ኢትዮጵያውያን ለ13 ተከታታይ ዓመታት አልሰለቹም፤ አልታከቱምም። ድካማቸውም ሆነ ልፋታቸው ከንቱ ሆኖ አልቀረም። አንዴ “ተሸጠ” ሌላ ጊዜ ደግሞ “እንዳይገነባ ተከለከለ” እየተባለ የኢትዮጵያውያኑ እድገትና ልማት ጠል በሆኑ አካላት ሲነገርበት የነበረው ሟርት ከሽፎ የተደከመለት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድ እውን ሆኖ ተከስቷል። ኢትዮጵያውያኑ ከወራት በኋላም ጆሯቸው ሲናፍቅ የነበረውን የ’ተጠናቀቀ’ ዜና ለመስማት ተቃርበዋል።
የሕዳሴ ግድቡ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያውያኑ ትርጉሙ ብዙ ነው። ምንም እንኳ ጀምሮ በማጠናቀቅ መካከል ያለው ውጣ ውረድ በእጅጉ ፈታኝ ቢሆንም ያንን ፈታኝ ጉዞ ለማለፍ የቱንም ያህል ለዓመታት ዋጋ ቢያስከፍልም የስኬት ጫፍ ላይ መድረስ መቻል ከልማትም ከእድገትም በላይ ነው። ግድቡ ለመጠናቀቅ ጫፍ መድረሱ የኢትዮጵያውያኑንና የመንግስትን መንፈሰ ጠንካራነት በአፍሪካም ሆነ በዓለም አደባባይ በደማቁ የሚያሳይ ነው። የሕዳሴ ግድቡ ከሚሰጠው የኤሌክትሪክ ኃይል ባለፈ የኢትዮጵያን አልደፈር ባይነት የደገመ ታሪክ ሆኖ መመዝገቡ ከምንም በላይ ነው።
ይህ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እስካሁን ባለው ሒደት ወጪው ሙሉ በሙሉ በመንግስት፣ በኢትዮጵያውያኑ እና በትውልደ ኢትዮጵያውያኑ የተሸፈነ መሆኑም እምብዛም ላያስደንቅ ይችላል፤ ምክንያቱም አንድ አገር ገንዘብ ስላለው ብቻ ያንን ማድረግ አይችል ይሆናልና የሕዝብ ብልሃትና የመንግስት ጥበብን የሚፈልግ ጉዳይ በመሆኑ ነው። ከዚህ የተነሳ የግድቡ መጠናቀቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለኢትዮጵያ የሚያጽፈው ታሪክ እጅግ በጣም ደማቅ ነው። በሌላ በኩልም ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ ስትገነባ በማን አለብኝነት ተነሳስታ ሳይሆን ፍትሃዊ የሆነ መንገድን በመከተል ነውና ይህም አካሄዷ የሚያስመሰግናት ነው።
የሕዳሴ ግድቡ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትን 13ኛ ዓመት በማስመለከት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የኦሮሚያ ክልልዊ መንግስት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ከሆኑት ከአቶ አማን አሊ ጋር ቆይታ አድርጎ ተከታዩን አጠናቅሯል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል የኦሮሚያ ክልልዊ መንግስት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ዋና ዳይሬክተር እንደነበሩ ይታወቃል፤ አሁን በምን ሁኔታ ላይ ነዎ? በዚህ ኃላፊነትስ ምን ያህል ቆዩ?
አቶ አማን፡- ታላቁ የኢትዮጵ ሕዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ በጽ/ቤቱ በኃላፊነት ደረጃ ቆይቻለሁ። ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ በጥቅሉ ወደ ዘጠኝ ዓመት ያህል በጽህፈት ቤቱ ሰርቻለሁ። በአሁኑ ወቅት በቻይና የሶስተኛ ዲግሪዬን (PHD) በመማር ላይ እገኛለሁ። ከሰሞኑ ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት ለእረፍት ነው።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ በነበሩበት የሕዳሴ ግድቡ ገና ጅማሬ ላይ እንደመሆኑ እና አዲስ አንደመሆኑ ምን አይነት ስራ ነውሰ ሲሰራ የነበረው?
አቶ አማን፡– በእርግጥ እንደተባለው በወቅቱ ጽ/ቤቱ ራሱ አዲስ ነው። እንዲያውም ስም ራሱ አልነበረውም ማለት ይቻላል። ዝም ብሎ የተገነባው አዲስ ጽ/ቤት ብቻ ነው። ቀደም ሲል የማይታወቅ፤ ግን ደግሞ አዲስ የሆነ ቢሮ ስለተሰራ ከዚያ ተነስተን መዋቅሩንና አሰራሩን ገነባን። መተዳደሪያ ደንብ እንዲዘጋጅ አደረግን። የቢሮውን የስራ ድርሻ ምን መሆን እንዳለበት ስርዓቱን ዘረጋን። የተለያየ የስራ ድርሻ እንዲኖርና የቢሮው ሰራተኛም እንዲሟላ አደረግን። እንዲሁም የሕዝቡ ድርሻ እና የመንግስትም አቅጣጫ ምን መሆን አለበት የሚሉትንና መሰል ስራዎችን ስናደራጅ ቆየን።
ከዚያ በኋላ የተሰራው ሕዝቡ በጉዳዩ ላይ እንዲሳተፍ እና በስራው ላይም እምነት እንዲጥል ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ከተለያዩ ቦታዎች ሰራተኞችንም በማምጣት ቢሮው በአግባቡ እንዲደራጅ ሊደረግ ችሏል። በወቅቱ የተሰራው ስራ በጣም ጠንካራ የሆነ ሲሆን፣ እሱ ስራ ዛሬም እንዲሁ ጥንካሬውን ይዞ ቀጥሏል።
በወቅቱ የኦሮሚያ ክልል ነዋሪ የሆነው አካል ሁሉ “ይህ ግድብ የእኔ ነው፤ ከድኅነትም ሊያወጣኝ የሚችል ነው፤ ከዚህ ታላቅ ግድብ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አገኝበታለሁ፤ ከዚህ ውስጥ አንዱ የኤሌክትሪክ ብርሃን ነው። ከዚህ በተጨማሪ የውጭ ምንዛሬም የማገኝበት ግድብ ነው። ሌሎች አገራት ለኢትዮጵያ ያላቸውን የተንሸዋረረ አመለካከትን የሚያስተካክልልን ነው።” በሚል አመለካከት እንደየችሎታው ሲንቀሳቀስ ነበር። ይህ የክልሉ ነዋሪ ንቅናቄው ሲደረግ የነበረው በግልም በቡድን ጭምር ነው።
ለሕዳሴ ግድቡ ስኬታማነት ኅብረተሰቡ አንዱ ከሌላው ሳይለይ አርሶ አደሩ፣ የመንግስት ሰራተኛውም ሆነ ሁሉም ከውስጡ ተሳትፎውን ሲያደርግ ነበር። በዚህች ምድር በሕይወት የሚንቀሳቀሰው ሁሉ ሕዳሴ ግድቡን መገንባት ይቻላል በሚል ጠንካራ መንፈስ ለግድቡ ተሳትፎውን አድርጓል። ከዚህም የተነሳ ብዙዎቹ ሰንጋቸውን ግመላቸውን፣ ዶሯቸውንም ጭምር ለግድቡ ስኬታማነት ሲሰጡ ነበር።
