የክፉ ትርክቶች ስለታማ ጫፎች

‹‹ ከአያያዝ ይቀደዳል፣ ከአነጋገር ይፈረዳል›› እንዲሉ አበው ማንኛውንም ጉዳይ በወጉ መጠቀም ካልቻልን ውጤቱ ሊከፋብን ይችላል። ይህን አባባል ያለ ምክንያት አላነሳሁም ። አሁን ላይ ተረቱን የሚጠቁሙ በርካታ እውነታዎች ቢያጋጥሙኝ እንጂ ።

በዛሬው ትዝብቴ ስለማህበራዊ ሚዲያው ጠቀሜታ የመዘርዘሩ ሃሳብ የለኝም። ስለጥቅሙ ከቱሩፋቱ የተጋራ ሁሉ አሳምሮ ያውቀዋልና። ይህ እውነታ እንዳለ ሆኖ በሚዲያው አጠቃቀም ላይ የሚፈጸሙትን ያልተገቡ ድርጊቶች ግን ላነሳ ግድ ይለኛል።

ጊዜው አልራቀም። በቅርብ ነው። አንዲት ወጣት በማህበራዊ ሚዲያ ብቅ ብላ ‹‹ብንሄድ ይሻላል›› የሚል መልዕክት ለጠፈች። እንዲህ በሆነ ማግስቱን ለጋዋ ወጣት ራሷን ስለማጥፋቷ ተሰማ። ይህ አስደንጋጭ እውነት በብዙዎች ዘንድ ሀዘን አጭሮ በስፋት ሲያነጋግር ቆየ። ጉዳዩ የተሰማውና ሲመላለስ የሰነበተው በዚሁ የማህበራዊ ሚዲያዎች መስኮት ነበር። በወቅቱ አስተያየት የሚሰጠው፣ ግምቱን የሚያስቀምጠው፣ የራሱን ፍርድ የሚገመድለው ሁሉ ስለ ልጅቷ ያሻውን ሲተነፍስ ከርሟል።

ጉዳዩ ግን በዚህ ብቻ አልተቋጨም። የወጣቷን ሞት ተከትሎ ‹‹ብንሄድ ይሻላል ›› የሚለውን መርህ የሚያራምዱ በረከቱ ። አሁንም ሃሳቡ በዚህ ብቻ አልቀረም። ሰዎቹ ቃሉን በድርጊት ተርጉመው ራሳቸውን ስለማጥፋታቸው አሳወቁ ። ይህ ሁሉ የሚሆነው በእኛ ሀገር ነው።

ወሬው እንደተለመደው በማህበራዊ ሚዲያዎች ተናፈሰ። ‹‹ጉድ…›› እያለ ሃሳቡን የሚኮንን ፣ የሚቃወመው፣ ሀዘኑን የሚገልጽ ፣ የሚናገረው ሁሉ በየአፍታው ተዥጎደጎደ ። የእነሱን ታሪክ በማስረጃዎች አስደግፈው ‹‹እንዲህ ሆነ ›› የሚሉ አጋጣሚውን ተጠቅመው ብዙ ለማለት ሞከሩ። ወጣቷ ወደ ሞት የተራመደችበት ቃል በአብዛኞች ዘንድ በቀላሉ እስኪለመድና ተረስቶ እስኪደበዝዝ መነጋገሪያ ሆኖ ከረመ።

ይህ ዓይነቱ አጋጣሚ ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ያለመጠቀምን እውነት የሚያመላክት ሀቅ ነው። ሆኖ ከተገኘ በኋላ አብዛኛው የሚሰነዝረው ሃሳብ ደግሞ ችግሩን የሚያባብስ እንጂ የሚታደግ አይደለም። ከተሞክሮ እንደተስተዋለውም ደጋግሞ የሚመላለሰው ያልተገባ ትርክት ብዙዎችን ከመኖር ወደ አለመኖር ለመለወጥ ጉልበቱን አሳይቷል።

ከሰሞኑ ደግሞ እንዲህ ዓይነቱ ታሪክ መልኩን ለውጦ ተከስቷል። አጋጣሚውን የከፋ የሚያደርገው ደግሞ በልጆች ሥነልቦና ላይ የማተኮሩ ጉዳይ ነው። ሌላውን ምሳሌ ላክል። በቅርብ ጊዜ በተለያዩ የማህበራዊ ገጾች ላይ ‹‹አፋልጉኝ›› የሚል ማስታወቂያ ሲመላለስ ሰንብቷል።

ብዙዎች እንደምንረዳው እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች በየአጋጣሚው ይነሳሉና ብርቅ ሆነው አያውቁም። የዚህኛው መልዕክት ግን ከሌሎች ለየት የሚያደርገውን ገለጻ ይዟል። የጠፋው ልጅ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ነው። ከዚህ በፊት ከቤት ወጥቶም ሆነ ርቆ አያውቅም። አሁን ከአካባቢው መጥፋቱ የታወቀው በራሱ እጅ ጽሑፍ በቁራጭ ወረቀት ከትቦ ባኖረው ደብዳቤ ሆኗል።

ልጁ ከቤት ከመውጣቱ በፊት የደብተር ቦርሳውን ፣ ከሚታወቅ ቦታ አኑሯል። በጻፈው መልዕክት ላይ ደግሞ እናት አባቱን ከልብ እንደሚወድ ተናግሯል። በጣም አስደንጋጩ ነገር ከዚህ በኋላ ማንም ሰው ‹‹እንዳይፈልገኝ›› ሲል ማስጠንቀቁ ነበር። ይህን መልዕክት በልጃቸው እጅ ተጽፎ ያገኙት ወላጆች የሚሆኑትን መገመቱ አያዳግትም። ያለፉበት ፈታኝ ጊዜ ከቃላት በላይ ነውና።

ትልቁ ስህተት የልጁ መጥፋት እንደታወቀ የተላለፈው የአፋልጉኝ ተማጽኖ ብቻ አለመሆኑ ነበር። በየማህበራዊ ሚዲያው ከተላለፈው መልዕክት ጋር ልጁ ጽፎታል የተባለው ማስታወሻ ጭምር አብሮ ተለጥፏል። በእኔ ግምት ትልቁ ችግር እንዲህ መደረጉ ላይ ነው። ዋናው ዓላማ ልጁን ፈልጎ ማግኘት ነበር ። እሱን ችላ ብሎ ከሌላ ገበና ማተኮሩ ግን የበርካቶች ዓይን እንዲወድቅበት አድርጓል።

ደግነቱ ከቀናት ፍለጋ በኋላ ልጁ በሰላም ከቤተሰቦቹ መገናኘቱ ተሰማ። ወላጆች ለፍለጋው የተባበሯቸውን ሁሉ አመስግነው የጠፋ ልጃቸውን ጉያቸው አስገቡ። ጉዳዩ ለእነሱ እንዲህ ቢቋጭም የደብዳቤው መልዕክት ያስከተለው መዘዝ ግን መንገዱን አራዘመ።

የዚህን ልጅ ታሪክ በየአጋጣሚው ሲመለከቱ የነበሩ እኩዮቹ ባነበቡት ታሪክ ቢሳቡ ይህን እውነት በራሳቸው ህይወት ይደግሙት ያዙ። በወላጆቻቸው ጭንቀት መሞላቀቅ የፈለጉ አንዳንድ ሕፃናት ሳይቀሩ ልጁ ባለፈበት መንገድ ሊመላለሱበት ሞከሩ። ውሎ አድሮ እንደ ‹‹ብንሄድ ይሻለናል›› አይነት ሁሉ ‹‹ ጠፍተናል አትፈልጉን›› ይሉት ብሂል መደጋገም ጀመረ።

ጉዳዩን መለስ ብለን ብንቃኘው ይህ ሁሉ የሆነው በማህበራዊ ሚዲያው ላይ የሚተላለፉ መልዕክቶች ከገብሱ ይልቅ ለግርዱ ትኩረት በመስጠታቸው መሆኑን እንረዳለን። እነዚህ ማህበራዊ ሚዲያዎች ልጁ ጽፎታል የተባለውን ታሪክ ለቤተሰቡ ትተው እንደተለመደው ‹‹አፋልጉኝ›› ላይ ብቻ ቢያተኩሩ ኖሮ ሌሎች ልጆች ደግመው ባልሞከሩት ነበር ።

ልጆች ልክ እንደነጭ ወረቀት ናቸው። ያዩትን በዋዛ አይረሱም። አእምሯቸውም አንዴ የመዘገበውን በቀላሉ ሊተወው አይቻለውም ። እናም በሌሎች ላይ የሆነውን ፈጥነው ለመተግበር ይፈጥናሉ።

ለልጆቹ ዘመኑ ለማህበራዊ ሚዲያው የቀረቡ አድርጓቸዋልና ምንም ጉዳይ ከእነሱ የሚያመልጥ አይደለም። በማህበራዊ ሚዲያው አጠቃቀም ወላጆች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ መምህራንና ሌሎች ከጎናቸው መሆን ካልቻሉ ይህን አሳሳቢ ጉዳይ በቀላሉ ሊሻገሩት ይከብዳቸዋል።

ብዙ ጊዜ እንደሚስተዋለው አንዳንዶች በሰው ስቃይ የራሳቸውን ማንነት መገንባትን ልምድ አድርገዋል። ገና በወጉ ያልተረጋገጠን መረጃ ተመርኩዘው የሚፈጥሩት ጠማማ ወሬ ስለቱ ሌሎችን ሳይጎዳ አይመለስም ። ዓላማና ግባቸው ገንዘብና ጥቅም ብቻ ነውና በአስተውሎት ስለትውልድ ማሰብን አያውቁትም።

ይህ ዓይነቱ ችግር ተዳጋግሞ ሲገኝ በሕግ አግባብ ሊዳኝ ግድ ይላል። የሚተላለፉ መልዕክቶች ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ካመዘነም በዝምታ ሊታለፍ አይገባም። ማህበረሰቡን ፣ትውልዱን ፣አመለካከትንና ተለምዶን የሚቀይሩ መስሎ ሲታይ አንድ የለውጥ ርምጃ መወሰድ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ በሕግ የተቋቋመው የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ተግባሩን ከውኖ ውጤቱን ሊያሳየን ይገባል።

እርግጥ ነው ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓለማ የሚጠቀሙት ሞልተዋል። በትንሹ በዚህ ሰሞን ማስተዋል የጀመረን አንድ ምሳሌ ልጥቀስ። የተወሰኑ ሰዎች በድንገት ብቅ ብለው ማንነታቸውን እያስተዋወቁ ችግራቸውን ይዘረዝራሉ። እነዚህ ሰዎች እንደ በርካቶች ከዩኒቨርሲቲ ገብተው የተማሩና ለዓላማ ሲታገሉ የቆዩ ናቸው።

አጋጣሚ ሆኖ ግን ህይወት ባሰቡት መንገድ አልቀናቸውም። ሥራ፣ መኖሪያና በቂ ምግብ አጥተዋል። ምርጫ ሲጠፋ፣ ችግር ሲብስ ግን በማህበራዊ ሚዲያው ብቅ ብለው ‹‹ ሥራ ስጡን፣ ከሙያችን አገናኙን›› ይላሉ። ይህን የሚያዩ ልበ ቀናዎች ደግሞ ‹‹አለናችሁ›› ለማለት አይዘገዩም። የሰዎቹን ችግር በወጉ ተገንዝበው ካሰቡት ያደርሷቸዋል። ይህ ዓይነቱ መልካምነት የማህበራዊ ሚዲያውን አጠቃቀም በጎ ገጽታ አስመስካሪ ነው።

አንዳንዶች የማህበራዊ ሚዲያቸውን የተቸገረን ለመርዳት፣ የታመመን ለማሳከም፣ ያዘነን ለማጽናናት ይጠቀሙበታል። የእነሱ በጎ አርአያነት ተፅዕኖ ፈጣሪ በሆነ ጊዜም በመንገዳቸው በርካቶችን ያስከትላሉ ። እንዲህ ዓይነቱ የማህበራዊ ሚዲያ ግንኙነት ፍጹም ጤናማና ውጤታማ የሚባል ነው። ተሞክሮውም በአግባቡ ሊቀጥል ያስፈልጋል።

በተቃራኒው የሚካሄዱ የራስ ወዳድነት ጉዞዎች ግን ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› እንዲሉ ልጓም ሊበጅላቸው ግድ ነው። የክፉ ትርክቶች ስለታማ ጫፎች የሚያደማው ጥቂቱን ብቻ አይደለምና ።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You