“በሚመጣው ዓመት መጨረሻ አስራ ሶስቱም ተርባይኖች ሥራ ይጀምራሉ ” – አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) የሕዳሴው ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈፃሚ

በተለያዩ የዓለም ሴራዎች እና ከውስጥም ባሉ ሰፋፊ ችግሮች ሳቢያ ከድህነት ጋር ተጣብቃ የኖረችው ሀገር፤ ከመሠረቱ የሕዝቡን ሕይወት መቀየር የሚችል ብድር ይሰጠኝ በዓባይ ወንዝ ላይ ኃይል ማመንጫ ልገንባ ስትል ሴረኞቹ ከለከሉ። ርዳታቸው ሕዝቡ ቆሎ እየቆረጠመ እስከ ዓለም ፍፃሜ እንዲኖር በማሰብ ነውና፤ የማይጠቅም ርዳታ እና ብድር በመስጠት ኢትዮጵያ ዘመኗን በድህነት እንድትማቅቅ ምኞታቸው መሆኑን በተግባር አሳዩ። ይህ ከሆነ እነሆ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ተቆጠረ፤ ይህንን የተረዳ አብዛኛው የሀገሪቱ ሕዝብ እልህ ውስጥ ገብቶ ቆየ።

ለእዚህ ዘመን ከነዳጅ በላይ የሚያስፈልገው የኤሌክትሪክ ኃይል በመሆኑ እና ኢትዮጵያን ካለችበት ድህነት ለማላቀቅ ዋናው ጉዳይ ይህ ነው በሚል የወቅቱ መንግሥት በቀዳማይ ኃይለሥላሴ ዘመን የተዘጋጀውን የሕዳሴው ግድብን ለመገንባት ማቀዱን በ2003 ዓ.ም ይፋ አደረገ። የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በይፋ የመሠረት ድንጋይ አስቀመጡ። ዘመናትን በዕልህ ያሳለፈው የኢትዮጵያ ሕዝብ በደስታ አበደ። ርዳታ እና ብድር ቢከለከልም በራሳችን አቅም እንገነባለን ሲል ቃል ገባ። ቃሉንም በተግባር አሳየ።

እነሆ አሁን ይህ ሕልም የሚመስል ዕቅድ ተግባር ላይ ውሎ ፍሬ እንደሚያፈራ ታየ። አሁን ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ሥራ ለመጀመር ጫፍ ደርሷል። ይህን መሠረት በማድረግ ከሕዳሴው ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ጋር ያደረግነውን ቆይታ በሚከተለው መልኩ አቅርበንላችኋል መልካም ንባብ፡-

 አዲስ ዘመን፡- የዘንድሮውን መጋቢት 24 ለየት የሚያደርገው ምንድን ነው?

ዶ/ር አረጋዊ፡- ባለፉት 13 ዓመታት ብዙ ውጣ ውረዶች ነበሩ። ሕዝቡ ተነሳስቶ የልማት ሥራውን ለማገባደድ በቁርጠኝነት አስተዋፅኦ ሲያድግ ቆይቷል። በእነዚህ ዓመታት እስከ አስራ ዘጠኝ ቢሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብ አዋጥቷል፤ ከገንዘብ በተጨማሪ በጉልበት ሠርቷል። ከመደበኛው የዲፕሎማሲ ሥራ ጎን ለጎን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራ ላይ ሀገር ቤትም ሆነ ውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ብዙ ተንቀሳቅሷል። ይህ ራስን ለመለወጥ እና ሀገርን ለማልማት የሚያደርገው ጥረት መጨረሻ ላይ ግድቡን ለማጠናቀቅ አስችሎታል ማለት እንችላለን። የቀረው ጥቂት ብቻ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ይህም ቢሆን ግን ብዙ ግብዓትን የሚጠይቅ በመሆኑ፤ ቁርጠኝነቱን አሁንም መቀጠል አለበት።

