«ኔት ወርክ የለም»?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ወደተለያዩ አገልግሎት መስጫ ተቋማት የሄደ ሰው በተደጋጋሚ ከሚያደምጣቸው ቃላት መሃል ‹‹ኔት ወርክ የለም ››የሚለውን አባባል የሚስተካከል ያለ አይመስለኝም፡፡ ግብር ለመክፈል ኔት ወርክ የለም፤ የኤሌትሪክ ቢል ለመክፈል ኔት ወርክ ለም፤ የውሃ ቢል ለመክፈል ኔት ወርክ የለም፤ የቤት ኪራይ ለመክፈል ኔት ወርክ የለም፤ ብር ከባንክ ለማውጣትና ለማስገባት ኔት ወርክ የለም ብቻ በአጠቃላይ ኔት ወርክ የለም የሚለው ቃል ሀገሩን አጥለቅልቆታል፡፡

በእርግጥ ይህ ሁሉ ኔት ወርክ የለም የምር ኔት ወርክ ስለሌለ ነው ወይስ ሰነፎችና ሙሰኞች የፈጠሩት ማምለጫ ? የሚለውን መፈተሽ ይገባል። እንደ እኔ ግን አልፎ አልፎ ከሚያጋጥመው የኔት ወርክ መቆራረጥ ውጪ በረባ ባልረባው ኔት ወርክ የለም በሚል ሰበብ አቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች ሳይቀሩ ‹‹ነገ ና፤ ከነገ ወዲያ ና›› በሚል ተገልጋይን ከፊት ለማራቅ የሚደረግ ሙከራ የሚበዛ ይመስለኛል፡፡

አብዛኞቹ አገልግሎት ሰጪ ተቋሞቻችን ለደንበኛ አገልግሎት ክብር ስለሌላቸው ተገልጋይን ከፊት ማራቅን እንደ አንድ ስልት ሲጠቀሙበት ማየት የተለመደ ነው፡፡ ለተቸገረ ደንበኛ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ችግሩን ተሸክሞ ከቢሮ ወጥቶ እንዲርቅ የማድረግ ስልትን ይጠቀማሉ፡፡ በአግባቡ ከመነጋገርና ችግርን ከመፍታት ይልቅ ‹‹አይሆንም፤ አይቻልም›› የሚሉ ሃሳችን በመደርደር ደንበኛ መፍትሄ ሳያገኝ እንዲሄድ ማድረግ የተለመደ ነው።

አብዛኞቹ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አርፍዶ በመግባትና ቶሎ በመውጣት፤ ሕዝብን በማጉላላት፤ ምልጃ በመጠየቅ፤ በትውውቅና ዘመድ አዝማድ መስራት፤ በማመናጨቅ ጭምር የተገልጋይን ቆሽት የሚያደብኑ መሆኑን የደረሰበት ያውቀዋል፡፡ ብዙዎችም ‹‹ሰው ጤፉ›› የሚባሉ አይነት ናቸው፡፡

አገልግሎት አሰጣጥ ሳይንስ ነው፤ ጥበብ ነው አልፎ ተርፎም ተሰጥኦንም የሚጠይቅ ሙያ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ቅንነትን ይፈልጋል፡፡ የደከሙ እናቶችን፤ አካል ጉዳተኞችን፤ እርጉዞችን እየተመለከተ ግድ የማይሰጠው ሰራተኛ ወይም ኃላፊ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥበብ ገብቶታል ማለት አይቻለም፡፡ ወይም ደግሞ አገልጋይ ነኝ ብሎ ራሱን መቁጠር አይችልም፡፡

ይህ ሰው ሳይንሳዊ እውቀቱ ቢኖረውም ቅንነት ካልታከለበት በመደበኛ ትምህርት ቤት ገብቶ የቀሰመው ዕውቀት የጋን ውስጥ መብራት ከመሆን አያልፍም፡፡ ከራሱ ተርፎ ለማኅበረሰቡ ጠብ የሚል ነገር የለውም፡፡

በርካታ ተቋማት የስነምግባር መርሆች ብለው መግቢያ በራቸው ላይ ዝርዝር ነጥቦችን በማስታወቂያ መልኩ ይለጥፋሉ፡፡ 12 ስነ ምግባር መርሆች ተብለውም ይታወቃሉ፡፡ ከእነዚህ ስነ ምግባር መርሆች ውስጥ በተራ ቁጥር አንድ የሚቀመጠው ቅንነት ነው፡፡ ቅንነት የሁሉም ነገር መሰረትና መነሻ በመሆኑ ቅድሚያ መሰጠቱ አግባብ ቢሆንም አተገባበሩ እና ክትትሉ ላይ ግን ጥያቄ የሚነሳበት ነው፡፡

