‹‹ የዓባይ ግድብ -የአምራች ኢንዱስትሪው መድኅን ›› አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ በመለስተኛ፣ በመካከለኛና በከፍተኛ ደረጃ የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ላይ የተሠማሩ ወደ 15 ሺ የሚሆኑ አምራች ኢንዱስትሪዎች ይገኛሉ። አምራች ኢንዱስትሪዎቹ ለውጭና ለሀገር ውስጥ የሚቀርቡ ምርትና አገልግሎቶችን ሲያቀርቡ የነበረው በበቂ ሁኔታ ባልተሟላ የኃይል መሠረተ ልማት እንደሆነ አይዘነጋም።

በኃይል መቆራረጥና መሰል ችግሮች የማምረት ሥራቸው እየተስተጓጎለባቸው፣ ምርት መበላሸትም እያጋጠማቸው እንደሚቸገሩ በተደጋጋሚ ያነሱ እንደነበር ይታወቃል። ምንም እንኳን መንግሥት በተለያዩ አማራጮች አምራች ኢንዱስትሪው እንዲበረታታ በሚችለው ሁሉ ለመደገፍ ጥረት ቢያደረግም ሆኖም ያለው የኃይል አቅርቦትና የኢንዱስትሪው ፍላጎት ለማመጣጠን ሳይቻለው ቆይቷል።

በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብም ሆነ ኢንዱስትሪ መር የሆነ የምጣኔ ሀብት እድገት ለማስመዝገብ አስተማማኝ የሆነ የኃይል አቅርቦት ደግሞ ወሳኝ ነው። በሥራ ላይ ያለው አምራች ኢንዱስትሪ በኃይል አቅርቦት ያሳለፈው ተግዳሮት ታሪክ ሊሆን፤ በዘርፉ አዲስ ኢንቨስትመንትም ለመሳብ በኢትዮጵያ ምቹ ጊዜ ላይ ተደርሷል።

ለመጠናቀቅ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የሚገኘው የህዳሴ ግድብ ለአምራች ኢንዱስትሪው ትልቅ እፎይታን እንደሚሰጥ ይጠበቃል። በሕዝብ ተሳትፎ ግንባታው ከዳር የደረሰው ታላቁ የህዳሴ ግድብ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፎ እንደሆነ አይዘነጋም። በተለይም ግብፅ የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ በግንባታው የ13 ዓመታት ጉዞ ለማስተጓጎል ያልፈነቀለችው ድንጋይ የለም ማለት ይቻላል። ዓለምአቀፉን ማኅበረሰብ በማስተባበር ጭምር ኢትዮጵያ የገንዘብም ሆነ የተለያየ ድጋፍ እንዳታገኝ፣ ግንባታውንም ለማስቆም ብዙ ርቀት ተጉዛለች።

ኢትዮጵያ የማንንም ሉዓላዊ ሀገር መብት ሳትጋፋ፣ በጋራ የመጠቀም መብቷን ለማስጠበቅ፣ የዲፕሎማሲ ጥረቷን በአሸናፊነት ተወጥታለች። ኢትዮጵያ ይዛ የተነሳችውን የፍትሐዊ ተጠቃሚነት መርሕ መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ መልማት ለጎረቤት ሀገሮችም የሚተርፍ እንደሆነ በዲፕሎማሲ ሥራዋ አጠናክራ ቀጥላለች።

የዓባይ ግድብ ግንባታ የተጀመረበት 13ኛ ዓመት እና ለመጠናቀቅ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረስ አስመልክቶ በተለይም የግድቡ መጠናቀቅ ያልተቆራረጠ አስተማማኝ የኃይል መሠረተ ልማት አቅርቦት ለሚያስፈልገው በተለያየ ዘርፍ ላይ ለተሠማራው አምራች ኢንዱስትሪ የሚሰጠውን እፎይታ፣ አጠቃላይ የአምራች ኢንዱስትሪውን እንቅስቃሴ በተመለከተ ከኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ጋር ቆይታ አድርገናል።

አዲስ ዘመን ፦ የዓባይ ግድብ ግንባታ ሊጠናቀቅ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛል፤ ይህንኑ በተመለከተ የተሰማዎትን ስሜት አስቀድመው ቢገልጹልን?

አቶ ታረቀኝ ፦ በቅድሚያ የዓባይ ግድብ ግንባታ ሊጠናቀቅ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ በመድረሱ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ደስ አላችሁ። እንኳን ደስ አለን! ለማለት እፈልጋለሁ። የግድቡ ግንባታ ከፍተኛ ድል የተገኘበት ወይንም ውጤት የተመዘገበበት ነው። ግንባታው እውን ወደመሆን መቃረቡ፤ ደስታውና ኩራቱ ከፍ ያለ ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ከተባበርንና አንድ ከሆንን አዲስ ነገር መሥራት እንደምንችል በተምሳሌነት የሚጠቀስ ግድብ ነው።

የሁላችንም ኢትዮጵያውያን ዐሻራ የታየበት፣ የሁላችንም ስኬት ነው። ለልጆቻችን፣ ለልጅልጆቻችን ትልቅ የሆነ ሐውልት ማስቀመጥ ችለናል። ከዚህ የተገኘው ልምድ ደግሞ እንደሀገር፣ እንደዜጋ፣ ታላላቅ የሆኑ ነገሮችን መሥራት እንደሚቻል ያሳያል። ስለ ዓባይ ብዙ ተብሏል። በተለያዩ የሙዚቃ ባለሙያዎችም ተዘፍኖለታል። ግን እንደሀገር ሳንጠቀምበት ቆይተናል።

ታሪክን ወደኋላ መለስ ብለን ብናስታውስ፤ ኢትዮጵያ የዓባይ መገኛ ሆና እያለ፤ እንዳትጠቀም በሕግ ለመገደብ ጥረት ተደርጓል። ግብፅ እና በተወሰነም ሱዳን ውሃውን ለሁለት በመክፈል የራስ የማድረግ ሁኔታ ነው የነበረው። ይህን ኢ-ፍትሐዊነት ሰብሮ ለመውጣት የተለያዩ ተግዳሮቶች ነበሩ። የአቅም ውስንነቱም ሌላው ፈተና ነበር። ኢትዮጵያ ከሌሎች የገንዘብ ብድር አግኝታ የራስዋ የሆነውን የውሃ ሀብት ለልማት እንዳታውል በተለይም ግብፅና የግብፅ ወዳጆች ከፍተኛ ጫና ለማሳደር ተንቀሳቅሰዋል።

ጫናው ግን ኢትዮጵያ ግድቡን ለመገንባት ያደረገችውን መነሳሳትና መነቃቃት ወደኋላ አላስቀረውም። ብድርም ሆነ ድጋፍ ለማግኘት የማንንም ደጅ መጥናት ሳያስፈልጋት ዜጎችን በማስተባበር በራስ አቅም መሥራት መቻሏን አሳይታለች።

ዜጎች በቂ ገቢ ሳይኖራቸው፣ መንግሥት ሠራተኛውም የተሻለ ክፍያ ሳይኖረው፣ በተለያየ የዓለም ሀገር የሚኖረው ትውልደ ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያዊ ለግድቡ ቅድሚያ በመስጠት በጋራ ተረባርቦ ከዳር ያደረሰው ነው። ይሄ ትርጉሙ ለእኛ ኩራት ሊሆን ይችላል። ግድቡን እንዳንገነባና እንዳንጠቀም ጥረት ሲያደርጉ ለነበሩ ኅዘን ነው።

አዲስ ዘመን፦ የዓባይ ግድብ መጠናቀቅ ሀገራዊ አቅምን በመፍጠር በኩል ያለው ድርሻና አያይዘውም የግድብ ግንባታው እንደ ሀገር የወደብ ባለቤት ለመሆን እየተደረገ ላለው ጥረት የሚፈጥረውን አቅም ቢገልጹልን?