ተማሪዎችም እንደ ማስቲካ እና ብስኩት አይነቱንም ለሰዎች በማቅረብ እንዲሁም በ25 ሺ፣ በ50 ሺ እና በ100 ሺ ብር ጭምር ቦንድም በመግዛት ተሳትፎ ሲያደርጉ ነበር። ሕጻናት ልጆችም በዚህ ግድብ ተሳትፎ አድርገዋል። በዚህ ግድብ ተሳትፎ ሲደረግ ብሔር፣ ኃይማኖት እና እድሜ ልዩነት አልነበረውም፤ የለውምም። ሁሉም ተሳትፎ ሲያደርግበት ቆይቷል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ አርብቶ አደሩም ሆነ አርሶ አደሩ ከድጋፉ ባሻገር የሕዳሴ ግድብ መገደቡ ለአየር ጸባዩም ለወንዞቹም ሆነ ለዝናቡ ድርሻው የጎላ ነው በሚል የየድርሻውን ሲያበረክት ቆይቷል። ይህ ነገሩ ሲታይ የነበረው ነገር በጣም አስደሳች ነው።
በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያውያኑን ተሳትፎ ማጤን ከተቻለ ትልቅ ነገር መስራት እንደሚችል የሚያሳይ ነው። ይህ ታላቅ ግድብ እንደቀላል የሚታይ ነገር አይደለም። በእርግጥ አገራችን ብዙ የሚነገርላት ታሪክ ያላትና የዚያ አኩሪ ታሪክ ባለቤትም ናት። ኢትዮጵያ በብዙ ጎዳናዎችም ድል ማስመዝገብ የቻለች ናት። ለምሳሌ አድዋን መጥቀስ ይቻላል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕብረት እና አንድነትን በመፍጠር የተለያየ ታሪክ መስራት የቻለ ሕዝብ ነው። ይህም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከእነዚህ ታላላቅ ድሎች ጋር መታየት የሚችል ነው። ምክንያቱም የተሰራው ትልቅ ታሪክ ነውና።
አዲስ ዘመን፡- እንደሚታወቀው ግድቡ ሲጀመር መሐንዲሱም፣ የገንዘብ ምንጩም የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው መባሉ እንደተጠበቀ ሆኖ ከውጭ ደግሞ ከእነ ግብጽ አይነት አገሮች ጫና ያለበት ነበር፤ በወቅቱ እርስዎ ገና ጅማሬው ላይ የነበሩ እንደመሆንዎና የተለያዩ ፉከራዎች ከውጪው ዓለም ይሰነዘር ስለነበር ውስጥዎ ‘ይቻላል/አይቻልም’ የሚል ጥርጣሬ አልተፈጠረብዎም ነበር?
አቶ አማን፡- ግድቡ ተጀምሮ በስኬት ስለመጠናቀቁ ምንም አይነት ጥርጣሬ አልነበረኝም። የግብጽ ፉከራ መነገር የጀመረው ከመቶዎቹ ዓመታት በፊትም ጭምር ነበር። በተለይ ደግሞ በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ የሚገነባ መሆኑን ስታውቅ ደግሞ ፉከራዋን ብታጠናክርም ችግር ያመጣል የሚል ነገር ውስጤ አልነበረም። በእርግጥ ግብጽ አጀንዳ ቀርጻ ወደ ሕዝቡ ስትለቅ ስለነበር በዚያ መረጃ አማካይነት ሕዝቡ ሲደናገር ነበር።
ያንን ያልተገባ መረጃ እና የሕዝቡን መደነጋገር ለማጥፋት ጊዜ ሊወስድ ችሏል። ለምሳሌ ሕዝቡ ባልተገባ መረጃ ሲደነጋገር የነበረው ለምሳሌ ግብጽ ከምታናፍሰው እና እውነት ካልሆነው መረጃ አንዱ “ግድቡን እናስቆማለን” የሚለው ይጠቀሳል። በተለይ ደግሞ አገሪቱ ወደተለያዩ የዓለም ክፍል በመንቀሳቀስ የሕዳሴ ግድቡ እንዲቆም ትማጸንም እንደነበር የሚታወቅ ነው።
እንዲያም ሆኖ የሕዳሴ ግድቡ ከመገንባት እንደማይቆም ልቦናችን መቶ በመቶ ያውቀዋል። ይሁንና ግብጽ የምትነዛውን መረጃ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ነው ለማለት ሁሉም እኩል ግንዛቤ ስለሌለው ሕዝቡ ቢደናገር የሚያስደንቅ አይደለም። ስለዚህ የሕዳሴ ግድቡን ማንም ሊያስቆመው እንደማይችል ለሕዝቡ ማስረዳት የግድ ስለነበር ያንን ማድረጉ ትንሽ ጊዜ ወስዶ ይሆናል የሚል እንጂ ስለመጠናቀቁ በወቅቱ ምንም አይነት ጥርጣሬ አልነበረኝም፤ የለኝምም።
ግብጽማ የዓባይ ወንዝ እንዳይነካ ብሎም በማንም እንዳይደፈር ለዘመናት ስትሰራ መቆየቷ የሚታወስ ነው። ሕዝቡ የዓባይ ወንዝን እንዳይነካ “ወንዙ ውስጥ ሰይጣን አለ፤ ከሚለው አንስቶ ሌሎችንም ማደናገሪያ ስልቶች ስትጠቀም ቆይታለች። ያልተገባ ፎቶግራፎችን ዲዛይን እያደረገች ሕዝብን ለማስፈራራትም ስትሞክር የነበረች አገር ናት።
ይህን የግብጽ ሴራና አካሔድ ‘ሕዝቡ ሐሰት ነው ወይስ እውነት’ በሚል ጥርጣሬ ውስጥ ሊገባ ይችል ይሆናል። ነገር ግን ግንዛቤው ሲፈጠርለት ሊረዳ ይችላል። በጥቅሉ ግን በወቅቱ ግብጽ ከምትሰራው ፕሮፓጋንዳ ጋር ተያይዞ በውስጤ አንዳችም ስጋት እንዳልነበረኝ መግለጽ እወዳለሁ። ግብጽ የግድቡን ስራ ለማስተጓጎል በምትሔደው ደረጃ ልክ አይደለችም። በኢትዮጵያ በኩል የተያዘው ዲፕሎማሲያዊ አካሔድ ያንን አካሄዷን ሁሉ ሽባ የሚያደርግ በመሆኑ ሊሳካላት አልቻለም፤ ከዚህ የተነሳ ይበል የሚያሰኝ ስራ ሲሰራ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- የሕዝቡ ተሳትፎ መልካም የሚባል እንደሆነ የሚታወቅ ነው፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በቆይታዎ ብዙዎች ሲሳተፉ እንደነበር አስተውለዋል፤ ድሃዋ እናት ከመቀነቷ፣ ጎዳና ተዳዳሪው ካለው ላይ ሲለግስም ቆይቷል። ሌላ ሌላውም እንዲሁ ቃል ከመግባት እስከ መስጠት ተሳትፎ አድርጓልና ከዚሁ ሁሉ ውስጥ ያስደነቅዎ እና ልብዎን የነካ ነገር ይኖር ይሆን?
