሪክ ኃይል በስፋት መገኘት እጅግ በጣም ወሳኝ ነው። ለዚህ ሁሉ መሠረት የሚሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ እና ለምረቃ መብቃት እጅግ በጣም በጉጉት የሚጠበቅ ነው። በተለይም እንደ ምጣኔ ሀብት መምህርነቴ ሳጤነው ለኢትዮጵያ አንድ ትልቅ የታሪክ ምዕራፍ ሆኖ ሊቆጠር የሚገባው ነው።

ምክንያቱም ባለፉት ዓመታት ለረጅም ዘመናት ይህን ዓይነት እድል ማግኘትም ሆነ ይህንን ዓይነት ሥራ ማሳካት አልተቻለም ነበር። ያለፈው ታሪካችን ይህንን ማሳካት አልቻለም።

የዓባይ ግድብ መጠናቀቅ ትራንስፖርት ላይ ከፍተኛ የሆነ በጎ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት ለነዳጅ የምናወጣውን ወጪ ልንቀንስ የምንችለው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን መጠቀም ስንችል ነው። ለዚህ ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል የግድ ነው። የሚጠናቀቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንደዚህ ዓይነቱ ኃይል የሚሻ መኪናን ያለ ኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት እንድንጠቀም የሚያግዝ ነው።

ኢኮኖሚው ደግሞ ሁሉንም ሴክተር የሚነካ ነው። ኢኮኖሚው ፖለቲካውንም ሆነ አመለካከታችንንም ጭምር የሚነካ ጉዳይ ነው። ስለዚህ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ወደመጠናቀቁ መቅረብ መቻሉ በቀላሉ ታይቶ የሚታለፍ አይደለም። በተለይ ደግሞ የዚህ ታላቅ ግድብ መጠናቀቅ፣ ለመጪው ትውልድ ከፍተኛ የሆነ የታሪክ ምንጭ ሆኖ የሚያገለግል ነው።

እንዲያውም ይህ ታላቅ ግድብ የታሪክ ማርሽ ቀያሪ ነው ማለት ይቻላል። የአሁኑ ትውልድ በርከት ያለ ፈተና እና ተግዳሮትን አልፎ የሠራው ሲሆን፣ በዚህ ሥራው ደግሞ በሌላ ሌላውም ተጠቃሚ መሆኑ እንዳለ ሆኖ በኢኮኖሚው መስክ የበለጠ ተጠቃሚ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ይህ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ መጪው ትውልድ ሊናገርለት የሚችለው ትልቅ ታሪክም ጭምር ነው። በመሆኑም በቀጣይ እየተወሳ የሚዘልቅ ግድብ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እውን ሆኖ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዘርፍ ተጠቃሚ እንዳትሆን የነበረው ፈተና በዋናነት ለምን ይመስልዎታል?

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- ምክንያቱም እንዳናድግ ስለሚፈልጉ ነው፤ ብዙዎቹ እኛ ኢትዮጵያውያን የምናገኘውን የኢኮኖሚ እድገት እና እሱን ተከትሎ የሚመጣ አቅም እንዳይኖር መፈለጋቸው ነው። እንዲሁም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንዳይሳካ በብዙ ሲጥሩ የነበረው እንደ ሀገር የሚገኝ ተሰሚነት እንዳናገኝ ስለሚፈልጉ ነበር። በርግጥ ይህ ታላቅ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠለት ጀምሮ እስካሁኗ ሰዓት ድረስ በብዙ ሲታትሩ እንደነበር የሚታወቅ ነው።

ስለዚህ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ደግሞ ‘ሀገሩ የእኔም ጭምር ነው፤ የሀገሬ እድገት እኔንም ይመለከተኛል። ሀገሬ አደገች ማለት የነገው ትውልድም ሆነ የልጅ ልጆቼም እድገት ነውና የእኔም የትውልድም ታሪክ ነው’ ብሎ የሚያስብ ማንኛውም ሰው በጉጉት የሚጠበቀው ግድብ ነው። ከዚህ የተነሳ አስፈላጊውን ድጋፍም የሚያደርግለት ነው።

ይህ ታላቅ ግድብ ደግሞ ክፉ ነገር እንዳይደርስበት ሌት ተቀን መጠበቅ የግድ ይላል። ተግተው ከሚጠብቁት የኢትዮጵያ ልጆች፣ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከአካባቢው ሕዝብ እና ሚሊሻም እንዲሁም ከመንግሥትም ጋር በመሆን እንደ ራስ ንብረት እና እንደ ራስ ሕይወት መከታተል እና ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ የሚጠበቅብን ጉዳይ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ይህ የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን እና መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥተውት የገነቡት ግድብ ነው፤ ቀጣዩን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ያለ ሕዳሴ ግድብ ብናስብ ምን ዓይነት ኢኮኖሚ ይኖራታል ብለው ያስባሉ?