አቶ ታረቀኝ ፦ ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛትም ሆነ ወደ ኢኮኖሚ ሊለወጥ የሚችል ሀብት ባለቤት ሆና ወደብ የሌላት በዓለም ላይ የመጀመሪያ ሀገር ናት። የግድቡ መጠናቀቅ ደግሞ ሀገራዊ አቅማችንን ያሳድግልናል። በተለይም በጂዲፒ ያለንን ድርሻ ከፍ ያደርግልናል። እንደ ኅብረተሰብ ደግሞ አብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ያስችላል።

ኢትዮጵያ የዓባይ ግድብን የገነባችው ሌላውን ለመጉዳት ሳይሆን የኃይል አቅርቦት ክፍተቷን ለመሙላት ወይንም በውሃ የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጭቶ ለመጠቀም ነውⵆ የወደብ ባለቤት ለመሆን ከሶማሊላንድ ጋር በሰጥቶ መቀበል ስምምነት ስትፈራረም እንዲሁ ሌላውን ለመጉዳት አይደለም። የወደብ አማራጮችን በማየትና የዓለም አቀፍ ሕግንም መሠረት በማድረግ ለመጠቀም እየተንቀሳቀሰች ነው ።

ኢትዮጵያ ለወደብ የምትከፍለው ክፍያ ከፍተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ የክፍያ ሁኔታ በየጊዜው መቀያየሩ የወጭ ምርትና የገቢ ምርት ተገማች እንዳይሆን እያደረገው ነው። የትራንስፖርት አገልግሎት ክፍያ እንዲጨምር ያደርጋል። የዋጋ መለዋወጥ ኢንቨስትመንትን በማዳከም ጉዳት ያስከትላል። አሁን ባለው አሠራር ለመጓጓዣ የሚወጣው ወጪ፣ ተጓጉዘው የመጡት እቃዎች ወደብ ላይ ለሚቆዩበት የሚከፈለው ክፍያና ተያያዥ የሆኑ ነገሮች የዋጋ ንረት (ኢንፊሌሽን) እያስከተሉ ነው። ስለዚህ በኑሮ ውድነት ውስጥ የራሱ ድርሻ አለው። በዚህም ተጎጂ የሚሆነው ተጠቃሚው ነው።

የራስ የሆነ የወደብ አገልግሎት መኖር የኑሮ ውድነትን በመቀነስ፣ የራስን ወጪና ገቢ ምርት ለመቆጣጠርና ግምታዊ የሆነ የጊዜ ሰሌዳ ለማውጣት ከማስቻሉ በተጨማሪ፤ የሀገር ሉዓላዊነትንም ለማስጠበቅ የራሱ ድርሻ አለው። በሌላ ሀገር ወደብ ተጠቅመን የምናስገባው ዕቃ በሙሉ ስለሚፈተሽ (ስክሪን ስለሚደረግ) እንደሀገር በምስጢር ልንጠብቀው የምንፈልገው ነገር እንኳን ቢኖር አንችልም። ይሄ ደግሞ የሀገር ሉዓላዊነትን ይዳፈራል። የሀገር ደኅንነትን ስጋት ላይ ይጥላል። ከዚህ አንጻር ነው የወደብ ባለቤት መሆን ጥቅሙ የትየለሌ ነው።

የወደቡ አስፈላጊነት ከኢንዱስትሪው አንጻርም ሲቃኝ፤ ምንም እንኳን ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪ የሚያደርገው የኃይል አቅርቦት ቢሆንም፤ ወደቡም ምርትና አገልግሎትን ወደ ውጭ ለመላክም ሆነ ወደሀገር ለማስገባት ወሳኝ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።

አዲስ ዘመን፦ አምራች ኢንዱስትሪው ለዓባይ ግድብ ግንባታ የነበረው አበርክቶ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ታረቀኝ፦ ለግድቡ ግንባታ የኢትዮጵያ ባለሀብት ቦንድ በመግዛት፣ በስጦታም በማበርከት ያደረገው ተሳትፎ ከፍተኛ ነው። ትልቅ ምስጋናም ያስፈልገዋል።

አዲስ ዘመን፦ የዓባይ ግድብ መጠናቀቅ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱን ታሳቢ በማድረግ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የተያዘ እቅድ አለ?

