ዓባይ የሁሉም ምንጭ

‹‹ዓባይ የግብጽ ሕይወት ነው›› የሚለው የግብጽ ትርክት ዓለም አቀፍ ሆኗል። ይህ ቃል ግን በምሁራኖቻቸው ተቀርጾ በፕሮፖጋንዳቸው ዝነኛ የሆነ ነው። ለመሆኑ ዓባይ ለኢትዮጵያ ምንድነው?

ዓባይ ለኢትዮጵያ ሁሉንም ነገር ነው። የሁሉም ነገር ምንጭ ነው። ይህ የሆነው በትርክት ሳይሆን በተፈጥሮ እና በሕዝብ ነው። ዓባይ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ሕይወት ጋር የተቆራኘ መሆኑን የሚያረጋግጠው በሕይወት እንቅስቃሴዎቻቸው ውስጥ ሁሉ ያለ መሆኑ ነው። የሰው ልጅ መሠረታዊ ነገር ውሃ ቢሆንም፤ ዓባይ ግን ከውሃነትም ባሻገር ነው። ዓባይ ቋንቋ ነው። ዓባይ ባህል ነው። ዓባይ ትውፊት ነው። ዓባይ ሥነ ልቦና ነው። ዓባይ ታሪክ ነው።

ዓባይ ቋንቋ ነው ሲባል፤ ግዝፈትን፣ ኃይለኛነትን፣ ለጋስነትን… ለመግለጽ ያገለግላል። ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ውስጥ በሴትም በወንድም ዓባይ የሚባሉ ሰዎች አሉ። በተረቶቻችን ውስጥ ግዝፈትን፣ ለጋስነትን፣ ሃይለኝነትን ለመግለጽ በብዛት እንጠቀመዋለን። በአጠቃላይ ዓባይ ኢትዮጵያ ሕዝብ ማንነትና ምንነት ነው።

ይህን የዓባይን እና የኢትዮጵያን ሕዝብ ቁጭት ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩን የሕዝብ ሀብት የሆኑት የሥነ ቃል የጥበብ ውጤቶች ናቸው። ዓባይ ለኢትዮጵያ የጥበብ ምንጭ ሆኖ ኖሯል። እነሆ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ሆኖ አሁን የኃይል ምንጭ ሊሆን ነው። የመሠረት ድንጋይ የተጣለበትን 13ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የዓባይን እና የኢትዮጵያን ሕዝብ ቁርኝት እናስታውስ።

የባህል ጥናትና የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ሥነ ቃል የአንድ ማህበረሰብ ምንነት ነው። ምክንያቱም ሥነ ቃል በመንግሥት ትዕዛዝ ወይም በአንድ ወገን ጫና የሚፈጠር ሳይሆን ማህበረሰባዊ ሥነ ልቦና የሚገለጽበት ነው። ሕዝብ ብሶቱንና ደስታውን የሚገልጽበት ነው። እነዚህ የስሜት መግለጫ የሆኑ የሥነ ቃል ሀብቶች ደግሞ የሚፈጠሩት ከሚታየው ነባራዊ ሁኔታ ነው። ለዚህም ነው የአንድ ማህበረሰብ ታሪካዊ ታሪክ ሲጠና ትውፊቱ መነሻ የሚሆነው።

እንግዲህ ዓባይ የኢትዮጵያውያን ማንነትና ምንነት ባይሆን ኖሮ ሥነ ቃሎቻችን እንዲህ በዓባይ አይጥለቀለቁም ነበር ማለት ነው። በተረትና ምሳሌዎቻችን ውስጥ ዓባይ አለ፤ የደስታና የሀዘን እንጉርጉሮዎቻችን ውስጥ ዓባይ አለ፣ በባህል ዘፈኖቻችን ውስጥ ዓባይ አለ፣ በስም አወጣጣችን ውስጥ ዓባይ አለ… ዓባይ በብዙ ነገሮቻችን ውስጥ አለ።

