የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ራሳቸውን የሚያገኙበት፤ የሕይወታቸውን ትልቁን ትውስታ ይዘው የሚወጡበት፣ ማንነታቸውን በሚፈልጉበት መንገድ የሚገነቡበትና ራሳቸውን የሚያንጹበት ስፍራ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ወደዚህ ተቋም ሲገቡም ከተለያየ አካባቢ፣ አኗኗር እና አስተዳደግ ከመጡ ተማሪዎች ጋር የመተዋወቅ እድል ይኖራቸዋል። በጊቢው በሚቆዩበት ወቅትም የሚኖራቸው ባህሪም አስቀድሞ ባላቸው ማንነት፣ በዙርያቸው በሚያፈሯቸው ጓደኞች እና ለሚገጥማቸው ማንኛውም ነገር በሚሰጡት ምላሽ ይወሰናል።
እነዚህ ተቋማት ከሚሰጡት ትምህርት ባሻገርም ተማሪዎች በጊቢው ሲቆዩ ለቀጣይ ሕይወታቸው ሊጠቅሟቸው በሚችሉ ክበቦች እና ክፍሎች ውስጥ እንዲሳተፉ ይደረጋል። በእነዚህ ተግባራት ላይ የመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች ደግሞ በንቃት ተሳትፎ በማድረግ ከጊቢው ሲወጡም ቀጥለው ለሚመጡ ተማሪዎች የሚጠቅም እና አርኣያ መሆን የሚችል ስምን ተክለው ይወጣሉ።
በዛሬው የወጣቶች አምዳችን የተማሪነት ጊዜያቸው ሳይገድባቸው እውቀታቸውን እና ጊዜያቸው ተጠቅመው ጓደኝነታቸውን እና ሕብረታቸውን ለመልካም ሀሳብ ካዋሉ ወጣቶች ጋር ነው።
አቤኔዘር አብዮት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒዬም ሜዲካል ኮሌጅ ውስጥ የሕክምና ተማሪ ነው። በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሕክምና ትምህርት ክፍልን ለመማር የመረጡ ተማሪዎች የሚማሩት በዚያው በሆስፒታል ውስጥ ነው። አቤኔዘርም በሆስፒታል ውስጥ ከሌሎች የሕክምና ተማሪዎች ጋር በሆስፒታል ውስጥ የመማር እድሉን አግኝተዋል። በመሆኑም ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ሆስፒታሉ ውስጥ ያሉ ታካሚዎችንም ሆነ የአገልግሎት አሰጣጡን በቅርበት የመመልከት እድሉ አላቸው።
አቤኔዘርና ጓደኞቸ በሆስፒታሉ ውስጥ አዲስ ተማሪ በመሆናቸው በክፍል ውስጥ የሚማሩበት እንጂ ለተግባር ትምህርት ገና የሆኑበት ሰዓት ነበር። ታዲያ ከእነሱ ቀድመው ወደ ጊቢው ገብተው የሚማሩ የሕክምና ተማሪ ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን አቤኔዘር ሆስፒታሉን ከጓደኞቹ ጋር ተዘዋውሮ ለማየት ሞክረዋል።
ከሀኪም የታዘዘላቸውን መድሀኒት መግዛት ያልቻሉ ታካሚዎች፣ እንደቤተሰብ ድጋፍ የሚፈልጉ የሚያዳምጣቸው፣ የሚጎበኛቸው ሰው የናፈቃቸው ታካሚዎች፣ ሆስፒታሉ ሰፊ እና የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጡበት በመሆኑ ታካሚዎች መሄድ የሚፈልጉበትን ክፍል በቶሎ ለማግኘት መቸገር (ቦታን በትክክል አለማወቅ)፣ በሆስፒታሉ ውስጥ በሚቆዩበት ጊዜ ሕክምናቸውን ጨርሰው እስከሚወጡ ድረስ በቂ ምግብ ማግኘት ያልቻሉ አቅሙ የሌላቸው ታካሚዎች፤ በሆስፒታሉ ውስጥ በብዛት የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው። እነዚህ ችግሮች አቤኔዘር እና ጓደኞቹን ከተማሪነት ባለፈ እንዲያስቡ አድርጓቸዋል።
ተማሪ ሆነው ሲቆዩም ችግሮቹን እንዲሁ ከመመልከት ይቅር የመፍትሄው አካል ለመሆን በማሰብ በሕብረት ድጋፎችን ማድረግ ጀመሩ፤ ይህም ሀሳብና ድጋፍ ለአንድ ዓመት ያክል ቆየ። ነገር ግን ይላል አቤኔዘር ‹‹ የሕክምና ትምህርት ስድስት ዓመት ይፈጃል። ይህን ሁሉ ዓመት ተምረን ስናበቃ ሀኪም/ ዶክተር እንባላለን። ነገር ግን ‹‹ ሜዲካል ዶክተር›› አልያም ሀኪም መባላችን ብቻውን በሆስፒታል ውስጥ የምናያቸውን ችግሮች አይፈታልንም። ስለዚህ ከስር ጀምሮ በጊዜ ሂደት እየተሰራባቸው መፍትሄ ሊሰጥባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ላይ በማተኮር እየሰራንባቸው እንገኛለን። ››
ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ በግላቸው እና በቡድን ያደርጉት የነበረውን ድጋፍ የተሻለ መፍትሄ ለማምጣት የተደራጀ አሰራር ያስፈልገው ነበር። በመሆኑም አቤኔዘር እና ጓደኞቹ በሆስፒታሉ ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን ጉዳዩ ወደሚመለከታቸው አካላት በመሄድ በቂ የሆነ መረጃን መሰብሰብ እና ጥናት ማካሄድ ጀመሩ። ‹‹መረጃ ለመሰብሰብ በሄድንባቸው ክፍሎች የነበረው ሀሳብ እና ድጋፍ እንድንቀጥልበት እና እዚህ እንድንደርስም አድርገውናል፤ ለዚህም እናመሰግናቸዋለን። ›› ይላል።
በሄዱባቸውም ክፍሎችም ሀሳባቸውን በመደገፍ የተሻለ አደረጃጀት ይኖረው ዘንድ የሚረዳ ስልጠና እንዲያገኙ እገዛ ተደርጎላቸዋል። ከወሰዷቸው ስልጠናዎች በመነሳት እና ሊያሳኳቸው በሚፈልጓቸው ሀሳቦች ላይ በመመርኮዝ ዓላማ፣ እቅድ፣ ራዕይ ያለው ቡድን መመስረት ቻሉ። ስሙንም ‹‹ ምርኩዝ የሕክምና ተማሪዎች ኢኒሼቲቭ ›› በማለት ሰየሙት። ‹‹ ምርኩዝ ›› ሌላኛው መጠሪያው ከዘራ ሲሆን እድሜያቸው የገፉ አዛውንቶች የታመሙ እና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ተደግፈው መድረስ የሚፈልጉበት ቦታ የሚጓዙበት ነው። በመሆኑም አቤኔዘር እና ጓደኞቹ የመሰረቱት ተነሳሽነትም በሆስፒታል ውስጥ ላሉ ታካሚዎች ምርኩዝ መፍትሄ፣ እፎይ መባያ መሆን ድካምን መጋራት ዓላማቸው ነው እና ምርኩዝ ሊሉት ችለዋል።
ዓላማውም በሆስፒታሉ ውስጥ ያሉ እገዛ የሚያስፈልጋቸውን ታካሚዎች በገንዘብም፤ በሀሳብም መደገፍ ሲሆን በዋናነት የሕክምና ተማሪዎች በሕክምና ተቋማት ውስጥ ሳሉ ለታካሚዎች የሚያሳዩትን የአገልጋይነት መንፈስ መጨመር ታካሚዎች በሚያገኙት አገልግሎት እንዲደሰቱ ማድረግ ነው።
ምርኩዝ የሕክምና ተማሪዎች ኢኒሼቲቭ በ18 የሕክምና ተማሪዎች የተመሰረተ ሲሆን አሁን ላይ የሶስተኛ ዓመት የሕክምና ተማሪ በጊዜው ግን የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች በነበሩ የተመሰረተ ነው። ይፋዊ አድርገው ተነሳሽነቱን ከጀመሩ ደግሞ አንድ ዓመት ከስምንት ወር ያክል ጊዜ ሆኗቸዋል። አሁን ላይ የሕክምና ተማሪዎች የሆስፒታሉ ማኅበረሰብ አካቶ 140 አባላት በውስጡ ይገኛሉ።
አቤኔዘር በምርኩዝ የሕክምና ተማሪዎች ኢኒሼቲቭ ውስጥ መስራችና አባል ነው። ኢኒሼቲቩ የራሱ ቦርድ፣ መስራች አባላት እና አጠቃላይ አባላት አሉት። በስሩም ሶስት ፕሮጀክቶችን ይዞ እየሰራ ይገኛል። ፕሮጀክት ጠያቂ፣ ፕሮጀክት ጠቋሚ እና ፕሮጀክት መድሀኒት ይገኙበታል። እንደ አቤኔዘር ገለጻ ፕሮጀክት ጠያቂ በምርኩዝ ኢኒሼቲቭ ውስጥ በመጀመሪያ ስራ የጀመረው ፕሮጀክት ነው። ዋናው ዓላማው ለታካሚዎች የስነልቦና ድጋፍ ማድረግ እና በሕክምና ተማሪዎች ዘንድ የአገልጋይነት ስብዕናን ማሳደግ ነው። በዚህ ፕሮጀክት አባላቱ በሚወጣላቸው ፕሮግራም በየሳምንቱ ዓርብ በሆስፒታሉ ያሉ ታካሚዎችን እንደ ሀኪም ሳይሆን እንደቤተሰብ እንደ ጓደኛ ይጠይቋቸዋል። በሶስት ወር አንዴ ደግሞ ከሌሎች ስፖንሰር እና ድጋፍ አድራጊ ተቋማት ጋር በመሆን የተለያዩ ዝግጅቶችን በማድረግ በሆስፒታሉ የሕጻናት የሕክምና ክፍል የሚታከሙ ሕጻናትን ያዝናናሉ ስጦታ ይሰጣሉ።
‹‹በየሳምንቱ ታካሚዎችን በምንጎበኝበት ወቅት ብዙ የተረበሹና የተቸገሩ፣ ሰው የናፈቃቸው ታካሚዎች እናገኛለን። አንዳንዶች ደግሞ ከሶስት ወር በላይ በሆስፒታል ውስጥ ሕክምና የሚያደርጉ ናቸው። እነዚህ ታካሚዎች የገንዘብ ችግር ባይኖርባቸውም አልጋ ላይ ተኝተው በመዋላቸው ብቻ የሚፈጥርባቸው የስሜት መረበሽ አለ።›› የሚለው አቤኔዘር፤ ማንኛውም የጤና ባለሙያም ሆነ ተማሪ ወደ እነሱ የሚቀርበው እንደ ሀኪም እንጂ እንደ ቤተሰብ አለመሆኑን አስታውሶ‹‹ እኛ ደግሞ የሕክምና ተማሪዎች መሆናችንን ትተን እንደቤተሰብ ስንቀርባቸው በጣም ደስተኞች ናቸው። በሚሰጡን ምላሽ ውስጥ የምናገኘውንም ምርቃት ለምደነዋል።›› አቤኔዘርና አባላቱ የሚጋሩት ሀሳብ ነው።
ሌላኛው በስራ ላይ ያለው ‹‹ ፕሮጀክት ጠቋሚ ›› ነው። ሆስፒታሉ የተለያዩ አገልግቶችን የሚሰጥ እና ሰፊ በመሆኑ ታካሚዎች በቀላሉ መሄድ የሚፈልጉበትን ቦታ ለማግኘት ይቸገራሉ። በምርኩዝ ኢኒሼቲቭ ውስጥ የተካተተው ይህ ፕሮጀክትም በጎ ፍቃደኛ ከሆኑ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እና ሌሎቸ ክበቦች ጋር በጥምረት በክረምት ወራት ላይ አሰማርተዋል። ነገር ግን አሁን ሰዓቱ የትምህርት በመሆኑ በጎፍቃደኛ ተማሪዎቹም በትምህርት ላይ ይገኛሉ። ኢኒሼቲቩ አሁን ላይ ሌሎች በጎፍቃደኞችን እየተቀበለ ሲሆን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ያስችል ዘንድ ለሁሉም ሰው ምቹ የሆነ እና በቀላሉ ማንኛውም ሰው ሊረዳው የሚችል በእጅ የሚያዝ ጠቋሚ ካርታ ለማዘጋጅ በሂደት ላይ ነው።
ሌላኛው ከሆስፒታሉ የአስተዳደር ክፍል ይሁንታን እየጠበቀ የሚገኘው ‹‹ ፕሮጀክት መድሀኒት ›› የተሰኘው ነው። ብዙ ሰዎች ከሀኪም የታዘዘላቸውን መድሀኒት በቶሎ ለማግኘት አለፍ ሲል ደግሞ በአቅም ማነስ ምክንያት መድሀኒቱን ገዝተው መጠቀም አይችሉም። ይህ ደግሞ በቀላሉ ሊታከሙ የሚችሉትን ሕመም ይዘው እንዲቆዩ እና ምናልባትም መድሀኒቱን በማጣት ሕይወታቸውን ማጣት ደረጃ ሊያደርሳቸው ይችላል። ችግሩን ለመቅረፍ እየተሰራ ያለ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አንጻር ምርኩዝ ኢኒሼቲቭም እንደ አንድ ፕሮጀክት ሊይዘው ችሏል። ፍቃድ ሲያገኝም የብዙዎችን ሕይወት ሊታደግ እና ጭንቀት ሊጋራ እንደሚችል አቤኔዘር ገልፇል።
ፕሮጀክቱ የሆስፒታሉን ማኅበረሰብ አካቶ በአብዛኛው በሕክምና ተማሪዎች የሚንቀሳቀስ ሲሆን የሕክምና ተማሪዎች በአንጻሩ ከሌሎች የትምህርት ክፍሎች በተለየ በጣም የታጠበ እና አብዛኛውን ሰዓታቸውን በትምህርት እና በጥናት ያሳልፋሉ። በዚህም ምክንያት እንደሌሎች ተማሪዎች ሰፊ የሆነ ሰዓት እንደሌላቸውና አብዛኛው ሰዓታቸው በቤተመጽሀፍት ውስጥ እንደሆነ ብዙዎች የሚስማሙበት ነው። ታዲያ ለምርኩዝ የሕክምና ተማሪዎች ኢኒሼቲቭ አባላት ከያዙት ዓላማ አንጻር ይህ አንዱ ተግዳሮት ነው። የማኅበሩ መስራች የሆነው አቤኔዘርም እንዲህ ይላል ‹‹ ይህ አሁንም ድረስ የምንቸገርበት ጉዳይ ነው። በተለይ ደግሞ ፈተና በሚኖርበት ሰዓት በጣም የተጣበበ ሰዓት ነው ሚኖረን። ›› ይላል ይህን ችግርም ለመፍታት በሀሳቡ የሚስማሙ አብረዋቸው የሚማሩ ተማሪዎችን አባል በማድረግ፣ የሰው ኃይል በመጨመርና የስራ ክፍፍሎችን በማድረግ የሚኖረውን መጨናነቅ ለመቀነስ እየሰሩ ነው። ›
ኢኒሼቲቩ ለሚያደርጋቸው ድጋፎችም የገንዘብ ምንጩ እነዚሁ አባላት ናቸው። ‹‹ ይህንን የአገልጋይነት መንፈስ ከተማሪነት ጀምሮ እያዳበርነው ከሄድን በሂደት የሚመጡት የጤና ባለሙያዎች ታካሚዎችን በማገልገል እና በመንከባከብ የማይደራደሩ ይሆናሉ።›› አቤኔዘር በሕክምና ተቋማት ውስጥ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑም አንስቷል።
በሆስፒታል ውስጥ የሚሰሩ እና በቀጥታ ከታካሚዎች ጋር የሚገናኙ የጤና ባለሙያዎች ከሚያስተናግዷቸው ከፍተኛ የታካሚ ቁጥር እና ከሚያሳልፉት ከፍተኛ የስራ ሰዓት ምክንያት የሚገጥማቸው የስሜት መወጠር ታካሚዎችን በአግባቡ ለማስተናገድ መቸገር ይታይባቸዋል። ሌላኛው በስፋት የሚታየው ችግር ደግሞ ታካሚዎች የታዘዘላቸውን መድሀኒት በቶሎ አለማግኘት በተለይም ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠየቅባቸው መድሀኒቶች እጥረት አለ። በዚህ ሰዓት የጤና መድህን የሌላቸው ታካሚዎች ከኪሳቸው ከፍተኛ ወጪ ለማውጣት ይዳረጋሉ። እነዚህን መሰል ተቋማት እና ማኅበራት መቋቋማቸው ችግሮችን ከስራቸው ለመፍታት ያስችላል።
ይህ በአንድ ሆስፒታል ውስጥ የተጀመረው የተማሪዎች ሕብረት በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች እንዳለ ሁሉ ምርኩዝም ሀሳቡ በእያንዳንዱ የሕክምና ኮሌጅ ውስጥ ማስፋፋት፣ በማዕከልነት የያዘውን የአገልጋይነት መንፈስ ሌሎች እንዲጋሩት ማድረግ፣ ከዚያም እንደ ዋና ችግር የሚታዩ የመድሀኒት እጥረት፣ ሰፋ ባለ መልኩ ለመስራት ጥረት ያደርጋሉ። ምርኩዝም በሌሎች ኮሌጆች ውስጥ በተዋወቀ ቁጥር የሚኖረው ተደራሽነትም እየሰፋ ይሄዳል በእቅድ ውስጥ የተያዘ ነው።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2016 ዓ.ም