አቶ አማን፡- ብዙ ነገሩ የሚዘነጋ አይደለም፤ አንዳንዴም የሚያስለቅስ ነገር አጋጥሞኝ ያውቃል። ሕዝቡ የሚያደርገው የተለያየ ተሳትፎ ልብን የሚነካ ነው። ሰው ራሱ ተቸግሮ እያለ የራሱ የሆነውን ነገር ሁሉ አሳልፎ ሲሰጥ ሲታይ ውስጥን የሚነካ ነው። ካለው ላይ ሳይሆን ከሌለው ላይ ያለስስት መስጠቱ ግድቡ ተገድቦ እንዲጠናቀቅ ቁርጠኛ መሆኑን የሚያመላክት ነው።
ከዚህ ሕዝብ ድጋፍ ጋር ተያይዞ በጣም የማልረሳውና ሁሌም የማስበው ነገር ሻሸመኔ ከተማ አንዲት ከሰል የምትሸጥን ሴት ነው። እርሷን የማልረሳበት ምክንያት የሕዳሴ ግድብ ቦንዱን አንድ ጊዜ ብቻ ገዝታ የምታበቃ አለመሆኗን ነው። ሁሌ ተስፋ ታደርጋለች እንጂ ተስፋ አትቆርጥም። ከሰሉን ሸጣ እጇ ላይ የሚኖረው መቶ ብርም ሆነ አንድ ሺ ብር ሔዳ ቦንድ ትገዛበታለች። ስለዚህም የእርሷ ከሁሉም ሰዎች የሚያስደንቀኝ መረዳት ይለይብኛል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ተማሪዎች ማስቲካውን ብስኩቱን ለሰዎች እያቀረቡ ቦንድ መግዛታቸው እንዲሁ የሚያስደንቀኝ ነገር ነው። በተጨማሪም እንደሚታወቀው የመንግስት ሰራተኞች የወር ደመወዛቸው ከወር እስከ ወር እንኳ በአግባቡ ሊያደርሳቸው የሚችል እንዳልሆነ ቢታወቅም የመንግስት ሰራተኛው ከዚሁ ከወር ደመወዙ እንዲቆረጥ በማድረግ ቦንድ መግዛት ችሏል። ይህ በራሱ በጣም አስገራሚ ነገር ነው። ምክንያቱም መንግስት ብቻውን የሚያደርገው ምንም ነገር የለም። ስለዚህ ከእነዚህ ጋር ተያይዞ አርሶ እና አርብቶ አደሩ ሊመሰገን ይገባዋል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- የሕዳሴ ዋንጫ በተለያዩ ክልሎች በመዘዋወር በርከት ያለ ገቢ ሲያስገኝ መቆየቱ የሚታወቅ ነው፤ ተራው ሲደርስ ወደ ኦሮሚያም ክልል በመድረስ እንዲሁ የድጋፍ ማሰባሰብ ስርዓቱ ቀጥሎ እንደነበር ይታወሳልና ይህ የዋንጫው ጉዞ የተጀመረው እንዴት ነበር?
አቶ አማን፡– ሕዝቡን በዚህ ታላቅ ግድብ ድጋፍ ላይ ለማነሳሳት የተለያየ ዘዴን ስንጠቀም ቆይተናል። ከዚህ ውስጥ አንዱ ዋንጫን መጠቀም ሲሆን፣ ይህ የሕዳሴ ግድብ ዋንጫ በተለያየ ቦታ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ አንዱ ተግባር ነበር። ዋንጫው በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች እና ከተሞች በተንቀሳቀሰ ጊዜ ባዶውን አይመለስም የሚል ነገር ስናሰርጽ ነበር። ገና ዋንጫው ጉዞ ሳይጀምር “ወደ እናንተ ዞን እና ከተማ ዋንጫው ሊመጣ ነው” በሚልም ማነቃቂያ ስናደርግ ነበር። ዋንጫው በገባበት ዞንም ሆነ ከተማ በሚያደርገው ቆይታ የቦንድ ግዥው እንዲፈጸም ይደረጋል። ይህ ድርጊት በጣም ውጤታማ እና የሚያስደንቀኝ ሆኖ የዘለቀ ነው። ደግሞም ሕዝቡን ለልማት የምናነሳሳ ከሆነ ወደኋላ የሚልበት ምንም ነገር የለውም። ይህንንም በተግባር ማሳየት ችሏል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት የሕዳሴ ግድቡ በጥሩ ሁኔታ ከመሆኑም በላይ ወደፍጻሜው እየገሰገሰ ነው፤ በመሃል ግን ስራው ሁሉ መዳከሙ የሚታወቅ ነው፤ በወቅቱ ግንባታው የተቀዛቀዘበት ነገር ምንድን ነበር?