ዓባይ እንዲህ እንደ ዛሬው በቁጥጥራችን ሥር ከመዋሉ በፊት በአስቸጋሪነቱ ተዘምሮለታል። ይሄውም በክረምት ወራት የዓባይ ወዲያ ማዶና የዓባይ ወዲህ ማዶ ሰዎችን ስለማያገናኝ ነው። ያኔ በዘመኑ ድልድይ የሚባል ነገር ስለማይታወቅ በዋና እና በእግር በመሻገር ብቻ ስለነበር ስለአስቸጋሪነቱ ተዘፍኖለታል። አብዛኞቹ ተረትና ምሳሌዎች፣ እንጉርጉሮዎች ግን ስለግዙፍነቱ ነው።

ከተረትና ምሳሌዎቻችን ውስጥ፤ ዓባይን ያላየ ምንጭ ያመሰግናል፣ ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል፣ ዓባይ ቢሞላ ተሻገር በሌላ፣ ዓባይ አንተ አየኸኝ ከደረት እኔም አየሁህ ከጉልበት፣ ዓባይና ስንቅ እያደር ይቀላል፣ ዓባይን በጭልፋ፣ የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማው፣ የሰው ቤት ዓባዩ… የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ። አብዛኞቹ ግዙፍነቱን የሚገልጹ ሲሆኑ አንዳንዶቹም ተጓዥነቱንና አስቸጋሪነቱን የሚገልጹ ናቸው። ዓባይን ያላየ ምንጭ ያመሰግናል የሚባለው አንድ ሰው ትንሽ ነገር ሲያደንቅ ነው፤ ከዚህም የበለጠ አለ ለማለት ነው። ለምሳሌ የአንዲት የገጠር ከተማን ሕዝብ ብዛት ለሚያደንቅ ሰው እነ አዲስ አበባን ለመግለጽ ‹‹ዓባይን ያላየ ምንጭ ያመሰግናል›› ሊባል ይችላል። የዓባይ ግዙፍነት ሌሎች ነገሮችን ለመግለጽ እንደ ማንፃፀሪያ ያገለግላል ማለት ነው። ዋና ዓላማችን ተረትና ምሳሌዎቹን ማብራራት ስላልሆነ እንደየዓውዳቸው እንጠቀማቸዋለን።

አሁን ከተረትና ምሳሌዎች (ምሳሌያዊ ንግግሮች) ወደ ቃል ግጥሞች እንሂድ። የቃል ግጥሞች በጣም ብዙ ናቸው። በተለይም በባህል ዘፈኖች ውስጥ ይደጋገማሉ። የባህል ዘፈኖች ሲባል በካሴት ወይም ሲዲ እና ዲ ቪ ዲ የወጡትን ሳይሆን እረኞችና ገበሬዎች የሚዘፍኑትን ለማለት ነው። ዓባይ ኢትዮጵያ ውስጥም ከእረኛ ጀምሮ እንደሚታወቅ የምናውቀውም በእነዚህ የሥነ ቃል ዘፈኖቹ ነው። ለምሳሌ የፍቅር ዘፈኖችን እንይ።

በድሮው ጊዜ ዓባይን መሻገር የሚቻለው በበጋ ወቅት ውሃው በመጠኑም ቢሆን ሲቀንስ ተጠብቆ ነበር። እንደ ዛሬው ድልድይ የለም፣ መኪና የለም። አንድ ከዓባይ ወዲህ ማዶ ያለ ኮበሌ ከዓባይ ወዲያ ማዶ ያለች ጉብል ካፈቀረ መገናኘቱ ከባድ ነበር። የሚገናኙት የበጋ ወቅት ጠብቀው ነው። የፍቅረኛው ናፍቆት ሲጠናበት በማሽላ ይመስላታል። እንዲህም ሲል ያንጉራጉራል።

ዓባይ ወዲያ ማዶ ማሽላ ዘርቼ

ወፎች ጠረጠሩት መሻገሪያ አጥቼ

‹‹ወፎች‹‹ ተብለው የተገለጹት ፍቅረኛውን የሚነኩበትን ሌሎች ወንዶች ነው። በዚህ ቅኔ ለበስ ግጥም ውስጥ ብሶቱን ይገልጻል። ከዓባይ ወዲያ ማዶ አፍቅሬ ማግኘት አልቻልኩም ማለቱ ነው። ባስ ሲልበት ደግሞ እንዲህ በማለት ፈጣሪን ይማጸናል።

አንቺ ወዲያ ማዶ እኔ ወዲህ ማዶ

አንገናኝም ወይ ተራራው ተንዶ?

ተራራ ተብሎ የተገለጸው የዓባይ ውሃ ነው። የያኔው አፍቃሪ ጸሎት ሰምሮ እነሆ ዛሬ ተራራው ተንዷል። ከዓባይ ወዲህ ማዶ ያለ አፍቃሪ ከዓባይ ወዲያ ማዶ ያለች ፍቅረኛው እንዲህ ህልም አትሆንበትም። ያ የከለከለው ተራራ በዓባይ ድልድይ ተንዷል። በፈለገው ቀን ሄዶ ፍቅረኛውን ማግኘት ይችላል።

የዓባይ ውሃ ክረምቱን ሙሉ እንዲህ ሰውን ያቆራርጥ ነበር። መገናኘት የሚቻለው በበጋ ወቅት ነው። ፍቅሩ ብሶበት የበጋ ወቅት የሚጠባበቀው አፍቃሪ እንዲህ ሲል ተስፋ በቆረጠ አንጀት ይዘፍናል።

ዓባይ ጉደል ብለው አለኝ በታኅሣሥ

የማን ሆድ ይችላል እስከዚያ ድረስ?

ታኅሣሥ የበጋ ወቅት የመጀመሪያው ወር ነው። ይሄን የበጋ ወቅት መጠበቅ ያልቻለ አፍቃሪ፣ ያለው አማራጭ በዋና መሻገር ነው። በርግጥ ይህ የሚሆነው ደግሞ ዋና ለሚችል ሰው ነው። ዋና የሚችለው ደግሞ እንዲህ ሲል ይዘፍናል።

እስኪ ልሻገረው ዓባይን በዋና

የጎጃም ልጅ ወዶ ምን እንቅልፍ አለና!

አፍቃሪው የሸዋ ሰው ሊሆን ይችላል። ወደ ጎጃም ለመሻገር ደግሞ በመሃል ዓባይ አለ። በነገራችን ላይ ዓባይ ውሃው ብቻ አልነበረም አስቸጋሪ። ወደ ወንዙ የሚያስገቡ መንገዶች ሁሉ ዳገትና ገደል ናቸው። በዋና እንኳን ለመሻገር ብዙ አስቸጋሪ መንገዶችን በእግሩ ሄዶ ነው። የወንዝ ዳር መንገዶች እንደሌላው ምቹ አይደሉም። ወደ ወንዙ ሲወርድ ቁልቁለት አለ፤ ከተሻገረ በኋላ ደግሞ አቀበት (ዳገት) አለ። ቁልቁል ሲወርድ እሷን ለማግኘት ነውና ይጨንቀዋል (በዚያ ላይ የውሃው ስጋት አለ) ከተሻገረ በኋላ ደግሞ በችኮላ አቀበቱን ይወጣዋል። ይሄኔ እንዲህ እያለ ይዘፍናል።

ዓባይ ቁልቁለቱን እምባዬ እያነቀኝ

ዓባይ አቀበቱን ላብ እያጠመቀኝ

መቅረትስ አልቀርም

እስከዚያው ጨነቀኝ።

የዓባይ ውሃ መሙላት አንዳንዴ ደግሞ ጥሩ አጋጣሚም ይፈጥራል። ይህ የሚሆነው ከዓባይ ወዲያ ማዶ ያለችዋ ተፈቃሪ አፍቃሪዋ ጋ ወዲህ ማዶ እንደመጣች ውሃው ከሞላ ነው። ምክንያቱም አትሄድም። ይህን አጋጣሚ ሲያገኝ

ዓባይ ሞላ አሉ ሞላ አሉ

እንደ ዕድሌ ሁሉ

እያለ ይዘፍናል። አንዳንዱ ደግሞ እንዲህ በማለት ቀጭን ትዕዛዝ ይሰጣል።

ዓባይ ቢሞላ ቢሞላ

ዞረሽ ነይ በሌላ!

በርግጥ እሷን ብቻ ሳይሆን ለራሱም እንዲህ ብሏል።

ዓባይ ሞላ ብየ ሞላ ብየ

አልቀርም ሸግየ

አንዳንዱ ደግሞ ትንቢት ይገለጥለታል። የዓባይ መሙላት እንዲህ አስቸጋሪ ሆኖ አይቀርም ያለ አፍቃሪ እንዲህ ብሎ ነበር።

ዓባይም ቢሞላ ቢሞላ

አለው አሉ መላ

የዚህ ትንቢት ፈጣሪ፣ ‹‹መላው›› ምን እንደሆነ አልነገረንም፤ ‹‹አለው አሉ መላ›› ብሏል። እነሆ መላው ተገኝቶ ዛሬ የዓባይ መሙላት ፍቅረኞችን መለያየት አልቻለም። ሰውየው የተናገረው ነገር ምናልባትም ድልድይ ሊሰራ እንደሚችል ታይቶት ነበር ብለን እንያዝለት።

የሥነ ቃል ዘፈኖችና ምሳሌያዊ አነጋገሮቻችን ብዙ ጥልቅ ሃሳብ ያላቸው ናቸው። ዓባይ ከኢትዮጵያውያን ጋር ያለውን ባህላዊና ታሪካዊ ትውፊት የሚያሳዩ ናቸው። የዓባይንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ሥነ ልቦናዊ ትስስር ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ ናቸው።

ዓባይ የጥንት ኢትዮጵያውያን አበው ብቻ አይደለም። ዓባይ ለዚህ ትውልድም ገናና ማንነት ነው። ይሄ ትውልድም ገናና ዐሻራውን ያሳረፈበት ነው። ይሄ ትውልድም የተጠበበበት ነው። ስለዓባይ ያልዘፈነ የለም፤ ያልተቀኘ የለም፣ ያልገጠመ የለም፣ ያልሳለ የለም፣ ያልተወነ የለም! ዓባይ ለብዙ ከያኒያን የጥበብ ምንጭ ሆኗል። ለዛሬው ዘፋኞችን ብቻ እናያለን። የሁለት ዘፋኞችን ስንኞች መልዕክት እንያቸው።

በ2003 ዓ.ም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ሲጣል ከዜናው እኩል ተሰምቷል። ስለሕዳሴው ግድብ ለሚሰሩ ፕሮግራሞች ሁሉ ማጀቢያ ነበር። የድምጻዊት ገነት ማስረሻ ‹‹ዓባይ ጭስ አልባው ነዳጅ›› የተሰኘው ዘፈን አሁን ድረስ የፕሮግራሞች ማጀቢያ ነው። ከዚያ ወዲህ ስለሕዳሴው ግድብ ብዙዎች ቢዘፍኑም ቀዳሚ በመሆኑ ይመስላል ይደጋገማል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ስንኞቹ ጥልቅ መልዕክት አላቸው። እስኪ ጥቂቶችን እንያቸው።

አደባልቆት ሲሄድ ጥቁር እና ነጩን

ግዮን አበሻ ነው ማን ይነካል ምንጩን!

ዓባይ አንተ እያለህ ታላቁ ወንዛችን

መሳለቂያ አንሆንም በድህነታችን።

አዎ! ዓባይን የሚያህል ግዙፍ ሀብት ይዘን መሳለቂያ ሆነናል። ለመዝገበ ቃላት የድህነት ትርጉም መፍቻ ሆነናል። ይሄ ሁሉ ሲሆን ከኢትዮጵያ ተነስቶ የኢትዮጵያን ጋራና ሸንተረር አቆራርጦ፣ የኢትዮጵያን አፈር እያደባለቀ የሚሄድ ነው። ‹‹አደባልቆት ሲሄድ ጥቁር እና ነጩን›› የሚለውን ቅኔ በየራሳችን መተርጎም ነው።

ዘመን ቢያስታርቀን ከዓባይ ብንስማማ

ይዘን ተጠጋነው አካፋና ዶማ

ዓባይ ለዘመናት ለቀረርቶና ለፉከራ የግጥም ምንጭ ብቻ ሆኖ ኖሯል። እነሆ 2003 ዓ.ም ላይ ግን ታሪክ ተቀየረ። አካፋና ዶማ ይዘን ተጠጋነው።