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡– ኢትዮጵያን ያለ ሕዳሴ ግድብ ብናስባት በትክክል የምንደግመው ያለፈውን ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ኋላቀርነትን ነው። በኢኮኖሚ ኋላቀርነት ማለት ለልመና ራስን መዳረግ እንደማለት ነው። ልመና ማለት ደግሞ እንደ ሀገር ሲሆን ከባድ ነው። ከዚህም በላይ ራስን በሌላ ሀገር እጅ ላይ እንደመጣል የሚቆጠር ነው። መለመን ማለት በሌሎች ድጋፍ ተመርኩዞ መንቀሳቀስ ማለት ነው።

ስለዚህ ኢትዮጵያን ያለ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማሰብ በጥቅሉ ያለፈውን በኢኮኖሚው በኩል የነበረውን ደካማ ታሪካችንን መድገም ነው። ርግጥ ነው ከዚህ ውጭ የሆኑ ጥሩ ጥሩ የሆኑ ታሪኮች እንዳሉን የሚታወቅ ነው፤ በብዙዎችም ዘንድ ሲነገር ይደመጣል። ነገር ግን እሱ ዓይነት ታሪክ ስላለን ብቻ ኋላቀር ከሆነው ኢኮኖሚያዊ ድኅነት ሊያላቅቀን አልቻለም።

አንዱ እና ትልቁ ነገር ከኋላቀርነታችን ሊያላቅቀን ያልቻለው የኤሌክትሪክ ኃይል ማጣታችን ጭምር ነው። ያለ ኤሌክትሪክ ኃይል የምንጠቀምባቸው የምርት መገልገያ መሳሪያዎችን ማንቀሳቀስ አንችልም። ፈጥነን በማምረት ተወዳዳሪነትን ማሳየት አንችልም። በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪነትን አሳይተን እና ገበያዎችን ሰብረን ገብተን የምናመርታቸውን እቃዎቻችንን በተሻለ ሁኔታ መሸጥ እና መገበያየት አንችልም።

በአሁኑ ወቅት ዓለም እየፈጠነ በመሄድ ላይ የሚገኘው አንዱ ትልቁ ነገር የተለያየ የኃይል ምንጭን በመጠቀሙ ነው፤ እንዲህም ሲባል ከፀሐይ፣ ከነፋስ፣ ከእንፋሎት እንዲሁም ከሃይድሮ ኤሌክትሪክ የሚገኘውን የኃይል ምንጭ በመጠቀም በመቻሉ ነው፡። በአሁኑ ወቅት በሀገራችንም ከተለያዩ የኃይል ምንጮች ኃይልን ለማግኘት እየተሠራ እንደሆነ ይታወቃል። ከፀሐይ የኃይል ምንጭ በማግኘት በኩል በይበልጥ እየተሠራ ያለ ሂደት አለ። በተመሳሳይ ከነፋስ ኃይልም በስፋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት እየተሠራ ይገኛል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከከርሰ ምድር በሚወጣ እንፋሎትም የኤሌክትሪክ ኃይል የማግኘቱ ሥራ እንዲሁ እየተሠራበት ያለ እንቅስቃሴ ሆኗል።

