የስፖርቱ ዘርፍ ከዓባይ ግድብ ምን ይጠብቃል?

በርካታ የስፖርት አይነቶች በተለያዩ ሀገራት የሚፈጠሩት እንደ የአካባቢው መልክአ ምድር፣ እምቅ አቅም፣ ባህልና ልምድ ወዘተ መነሻ አድርገው ነው። እንደ አፍሪካ ባሉ ሀገራት ዘመናዊ ስፖርቶች የተዋወቁት ግን ከዚህ በተለየ መንገድ በብዛት ከቅኝ ግዛት ታሪክ በተገናኘ ነው። በኢትዮጵያም ዘመናዊ ስፖርቶች በብዛት የተዋወቁትና የተስፋፉት ከፋሽት ጣሊያን ወረራ እንዲሁም ከፈረንሳዮች ጋር በተገናኘ መሆኑን የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ በውሃ ሀብት የታደለች ሀገር ብትሆንም እንደ ሀገር የሚዘወተሩ የውሃ ስፖርት አይነቶች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው ለማለት እንኳን የሚያስደፍሩ አይደሉም። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታወቀውና የሚዘወተረው የውሃ ስፖርት አይነት በተለያዩ ሆቴሎች በትንንሽ ገንዳዎች ውስጥ የሚከናወኑትና በኦሊምፒክ መድረኮች በኮታ የምንሳተፍባቸው ብቻ ናቸው። ለዚህ ደግሞ አንዱ ምክንያት ተደርጎ የሚቆጠረው በሌሎች ሀገራት የሚዘወተሩ የውሃ ስፖርቶች የሚፈልጉት ምቹ የውሃ አካል አለመኖር ሊሆን ይችላል። በበርካታ ሀገራት የውሃ ስፖርቶች አይነታቸው ቁጥር ስፍር የለውም። በውሃ አካላት ላይ እና ውስጥ ተከፋፍለው የሚካሄዱ የስፖርት አይነቶች ብቻ ተቆጥረው የሚያልቁ አይደሉም።

ከ250 ኪሎ ሜትር በላይ የሚንጣለለው የዓባይ ግድብ ሌላውን ትተን በውሃ አካላት ላይ የሚካሄዱ ነገር ግን በኢትዮጵያ ተሞክረው የማያውቁ በትንሹ ከሃያ የማያንሱ የውሃ ስፖርቶች እንዲፈጠሩ የማድረግ አቅም ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል። በበርካታ ሀገራት ከተለመደው የተለያዩ የጀልባ አይነቶች ውድድር አንስቶ በውሃ ውስጥና ላይ እስከሚከወኑ በርካታ ፉክክሮችን መፍጠር ይቻላል። ከዚህ ባሻገር ሌሎች በግልና በቡድን የሚካሄዱ የመዝናኛና የውድድር የውሃ ስፖርቶችን መፍጠር የሚቻልበት እድል ጠባብ እንደማይሆንም እንደ ዓባይ አይነት ግዙፍ ግድቦችን የገነቡ ሀገራትን ተሞክሮ መቅሰም ይችላል።

በታላቁ የስፖርት መድረክ ኦሊምፒክ ውድድርና ፉክክር የሚካሄድባቸው የውሃ ስፖርቶች አንድና ሁለት አይደሉም። (swimming, diving, water polo, rowing, sailing, canoe flat­water, canoe slalom, artistic swimming, marathon swim­ming, and surfing)በስፋት የሚታወቁ የኦሊምፒክ ስፖርቶች ናቸው። የዓባይ ግድብ እነዚህ ስፖርቶች በኢትዮጵያ እንዲፈጠሩ ሊያደርግ ይቻለዋል። ከነዚህ ስፖርቶች የተወሰኑት ላይ እንኳን ጥናት አድርጎ በሂደት እንዲለመዱና እንዲዘወተሩ ማድረግ  የሚቻልበት እድል ዝግ አይሆንም። ሁሉም ነገር መነሻ ይኖረዋል፣ መቼም በነዚህ ስፖርቶች አሁን ላይ በኦሊምፒክና በሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች ወርቅ የሚያፍሱ ሀገራት ዛሬ ለትልቅ ደረጃ የበቁት ከስፖርቶቹ ጋር አብረው ስለተፈጠሩ አይደለም። በሆኑ አጋጣሚዎችና ሁኔታዎች ስፖርቶቹን ተላምደው፣ አጎልብተውና ሰርተውበት ነው ለትልቅ ደረጃ የበቁት። እኛም አዳዲስ ስፖርቶችን ከመሞከር የሚከለክለን ነገር የለም። ካለመሞከር መሞከር ሁሌም የተሻለ ነውና።

መጀመሪያ እኛ ካለን አቅምና ሁኔታዎች ተነስቶ በጥናቶች ላይ በመመርኮዝ ስፖርቶቹን ማስተዋወቅ፣ በሂደትም የማላመድና የማጎልበት ብሎም በፕሮፌሽናል ደረጃ ማምጣት በቀጣይ የሚታይ ጉዳይ ይሆናል።