ማደሪያ ሳይኖረው ግንድ ይዞ ይዞራል

የሚባለው ተረት ከእንግዲህ ይቀራል

እንዲህ እንደ ዛሬው መልካም ቀን ሲመጣ

ግንድም ይዘህ አትዞር ማደሪያም አታጣ።

አዎ! ተረት እውን ሆነ። ‹‹ዓባይ ማደሪያ የለውም ግንድ ይዞ ይዞራል›› የሚለው ተረትና ምሳሌ ራሱ ተረት ሆነ። ዓባይ ማደሪያ አገኘ፤ ሥራው ግንድ ይዞ መዞር ሳይሆን ኃይል ማመንጨት።

ዓባይ እኔና አንተ ሳይሉን ቸር ሆነን

ፎከሩብን እንጂ ማን አመሰገነን!

በራሳችን ውሃ በረሳችን አፈር

ተዘባበቱብን ተመጠጠ ከንፈር!

ዓባይ ለዘመናት ለኢትዮጵያ ምንም ሳይጠቅማት ግብጽንና ቅኝ ገዥ ሀገራትን ሲያወዳጅ ኖሯል። ግብጽን አበልጽጓል። ኢትዮጵያ ግን አልተመሰገነችም፤ እንዲያውም መሳለቂያና መዘባበቻ አደረጓት። በራሷ ውሃና አፈር መሳለቂያ ሆነች፤ በሌለችበት እንደፈለጋቸው ይፈራረሙበታል፤ ይወዳጁበታል። አቅም የላትም፣ አትገነባውም የሚል ንቀት መሆኑ ነው።

ስንት ዘመን ቁጭት ስንት ዘመን ግጭት

ስንት ዓመት በጣሳ ስንት ዓመት በወጪት!

ፍሰስበትና በሀገርህ ሜዳ

የሚቆጣም ካለ ያበጠው ይፈንዳ!

አሁን ተረቱም ፉከራውም ይበቃል፤ ‹‹ዓባይን በጭልፋ፣ ዓባይን በወጪት…›› የሚሉ ተረትና ምሳሌዎች ወደ እውን ይቀየሩ። እነሆ ዓባይ ይገደብ እንደማለት ነው፤ ‹‹አትገድቡም›› የሚል ካለም ኢትዮጵያውያን ያውቁበታል ለማለት ነው።

መቼም የዓባይ ነገር ከተነሳ ከወንዙ እኩል ስመ ገናና የሆነችው ድምጻዊት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) በሁላችንም ልብ ውስጥ ናት። አንድ ለሙዚቃ ምንም ቅርበት የሌለው ሰው ‹‹እስኪ የአንድ ዘፋኝ ስም ተናገር›› ቢባል ‹‹ጂጂ›› ማለቱ አይቀርም። ጂጂ ከዓድዋ እና ከዓባይ እኩል ስሟ ይነሳል፤ ምክንያቱም ዓድዋንም ዓባይንም በብዙዎች ልብ ውስጥ እንዲሰርጹ አድርጋለች። መዝፈን ቢሉ ዝም ብሎ መዝፈን ሳይሆን ልብን ሰርስረው በሚገቡ ጥልቅ ስንኞች በመቀኘት ነው።

ጂጂ ለዓባይ የዘፈነችው ሊገደብ ነው ሲባል አይደለም፤ ማንም ባላሰበበት ወቅት ነው። እውነተኛ ጥበብም እንዲህ ነው፤ ቀድሞ ይተነብያል፤ የሌሎችን ዓይንና ልብ ይከፍታል። ጂጂ ዓባይን እንዲህ ስትለው ኖራለች።