አቶ ታረቀኝ፦ እንደ ሀገር ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ ኢንዱስትሪ ነው። እንደ አንድ ዘርፍም ሲታይ ፋይዳዎች አሉት። ከፋይዳዎቹ አንዱ ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ነው። በአነስተኛ መሬት ላይ የተቋቋመ ኢንዱስትሪ ብዙ የሰው ኃይል የሚይዝ በመሆኑ ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጠራል።

የተመረተውን ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግ ሁለተኛው ፋይዳ ነው። ተኪ ምርት በማምረት ከውጭ የሚገባውን በማስቀረት በከፍተኛ ሁኔታ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ማዳንም ሌላው ነው። ለሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት (ጂዲፒው)ም ድርሻ አለው። የኋላ ታሪካችን እንደሚያሳየው ከነዳጅና የተለያዩ ማዕድናት ከሚገኝ ገቢ ካልሆነ በስተቀር አብዛኞቹ ሀገሮች በኢኮኖሚ ያደጉበት መሠረታቸው ኢንዱስትሪ ነው። ኢትዮጵያ በጂዲፒ ያላት ድርሻ በኢንዱስትሪ ዝቅተኛ ነው። ከሰባት በመቶ በታች ነው። አብዛኛው በግብርና ነው። ከዚህ ካለፈም በአገልግሎት ነው። ስለዚህ ለሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት (ጂዲፒ) ድርሻ ኢንዱስትሪው በጣም ማደግ ይኖርበታል። ማደግ ካለበት ደግሞ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ኢንዱስትሪው ላይ ይጠበቃል። አሁን ባለው የውጭ ምንዛሪ እየተገኘ ያለው የመጀመሪያ ከሚባለው የግብርና ምርት ነው። ምርቱ የሚቀርብላቸው እሴት ጨምረው በእጥፍ ዋጋ እያገኙበት ነው። በራሳችን እሴት ጨምረን ማቅረብ ብንችል ተጠቃሚ እንሆናለን። ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድም ጥቅሙ ይጨም ራል።

መንግሥት አምራች ኢንዱስትሪው እንዲያድግ ቁርጠኛ ሆኖ እየሠራ ነው። በአሁኑ ጊዜም በገበያ የሚመራ ኢንዱስትሪ እንዲኖር ግልጽ የሆነ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ አዘጋጅቷል። በገበያ የሚመራ ኢንዱስትሪ ማለት የተገልጋዩን ወይንም የሸማቹን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ምርት እንዲያመርት ማለት ነው። ምክንያቱም ኢንዱስትሪው ካመረተ በኋላ ገዥ ከሌለው፣ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ቴክኖሎጂ ማሻሻል ካለበት ያሻሽላል። ምርት መቀየር ካለበትም ይቀይራል። ሁልጊዜም ገበያው  የሚመራው መሆን ይኖርበታል።

ሌላው ኢንዱስትሪን ከግብ የሚያደርሰው የግሉ ዘርፍ (ፕራይቬት ኦርየንትድ) መሆን አለበት። ምክንያቱም መንግሥት ግልጽ ሚና ይኖረዋል እንጂ ኢንዱስትሪ ውስጥ እራሱ ገብቶ ሊያሳካ አይችልም። ስለዚህ መንግሥት ብሔራዊ ወይንም ሀገራዊ ባለሀብት ላይ ትኩረት አድርጎ የመደገፍ ሚና ነው የሚወጣው። ኢንደዱስትሪው የሚፈልገውን ነገር ማሻሻል፣ በተለይም ከባቢያዊ ሁኔታ የሚፈጥረውን ምቹ ሁኔታ መጠቀም ይገባል።

ይሄ ማለት የፋይናንስ፣ የኃይል፣ የመሬት፣ የግብዓት የሠለጠነ የሰው ኃይል ኢንዱስትሪው በሚፈልገው ጊዜ ማቅረብ ማለት ነው። አሁን ላይ የፋይናንስ አቅርቦቱ ወደ ግል እየሄደ ነው። ይሄ ጥሩ ነው። ፖሊሲውም ያበረታታል።