ይህ የሕዳሴው ግድብ የቁጭት ልማት ነው። የሕዝቡ ቁጭት እና ቁርጠኝነት ከዳር ያደረሰው የሕዳሴው ግድብ የሚያስገኘው ጥቅም ሲታይ ደግሞ፤ ሕዝቡ የበለጠ የጋራ ልማት ምን ያህል እንደሚጠቅም በደንብ ያረጋግጣል። በዚህ በዓል ጽሕፈት ቤታችን ለሕዝቡ ምስጋና የሚያቀርብ ሲሆን፤ በቀጣይም በርታ ብሎ ከዚህ በኋላም ኢትዮጵያ የብዙ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ባለቤት በመሆኗ በእነዚህ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይም ተመሳሳይ ግድብ እንሰራለን። ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ሀገራትም የኤሌክትሪክ ኃይል ለማምረት መረባረብ አለበት የሚል ጥሪ እናቀርባለን።

አዲስ ዘመን፡- የሕዳሴው ግድብ አሁን በምን ደረጃ ላይ ነው?

አረጋዊ ዶ/ር፡- አሁን ያለበትን ደረጃ በተለያዩ ሚዲያዎች ሲገለጽ እንደነበር ይታወቃል። የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም ማጣት ችግርም ሆነ የኑሮ ውድነትን እና ሌሎችም ብዙ ችግሮች ቢያጋጥሙትም ተቋቁሞ ያለማቋረጥ ባደረገው አስተዋፅኦ አሁን ወደ 95 በመቶ ግድቡ ተጠናቋል ማለት ይቻላል። የሲቪል ኢንጂነሪንግ ሥራዎች ለማለቅ እጅግ ተቃርበዋል። ስለዚህ አሁን 98 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ አካባቢ ደርሷል።

ነገር ግን ኤሌክትሪካል እና መካኒካል ሥራዎች ትንሽ የተወሰነ ጊዜ ይጠይቃሉ። በዚህ ዓመት ቴክኒካል ሥራዎቹን በማቀላጠፍ አምስቱ ተርባይኖች ሥራ ይጀምራሉ የሚል ዕቅድ ይዘናል፤ ይሳካልናል ብለን እናምናለን። በቀጣይ ዓመት ደግሞ ቀሪዎቹ ተርባይኖች ሥራ እንደሚጀምሩ ኢንጂነሮቹ ዕቅዳቸውን በሪፖርት መልክ አቅርበዋል። ስለዚህ በሚመጣው ዓመት መጨረሻ አስራ ሶስቱም ተርባይኖች ሥራ ይጀምራሉ የሚል ተስፋ አለን። ያ ማለት በግድቡ ኃይል የማመንጨት ሥራችን ሙሉ ለሙሉ ስኬታማ ሆነ ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፡- ከዚህ በኋላስ የሕዝቡ ተሳትፎ ምን መምሰል አለበት ይላሉ?

አረጋዊ ዶ/ር፡- የገንዘብ ተሳትፎ አሁንም አስፈላጊ ነው። በእውነቱ ሕዝቡ ገንዘብ ማዋጣቱን አላቋረጠም። አሁን ግድቡ ላይ እየተገኘ ያለው ውጤት መመዝገብ የቻለው አንድም ሕዝቡ ድጋፉን ባለማቋረጡ ነው። ግድቡ ‹‹ሕይወቴን ይቀይርልኛል፤ ከርዳታ እና ከብድር ውጭ የሆነ የዕድገት ፈለግ እያሳየኝ ነው። ከብዙ ጫና ነፃ ያወጣኛል፤ የኢኮኖሚ ነፃነቴን ያጎናፅፈኛል፤›› ብሎ ስላመነ አሁንም ሕዝቡ ድጋፉን ቀጥሎበታል።

ግድቡ የሕዝቡ አንድነት የሚጠናከርበት ከመሆን ባሻገር፤ የገንዘብም ሆነ የሀብት ማከማቸት ጥቅምንም አሳይቷል። አሁንም የቦንድ ግዢም ሆነ ርዳታው እየቀጠለ ነው። ለምሳሌ አንድ ነጥብ አራት ቢሊየን ብር በዓመት ተሰብስቧል። በዚህ ስድስት ወር ደግሞ ካቀድነው በላይ እየተሰበሰበ ነው። ለምሳሌ በትንሹ በየጊዜው በ‹‹8100 A›› በስልክ ጥሪ በየወሩ ወደ 12 ሚሊየን ብር ይሰበሰባል። ይህ ገንዘብ ተጠራቅሞ ብዙ ይሆናል።

በቦንድ ግዢም ሆነ በስጦታ አስተዋፅኦ የማድረግ እንቅስቃሴው አሁንም ያለማቋረጥ እየቀጠለ ነው። የሚገርመው ሕዝቡ በብዙ ጫና ውስጥ ሆኖ ሳይቀር ለሕዳሴ ግድቡ ማዋጣቱን አላቋረጠም። ይህ በጣም አስደናቂ ነው። ስለዚህ ለቀጣይ ልማትም ሆነ ለእዚህ ግድብ መጠናቀቅ እና አዲስ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ለመድረስ ያለው ጉጉት እና ፍላጎት እንዲሁም ያለው ሀገራዊ ስሜት ትልቅ መሆኑን አይተናል። በጽሕፈት ቤታችን የሕዝቡ አስተዋፅኦ እጅግ የሚያስደስተን መሆኑን ለመግለፅ እወዳለሁ።

ግድቡ እስኪያልቅ ድረስ ሕዝቡ ተነስቷል። በዛ መንፈስ መቀጠል አለበት። ከዛ ቀጥሎ ግድቡን ማነፅ ቢያልቅም፤ ሌሎች ተያያዥ ሥራዎችም አሉ። የአካባቢ ጥበቃ ሥራ አለ። አካባቢውን በአረንጓዴ ልማት መሸፈን ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም። በአረንጓዴ ልማት መሸፈን ካልተቻለ ውሃው አፈሩን እየጠረገ ወደ ግድቡ ይገባና የግድቡን እድሜ ሊያሳጥረው ይችላል። ስለዚህ ግድቡ በደለል እንዳይሞላ የአካባቢ ጥበቃ ሥራው ላይ ጠንክሮ መሳተፍ የግድ ነው።

ሌላው የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ የመስመር ዝርጋታ እና የኃይል ማከማቻ ግንባታ ሥራ ነው። ኤሌክትሪክ በየገጠሩ መዳረስ አለበት። በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የገጠር አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ዝርጋታው መከናወን አለበት።

ከዚህ በኋላ በዋነኛነት መሠረታዊ ሥራዎች የሚባሉት የአካባቢ ጥበቃ ሥራውን ማካሔድ እና የዝርጋታ ሥራውን ማቀላጠፍ ነው። እነዚህ ሥራዎች ተያያዥ ናቸው። ስለዚህ ግድቡ ተጠናቀቀ ሲባል ሥራው አለቀ ማለት አይደለም። ለእነዚህ ሥራዎች ሕዝቡ አብይ አስተዋፅኦ እንዲኖረው ያስፈልጋል። ሌላው በዋናነት መዘንጋት የሌለበት ተፅዕኖዎች አሉ። የውጭውን ተፅዕኖ ለመከላከል ሕዝቡ አንድነቱን አጠናክሮ ማንኛውም የልማት ሥራ ሀገርን የሚጠቅም በመሆኑ የግድብ ግንባታም ሆነ የአረንጓዴ ልማት እንዲሁም ሌሎች ልማቶች እንዲፈፀሙ እና ሥራ ላይ እንዲውሉ ማድረግ ይጠበቅበታል።

አዲስ ዘመን፡- ግብፅ በተለያየ ጊዜ በተለያየ መልኩ የምታሳየው አቋም አለ። ስለግብፅ አቋም ምን ይላሉ?

