የብሪታንያ ፓርላማ አከራካሪውን ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ እቅድ አፀደቀ

የብሪታንያ ፓርላማ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ እቅድ አፀደቀ።

ከሁለት ዓመት በላይ ውዝግብ ሲነሳበት የቆየውና ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሽ ሱናክ ይፋ ያደረጉት እቅድ ጥገኝነት ጠያቂዎች ጥያቄያቸው ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ በሩዋንዳ እንዲቆዩ የሚያደርግ ነው።

በብሪታንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት “ሕገወጥ” ነው ተብሎ ውድቅ የተደረገው፤ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች “ከሰብዓዊነት የራቀ ነው” በሚል ሲተቹት የቆዩት እቅድ ከትናንት በስቲያ በብሪታንያ ፓርላማ ሕግ ሆኖ እንዲወጣ ድምፅ ተሰጥቶበታል።

ይህን ተከትሎም ከ10 እስከ 12 ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ ጥገኝነት ጠያቂዎችን በአውሮፕላኖች ወደ ሩዋንዳ ማጓጓዝ እንደሚጀመር ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ የገለጹት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቃዋሚዎቻቸው ሕጉ እንዳይፈጸም ግፊታቸውን እንዲቀጥሉ ያደርጋል በሚል ምን ያህል ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ስለመታቀዱ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

ቢቢሲ ግን በሕገወጥ መንገድ ወደ ብሪታንያ የገቡ ከ52 ሺህ በላይ ስደተኞች ወደ ኪጋሊ እንደሚላኩ ነው የዘገበው።

ይሁን እንጂ ወደ ሩዋንዳ እንዲመለሱ የሚወሰንባቸው ስደተኞች በፍርድቤት ይግባኝ መጠየቅና መከራከር ይችላሉ መባሉ የእቅዱን በተያዘለት ጊዜ ተፈጻሚነት ጥርጣሬ ውስጥ ከቶታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ በበኩላቸው የየትኛውም ሀገር ፍርድ ቤት ሕጉን ተፈጻሚ ከማድረግ አያግደንም ሲሉ ተደምጠዋል።

በ2022 በአነስተኛ ጀልባዎች 45 ሺህ 774 ሕገወጥ ስደተኞች ወደ ብሪታንያ የገቡ ሲሆን፥ ባለፈው ዓመት አኃዙ ወደ 29 ሺህ 437 ዝቅ ብሏል።

ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላኩ እቅድ ተፈጻሚ ከሆነም ወደ ብሪታንያ የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር በእጅጉ መቀነስ ይቻላል ተብሏል።

ብሪታንያ ወደ ሩዋንዳ ለምትልካቸው ጥገኝነት ጠያቂዎች በነፍስ ወከፍ 215 ሺህ ዶላር እንደምታወጣ ማሳወቋ የሚታወስ ነው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You