ከእነዚህ ሁሉ የምንጠቀመው የኤሌክትሪክ ኃይል አለ። ነገር ግን በአብዛኛው ከፍተኛ እና ጥሩ ነው ተብሎ የሚገመተው እና የሚታመንበት ከውሃ የሚገኝ ሃይድሮ ኤሌክትሪከ ኃይል ነው። ይህ ማለት ደግሞ በቅርቡ ፍጻሜውን አግኝቶ ይመረቃል ተብሎ የሚጠበቀው እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዓይነቱ ነው። ይህ የሕዳሴ ግድብ ደግሞ የሚመነጨው ኃይል ከፍ ያለ በመሆኑ ሊሰሩ የታቀዱ በርካታ ሥራዎችን በአግባቡ ማሳለጥ የሚያስችል አቅም ያለው ነው። ኢኮኖሚው እያደገ እና እየዳበረ ሲሄድ በሕዳሴ ግድብ ብቻ ተወስነን የምንቀር አይደለንም፤ ወደፊት የተለያዩ ግድቦችን ከመሥራት ባለፈ ኢኮኖሚያችንም እያደገ የሚመጣበት ጊዜ ይሆናል።

በርግጥ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጨዋታውን የሚቀየር (Game Changer) ግድብ ነው። ኢትዮጵያውያኑ የሠሩት ይህን ዓይነት ግድብ ነው። ስለሆነም ይህን ታላቅ ግድብ በሚገባው መጠን መጠቀም የሚጠበቅብን ነው። ግድቡ ኃይልን የሚያመንጭ ብቻ ሳይሆን አብሮ ጎን ለጎን መታሰብ ያለበት የኃይል ማስተላለፊያውን (Transmission) እና የሥርጭቱን (distribution) ጉዳይ በሚገባ ከተገኘው እና ከመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በማገናኘት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋሉ ተገቢ ነው።

ዋናው ነገር ማመንጨት ብቻ መሆን የለበትም። የተገኘውን የኤሌክትሪክ ኃይል አስፈላጊው ጥቅም ላይ በማዋል ውጤታማ መሆን መቻል ነው። ይህን ስናደርግ በትክክለኛው መንገድ መሆን አለበት። እንዲህ ማድረግ ስንችል ተበጣጥሶ የሚመጣን እና ተቆራርጦ የሚደርስን የኃይል ችግር ማስወገድ እንችላለን።

እንደዚያ ማድረግ ከቻልን ደግሞ ከእሱ ጎን ለጎን የኃይል ማስተላለፍ ዘዴዎችንን (transmission mechanism) እንዲሁም የማስተላለፊያ መስመሮችን ዘመናዊ ማድረግ የግድ ይለናል። በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃቀማችንንም እንዲሁ ልናዘምን ይገባናል፡

እንደሚታወቀው የኤሌክትሪክ ኃይልን በተመለከተ ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ ሁለት ዓይነት ነው። አንደኛው የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት (Ethiopian Electric Utility) ነው። ይህ የአገልግሎት ጉዳይ አሁንም ቢሆን ከፍተኛ የሆነ ድክመት እና ችግር ያለበት ነው። ስለሆነም ይህንን ድክመት በግልጽ አውጥቶ መናገር እና ማስተካከልን የሚጠይቅ ነው።

ይህ ተቋም የመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል ሥራ ላይ እንዲውል አደረገ የሚባለው በየቤታችን፣ በየፋብሪካችን፣ በየኢንዱስትሪዎቻችን እና በተፈላጊ ቦታ ሁሉ ደርሶ ጥቅም ሲሰጥ ነው። ስለሆነም የዚህ አገልግሎት አጠቃቀም ሁኔታ መስተካከል አለበት ባይ ነኝ። ዋናው ጉዳይ ኃይል ማመንጨት ብቻ እንዳልሆነ መታወቅ አለበት። ርግጥ የሕዳሴ ግድቡን ገድበን ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል ደረጃ ላይ መገኘት በራሱ በጣም በጎ ተግባር ነው፤ ኃይል በራስ አቅም ማመንጨት መቻል እጅግ በጣም ታሪካዊ ነገር ነው። በጣምም ትልቅ ስኬት ነው። አሁን ላለው ትውልድ እና በአሁኑ ሰዓት ላለው አመራር ሁሉ እጅግ በጣም ትልቅ ድል ነው። ይበልም የሚያሰኝ ነው። ነገር ግን ከዚህ ጎን ለጎን የኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃቀሙ ላይ መሻሻል የሚገባቸው በሰው ኃይል ደረጃም ቢሆን በሌላ ሌላ አመራርም ቢሆን መስተካከል የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ መጠቀስ ያለበት ነው።

ዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- እኔም አመሰግናለሁ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You