አምራች ኢንዱስትሪው በኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ መደገፍ ይኖርበታል። ጥናትና ምርምርም ማካሄድ ይጠበቅበታል። ትላልቅ የሚባሉት ኢንዱስትሪዎች የራሳቸው ጥናትና ምርምር ማዕከል አላቸው። የራሳቸው የሆነ የምርት ፎርሙላ አላቸው። ለአብነት የኮካኮላ አምራች ኢንዱስትሪን ብንወስድ በጥናትና ምርምር ያገኘው የራሱ የሆነ ፎርሙላ አለው። ለማንም አይሰጥም። የመንግሥት ተቋማት የሚያደርጉት ጥናትና ምርምር ቢኖርም ኢንዱስትሪዎቹ በራሳቸው የሚያከናውኑት ጥናትና ምርምር አላቸው። ስለዚህ ኢንዱስትሪዎቹ ጊዜው ከሚጠይቀው ጋር የሚራመድ ቴክኖሎጂ እንዲኖራቸው፣ አዲስ ስልተምርቶችን መከተል እንዲችሉ የመደገፍ ሥራ መሥራትም ይጠበቃል።

የኢንዱስትሪ እድገቱ አንዴ ከፍ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዝቅ ማለት የለበትም። ፈጣን፣ ቀጣይነት ያለው፣ አካታች የሆነ የኢንዱስትሪ እድገት ነው መኖር ያለበት። ስለዚህ አዲስ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ተዘጋጅቷል። ይህን መነሻ ያደረገ ስትራቴጂም ተዘጋጅቷል። ከስትራቴጂው አንዱ የተኪ ምርት ስትራቴጂ ነው። ተኪ ምርት ከውጭ ሀገር የሚገቡ የኢንዱስትሪ ምርቶች በሀገር በማምረት መጠቀም ማለት ነው። መጠቀም ብቻ ሳይሆን፣ በሀገራችን ምርትም መኩራት ያስፈልጋል። ስትራቴጂው ስኬታማ እንዲሆን መሥራት ይጠበቅብናል።

ኢንዱስትሪዎቹ በጥራት፣ በዋጋ፣ በጊዜ ተወዳዳሪ መሆን ይኖርባቸዋል። በዚህ ረገድ አበረታች የሆኑ ለውጦች እየታዩ ነው። ጅምሩን እየሰፋ እንዲሄድ ማድረግ ያስፈልጋል። መንግሥት በስትራቴጂ መደገፍ፣ መሻሻል ያለበትን ሕግና አሠራርንም ያሻሽላል። ሰሞኑን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያስቀመጠው አቅጣጫ ለኢንዱስትሪ ዘርፉ ትልቅ መነቃቃትን የሚፈጥር ነው።

አቅጣጫው የመንግሥት ግዥዎች ከሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲፈጸም የሚል ነው። አብዛኛውን ግዥ የሚፈጽሙት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ናቸው። ስለዚህ ግዥውን ከሀገር ውስጥ አምራቾች ሲፈጽሙ፣ኢንዱስትሪዎቹ በተሻለ ጥራትና አቅርቦት ለመወዳደር ያስችላቸዋል። ውሳኔው ለአምራች ኢንዱስትሪው ትልቅ ዕድል ነው ።

ለሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች ቅድሚያ ይሰጥ ማለት ጥራት የሌለውንም መንግሥት ይወስዳል ማለት እንዳልሆነ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል። ዕድሉ የተሻለ ጥራትና ዋጋ ላላቸው፣ በጊዜው ማቅረብ ለሚችሉ ነው። አሁን የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ የአምራች ኢንዱስትሪው ለረጅም ጊዜ ሲያቀርበው የነበረው ጥያቄ ነው። የአምራች ኢንዱስትሪውን ቅሬታንም ይፈታል።

አዲስ ዘመን፦ አምራች ኢንዱስትሪውን እየፈተኑት ያሉት ወይንም እያጋጠመው ያለው ተግዳሮት በዋናነት ምንድነው? ከፍተኛ ኃይል የሚፈልገው የኢንዱስትሪ ዘርፍስ ተለይቷል? አምራች ኢንዱስትሪውስ ምን ያህል ነው?