የማያረጅ ውበት የማያልቅ ቁንጅና

የማይደርቅ የማይነጥፍ ከዘመን የፀና

ከጥንት ከፅንስ አዳም ገና በፍጥረት

የፈሰሰ ውሃ ቀድሞ ከገነት

ጂጂ የዓባይን ታሪካዊና ጥንታዊነት ነው የነገረችን። ዓባይ የማያረጅ ውበት መሆኑ ደግሞ ቀደም ሲል ያየናቸው የማህበረሰቡን ሥነ ልቦና የሚገልጹ ሥነ ቃሎችም ይነግሩናል። ከሰው ልጅ ፍጥረት ጋር ያለውን ቁርኝትና የሥልጣኔ አስጀማሪነቱን ትነግረናለች። ‹‹ግርማ ሞገስ የሀገር ፀጋ የሀገር ልብስ›› እያለች የዓባይና የኢትዮጵያን ታሪካዊና ተፈጥሯዊ አንድነት ትነገረናለች።

ዓባይ

የበረሃ ሲሳይ

ብነካው ተነኩ! አንቀጠቀጣቸው

መሆንህን ሳላውቅ ሥጋና ደማቸው!

ይሄ እንግዲህ የዘመኑን ወቅታዊ ሁኔታ እንኳን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። ዓባይ ለግብጻውያን ሥጋና ደማቸው ነው፤ ሲነካ ያንቀጠቅጣቸዋል። ለዚህም ነው በመገናኛ ብዙኃኖቻቸው የውሸት ዜና ሳይቀር የሚያሰራጩት። ግብጾች ምንም ዓይነት ውስጣዊ ችግር ቢያጋጥማቸው ከዓባይ ፕሮፖጋንዳ ዝንፍ አይሉም። እንዲህ ዓይነቱን እውነታ ነው የጂጂ ስንኞች የሚነግሩን።

የሚበሉት ውሃ የሚጠጡት ውሃ

ዓባይ ለጋሲ ነው በዚያ በበረሃ

ልብ በሉ እነዚህን ስንኞች! የሚበሉት ውሃ፤ የሚጠጡት ውሃ። እንዲህ ላወቁበት ውሃ የሚጠጣ ብቻ ሳይሆን የሚበላም ነው። ውሃን የምናውቀው እንደሚጠጣ ነው፤ በልማድ ውሃ ይበላል አንልም፤ በሳይንሳዊ ጥበብ ግን ውሃ ይበላል። ልክ እንደ ግብጽ ላወቀበት ማለት ነው። ‹‹ውሃ እንዴት ይበላል?›› ሳይንሳዊ ማብራሪያ የሚያስፈልገው አይመስለኝም!

ዓባይ ዓባይ

ዓባይ ወንዛወንዙ

ብዙ ነው መዘዙ!

አዎ! የዓባይ ጉዳይ የባለቤቶች ብቻ አልሆነም። ከአውሮፓ እስከ እስያ፣ ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ እጃቸውን አስገብተውበታል። ሀገራት ተጣልተውበታል፤ ተወዳጅተውበታል። በዓለም አደባባይ ስሙ የተነሳባቸው አጋጣሚዎች ብቻ ናቸው። ዓባይ ጓዙም መዘዙም ብዙ ነው።

ዓባይ የወንዝ ውሃ አትሆን እንደሰው!

ተራብን ተጠማን ተቸገርን ብለው

አንተ ወራጅ ውሃ ቢጠሩህ አትሰማ

ምን አስቀምጠሃል ከግብጾች ከተማ?

ዓባይ ሰው አይደለም፤ እንዳደረጉት ይሆናል። ከገደቡት ይገደባል። በዚህ የጂጂ ስንኝ ውስጥ እንደ ሰው ታናግረዋለች። መልዕክቱ የሚነግረን ግን እኛም እንደ ግብጾች ማድረግ እንዳለብን ነው።

እጅጋየሁ ሽባባውም ሆነች ሌሎች ከያኒያን ዓባይን በጥበባቸው ገልጸዋል። ከእነዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የእረኞችና የገበሬዎች እንጉርጉሮዎች ቀድመው ዓባይን ተረድተውታል። ከዚህ የምንረደው ዓባይ ግብጽ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥም ሕይወት እንደነበር ነው። ከዚህ በኋላ ዓባይ የጥበብ ብቻ ሳይሆን የኃይልም ምንጭ ይሆናል!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You