ቅንነት ተራ ቁጥር አንድ ሆኖ እንደተቀመጡ የትኛው ሰራተኛ ነው በዚህ ደረጃ ትኩረት ሰጥቶ በቅንነት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ የሆነው። እንደፋሽን በየቦታው የበዛው ‹‹ኔት ወርክ የለም›› የሚለው ምላሽስ ምን ያህል እውነተኛ ነው፡፡ ወይንስ ተገልጋይን ለማራቅና ለሙስና ለማመቻቸት ከቅንነት ውጪ እየተሰራ ያለ ስራ ነው፡፡

በየቦታው ተዘዋውሮ ለተመለከተው ሕብረተሰቡ ከተማረረባቸው ቃላት ውስጥ ‹‹ኔት ወርክ የለም ›› የሚለው ቀዳሚው ነው፡፡ ‹‹ኔት ወርክ የለም ››የሚለውን ቃል የሚሰማ ተገልጋይ ወሽመጡ ቁርጥ ይላል፡፡ ጉዳዩን ጨርሼ ቶሎ ወደ ስራዩ እመለሳለሁ ብሎ ያሰበ ሁሉ ፊቱ በሀዘን ድባብ ይዋጣል፡፡ ኔት ወርክ እስኪመጣ ድረስም ወዲህ እና ወዲያ እያሉ መጠበቅም ግድ ይሆንበታል፡፡ በአጠቃላይ ኔት ወርክ የለም የሚለው ከንግግሩ ጀምሮ ይዟቸው የሚመጣው መዘዘም ሁሉ አሰልቺዎች ናቸው፡፡

ከሁሉ የከፋው ደግሞ ጠፋ የተባለው ኔት ወርክ የሚመጣበት ጊዜ አለመታወቁ ነው፡፡ ደቂቃዎችን ይቆይ ሰዓታትን አለፍ ሲልም ቀናትን ሊቆይ ይችላል፡፡ ይህንን የሚያውቀው አንዳንድ ጊዜ ቴሌ ብዙ ጊዜ ግን አገልግሎቱን የሚሰጡት ሰራተኞች ናቸው፡፡ የአገልጋይነት መንፈሱ ያላቸውና ቅን የሆኑ አገልጋዮች ኔት ወርክ ጠፋ ሲባል እነሱም ይጨነቃሉ፤ የተገልጋዩ እንግልት ይሰማቸዋል፡፡

የኔት ወርክ መጥፋትን እንደ ሰርግ የሚቆጥሩ ለተቀመጡበት ቦታ የማይመጥኑ ሰነፍ እና ሙሰኛ ሰራተኞችና አመራሮችም አሉ፡፡ አጋጣሚውን በመጠቀም ከቢሮ ሾልኮ ለመውጣትና የራሳቸውን ጉዳይ ለማከናወን ሲጠቀሙበት ይታያል። አንዳንዶቹም በተሽከርካሪ ወንበራቸው ላይ ተቀምጠው ስልካቸውን መነካካት ደስታ ይሰጣቸዋል፡፡

ብዙዎች እንደሚናገሩት ግን ሲስተሙን በመነካካት ኔት ወርክ እንዲጠፋና ሕብረተሰቡ እንዲጉላላ ያደርጋሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ተገልጋዩ ሲጨንቀው በሙስና ጉዳዩን ለማስጨረስ ይገደዳል፡፡ ሙሰኞችም ስራቸውን ያጧጡፋሉ፤ ኪሳቸውን ያደልባሉ፡፡ ስለዚህም ኔትወርክ የለም የሚለው አባባል ለሙሰኞች የማይደርቅ የገቢ ምንጭ ሆኗል ማለት ነው፡፡