አረጋዊ ዶ/ር፡– ግብፆች ኢትዮጵያ ራሷን እንድትችል እና የተፈጥሮ ሀብቷን እንድትጠቀም አይፈልጉም። ይህ በግልፅ መታወቅ አለበት። ምክንያታቸው ኢትዮጵያውያን ውሃ እና አፈራቸውን በአግባቡ መጠቀም ከጀመሩ እነርሱ የሚጎዱ ይመስላቸዋል። ሌላው የለመዱትን ነገር እንደሚያጡ እያሰቡ ስጋት ውስጥ ናቸው። አፈሩንም ሆነ ውሃውን ያለምንም ጠያቂ እንደፈለጉ ከመጠቀማቸው ብዛት ‹‹ውሃው የእኛ ብቻ ነው›› እስከ ማለት ደርሰዋል። ስለዚህ የቀኝ ግዛት አስተሳሰባቸው እና ስግብግብነታቸው አለቀቃቸውም።

በቅርቡ በተካሄደው ድርድርም የሶስትዮሽ ድርድር አንፈልግም ሲሉ እንደነበር ይታወሳል። ሌላ አካል መጨመር አለበት የሚል ሃሳብ እያቀረቡ ነው። ውሃው የራሳችን ሆኖ ሌላ ውሃው ላይ የማያገባው አካል ጣልቃ እንዲገባ መፈለጋቸው የሚገርም ነው። ውሃው 86 በመቶ የሚሆነው የሚነሳው ከኢትዮጵያ ነው። ያም ቢሆን እኛ ብቻችንን እንጠቀም አላልንም። አብረን እንጠቀም፤ አብረን እንልማ ብለናል። ‹‹አብረን ተባብረን ካለማን ከራሳችን አልፈን ለሌሎችም መትረፍ እንችላለን›› ብለን ብናስረዳቸውም አልገባ ብሏቸዋል። ከተጠናወታቸው የስስት አስተሳሰብ ሊወጡ አልቻሉም።

ግብፆች ሌሎች እነርሱን የሚደግፉ ኃይሎችን በማካተት ተፅዕኖ ለመፍጠር ይሞክራሉ። በዓለም ደረጃ እንደሚታወቅው ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ብድር እንዳታገኝ አድርገዋል። በርግጥ እነርሱ መጥፎ አስበው ይህንን ቢፈፅሙትም በአንድ በኩል ይህንን መፈፀማቸው ለእኛ ጥሩ ሆኗል። ምክንያቱም ራሳችን ተፍጨርጭረን በአፍሪካ ትልቁን በዓለም ደግሞ ትልቅ ናቸው ተብለው ከሚጠቀሱ አስር ግድቦች መካከል አንዱን መሆን የሚችል ግድብ በራሳችን አቅም ገንብተናል። ይህ ለእኛ ከዚህ በፊት ያልሞከርነው እና ያላገኘነው ትልቅ ትምህርት ሰጪ ሆኗል።

በራሳችን ዕውቀት፣ በራሳችን ጥረት፣ በራሳችን ጉልበት እና በራሳችን ገንዘብ ማደግ እንደምንችል አረጋግጠናል። እነርሱ ክፉ ቢያስቡም እኛ መልካም ሆኗል። በርግጥ ግብፆች አሁንም ዝም አይሉም። ነገር ግን እንዲያውም በእዚህ ግድብ ላይ አስተዋፅኦ ቢያደርጉ፤ የምናደርገውን የአረንጓዴ ዘመቻን ቢደግፉ የተሻለ ዘላቂና ቀጣይ የሆነ ተጠቃሚ ይሆኑ ነበር። ተርባይኖቹ ውሃውን አያቆሙትም፤ ሥራቸው ኃይል አመንጭተው ማለፍ ነው። ይህ ገብቷቸው ቢተባበሩ ለእነርሱም ይጠቅማቸዋል። አሁንም በእኛ በኩል ያለው አቋም ተመሳሳይ ነው። ግብፆች የተለያዩ መንገዶችን እየተጠቀሙ አፍራሽ ሃሳባቸውን ከሚያራምዱ በወንድማማችነት አብሮ ስለማደግ ቢያስቡ ይሻላቸዋል የሚል እምነት አለኝ።

አዲስ ዘመን፡- በተደጋጋሚ ከሚያነሷቸው አስገራሚ ሃሳቦች መካከል አንደኛው እኛ ገብተን የግድቡን ሁኔታ እንቆጣጠር የሚል ነው። እዚህ ላይ ምላሾት ምንድን ነው?

