የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ በ2021 የቲቢ በሽታ ዓለም አቀፍ ስርጭትን አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት በዓመት 10 ሚሊዮን የሚገመት የዓለም ሕዝብ በቲቢ በሽታ እንደሚታመም አመልክቷል። በአንድ ዓመት ውስጥ ደግሞ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚጠጋ የዓለም ሕዝብ በቲቢ በሽታ ሕይወቱ እንደሚቀጠፍ ሪፖርቱ ጠቁሟል። ኢትዮጵያም በዓለም ላይ በቲቢ በሽታ በከፍተኛ ደረጃ ከተጠቁ 30 ሀገራት መካከል አንዷ ናት።
በኢትዮጵያ በ2015 ዓ.ም 137 ሺ ሰዎች በቲቢ በሽታዎች እንደታመሙ መራጃዎች ያሳያሉ። በአንድ ዓመት ውስጥ ደግሞ 16 ሺ የሚጠጉ የቲቢ ታማሚዎች ሕይወት መቀጠፉን እነዚሁ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በቅርቡ ከጤና ሚኒስቴር በወጣ ሪፖርት መሰረት ደግሞ በኢትዮጵያ በዓመት 156 ሺ የቲቢ ታማሚያን አሉ ተብሎ የሚገመት ሲሆን 134 ሺ ያህሉ ደግሞ የቲቢ በሽታ እንዳለባቸው ተረጋግጦ በአንድ ዓመት ወስጥ ለሕክምና እንደሚቀርቡ ተረጋግጧል። 20 ሺ የሚሆኑት ደግሞ ወደ ሕክምና ተቋም እንዳልመጡ መረጃው ጠቁሟል።
እነዚህ ቀሪ ወደ ሕክምና ተቋም ቀርበው ሕክምና ያላገኙ ዜጎች የቲቢ በሽታን የማስተላለፍ አቅማቸው ከፍተኛ መሆኑና አሁን በኢትዮጵያ የሚታየውን የቲቢ ስርጭት ክፍ በማድረግ ረገድ አስተዋፅዋቸው ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል። ከዚህ አንፃር ሁሉም ሰው ለቲቢ በሽታ ተጋላጭ ነው ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል። የቲቢ በሽታን ለመከላከልና ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ታዲያ የጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ የሌሎች ባለድርሻ አካላትን ትብብርና ርብርብ ይጠይቃል። ዓለም አቀፍ ሁኔታው የሚያሳየውም ቲቢን የማጥፋት እንጂ የማቆም አይደለም።
አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ መድሃኒቱን የተላመደ ቲቢ ከፍተኛ ስጋት እየሆነ መጥቷል። ምንም እንኳን መድሃኒቱን የተላመደ ቲቢ ከዛሬ አስራ አምስት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ያልነበረ ቢሆንም ከቅርብ ግዚያት ወዲህ ግን በዚህ በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። እንዲያም ሆኖ ግን መደበኛውን ቲቢ ለመከላከል በተሰሩ ጠንካራ ስራዎች ኢትዮጵያ መድሃኒቱን የተላመደ የቲቢ በሽታ ስርጭት ካለባቸው ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ወጥታለች።
የዘንድሮው የዓለም ቲቢ ቀን ‹‹የቲቢ በሽታን ለመግታት ግዜው አሁን ነው!›› በሚል መሪ ቃል በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ38ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ23ኛ ግዜ ተከብሯል። ከዚሁ ጎን ለጎንም 10ኛው የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ ጉባኤ “lungs unbound: charting paths beyond TB recovery” በሚል መሪ ቃል ከሰሞኑ ተካሂዷል።
ዶክተር ራሄል አርጋው የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ ፕሬዚዳንት ናቸው። በሞያቸው ደግሞ የሕፃናት፣ የፅኑ ሕሙማንና የሳምባ ሕክምና ሰብ ስፔሻሊስት ሃኪም ናቸው። እርሳቸው እንደሚናገሩት፣ የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ የጤና ባለሞያዎች ማሕበር በሳምባና ፅኑ ሕሙማን፣ በቀዶና በልብ ሃኪሞች አማካኝነት ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ነው የተመሰረተው። በኢትዮጵያ የሚታዩትን ከሳምባና ከፅኑ ሕሙማን ጋር የተያያዙ የሕክምና አሰጣጥ ችግሮችን ለመለየትና ለችግሮቹም መፍትሄ ለማምጣት በሚል ዓላማም ነው ማሕበሩ የተቋቋመው።
ማሕበሩ በአስር ዓመታት ጉዞው በአባላቱ አማካኝነት በዚሁ ሕክምና በኩል ያሉ ክፍተቶችን በመለየት የሞያተኞችን እውቀት የመገንባት፣ ክህሎትን የማሳደግና በየዓመቱ በሚያካሂደው ጉባኤው አዳዲስ የጥናት ግኝቶችን ለማኅበረሰቡ የማሳወቅ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። በቅርቡ ደግሞ በኢትዮጵያ ከሚገኙ መንግስታዊ ያልሆኑ ደርጅቶች ጋር በመሆን የምርምር ስራዎች ላይ እየተሳተፈ ይገኛል። ማኅበረሰቡ በሳምባ ሕክምና ላይ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ የጤና ትምህርቶችን የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም ይሰጣል።
ማኅበሩ እያከናወናቸው ካሉ ተግባራት መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው የቲቢ በሽታን ለማጥፋት ጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እያደረገ ያለው ርብርብ ነው። የቲቢ በሽታን ለመከላከልና ለማከም የሚያስችሉ የሕክምና መምሪያ በማዘጋጀት፣ ባለሞያዎችን በማሰልጠን፣ የቲቢ ስርጭት ሞት ምጣኔ ላይ የሚዳስሱ ምርምሮችን በማድረግና የፖሊሲ ግብአቶችን በማቅረብ በኩልም ማሕበሩ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።
ፕሬዚዳንቷ እንደሚሉት፣ ቲቢ በአሁኑ ግዜ በጥሩ ሁኔታ መቆጣጠር ከተቻሉ በሽታዎች ውስጥ አንዱ ነው። ሆኖም ቲቢን አስመልክቶ የሚመጡ አዳዲስ የምርመር ውጤቶች ቲቢ ከታከመ በኋላ ሌሎች ተጓዳኝ የሆኑ የሳምባና የአየር ባንቧ ሕመሞችም ሊከሰቱ እንደሚችሉ እያሳዩ ይገኛሉ። ይህን ሁኔታ በመረዳት ኢትዮጵያ ቲቢን አክማ ብቻ ሳይሆን ከቲቢ በኋላ ያሉትን ድጋፋዊ ምርመራዎች እንዴት አድርጎ መስራት፣ ታማሚዎችን ማከምና እነዚህን ታካሚዎች በምርምር ለይቶ እንዴት የተሻለ ሕክምና መስጠት እንደሚቻል ከተለያዩ ጤና ተቋማት ከተውጣጡ የዘርፉ ባለሞያዎች ጋር ውይይት ተደርጓል፤ ወደፊትም ይደረጋል።
ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመሆን ማህበሩ በተለይ በቲቢ ምርመራ ውስጥ ሰዋዊ አስተውሎት /artificial intelegent/ ላይ ተመሰረተ የሳምባ ኤክስሬይ በማንሳት የሳምባ ካንሰርና የቲቢ ምርመራና ልየታን የሚያቀላጥፍ ፕሮጀክት እያከናወነ ይገኛል። በሳምባ ካንሰር ላይ ከፍተኛ ውጤት ያመጣል ተብሎ የሚጠበቅ ፕሮጀክት ላይም በተመሳሳይ ማህበሩ እየተሳተፈ ነው። ለሳምባ ካንሰር አጋላጭ ሁኔታዎችን በመለየትና ሕክምናዎችን በማቀላጠፍ ውጤታማ የሕክምና አሰጣጥ ሂደት ለማምጣትም ስራዎችን እየሰራ ነው።
በትምባሆና አየር ብክለት ቁጥጥር ላይም ማኅበሩ ስራዎችን እየሰራ የሚገኝ ሲሆን በዚህ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያ ያፀደቀችውን የትምባሆ ቁጥጥር አዋጅ ላይ ሞያዊ ድጋፍ አድርጓል። ሀገራዊ የቲቢ ስርጭት ጫናን ለመቀነስ በሚደረገው ርብርብም በተለይ የራሱን ፕሮግራም በማዘጋጀት የቲቢ በሽታ ታማሚዎች ልየታ ላይ ብዙ ስራ ሰርቷል። ከዚሁ ጎን ለጎን በቲቢ በሽታ ዙሪያ ምርምር ስራዎችን ያከናውናል። ለጤና ሚኒስቴርም ሞያዊና ቴክኒካዊ ድጋፍ ያደርጋል።
በጤና ሚኒስቴር የቲቢ ስጋ ደዌና ሌሎች የሳምባ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ኃላፊ አቶ ታዬ ለታ በበኩላቸው እንደሚገልፁት፣ በኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ 156 ሺ የቲቢ በሽታ ታማሚዎች እንዳሉ ይገመታል። ከነዚህ ውስጥ 134 ሺ ያህሉ የቲቢ ታማሚዎች ተለይተው ሕክምና እየተከታተሉ ይገኛሉ። ከዚህ አንፃር ሀገራዊ የቲቢ በሽታ ስርጭት ጫና ሲታይ ከ100 ሺ ሰዎች 126 የቲቢ በሽታ አለባቸው ተብሎ ይገመታል።
ከ100 ሺ በላይ የቲቢ ታማሚዎች በዓመት አሉ ማለት ደግሞ የበሽታው ጫና ከፍተኛ መሆኑን ይጠቁማል። ከፍተኛ የሆነ የቲቢ ስርጭት በማኅረሰቡ ውስጥ እንዳለም ያሳያል። ይህን ለመከላከልና ለማከም ደግሞ በጤና ሚኒስቴር በኩል ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል። ለምሳሌ በዚህ ዓመት ውስጥ 156 ሺ የቲቢ ታማሚ እንዳሉ የታወቀ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 134 ሺ ያህሉ ተለይተው ሕክምና እንዲከታተሉ እየተደረገ ነው። ሕክምናውም ለስድስት ወር ይሰጣል። አንዳንዴ ግን ሕክምናው እንደህመሙ ሁኔታ ታይቶ እስከ አስር ወርም ሊሰጥ ይችላል።
ይሁንና ቀሪ 20 ሺ የሚሆኑ የቲቢ ታማሚያን በማኅበረሰቡ ውስጥ አሉ። እነርሱን ለይቶ ሕክምና እንዲያገኙ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ከነዚህ ውስጥ አንዱ በቲቢ ላይ ቅስቀሳዎችን በማድረግ ማኅበረሰቡ በጤና ኤክስቴንሽን በኩል ማንኛውም ሰው አንድ ሁለት ሳምንትና ከዚያ በላይ የቆየ ሳል ካለበት ወደጤና ተቋም ሄዶ ምርመራ በማድረግ ሕክምና እንዲጀምር የማድረግ ስራ ነው።
ኃላፊው እንደሚያብራሩት፣ ቲቢ በአብዛኛው የሚተላለፈው ከአፍና ከአፍንጫ በሚወጡ ብናኞች ነው። ዋነኛው የመተላለፊያ መንገድ ደግሞ ትንፋሽ ነው። ይህን ለመከላከል የመጀመሪያው ስራ በቲቢ ዙሪያ የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ነው። ሁለተኛ ማንኛውም ሰው ታሞ ወደ ሕክምና ተቋም ሲመጣ ስለሕመሙ ተጠይቆ ሁለት ሳምንትና ከዚያ በላይ ሳል ካለበት የቲቢ በሽታ ሊሆን ስለሚችል ምርመራ ተደርጎለት ሕክምና እንዲከታተል ይደረጋል።
ሶስተኛውና አሁን ላይ እየተከናወነ ያለው የበሽታውን ምልክት በመጠየቅ የመለየት ስራ ነው። በተጨማሪም ሌላ የሕክምና መሳሪያ በመጠቀም በሽታውን የመለየት ስራ መስራት ያስፈልጋል። ከዚህ አንፃር ሰዋዊ አስተውሎት /artificial inntelegent/ የሚሰራ ኤክስሬ በመጠቀም ቲቢ ያለባቸውም ወይም የቲቢ ምልክት ያለባቸውን ሰዎች ቀድሞ ምርመራ እንዲያደርጉ የሚያስችል መሳሪያ ወደ ሀገር እንዲገባ እየተደረገ ነው። መሳሪያው ወደ ሀገር ውስጥ እንደገባ ምርመራው በተለያዩ ሆስፒታሎችና ሌሎች የጤና ተቋማት ስራ ላይ እንዲውል ይደረጋል። በዚህ ኤክስሬ መሳሪያ የቲቢ ምልክት የተገኘባቸው ሰዎች ሌሎች ምርመራዎችን በማድረግ ሕክምና እንዲያገኙ ይደረጋል።
ቲቢ የትኛውንም ሕብረተሰብ ክፍል ሊያጠቃ የሚችል በሽታ ነው። ይሁንና አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ከ15 አስከ 54 እድሜ ክልል ውስጥ ያሉትን ነው እያጠቃ የሚገኘው። ይህም 70 ከመቶ ያህሉን ድርሻ የሚወስድና በሽታው አምራቹን የሕብረተሰብ ክፍል ምን ያህል እያጠቃ እንዳለ ያሳያል። በተዘዋዋሪም በሽታው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እየጎዳ እንዳለ ይጠቁማል። ከዚህ አኳያ የትኛውም የመንግስት ሴክተር መስሪያቤትም ይሁን ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ብሎም ማሕበረሰቡ ቲቢን በማጥፋት ሂደት ትልቅ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
የቲቢ በሽታ ስርጭት ጫናን ለመቀነስ በጤና ሚኒስቴር በኩል የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ከነዚህ ውስጥ አንደኛው በቲቢ በሽታ ዙሪያ ሕብረተሰቡ ያለውን ግንዛቤ ማስፋት ሲሆን ይህም በተለይ ሁለት ሳምንትና ከዛ በላይ ሳል ያላባቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ወደሕክምና ተቋም መጥተው እንዲመረመሩና ቲቢ ካለባቸው ሕክምናውን እንዲከታተሉ ያስችላል። ይህ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራም በጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያዎች በኩል እየተከናወነ ይገኛል።
ሁለተኛው ደግሞ የቲቢ በሽታን በመከላከል ዙሪያ የግል ጤና ተቋማት እንዲሳተፉ ማድረግ ሲሆን በተለይ ወደ ግል ተቋም ለሌላ ሕክምና ሚሄዱና ሳል ያለባቸው ሰዎች ቲቢ እንደሚመረመሩ የማድረግ ስራ ነው። በግል ጤና ተቋማትም ስልጠናዎችን በመስጠት ተቋማቱ ቲቢን ለይቶ የማከም ስራ ላይ እንዲሳተፉ የማድረግ ስራዎችም እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ሶስተኛው ቲቢ ይገኝባቸዋል ተብለው የሚገኙ ቦታዎችን በመለየት በነዚህ ቦታዎች ላይ ምርመራዎች እንዲካሄዱና ቲቢ ሲገኝባቸው ወደ ሕክምና እንዲመጡ የማድረግ ሥራ ነው። ሌላውና አራተኛው ስራ የቲቢ ምርመራ መሳሪያዎችን ማሻሻል ነው። ከዚህ በፊት ለቲቢ ምርመራ ማይክሮስኮፕ ብቻ ነበር ስራ ላይ የሚውለው።
አሁን ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ አሁን ላይ ለቲቢ ምርመራ ስራ ላይ እየዋሉ ያሉ መሳሪያዎችን ወደሀገር ውስጥ በማስገባት የቲቢ ምርመራዎች እየተደረጉ ይገኛሉ። ይህም ቲቢን በቀላሉ ለማግኘት ከማገዙም በላይ ታማሚዎችን በፍጥነት ለይቶ የማከሙን ስራ ለማቀላጠፍ በእጅጉ ይረዳል። በአምስተኛ ደረጃ ደግሞ የቲቢ ታማሚዎችን የመለየት ስራ እየተከናወነ ሲሆን ከዚህ በፊት ምልክቱን በመጠየቅ ሲከናወን የነበረው የቲቢ ልይታ ስራ በአርተፊሺያል ኢንተለጀንስና በራጅ የተደገፈ የመለየት ስራ እየተሸጋገረ ነው።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21 ቀን 2016 ዓ.ም