አቶ ታረቀኝ፤ አምራች ኢንዱስትሪው ተግዳሮቶቹ የተለያዩ ናቸው። ከዚያ ውስጥ የኃይል አጠቃቀም አንዱ ነው። የኃይል አጠቃቀምን ከሚገድቡት ደግሞ በቂ የሆነ የኃይል አቅርቦት አለመኖር፣ መቆራረጥና መዋዠቅ ነው። ይህ ሲሆን በበቂ ሁኔታ ማምረት አለመቻል ያጋጥማል። በበቂ ሁኔታና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ቢያገኙ የማስፋፋት ሥራ በመሥራት ምርታቸውን በእጥፍ ለማሳደግ የተዘጋጁ አ ምራች ኢንዱስትሪዎች አሉ።

በኃይል አቅርቦት ውስንነት ከፍተኛ የሰው ኃይል መያዝ የሚችሉ ኢንዱስትሪዎች የሥራ ዕድል እንዳይፈጥሩ አድርጓል። የዓባይ ግድቡ መጠናቀቅ በኃይል እጥረት ምክንያት ወደኃላ የቀሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲያንሠራሩና እንዲጠናከሩ ከማድረጉም በላይ ተጨማሪ ኢንቨስትመንትንም ለመሳብ ፋይዳው የጎላ ነው።

ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ የአምራች ደረጃ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ይፈልጋሉ። ከፍተኛ ኃይል ከመጠቀም አንጻር ለምሳሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ እራሱን የቻለ ኃይል ይፈልጋል። ይህ መሆኑ ረዘም ያለ የሥራ ጊዜ እንዲኖራቸው ያስችላል። እንደ ብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ያሉ በትልልቅ አምራች ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚመደቡ በመሆናቸው ከፍተኛ ኃይል ይጠቀማሉ። በቂ የሆነ የኃይል አቅርቦት ምቹ ሲሆን፣ በተጨማሪ ትላልቅ የሚባሉ ኢንዱስትሪዎች ይመጣሉ። አሁንም ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች መምጣት ጀምረዋል።

ኢንዱስትሪዎቹ ምን ያህል ናቸው ለሚለው። ኢንዱስትሪ አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ በሚል ይከፈላሉ። አጠቃላይ ያለውን የኢንዱስትሪ ብዛት እያጠናን ቢሆንም፤ እንደሀገር ወደ 15ሺ ኢንዱስትሪዎች በሥራ ላይ ይገኛሉ። አብዛኞቹም በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ የሚገኙ ናቸው።

እነዚህ በሥራ ላይ የሚገኙት ኢንዱስትሪዎች አስተማማኝ የሆነ የኃይል አቅርቦት ማግኘት ከቻሉ የማምረት አቅማቸው ይጨምራል። የበጀት ዓመቱ የስድስት ወር ግምገማ እንደሚያሳየው ለኢንዱስትሪ የሚቀርበው ኃይል ቀደም ሲል ከነበረበት አድጓል። አቅርቦቱን የበለጠ ለማሻሻል ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ድርጅት ጋር በጋራ ለመሥራት ኮሚቴ አዋቅሮ እየሠራ ይገኛል።

አዲስ ዘመን ፦ አምራች ኢንዱስትሪው የኃይል አቅርቦቱ ብቻ ሳይሆን ለምርት የሚያውለው ጥሬ እቃም በየጊዜው ዋጋ መናርና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ተወዳዳሪነቱ ላይ ተፅዕኖ እንዳለው ያነሳል። እዚህ ላይ ምላሽዎ ምንድነው?

አቶ ታረቀኝ፤ እውነት ነው አምራች ኢንዱስትሪው የግብዓት ችግር ያነሳል። አብዛኞቹ ግብዓቶች ከውጭ በግዥ የሚገቡ ናቸው። አሁን ባለው የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ላይ እንደተቀመጠው አንድ ኢንዱስትሪ ከሀገር ውስጥ የሚጠቀመው ግብዓት ምንያህል ነው የሚለው ይታያል። ወይንም ይለያል። በሚሠራው የልየታ ሥራ መቶ በመቶ ከሀገር ውስጥ ግብዓት የሚጠቀም ኢንዱስትሪ ይበረታታል። ምክንያቱም ኢንዱስትሪዎች የውጭ ሀገር የግብዓት ጥገኛ እንዲሆኑ አይፈለግም። የወደፊት አቅጣጫም የሀገር ውስጥ ግብዓት ጥቅም ላይ እንዲውል ማስቻል ነው።