አረጋዊ ዶ/ር፡- እነርሱማ ከዚህ የሚመነጨውን ውሃ የእኛ ነው እስከ ማለት የደረሱ ናቸው። ስለዚህ ውሃው የእኛ ነው ካሉ፤ ግድቡንም ገብተው ለመቆጣጠር ማሰባቸው አያስገርምም። ይህ ሃሳብ አሁን የጀመሩት ሃሳብ አይደለም። ድሮ ገና በ640 ዓ.ም የባህር በራችን አዶሊስ እያለ በአዶሊስ በኩል መጥተው ጦርነት ከፍተዋል። ጦርነቱን ያካሔዱበት ምክንያት በአዶሊስ በኩል ገብተው የዓባይን ምንጭ ለመቆጣጠር ተመኝተው ነበር። ነገር ግን ክፉኛ ሊረሱት በማይችሉበት መልኩ ተመተው ተሸንፈው ተመልሰዋል።

ከዛ ሽንፈታቸው በኋላ ግን ግብፆች አንዴ ከተሸነፉ በኋላ በቀጥታ ራሳቸው ለውጊያ አልመጡም። ነገር ግን በተዘዋዋሪ በተላላኪዎቻቸው አማካኝነት ኢትዮጵያ ውስጥ ግርግር እንዲፈጠር፣ ሀገር እንድትተራመስ እና ገብተው ቁጥጥር እንዲደረግ ብዙ እየሠሩ ናቸው። አቅም አጥተው እንጂ ወረራም ከማካሔድ ወደኋላ አይሉም ነበር። ስለዚህ ሙሉ ለሙሉ ውሃውን ለመቆጣጠር ያላቸው ዕቅድ እስከ አሁን የባዕዳን አገዛዝ አስተሳሰብ እንደተጠናወታቸው መቀጠሉን የሚያሳይ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ከግብፆች ወደ ራሳችን እንመለስ እና በርግጥ የሕዳሴው ግድብ ቱርፋቱ ምንድን ነው?

አረጋዊ ዶ/ር፡– የእዚህ ግድብ ጥቅም ሲነሳ የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ሕይወት የሚነካ ነው። አንደኛ የሚያመነጨው ኃይል እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ያላገኙ ሰዎች ኤሌክትሪክ የማግኘት ዕድል ይኖራቸዋል። ገጠር ኤሌክትሪክ ከገባ ሕዝቡ ከጨለማ ይወጣል። የገጠር ሕዝብ ከጨለማ ከወጣ ቀን ብቻ ሳይሆን ማታም ሥራ መሥራት ይችላል። ለገጠሩ ሕዝብ ማረሻ እና ማጨጃን ጨምሮ ሌሎችም ቀን እና ሌሊት መሠራት ያለባቸውን ሥራዎች ለመሥራት ያስችላል።

የኤሌክትሪክ ኃይል በቅርብ መኖር መሬትን ለማልማትም ሆነ ሕዝብ የሚፈልገውን ቁሳቁስ ለማሟላት ያስችላል። የሥራ ዕድልም ይፈጠራል። ስለዚህ ጥቅሙ ሰው እየገባው ነው። የኤሌክትሪክ ኃይሉን ሽያጭ ላይ በማዋልም የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ያስችላል። እኛ ያላመረትናቸውን መድኃኒት እና ሌሎችም እጅግ ወሳኝ የሆኑ ምርቶችን እና የተለያዩ ግብዓቶችን የመሳሰሉ ከውጭ የሚገቡ ነገሮችን ለመግዛት የውጭ ምንዛሪ የምናገኝበት ሁኔታ ይኖራል። የሚያስፈልገንን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ይረዳል ማለት፤ ራሳችንን ችለን የማንንም ርዳታ እና ብድር ሳንጠብቅ ማደግ እንችላለን ማለት ነው። ይህ በመላው ሕዝብ ላይ በጎ ተፅዕኖ አለው። ይህ ፕሮጀክት ትልቅ ነው በሚል በሁሉም የሚደገፈው፤ ለእዚህ ነው። አዲስ የኢኮኖሚ ግንባታ የራስን አቅም በነፃነት በመጠቀም ቀጣይነት ያለው ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- በዓድዋ ድል ለመላው አፍሪካውያን ሞዴል መሆን ችለናል። በተመሳሳይ መልኩ ከሕዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ለሚመጣው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ሞዴል በመሆን በኩል የሚኖረን አስተዋፅኦ ምን ያህል ነው?

አረጋዊ ዶ/ር፡- እስከ አሁን ድረስ በዓለም ተዘርግቶ ያለው የኢኮኖሚ መስተጋብር ድሮ ቀኝ ገዢዎች ባሰመሩት መሥመር ላይ የተመሠረተ ነው። ለታዳጊዎች እንሠራለን፤ እንደግፋለን ይላሉ፤ ነገር ግን ውሸት ነው። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት ጀምሮ ኢትዮጵያ ርዳታ እና ብድር ታገኛለች። ነገር ግን ከድህነት እና ከብድር ከርዳታ አልወጣችም። ለምን የሚለውን ጥያቄ ማንሳት አለብን። ምክንያቱም የሚሰጡን ርዳታም ሆነ ብድር አንቆ የሚይዝ ገመድ አለው።

በኃያላኑ መንግሥታት ቤት ነፃ ምሳ የለም። ርዳታም ሆነ ብድር የሚሰጡን በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ ለእነርሱ ብድር ወለድ እየከፈልን፤ ለርዳታቸውም እጅ እየነሳን እጃችን ተጠምዝዞ እንዲኖር እያደረገን ነው። ከዚህ ታግለን ነፃ መውጣት አለብን። የእዚህ ግድብ ታላቅነት የሚገለፀው በዚህ መልኩ ነው።

ብዙ የአፍሪካ ሀገሮች በዚህ ገመድ የታሰሩ ናቸው። አፍሪካውያን የማናድገው ለእዚህ ነው። የባዕዳን አገዛዝ ከተወገደ በኋላ የሆነው ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች ሀገሮች ነፃ ሀገር ቢባሉም የፖለቲካ ነፃነት እንጂ የኢኮኖሚ ነፃነት የላቸውም። ኢኮኖሚው የባዕድ አገዛዝ እንደነበረው በዛው ቀጥሏል። አሁንም በተዘዋዋሪ መንገድ ብዝበዛቸው ቀጥሏል። ጣሊያን ኢትዮጵያን እንዲገዛ እነርሱም ብዝበዛቸውን እንዲቀጥሉ መላው ቀኝ ገዢዎች ሲደግፏቸው ቆይተዋል። ቁጥጥራቸው እንዲቀጥል በዓለም ላይ ጦርነት አቅደው ነበር። ኢትዮጵያ ላይ የተካሔደው ዘመቻም ሆነ ኢትዮጵያን ለማንበርከክ የሠሩት ሥራ ስኬታማ መሆን አልቻለም። ምክንያቱም ሕዝቡ በአንድነት ተሳትፎ፤ ዓድዋ ላይ ዘምቶ ጣሊያንን ድል መታ።

መሸነፋቸው ቀኝ ገዢዎችን በሙሉ በጣም አስቀይሟል። ነጮች ያንን ታሪክ ለመቀልበስ ብዙ ጥረት አድርገዋል። የአፍሪካ ሀገሮች ከዚህ ትምህርት ብዙ ወስደዋል። ታግለው አባርረዋል። ነገር ግን አሁንም ቢሆን መርሳት የሌለብን የኢኮኖሚ ነፃነታቸውን ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ ነፃነታችንን አልተጎናጸፍንም።

ስለዚህ ይህ ግድብ ያለ እነርሱ ዕርዳታ እና ብድር ተጠናቆ ፍሬ ሲያፈራ፤ ለአፍሪካውያን እና ለመላው ያላደጉ ሀገሮች በጣም ትልቅ ትምህርት ይሆናል። ሀገራት የፖለቲካ ነፃነታቸውን ማግኘትን በተመለከተ ከኢትዮጵያውያን ከዓድዋ እንደተማሩት የኢኮኖሚ ነፃነትን በተመለከተም፤ ከዚህ ግድብም ሊማሩ ይችላሉ። የኢኮኖሚ ነፃነታቸውንም በምን መልክ ሊጎናፀፉ እንደሚችሉ ያስባሉ።

እናም የሕዳሴው ግድብ እንድምታው አንድነትን ያጠናክራል። አንድ ሆነን ከተነሳን ያለንን ችግር በቀላሉ መፍታት እንችላለን የሚለውን አስተሳሰብ ያሰርፃል። ነገር ግን ከሕዳሴው ግድብ በተጨማሪ አሁንም ሆነ በቀጣይ በአንድነት ለመሥራት መነሳት አለብን። አንድ ሆነን ካልተነሳን ግን ችግሮቹ እንዳሉ ይቀጥላሉ።

አዲስ ዘመን፡- የሕዳሴው ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የሕዳሴው ግድብ እንዲገነባ የተቋቋመ ነው። የሕዳሴው ግድብ ደግሞ ሊጠናቀቅ ከጫፍ ደርሷል። ከተጠናቀቀ እና አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ጽሕፈት ቤቱ ዕጣ ፈንታው ምንድን ነው?

አረጋዊ ዶ/ር፡- ይህ ጽሕፈት ቤት ለሕዳሴው ግድብ መገንባት የተቋቋመ ቢሆንም፤ ግንባታው ካለቀ በኋላ ሥራው ምን ይሆናል የሚለው በብዙ ሰዎች ውስጥ ጥያቄ ነው። ነገር ግን ብዙ ሥራዎች አሉበት። ኢትዮጵያ ከዘጠኝ ያላነሱ ድንበር ተሸጋሪ ወንዞች አሏት። እነዛ ወንዞች ልጓም አላደረግንባቸውም፤ እንዲሁ እየፈሰሱ ነው። ስለዚህ እነዛ ላይም ትላልቅ የሕዳሴ ግድብን የሚያክሉ ወይም ተመሳሳይ ግድቦችን መሥራት እና ሀገር ማልማት ይጠበቅብናል። ስለዚህ አንዱ ትልቁ ሥራ ይህ ነው። ሌላው ከላይ እንደገለፅት ጽሕፈት ቤቱ የአካባቢ ጥበቃ ሥራንም ይሠራል።

አካባቢውን በደን ማልበስ ያለበለዚያ በደለል ምክንያት ግድቦቹ የሚኖራቸው አጭር ዕድሜ ነው። አካባቢዎቹ በደን ካልተሸፈኑ እና ወደ ግድቦች የሚገባው ውሃ ንፁህ ካልሆነ ደለል እየሞላ አገልግሎታቸው አጭር ይሆናል። ይህንን የመሳሰሉ ብዙ ሥራዎች ስላሉ ጽሕፈት ቤት እነዚህን ታሳቢ አድርጎ ዝግጅት እያደረገ ነው።

ተሞክሮዎችም ማሰባሰብ እና ወደ ሌላ የሥራ መስክ እና ወደ ሌላ ወንዞች ምልከታ እንዲደረግ የሚሠራበት ሁኔታ ይኖራል። አሁንም ለሚመለከታቸው አካላት እያሳሰበ ነው። በቅርቡ ከሥራ አስፈፃሚው አካል ጋር በነበረን ግንኙነት ይህ ነገር ተነስቶ ጥናት እንዲቀርብ አቅጣጫ ተሰጥቷል። ስለዚህ የጽሕፈት ቤቱ ሥራ እንዲሁ የሚቆም አይደለም።

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ አመሰግናለሁ።

ዶ/ር አረጋዊ፡– እኔም በጣም አመሰግናለሁ።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You