የሰሜን ኮሪያ መረጃ መንታፊዎች የደቡብ ኮሪያን የመከላከያ ኩባንያዎች ማጥቃታቸው ተነገረ

የሰሜን ኮሪያ መረጃ መንታፊዎች የደቡብ ኮሪያን የመከላከያ ኩባንያዎች ማጥቃታቸው ተነገረ።

የሰሜን ኮሪያ መረጃ መንታፊ ቡድኖች ለአንድ ዓመት ያህል አጠቃላይ ጥቃት በመክፈት የደቡብ ኮሪያን የመከላከያ ኩባንያዎች የውስጥ ኔትወርክ በመስበር መረጃ መስረቃቸውን የደቡብ ኮሪያ ፖሊስ በትናንትናው ዕለት አስታውቋል፡፡

ዛሩስ እና ኪምሱኪ ተብለው የሚጠሩት እነዚህ የመረጃ መንታፊ ቡድኖች ከሰሜን ኮሪያ የደኅንነት ቢሮ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው እና በመከላከያ ኩባንያዎች ዳታ ሲስተም ውስጥ የተሳሳተ ኮድ ማስገባታቸውን ፖሊስ ገልጿል።

ፖሊስ ከብሔራዊ የደኅንነት ቢሮ እና ከግል ዘርፍ ባለሙያዎች ጋር በመሆን መንታፊዎቹን በአይፒ አድሬስ እና በተጠቀሙት ማሌዌር አማካኝነት መለየት ችሏል።

በፈረንጆቹ 2022 በተጀመረው በዚህ ጥቃት፣ መንታፊዎች በኩባንያው ፐብሊክ ኔትዎርክ ውስጥ የተሳሳተ ኮድ በማስገባት የውስጥ ለውስጥ መረጃ ልውውጡ እንዲታወክ እና ሲስተሙን ከጥቃት የሚጠብቀው የሴኩሪቲ ፕሮግራም በጊዜያዊነት እንዳይሠራ አድርገዋል ብሏል ፖሊስ።

መንታፊዎች ለግል እና ለኦፊሴላዊ ኢሜል ተመሳሳይ የይለፍ ቃል የሚጠቀሙ የኩባንያው ሠራተኞች ያሳዩትን የደኅንነት ክፍተት በመጠቀም የመከላከያ ኩባንያዎችን ኔትወርክ ሰብረው በመግባት ምስጢራዊ መረጃ ወስደዋል።

ፖሊስ ጥቃት የደረሰበት ኩባንያ የትኛው እንደሆነ እና የተወሰደው የመረጃ አይነት ምን እንደሆነ ግልጽ አላደረገም።

ደቡብ ኮሪያ በዓለም ቀዳሚ ከሚባሉት የጦር መሣሪያ ላኪ ሆና ብቅ ብላለች። በቅርብ ዓመታት ውስጥ ሀገሪቱ ዋጋቸው በቢሊዮን ዶላሮች የሚገመት ሜካናይዝድ ሀውቲዘር፣ ታንክ እና ተዋጊ ጀቶችን ለመሸጥ ስምምነቶች ተፈራርማለች።

የሰሜን ኮሪያ የመረጃ መንታፊ ቡድኖች በደቡብ ኮሪያ የፋይናንስ ተቋማት፣ የሚዲያ ተቋማት እና በውጭ የመከላከያ ኩባንያዎች እንዲሁም በ2024 በኑክሌር ኃይል ኦፕሬተር ላይ ጥቃት አድርሰዋል።

ሰሜን ኮሪያ ግን ከጥቃቶቹ ጀርባ እጇ እንደሌለበት ታስተባብላለች።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You