አቶ አማን፡- በወቅቱ ደንግጬያለሁ። ያስደነገጠኝ ነገር ምንድን የተባለ እንደሁ ስራሽን እየሰራሽ ባለበት እንቅስቃሴ ውስጥ የምታስቢው ስራዬን እየሰራሁ ነው በሚል ነው። የምትንቀሳቀሽውም ስራውም ስኬታማ ይሆንልኛል በሚል ነው። ቁማር መሆኑ ሲታወቅ ደግሞ ያሳዝናል።
እኛ “የሕዳሴ ግድቡ በጥሩ ሁኔታ እየተገነባ ነው፤ ይሳካል፤ ያለበት ደረጃም ጥሩ ነው፤ ሁሉም ነገር በስኬት እየተጓዘ ነው፤ ቦንዱን ጨምሮ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው” እያልን እያነቃቃን እና እያነሳሳን ባለበት ጊዜ፤ በተለይም “በሰው እጅ የቦንዱ ሽያጭ የሚገባበት ሁኔታ የለም፤ የሚከናወነው በባንክ ነው። ስለዚህ ገንዘቡ ግልጽነት ይኖረው ዘንድ በመንግስት ካዝና እንጂ በግለሰብ እጅ የሚገባበት ሁኔታ አልነበረም።” እየተባለ ባለበት “በመንግስት ካዝና የገባው ገንዘብ አሰራሩ እና አተገባበሩ ችግር አለበት” የሚለውን ነገር ስንሰማ ደግሞ ደንግጠናል።
እንደዚያው ደግሞ ሕዝቡ “ገንዘባችን ተበልቶና ጠፍቶ ይሆን!? የት ገብቶ ይሆን?” እያለ ቅር በሚሰኝበትና በተሰኘበት ጊዜ ማዘን አይቀርም። ቀደም ሲል ሕዝቡን ስናነቃቃ የምንናገረው አፋችንን ሞልተን ነው። ለማስረዳትና ለማነሳሳት መቶ በመቶ በራስ መተማመን ላይ በመሆን ነበር። ደግሞም ምንም አይነት ችግር አይመጣብንም በሚል ሕዝብን ካነሳሳን በኋላ ቆይቶ በሕዳሴ ግድቡ ዙሪያ “ይህ እና ያን አይነት ችግር አለበት፤ የተለያየ አይነት ችግር ተፈጥሮበታል፤ ይህን ያህል ብር ከዚህኛው ባንክ ቅርንጫፍ ወጥቷል፤ የግንባታ ስራውም ችግር አለበት” የሚል ነገር ሲፈጠር በወቅቱ በጣም ልብ የሚሰብር ነገር ነው የሚሆነው።
ወዲህ አንቺ በንጽህና ጊዜሽንና ሁለንተናሽን ሰጥተሽ፣ የወር ደመወዝሽን ለቀሽ ጠንክረሽ መስራትሽን ስታስቢ በእጅጉ ይሰማሻል። ስለዚህም ተጨማሪ ድጋፍ ሰዎች ፊት ቆመሽ ለመጠየቅም ይከብድሻል። ትልቁ ነገር ሕዝብ ዘንድ ቀርበሽ “ድጋፍ አድርጉ፣ ይህን አድርጉ፣ ያንን አድርጉ፣ ይህን እያደረግን ነውና ግንባታው በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው” እያልሽ እንደከዚህ ቀደሙ በልበ ሙሉነት ድጋፍ ለመጠየቅ በራስ መተማመን አይኖርሽም። እኔ ይህ ሁኔታ ተፈጥሮ እያለ ከአንድ ዓመት በኋላ የትምህርት እድሉን ስላገኘሁ ሶስተኛ ዲግሪዬን ለመማር ወደውጭ አገር በማቅናት ትምህርት ቤት ገባሁ።
ነገር ግን በኋላ ላይ ችግሮች ናቸው የተባሉ ሁሉ ሊስተካከሉ እና በቁጥጥር ስር ሊሆኑ ችለዋል። በተለይም መንግስት ተፈጠሩ የተባሉ ችግሮችን በአግባቡ ማስተካከል ችሏል። እውቀቱ ያላቸውን ሰዎች ከውጭ አገር ድረስ በማስመጣትም እንዲሁ ከአገር ውስጥም በማሳተፍ መፍረስ ያለበት ፈርሶ፣ እጥረት ያለበትም እንደገና ተሰርቶ በጥሩ ሁኔታ እንዲሰራ መደረግ መቻሉ በጣም ያስደንቀኛል፤ ያስደስተኛልም። በአሁኑ ወቅት ጠቅላላ የግድቡ ስራ 95 በመቶ ላይ ደርሷል መባሉን ከቀናት በፊት በመስማቴ ደስተኛ አድርጎኛል። እግዚአብሔርንም ‘ይህ ታላቅ ግድብ ተጠናቅቆ በአይኔ ሳላይ እንዳይገድለኝ’ በሚል ስለምነው ነበር።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት የሕዳሴ ግድቡ በተከታታይ ለአራት ዓመታት ውሃ በአግባቡ ሲሞላበትና ከዚሁ ተነስቶ መብራትም ከተወሰኑ ተርባይኖች ለማግኘት ተችሏል፤ ይህን ተከትሎ ምን አይነት ስሜት ተሰማዎ?