እንደ አሜሪካ ያሉ ሀገራት በኦሊምፒክ በርካታ ወርቆችን ጠራርገው የሚወስዱት በውሃ ስፖርቶች ነው። አንድ የውሃ ዋና ተወዳዳሪ ብቻ ስምንት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በአንድ ኦሊምፒክ ጠራርጎ የወሰደበት አጋጣሚ እዚህ ጋር ምሳሌ ተደርጎ ሊጠቀስ ይችላል። ያደጉት ሀገራት ያም አልበቃ ብሏቸው ዳንሶቻቸውን ጭምር በኦሊምፒክ ስፖርት እንዲካተቱ ማድረግ በኦሊምፒክ የሚሰበስቡትን የሜዳሊያ ቁጥር ለመጨመር ሌት ከቀን መስራት ከጀመሩ ሰነባብተዋል።

ኢትዮጵያ በሌሎች በተለመዱና ለረጅም ዓመታት በሚዘወተሩ ስፖርቶች ውጤታማነት ላይ ያልተመለሱ ብዙ ጥያቄዎች ቢኖሩም አዳዲስ ነገሮችን መሞከሩ ክፋት የለውም። በእጃችን ያሉትን ተጠቅመን ውጤታማ አልሆንም ማለት በአዳዲስ ነገሮች አይሳካልንም ማለት አይደለም። ማን ያውቃል ምናልባትም አብረውን ከከረሙት ይልቅ በአዳዲሶቹ ተክነን እንገኝ ይሆናል። ይህም በአትሌቲክስ፣ ቦክስ፣ ብስክሌት ወዘተ ብቻ ተወስኖ ዘመናትን የተሻገረውን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ተሳትፎ በሂደት ወደ ተጨማሪ ስፖርቶች ለማሳደግ በር ይከፍታል ብሎ ማሰቡ የዋህነት ሳይሆን ብልህነት ነው። ዛሬ ላይ ይህ ለብዙዎች ላይመስልና ላይዋጥ ይችላል፣ ነገር ግን ሁሉም ነገር ከትንሽ ተጀምሮ ወደ ትልቅ ደረጃ እንደሚያድግ ፈላስፋ መሆንን አይጠይቅም።

ይህን በሃሳብ ደረጃ ይዞ በባለሙያዎች ጥናት በማስደገፍ ነገን አርቆ መመልከት የሀገሪቱን ስፖርት በበላይነት ከሚመሩ አካላት ይጠበቃል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ የስፖርት ትንሳኤ

የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበት የዓባይ ግድብ ከ13 ዓመታት የግንባታ ሂደት በኋላ ዘንድሮ ይጠናቀቃል። ግድቡ የኢትዮጵያውያን የዘመናት ጥያቄ ሲመልስ የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ብቻ አይደለም። ብዙ በረከቶችንም ይዞ እንደሚመጣ ይጠበቃል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ከጨለማ ህይወት እንደሚያወጣው ሁሉ በጨለማ ለሚጓዘው የኢትዮጵያ ስፖርትም የራሱን በረከቶች ይዞ እንደሚመጣ ማሰቡና በዚያው ልክ መዘጋጀቱ ተገቢ ይሆናል።

ግድቡ ከኃይል ማመንጨት ባሻገር የሚኖረው ትልቅ ጥቅም ከቱሪዝም ጋር የተያያዘ እንደሚሆን ቀደም ሲል ተነግሯል። ለዚህም መንግሥት ምቹ የቱሪዝም መስህቦችን በአካባቢው ለመፍጠር የተለያዩ ንድፎችን እንደሚያዘጋጅ ይፋ አድርጎ ነበር። የግሉ ባለሀብትም አካባቢውን በማልማት ሊፈጥር የሚችለው ልዩ የቱሪዝም መዳረሻ በጉጉት የሚጠበቅ ይሆናል። ይህ ደግሞ ግድቡ ለተገነባበት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገርም ለስፖርቱ እድገትና ለውጥ የራሱን ጠጠር እንደሚጥል መገመት አይከብድም።

የዓባይ ግድብ የተሠራበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከዚህ ቀደምም ይሁን አሁን በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ከፍ አድርገው በኩራት ያውለበለቡ በርካታ ከዋክብት የፈለቁበት ነው። ያምሆኖ ክልሉ አሁንም ድረስ በስፖርት መሠረተ ልማቶች እዚህ ግባ የሚባል ነገር የለውም። ይህም ክልሉ ያለውን የስፖርት እምቅ አቅም በተገቢውና በሚፈለገው መንገድ አውጥቶ እንዳይጠቀም አንዱ እንቅፋት እንደሆነ በድፍረት መናገር ይቻላል።

ያምሆኖ አሁንም ድረስ ከዋክብት ስፖርተኞች በራሳቸው ልፋትና ጥረት ከዚያ ክልል ተነስተው በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ስም እየገነቡ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ስትመለስ የዋልያዎቹ ወሳኝ የአጥቂ መስመር ተጫዋች የነበረው ሳላዲን ሰዒድ መነሻው ከዚሁ ክልል አዋራማ ሜዳዎች ነበር።