አንድ ጓደኛዬ የገጠመውን እዚህ ጋር ባነሳ ለዚሁ አባባሌ ማሳያ ይሆንልኛል፡፡ ጓደኛዬ ነጋዴ ነው፡፡ እንደልማድ ሆኖበት ግብር የሚከፍለው በመጨረሻዎቹ ቀናት ነው፡፡ ይህንን የሚያውቁ የገቢ መስሪያ ቤቱ ሰራተኞች በመጨረሻዎቹ ቀናት ኔት ወርክ የለም በሚል ስራ ያቆማሉ፡፡ ጓደኛዬም የሚመጣበትን ቅጣት እያሰበ ይጨነቃል፡፡ ቅጣቱ ደግሞ ከፍተኛ ከመሆኑም ባሻገር ብዙ መጉላላትን የሚያስከትል ነው፡፡ የጨነቀው እርጉዝ ያገባል እንደሚባለው እሱም ሆነ ሌሎች ነጋዴዎቹ ጉዳያቸውን በምልጃ ለማስፈጸም ይገደዳሉ፡፡

ይኸው የእኔ ጓደኛም በተደጋጋሚ በዚህ መልኩ ጉዳዩን እያስፈጸመ ይገኛል፡፡ ኔት ወርክ የለም የሚለው አባባልም ተገልጋይን አጣብቂኝ ውስጥ ለመክተት የተዘረጋ ስልት ነው ይላል፤ በተደጋጋሚ ከደረሰበት ችግር በመነሳት፡፡ ስለዚህም ‹‹ኔት ወርክ የለም›› ሲባል እውነት ነው ወይ ? የሚለውን መፈተሹ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ካልሆነም ተገልጋዩ ኔት ወርክ መሄዱን የሚያረጋግጥበት መንገድ ሊኖር ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን አሁንም በኔት ወርክ የለም ሰበብ ብዙዎች ለሙስና መጋለጣቸው አይቀሬ ነው፡፡

ውጤቱን በጉጉት እና በተስፋ ለሚጠብቅ ተስፈኛ ሕዝብን ኔት ወርክ የለም በሚል ተስፋ እንዲቆርጥ ማድረግ ምን ያህል ኢሞራላዊ ድርጊት እንደሆነ የደረሰበት ሁሉ ያውቀዋል፡፡

ግልጽ የሆነ አገልግሎት ለአገልግሎት ፈላጊው ሕዝብ ማቅረብ ግዴታ ሲሆን ለተገልጋዩም መብት ነው፡፡ በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 12 እንደተደነገገው የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 12/2/ “ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ ይሆናል” በማለት ደንግጓል፡፡

ከዚህ ሕገመንግስታዊ አንቀጽ የምንማረው አገልጋዩ ለተገልጋዩ መስጠት የሚገባውን አገልግሎት የሚሰጥበትን አሠራር ካልዘረጋ፣ በዘረጋው አሠራር መሠረት አገልግሎት ለመስጠት የገባውን ቃል ግልጽነትና ጥራት ባለው መንገድ ካልሠጠ እና የመንግሥት ሕጎችን፣ ደንቦችን መመሪያዎችንና አሠራሮችን ካልፈፀመ ወይም ካላስፈፀመ ተጠያቂ ይሆናል፡፡

በዚህ መሠረት ሊሠጥ የሚገባው አገልግሎት ቃል ለተገባለት ሕዝብ/ዜጋ መድረስ አለመድረሱ ሲጋለጥ ቃሉን የጠበቀና ያሳካ የሚመሰገንበት፣ የሚበረታታበትና የሚሸለምበት አሰራር ሊኖር ይገባል፡፡ በአንጻሩ በገባው ቃል መሠረት ያልፈፀመ የሚመከርበትና የሚወቀስበት እንዲሁም ሆን ብሎ ያጠፋ ከሆነ ሕጋዊ ሥርዓቱን ተከትሎ የሚጠየቅበትና የሚቀጣበት ሥርዓት በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ ተግባራዊ ሊሆን ይገባል፡፡

የዚህ መርህ መሠረታዊ ቁምነገር ዜጎች በቂ መረጃ ያላቸው ሆነው ተገቢውን አቋም መያዝ የሚያስችላቸው መሆኑ ዋንኛው ጉዳይ ሆኖ መረጃ በማጣት ምክንያት ያለአግባብ የሚፈጠር አለመግባባት፣ አለመተማመንና ጥርጣሬን ከማስወገዱም በላይ ስህተትን በቀላሉ ለማወቅና ለመፍታት የሚችልበት ሁኔታን መፍጠሩ ነው። አገልግሎትን ለተገልጋዩ ግልጽ ማድረጉ ኔት ወርክ የለም እያሉ ለሚያጭበረብሩትም መፍትሄ ሳይሆን አይቀርም፡፡

ግልጽነትን ከማስፈን ባሻገር ቢያንስ የእያንዳንዱን ተቋም አሰራር መፈተሽ፤ መከታተልና መደገፍ የመንግስት አንዱ የትኩረት አቅጣጫ መሆን ይኖርበታል፡፡ ከዚህ አንጻር ሰሞኑን የመንግስት ከፍተኛ ስራ ኃላፊዎች እያደረጉት ያለው የክትትልና ድጋፍ አካሄድ የሚበረታታ ነው፡፡

የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ከከተማ እስከ ገጠር በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚባል መልኩ አርሶ አደሩ ድረስ በመውረድ ምልክታ እያደረጉ ነው፡፡ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እያደረጉት ያለው ምልከታ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ክልሎች ያሉ ሐብቶችና ጸጋዎችን በአግባቡ ለመጠቀም እንዲቻል እና የሚነሱ ቅሬታዎችንም ከኀብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ ለመፍታትም በር የሚከፍት ነው፡፡

በማንኛውም መንገድ ሕህዝብ መደመጥን ይፈልጋል፡፡ ለጥያቄዎቹ ተግባራዊ ምላሽ ይሻል፤ ካልሆነም ጥያቄዎቹ ምላሽ ያላገኙበትን ተጨባጭ ምክንቶች ማዳመጥን ይፈልጋል፡፡ ይህ ካልሆነ ሰሚ እንዳጣ፤ ተገቢው ክብር እንዳልተሰጠውና እንደተናቀ ሊቆጥር ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የመጨረሻ ውጤቱ በመንግስትና በሕዝብ መካከል መራረቅን ይፈጥራል፡፡ አሁን አሁን በኔት ወርክ ሰበብ እየተራራቀ ያለውን የአገልጋይና ተገልጋይ ግንኙነት ለመፈተሽም እድል ይሰጣል፡፡

በተለይም በዚህ የቴክኖሎጂና የግሎባላይዜሽን ዘመን ከሕዝብ እርቆ ሀገርን መምራት ከማይቻል ሁኔታ ላይ ደርሰናል፡፡ የእያንዳንዱ ዜጋ ድምፅ ዋጋ እንዳለው ሁሉ፣ የእያንዳንዱ ዜጋም ጥያቄ ዕውቅና መስጠት ሊታለፍ ከማይችልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ከሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ውጪ የሆኑ ድርጊቶች ተቀባይነት እያጡ፣ በሕዝብ ይሁንታ ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎች ተቀባይነት እያገኙ መሄድ ጀምረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ መለመድ ካለባቸው መልካም ተግባራት ውስጥ የሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ማክበር አንዱ ነው፡፡ አገር በመምራት ላይ ያለው ገዥ ፓርቲም ሆነ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ መስጠት ያለባቸው የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት የሆነውን ሕዝብ ማክበር ነው፡፡

ከሰሞኑ በመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አርሶ አደሩ ድረስ በመውረድ እየተደረጉ ያሉ ክትትሎች አንዱ የሕዝብ እውነተኛ ስሜት ማግኛ መንገድ ስለሆነ ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባው ነው፡፡

በእርግጥ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የመሰረተ ልማት እጥረት የሚታይባቸው ናቸው፡፡ ከአቅም ውስንነት አንጻር በየተቋማቱ በቂ ኔት ወርክ ዘርግቶ ተገልጋይን ማርካት ላይቻል ይችላል፡፡ ሆኖም በዚህ ሽፋን ግን ሕዝብን ማጉላላትና አልፎ ተርፎም ለምልጃ ማዘጋጀት ግን ይቅር የማይባል ኃጢያት መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡

የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ተዘዋውሮ መመልከት የቻለ ሰው ኔት ወርክ የለም የሚለው አባባል ብዙዎችን የሚያስበረግግና ተስፋ የሚያስቆርጥ መሆኑን ለመረዳት አያዳግተውም። በኔት ወርክ የለም ሽፋን በርካታ ተገልጋዮች ለእንግልትና አለፍ ሲልም ለሙስናና ብልሹ አሰራር ተጋልጠዋልና ሳይቃጠል በቅጠል እንደሚባለው ከወዲሁ የግልጽነት አሰራርን ማስፈን ለነገ የማይባል መፍትሄ ነው፡፡

አሊሴሮ

አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2016 ዓ.ም

Recommended For You