የግብዓት አቅርቦት ክፍተት ካለ ደግሞ የግብዓት ልማት ላይ መሥራት ነው። በዚሁ መሠረትም ለተኪ ምርት ዝግጅት ስናደርግ ያለንን ቴክኖሎጂ፣ የሰው ኃይል፣ አሁን ያሉት ኢንዱስትሪዎች የሚጠቀሙት የግብዓት አይነት፣ በስንት ጊዜ ልናሳካው እንችላለን የሚለውን ለማወቅ ከግብዓት በመነሳት ሥራዎች ሠርተናል። ኢንዱስትሪዎቹ ግብዓትን በቀላሉ ማግኘት የሚችሉ ከሆነ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ልናሳካ እንችላለን ብለን ነው በእቅድ የያዝነው።

የሰው ኃይል ላይ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል ያልነውን ደግሞ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ስኬት ማስመዝገብ ይቻላል በሚል ነው። ነገር ግን አሁንም ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ማምጣት አለብን ብለን ያስቀመጥነው በአስር ዓመት ጊዜ ውስጥ ነው።

አሁን ላይ የግብዓት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት እየተሠራ ነው። ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የውጭ ምንዛሪ ቅድሚያ እንዲያገኙ ተደርጓል። ከፍላጎት አንጻር በቂ ባይሆንም ሀገሪቱ ከምታመነጨው የውጭ ምንዛሪ ትኩረት ሰጥታ ዘርፉን እየደገፈች ነው። የውጭ ምንዛሪ ሳይፈልጉ የራሳቸውን ግብዓት ከውጭ የሚያስመጡ ኢንዱስትሪዎች አሉ። ከግብር (ታክስ) ነፃ ናቸው። ያመረቱትን ምርትም ለውጭ ገበያ ነው የሚያቀርቡት። ግብዓት የሚያስመጡትም አብዛኞቹ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ናቸው፡

በተለያየ ምከንያት ማምረት አቁመው የነበሩና በከፊል ያመርቱ የነበሩ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ወደ 390 ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ ማስገባት ተችሏል።

አዲስ ዘመን፤ – የኢንዱስትሪዎቹ አንዱ የመወዳደሪያ መስፈርት ጥራት ነው። ማነው ክትትልና ቁጥጥሩን የሚያከናውነው? ተጠያቂነታቸውስ?

አቶ ታረቀኝ፤ የቁጥጥር ሥራን የሚሠሩ የተለያዩ ተቋማት አሉ። አንዱ የኢትዮጵያ ጥራት ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ነው። ለምርቱ ደረጃ ያወጣል። በወጣው ደረጃ መሠረት ምርቱ መመረቱ በቤተሙከራ ውስጥ የምርት ምርመራ ወይንም ፍተሻ ይለያል። ደረጃዎቹ ሁለት አይነት ናቸው። አንዱ አስገዳጅ ሲሆን ሌላው ደግሞ አስገዳጅ ያልሆነ ነው።

ለምሳሌ ከምግብና ከመጠጥ ጋር የተገናኘ ከሆነ ምርቱ የተመረተበትና የሚያበቃበት ጊዜ፣ ምርቱ የተመረተበት ግብዓት፣ አጠቃላይ መረጃ የያዘ መግለጫ ሊኖረው ይገባል። ይሄ አስገዳጅ ደረጃ ነው። ስለዚህ በዚህ በኩል ደረጃ የሚያወጣና ደረጃ የሚቆጣጠር አለ። በተለይም ከምግብና መጠጥ ጋር የተያያዘውን የኢትዮጵያ መድኃኒትና ቁጥጥር ባለሥልጣን የቁጥጥርና ክትትል ኃላፊነቱን የሚወጣው።

የጥራት ጉዳይ ድርድር ውስጥ አይገባም። የጥራት ጉዳይ በቸልታ የሚታለፍ ከሆነ የኢንዱስትሪ ዕድገት አይታሰብም። የኢንዱስትሪ ማደግ ብቻ ሳይሆን፤ የተጠቃሚውም ፍላጎት መሟላት አለበት። ስለዚህ ለኢንዱስትሪ እድገት ወሳኙ ሸማች ነው። ከዚያ ውጭ የኢንዱስትሪዎች ዘላቂነት ጉዳይ ነው። አንዱ ከኃይል አቅርቦት ጋር ይያያዛል።