ሳላዲን ወርቅ ከሚፈልቅበት ክልል ተነስቶ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ተፅእኖ በመፍጠር ስሙን በወርቅ ቀለም የፃፈ ኮከብ ነው። ሳላዲን በዚህ ደረጃ የሚጠቀስ በክልሉ ብሎም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ይቀመጥ እንጂ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ዛሬም ድረስ በርካታ ሳላዲኖች መኖራቸውን ወደ ስፍራው ተጉዞ መንገድ ዳር በአዋራማ ሜዳዎች ኳስ ሲያንከባልሉ የሚውሉ ታዳጊዎችን መመልከት በቂ ነው።

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ በእግር ኳስ ብቻ አይደለም የታደለው፣ በአትሌቲክሱም ከኦሊምፒክ እስከ ዓለም ቻምፒዮና ብሎም እስከ አፍሪካ ጨዋታዎች በወርቅ የደመቁ ከዋክብት የፈሩበት ስፍራ ነው። ኢትዮጵያ በ2016 የሪዮ ኦሊምፒክ አንድ የወርቅ ሜዳሊያ ብቻ ስታስመዘግብ በባዶ እጅ ከመመለስ የታደገችን ወርቃማዋ አትሌት አልማዝ አያና የዚሁ ክልል ፍሬ ነች። አልማዝ ሪዮ ኦሊምፒክ ላይ በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ስታጠልቅ ለ23 ዓመታት ያልተደፈረውን የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን በመንካት ጭምር ነው። በዚያው ኦሊምፒክ በ5ሺ ሜትር ሌላ ወርቅ ለማጥለቅ ተቃርባም ለጥቂት ነበር የብር ሜዳሊያ አሸናፊ የሆነችው። አልማዝ ከኦሊምፒክ ባሻገር ከዓለም ቻምፒዮና እስከ የግል የማራቶን ውድድሮች አሁንም ድረስ የኢትዮጵያ ኩራት የሆነች አትሌት ነች።

የአልማዝን ፋና ተከትላ በቅርቡ በአትሌቲክሱ ዓለም ገናና ስምና ዝና እየገነባች የምትገኘው ኮከብ አትሌት ፅጌ ዱጉማም ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ማህፀን የወጣት ናት። ይህች ጥቁር እንቁ ዘንድሮ ግላስጎው በተካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የ800 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ በማስመዝገብ ክልሉ ከረጅም እስከ አጭር ርቀት ሩጫ ትልቅ አቅም እንዳለው በተግባር አረጋግጣለች። ከዚህ ታሪካዊ ድሏ ከሳምንታት በኋላ ወደ ጋና አክራ ፊቷን በመመለስ በአፍሪካ ጨዋታዎች በርቀቱ ያስመዘገበችው የወርቅ ሜዳሊያም የቅርብ ጊዜ ትውስታና ሌላ ታሪክ ነው።

ከእግር ኳስ እስከ አትሌቲክስ የጀገኑ እነዚህ አትሌቶች ከቤኒሻንጉል ክልል የተገኙት በራሳቸው ልፋትና ጥረት እንጂ በተመቻቸ መንገድ ተጉዘው አይደለም። ክልሉ አሁንም ድረስ ያለውን የስፖርት አቅም አውጥቶ እንዲጠቀም የሚያግዙ መሰረተ ልማቶች የሉትም። በግልም ይሁን በመንግስት ስር የሚገኙ የተለያዩ የስፖርት ክለቦችንም ፈልጎ ማግኘት አዳጋች ነው። በአሶሳ ከተማ የተጀመረው ትልቅ ስቴድየም እንኳን ለአስራ አምስት አመታት ግንባታው የት እንደደረሰ ዛሬም ድረስ በግልፅ የሚታወቅ ነገር የለም።

ስፖርት የሚያድገውና የሚስፋፋው በከተማ ነው። ከተሞች ባደጉ ቁጥር የስፖርት መሰረተ ልማቶች ብሎም የስፖርት ክለቦች እያደጉ መሄዳቸው የማይታበይ ሀቅ ነው። የዓባይ ግድብ መጠናቀቅ እንደ ሀገር ይዞ የሚመጣው ፋይዳ እንዳለ ሁሉ ግድቡ የሚገኝበትን ክልል በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ማሳደጉ እንደማይቀር ከወዲሁ መገመት አያዳግትም። ክልሉ አደገ፣ ከተሞች ተስፋፉ ማለት ደግሞ ስፖርቱም የእድገቱ ተቋዳሽ የሚሆንበት እድል ጠባብ አይደለም። ይህም በተመቻቹና ዘመናዊ በሆኑ መንገዶች ብዙ ሳላዲን ሰኢዶችን፣ በርካታ አልማዝ አያናዎችን ማፍራት የማይቻልበት ምክንያት እንደማይኖር ከተስፋም የዘለለ ትርጉም ይኖረዋል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You