አቶ አማን፡- በወቅቱ ያለሁት ለትምህርት በሔድኩበት ውጭ አገር ነው። በተለይም የውሃ ሙሌቱን በተመለከተ የተከታተልኩት በመገናኛ ብዙሃን አማካይነት ነው። እውነት ለመናገር አይኖቼን የሞላው እንባ ነው። በዚህ ጊዜ አገሬ ኢትዮጵያ ሆኜ ብሆን ኖሮ ስልም ተመኝቻለሁ። ይህን ደስታ በስፍራው ሆኜ ማጣጣም ብችል ኖሮ ብዬም አስቤያለሁ። እናም ልክ ቡና ተክለሽ የመጀመሪያውን የምስራች ስታገኚ የሚሰማሽ አይነት ሁኔታ ነበር የተመለከትኩት።
አዲስ ዘመን፡- የሕዳሴ ግድብ ላይ ተሳትፎ ለማድረግ የትኛውም ብሔርና ኃይማኖት ልዩነትን አልፈጠረም፤ የሕዳሴ ግድቡ የኢትዮጵያን ሕዝብ በማያያዙ እና አንድነትን በመፍጠሩም በኩል የተጫወተው ሚና እንዴት ይገለጻል?
አቶ አማን፡- የሕዳሴ ግድቡ የሁላችንም ንብረት በመሆኑም አንድ በማድረጉ ላይ ትልቅ ትርጉም አለው። እና ያለን ሀብት ነገ ተነገወዲያ እየበረከተና እየሰፋ ገቢ የሚያስገኝ ነው ማለት ነው። ልክ እንደታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁሉ በሌሎችም ሀብቶቻችን ላይ መገንባት የሚቻል በመሆኑ ያለንን ይህን ሀብት ራሱ ሀብትን እያስፋፋ የሚሄድ በመሆኑ በዚህ ሀብት ላይ ሕዝቡ ሲወያይና ድጋፍ ሲያደርግ ልክ እንደ ራሱ ልጅ ያየዋል ማለት ነው።
ሕዝቡ የሕዳሴ ግድቡን እንዳገኘው ልጅ፣ ጌጥና ንብረት ስለሚያየው እርስ በእርስ የሚግባባት ነው። ሕዝቡ ባለው ሀብት ላይ ሲመካከር ሐሳቡ አንድ ነው። ስለዚህም አንድነትን በመፍጠሩ በኩል ሕዳሴ ግድቡ ሚናው የጎላ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ዘንድሮ የሕዳሴ ግድቡ 13ኛ ዓመቱ ነው፤ ይህንን ምክንያት በማድረግ እርዳታ እና ድጋፍ ያደረጉ ሰዎች እውቅና እና ምስጋና ይሰጣቸዋል ተብሎ ይጠበቃልና በዚህ ላይ ያለዎትን አተያይ ቢገልጹልን።
አቶ አማን፡- በነገራችን ላይ በጉዳዩ ላይ ተሳትፎ ያላቸውን ሰዎች እውቅና መስጠትና መሸለም ከሚለው ሐሳብ ስጀምር በሕዳሴ ግድቡ ስኬት ሊመሰገን እና እውቅና ሊሰጠው የሚገባው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ሕዝቡ ድርሻው ትልቅ ነው። ስለዚህም በአንደኛ ደረጃ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊመሰገን እና እውቅና ሊሰጠው ይገባዋል ባይ ነኝ። ሁለተኛው ደግሞ አንዳች ሳይኖራቸው ከጉድለታቸውና ጥቂት ካላቸው ነገር ደጋግመው ለመስጠት ላላንገራገሩ አካላት እውቅናውም ምስጋናው ሊሰጣቸው ይገባል።
ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ቀን እና ምሽት ሳይሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በንቃት ሲጠብቁና ከጠላትም ሲከላከሉ ለቆዩት የአገር መከላከያ ሰራዊቶች መንግስት ተገቢውን እውቅና ሊሰጣቸው ይገባዋል ባይ ነኝ። በጥቅሉ ግን ልዩ ተሸላሚ ተብሎ ሊመሰገንም እውቅና ሊሰጠውም የሚገባው ራሱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፤ ይህ እንዳለ ሆኖ እርስ በእርስ ደግሞ እኛ ራሳችን ልንመሰጋገንና እውቅና ልንሰጣጥ ይገባናል እላለሁ። ስለዚህ ልዩ ተሸላሚ ተብሎ ብቻውን ሽልማት ሊወስድ የሚችል አለ ብዬ እምብዛም አላምንም። ምክንያቱም ሁሉም በገንዘቡ፣ በእውቀቱ እና በጉልበቱ የተቻለውን ዋጋ ሁሉ የከፈለ በመሆኑ ነው። እንዲያም ሆኖ ግን በዚህ ታላቅ ግድብ ላይ መላልሰው ጉልበታቸውን፣ እውቀታቸውንና ገንዘባቸውን ሳይሰስቱ ለደከሙ አካላት ምስጋና እና እውቅና መስጠቱ የሚከፋ አይሆንም። ይህን ማድረግ ደግሞ በቀጣይ ለሚሰራው የልማት ስራ ትልቅ ድርሻ ያለው በመሆኑ ምስጋናውና እውቅናው ቢሰጥ መሆን ያለበትና መልካም የሆነ ድርጊት ነው የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 95 በመቶ መድረሱ ወደፍጻሜው መቃረቡን ያሳያል፤ የቀረችውን አምስት በመቶ በምን አግባብ ሊሰራና ሊጠናቀቅ ይገባል ይላሉ?
አቶ አማን፡- በአሁን ሰዓት የሕዳሴ ግድቡ መጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንገኛለን፤ ስለዚህ የሕዳሴ ግድቡን ሳናጠናቅቅ ‘እፎይ!’ ልንል አይገባም። ስለዚህ ፍጻሜው ስር ደርሰን ልናርፍ አይገባም። እስከ ዛሬ ድረስ የየበኩላችንን በማድረግ ወደፍጻሜው ተቃርበናል። ይህን ስናደርግ ደግሞ ሳንልፈሰፈስ፣ ሳንደክምና ለፕሮፓጋንዳ እጅ ሳንሰጥ ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ በዚህ በመጨረሻው ትንቅንቅ ላይ ተሳታፊ ከሆነ ከፍጻሜው የሚገኘውን ትሩፋት ተቋዳሽ ይሆናል ማለት እፈልጋለሁ። በአሁኑ ወቅት ትሩፋቱን ልንቋደስ ከጫፍ እንደመድረሳችን ለፍጻሜው እንቀደመው ሁሉ ከሁላችንም ድጋፍ ያሻል እላለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ ከልብ እናመሰግናለን።
አቶ አማን፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
በአስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም