ከሁለት ዓመት በፊት የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮናን ያዘጋጀችው የሰርቢያ መዲና ቤልግሬድ ሌላኛውን አትሌቲክስ ውድድር አዘጋጅነት ያገኘችበትን የዓለም ሀገር አቋራጭ ቻምፒዮና በስኬት አጠናቃለች። በአንድ ቀን ውድድሩ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ሀገራትም ወደየሀገራቸው በመመለስ ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆነውና በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ደረጃን መያዝ የቻለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድንም ዛሬ ማለዳ ሀገሩ ይገባል።
እጅግ ከባድ ከሚባሉና በፈተና ከተሞሉ ውድድሮች መካከል አንዱ በሆነው ሀገር አቋራጭ ውድድር የምሥራቅ አፍሪካ አትሌቶች ሁሌም የተሻለ ውጤታማ ይሆናሉ። ከትናንት በስቲያ በተካሄደው 45ኛው ቻምፒዮና ላይም የኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ አትሌቶች በተለመደው የበላይነት ውድድራቸውን አጠናቀዋል። ከውድድሩ አስቀድሞ በረጅም ርቀት ሩጫ የተካኑት እነዚሁ ሀገራትና አትሌቶቻቸው የአሸናፊነት ግምት አግኝተው እንደነበረ ይታወሳል። በዚህም መሠረት በርካታ ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ የዓለም ሀገራት ቻምፒዮና የሆነችው ኬንያ በአምስቱ ውድድሮች 6 የወርቅ፣ 2 የብር እና 3 የነሐስ በጥቅሉ 11 ሜዳሊያዎችን አስመዝግባለች። ኢትዮጵያ ደግሞ 2 የወርቅ፣ 6 የብር እና 2 የነሐስ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎችን አግኝታለች። 1 የወርቅ፣ 1 የብር እና 3 የነሐስ ሜዳሊያዎችን ያገኘ ችው ኡጋንዳ ደግሞ በ5 ሜዳሊያዎች ሦስተኛውን ደረጃ ልትይዝ ችላለች።
ቻምፒዮናው ከ20 ዓመት በታች የ6 ኪሎ ሜትር ሴቶች ውድድር የተጀመረ ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በሚታወቁበት አረንጓዴው ጎርፍ አጨራረሳቸው የበላይነቱን ለመያዝ ችለዋል። ኢትዮጵያዊያን እና የኬንያ አትሌቶች እየተፈራረቁ ሲመሩት በነበረው ውድድር ከ800 ሜትር በኋላ የውድድሩ አሸናፊ የሆነችው ወጣቷ አትሌት ማርታ አለማየሁ የሀገሯን ልጆች አስከትላ በመግባት የወርቅ ሜዳሊያውን አጥልቃለች። ርቀቱን ለመሸፈን 19:28 የሆነ ሰዓት የፈጀባት አትሌት ማርታ አሸናፊ ለመሆን እንደሮጠች ከውድድሩ በኋላ ተናግራለች። ከዓለም አትሌቲክስ ጋር በነበራት ቆይታ ‹‹ጠንካራ ዝግጅት ስናደርግ በመቆየታችን፤ የሮጥኩት ለማሸነፍ ነበር። ከአሸናፊነቴ በላይ ግን ውድድሩ ለቀጣይ የሩጫ ህይወቴ ከፍተኛ ሚና አለው›› ስትል ተናግራለች።
ላለፉት 29 ዓመታት የምሥራቅ አፍሪካ አትሌቶች ብቻ እየተፈራረቁ ከ1 እስከ 10 ባለው ደረጃ በሚወጡበት የወጣቶች ውድድር፤ በሴቶች 6ኪሎ ሜትር ሩጫ ኢትዮጵያዊያኑ አሳየች አይቸው እና ሮቤ ዲዳ በጥቂት ሰከንዶች ልዩነት ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።
ቀጣዩ ውድድር የወጣት ወንዶች 8ኪሎ ሜትር ሩጫ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ኬንያዊያን እና ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ቀዳሚዎቹን 10 ደረጃዎች ይዘዋል። እጅግ ጠንካራ ፉክክር በታየበት በዚህ ውድድር ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች በድጋሚ የወርቅ ሜዳሊያን ለማስመዝገብ ቢጥሩም በኬንያዊው አትሌት ሳሙኤል ኪባዚ የአንድ ሰከንድ ብልጫ ተወስዷል። ብርቱ ትግል ሲያደርግ የነበረው መዝገቡ ስሜ 22ደቂቃ ከ41 ደቂቃ በሆነ ሰዓት የብር ሜዳሊያውን አሳክቷል።
ቀጣዩ ውድድር ድብልቅ ሪሌ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ቀጣዩን የብር ሜዳሊያ ያገኘችበትም ነው። ከምሥራቅ አፍሪካ አትሌቶች ባሻገር እንግሊዛዊያንም ጠንካራ ፉክክር ባደረጉበት በዚህ ውድድር ለአሸናፊነት ከነበረው ትንቅንቅ በላይ ከፍተኛ ትኩረት አግኝቶ የነበረው የኢትዮጵያዊቷ አትሌት ተጋድሎ ነበር። አትሌት ብሪ አበራ በቅብብል ወቅት በደረሰ አጋጣሚ የአንድ እግር ጫማዋ ቢወልቅባትም ባዶ እግሯን በመሮጥ ሜዳሊያው ለኢትዮጵያ ገቢ እንዲሆን አስደናቂ ተግባር አሳይታለች። ከኬንያ ቡድን 28 ሰከንዶች ዘግይቶ የገባው ቡድኑ ምናልባትም አጋጣሚው ባይፈጠር የወርቅ ሜዳሊያው የኢትዮጵያ የሚሆንበት እድል ሰፊ መሆኑ ግልጽ ነው።
እጅግ ተጠባቂው የአዋቂዎች 10 ኪሎ ሜትር በተለይ የኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ አትሌቶች ትንቅንቅ ከፍተኛ ትኩረት አግኝቶ ነበር። በዚህም የአምናው አሸናፊ ጃኮብ ኪፕሊሞ እና በሪሁ አረጋዊ በድጋሚ በሰከንዶች ልዩነት ተቀዳድመው ገብተዋል። በሴቶች መካከል በተካሄደው የአዋቂዎች ውድድር ግን ኢትዮጵያ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ልትካተት አልቻለችም።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም