እስራኤል የተኩስ አቁም ተደራዳሪ ቡድኗን ከዶሃ አስወጣች

እስራኤል የተኩስ አቁም ተደራዳሪ ቡድኗን ከኳታር አስወጣች።

በኳታርና ግብፅ አደራዳሪነት በዶሃ ሲካሄድ የቆየው ንግግር በሃማስ ቅድመ ሁኔታዎች ምክንያት ሳይሳካ መቅረቱን የእስራኤል ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

በድርድሩ ላይ ለተሳተፉት የእስራኤል የስለላ ድርጅት ኃላፊ ቅርበት ያላቸው ግለሰብን ዋቢ አድርጎ ሬውተርስ እንደዘገበው፥ እስራኤል በጋዛ የሚገኙት የሃማስ መሪ ያህያ ሲንዋር ድርድሩን እያወኩ ነው በሚል ከሳለች።

ሃማስ በበኩሉ እስራኤል የተኩስ አቁም ድርድሩ እንዲጓተት የምትፈልገው በጋዛ ድብደባዋን ለመቀጠል ነው ሲል ወቅሷል።

እስራኤልና ሃማስ ለስድስት ሳምንታት ተኩስ አቁመው ከ130 የእስራኤል ታጋቾች 40ዎቹ እንዲለቀቁ ነበር ድርድር ሲደረግ የቆየው።

ሃማስ የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ ሙሉ በሙሉ የሚወጡበትና ጦርነቱ የሚቆምበትን እንጂ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ላይ መደራደር እንደማይፈልግ መግለጹ ተዘግቧል።

የፍልስጤሙ ቡድን በጦርነቱ ምክንያት ወደ ደቡባዊ ጋዛ የተፈናቀሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱም ጠይቋል።

እስራኤል ሃማስ በጠየቀው ልክ ባይሆንም የተወሰኑ ፍልስጤማውያን ወደ ሰሜናዊ ጋዛ በመመለስና ከ700 እስከ 800 ፍልስጤማውያን እስረኞችን በመፍታት ታጋቾችን ለማስለቀቅ ተስማምታ ነበር።

ይሁን እንጂ ሃማስ ፍልስጤማውያን ተኩስ እንዲቆም እንደማይፈልጉ ያመላከተ “ቅዠት” የሚመስል ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ።

ከዚህ ቀደምም የቡድኑን ቅድመ ሁኔታዎች የሚያጣጥሉት ኔታንያሁ ጦራቸው ከጋዛ እንደማይወጣና ጦርነቱ እንደሚቀጥል የሚያሳይ መግለጫ አውጥተዋል።

በቴልአቪቭ የሚገኙ ከ300 በላይ የታጋቾች ቤተሰቦች በአስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርሶ ታጋቾቹ እንዲለቀቁ በሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር ቢሮ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።

እስራኤል የፀጥታው ምክር ቤት በጋዛ በአስቸኳይ ተኩስ እንዲቆም የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ባፀደቀ ማግስት ተደራዳሪዎቿን ከዶሃ አስወጥታለች።

በራፋህ እና በሌሎች ከተሞች እየፈጸመችው ያለው ጥቃትም ይበልጥ እየጨመረ መሄዱን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አኃዛዊ መረጃዎች ያሳያሉ።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2016 ዓ.ም

Recommended For You