ለምሳሌ አንድ ኢንዱስትሪ የሚጠቀመው የኃይል አይነት አረንጓዴ ኃይል(ግሪን ኢነርጂ)፣ ኒኩሌየር ኃይል፣ የዲዝል (ጋዝ) ኃይል ነው የሚለው መታወቅ አለበት። ኢንዱስትሪው እንደሚጠቀመው የኃይል ሁኔታ ገበያ ላይ የሚያወጣው ምርት ዋጋ ይለያያል። ግሪን ኢነርጂ ተጠቅሞ ከሆነ የተሻለ ዋጋ ያገኛል። ይሄ በአብዛኛው ለውጭ ገበያ በሚቀርበው ምርት ላይ የሚስተዋል የገበያ ሁኔታ ነው። በአካባቢ ላይ በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት የሚያደርስ ኃይል አጠቃቀምም በኢንዱስትሪ ዘርፍ ተመራጭ አይደለም።

አካታች አለመሆንም እንዲሁ ተመራጭ አያደርገውም። ለምሳሌ አሁን በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ርካሽ የሆነ የሰው ኃይል ስለመኖሩ ነው የሚነገረው። ይሄ ግን ወደፊት የሚቀጥል አይሆንም። ሰው በሠራው ልክ ክፍያ ማግኘት አለበት። ከሰው ጉልበት ብዝበዛ ጋር ነው የሚያያዘው። ሌላው አሳታፊነት ውስጥ መካተት ያለበት ሴቶችና ወንዶች፣ አካል ጉዳተኞች ኢንዱስትሪ ውስጥ መኖር ያለባቸው መስፈርቶች ናቸው። እነዚህ ሁሉ የኢንዱስትሪው የምርት ማረጋገጫዎች ናቸው። ኢንዱስትሪዎች የጥራት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀትም በየጊዜው ይሰጣቸዋል።

አዲስ ዘመን ፦ወቅታዊው የሀገር ሠላምና ኢንዱስትሪው እንዴት ይታያል?

አቶ ታረቀኝ፦ ሠላም አለመኖር መጀመሪያ የሚጎዳው ኢንዱስትሪውን ነው። ሠላም ከሌለ ነባር ኢንቨስትመንቶች የመቀጠል እድላቸው አነስተኛ ነው። ተጨማሪ ኢንቨስትመንትን መሳብ አይቻልም። በአሁኑ ጊዜ በግጭቱ ሥራቸው ተስተጓጉሎ የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እየተመለሱ ነው። ኤክስፖርት የጀመሩም አሉ።

በቀጣይ መሻሻል ያለበት ለኢንቨስመንት ያለን አተያይ ነው። የፀጥታ ችግር በሌለበትም ኢንቨስትመንት የሥራ ዕድል፣ ቴክኖሎጂ ይዞ እንደሚመጣና ለሀገር እድገት አስፈላጊ እንደሆነ አለመገንዘብና በመልካም ያለመቀበል ሁኔታ ይስተዋላል። የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ያስፈልጋል። የፖለቲካ ተቃውሞ ሲነሳ ኢንቨስትመንትን ማዕከል የማድረግ ሁኔታም መስተካከል አለበት።

አዲስ ዘመን ፦የዓባይ ግድብ ተጠናቅቆ የኃይል አቅርቦት ችግሩ ከተፈታ ከአምራች ኢንዱስትሪው ምን ይጠበቃል?

አቶ ታረቀኝ፦ አምራች ኢንዱስትሪዎች የኃይል አቅርቦት ችግራቸው ከተቃለላቸው በኋላ የማምረት አቅማቸው ማደጉን ማረጋገጥ አለባቸው። ተጨማሪ ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት የበለጠ ለመሥራት መነሳሳት ይኖርባቸዋል። እንደመንግሥትም ደግሞ በቂ የሆነ ኃይል መኖሩንና በዋጋም ርካሽ እንደሆነ ማስተዋወቅ ይጠበቃል።

አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።

አቶ ታረቀኝ፦ እኔም አመሰግናለሁ።

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You