የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማቱ ተጠቃሽ ውጤት

ኢትዮጵያ ከምርትና አገልግሎት ጥራት ጋር ተያይዞ የሚገጥሟትን ችግሮች ለመፍታት፣ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆንና ያላትን የኢኮኖሚ ድርሻ ለማሳደግ እየሠራች ትገኛለች።የአገር ውስጥ አምራቾችና ላኪዎች በዓለም አቀፍ የገበያ መዳረሻዎች የዓለምን ገበያ ሰብረው መግባት እንዲችሉ በተለይም ከጥራት ጋር ተያይዞ እየገጠማቸው ያለውን ፈተና ለማሸነፍ ብቃት ያላቸው የብሔራዊ የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማት መኖራቸው የግድ ነው።

ለዚህም የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎትን በማጠናከር ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ያላትን የኢኮኖሚ ድርሻ ማሳደግ እንድትችል ሰፋፊ ሥራ እየተሰሩ ስለመሆናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።በተለይም በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን አክሪዲቴሽን ግዴታ እየሆነ በመጣበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያም በዚህ በኩል ዘመኑን የዋጀ አሰራር በመከተል አበረታች ውጤት እያስመዘገበች ስለመሆኑ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ የሚኒስቴሩ የብሔራዊ የጥራት መሠረተ ልማት ማረጋገጫ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እንዳለው መኮንን፤ ኢትዮጵያ ብሔራዊ የጥራት መሠረተ ልማት ተቋም ከገነቡ ስድስት የአፍሪካ ሀገራት አንዷ መሆን መቻሏን አብስረዋል።በዚህም የጥራት መሠረተ ልማት ደረጃን ከሚያሟሉ፣ በጣም የለማና በእጅጉ ያደገ አቅም ካላቸው ከእነዚህ ሀገሮች መካከል ተጠቃሽ መሆኗን አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ “ፓን አፍሪካን ኳሊቲ ኢንፍራስትራክቸር” የተሰኘ ተቋም በየዓመቱ የአፍሪካን የጥራት መሠረተ ልማት ደረጃን በአራት ነጥብ ከፋፍሎ የሚመዝን ተቋም ነው።በመሆኑም ተቋሙ በ2023 ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያ ባከናወነቻቸው ጠንካራ የተቋማት ሥራዎች ሶስት ነጥብ አራት ውጤት በማምጣት እንደ አፍሪካ ከተመረጡ ስድስት የለሙ፣ ያደጉና አቅም ያላቸው ሀገራት ተርታ ተመድባለች።

ሀገሪቱ በጥራት መሠረተ ልማት ልኬት እኤአ በ2014 እና 2017 በነበራት ሪፖርት ሁለት ነጥብ አራት ወይም በከፊል የለሙ እና የጥራት መሠረተ ልማት አገልግሎት ከሚሰጡ ሀገራት ደረጃ ተርታ ተሰልፋ እንደነበር አስታውሰው፣ በ2020 በተለያየ ዘርፍ የጥራት መሰረተ ልማቷን በማሳደግ ከፍ ያለ ዕድገት በማስመዝገብ ሶስት ነጥብ ሁለት ውጤት አስመዝግባ እንደነበርም ገልጸዋል።በዚያም ቢሆን በከፊል መልማት ከሚለው ደረጃ የተሻገረች አልነበረችም ያሉት አቶ እንዳለው፤ በተከናወነው ጠንካራ የተቋማት አደረጃጀት ሥራ በ2023 ሶስት ነጥብ አራት በማምጣት እንደ አፍሪካ ከተመረጡ ስድስት የተሻለ አገልግሎት ሰጪ ሀገራት መካከል አንዷ ሆናለች ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ፤ ይህንን ደረጃ ያገኘችው በሀገር ውስጥ ባለው እንቅስቃሴዋ ብቻ ተመዝኖ ሳይሆን በአህጉራዊና በዓለማቀፋዊ ዕይታ ጭምር ታይቶ እንደሆነ የገለጹት አቶ እንዳለው፤ የተመዘገበው ውጤት በዘፈቀደ የተገኘ እንዳልሆነ ተናግረዋል።መንግሥት ላለፉት አራትና አምስት ተከታታይ ዓመታት ባደረገው መጠነ ሰፊ የተቋማት ሪፎርም ሥራ የተገኘ ውጤት መሆኑን አስታውቀዋል።

ይህ የተቋማት ሪፎርም ሥራ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ ችሏል ሲሉ ጠቅሰው፣ ለተመዘገበው አበረታች ውጤትም ገለልተኛ የሆኑ ተቋማት ምስክርነት መስጠታቸውን ተናግረዋል፤ እነዚህ ተቋማት ኢትዮጵያ በብሔራዊ ጥራት መሰረተ ልማት በዓለም አቀፍ እንዲሁም በአህጉር ደረጃ ያለችበትን የአቅም ደረጃ በሪፖርት ማስታወቃቸውን አመልክተዋል፡፡

‹‹የጥራት ጉዳይ የሁሉም የማኅበረሰብ አካል ጉዳይ ነው፤ ጥራት የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት ነው›› ያሉት አቶ እንዳለው፤ ሁሉም ዜጋ ተቋማቱ ያሉበትን ደረጃ ማወቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል።ጥራት የሌለውን ምርት የትኛውም የገበያ መዳረሻ ወስዶ መሸጥ እንደማይቻል ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ብሔራዊ የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማትን ገንብታ በአፍሪካ ይህን መስፈርት ካሟሉ አገራት መካከል አንዷ መሆኗ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ገልጸዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ከጠቀሜታዎቹ አንደኛው የኢንዱስትሪም ሆነ የግብርና ምርቶችን የጥራት ደረጃ በመቆጣጠር ማኅበረሰቡ ከጤና፣ ከአካባቢና ከደህንነት አንጻር ደህንነታቸው የተጠበቀ ማናቸውንም አይነት ምርቶች ማግኘት እንዲችል ያደርጋል።ሁለተኛ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ገበያ የምትልካቸውን የግብርና፣ የኢንዱስትሪና የማዕድን ምርቶችን ተቀባይ አገራት በሚፈልጉት የጥራት ደረጃ መላክ ያስችላል።ይህም እንደ ተቋም ተቋማትን ተወዳዳሪ የሚያደርግና እንደ አገርም አገር ተወዳዳሪ እንድትሆን በዚህም የአገር ኢኮኖሚ እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋጽኦን ያበረክታል ነው ያሉት።

የማንኛውም ምርት መወዳደሪያው ጥራት አልያም ዋጋ ነው ያሉት አቶ እንዳለው፤ ይህን ጥራት ሊያረጋግጡ የሚችሉ የብሔራዊ የጥራት መሰረተ ልማት ተቋማት አራት ቴክኒካል ተቋማት መሆናቸውን ተናግረዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ከእነዚህ ተቋማት መካከልም አንደኛው፤ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ሲሆን፣ ይህም ደረጃዎችን የሚያወጣና ያወጣቸውን ደረጃዎች እንዲተገበሩ የቴክኒክ ድጋፍና ስልጠና የሚሰጥ ነው።ሁለተኛው የኢትዮጵያ የተስማሚነትና የዘና ድርጅት ነው።ይህ ተቋም ምርቶች የተቀመጠላቸውን መስፈርት ማሟላት አለማሟላታቸውን የሚያረጋግጥ ነው።ሶስተኛው መሳሪያዎች በትክክል ስለመስራታቸው በካሊቢሬሽን የሚያረጋግጠው የኢትዮጵያ የስነ-ልክ ኢንስቲትዩት ሲሆን፣ አራተኛው ምስክርነት የሚሰጠው የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ነው።እነዚህ አራት ተቋማት ከጥራት ጋር ተያይዞ ቴክኒካል ሥራ የሚሠሩ ተቋማት ናቸው።

ከዚህ ባለፈም ሁሉም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የቁጥጥር ሥራ እንደሚሠሩ የጠቀሱት አቶ እንዳለው፤ በተለይም በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በህጋዊ ስነ-ልክ ሚዛኖች፣ መስፈሪያዎች፣ ነዳጅ የሚጭኑ ቦቴ ተሽከርካሪዎች፣ የነዳጅ ማደያዎችና፣ ማኅበረሰቡ በየዕለቱ የሚጠቀምባቸው ሚዛንና መስፈሪያዎች ትክክለኛነትን የማረጋገጥ ሥራ በሕጋዊ ስነ- ልክ በኩል እንደሚሰራ አብራርተዋል።

ተቋማቱ በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ መጠን ያለው መዋዕለ ንዋይ ወጥቶባቸው ሪፎርም ሲደረግባቸውና አቅማቸው ሲገነባ መቆየቱን የጠቀሱት አቶ እንዳለው፤ ተቋማቱን በአገር ውስጥ ማቋቋም ብቻ በቂ አይደለም ይላሉ።በአህጉር ደረጃ ከፍ ማለት እንዲችሉ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ትስስር በመፍጠር በዓለም አቀፍና በአህጉር ደረጃ ከሚገኙ ተቋማት ጋር በቀጥታ ተወዳዳሪ መሆን ተችሏል ነው ያሉት።እነዚህ በብሔራዊ፣ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ ተቋማት ገለልተኛ በሆነው በአፍሪካ ኳሊቲ ኢንዴክስ 2023 ተገምግመዋል።

ተቋማቱ እኤአ በ2014 እና በ2017 ተገምግመው ሁለት ነጥብ አራት ያስመዘገበችው ኢትዮጵያ፣ በወቅቱ በከፊል ከለሙ ተቋማት ተርታ እንደነበረች አቶ እንዳለው አስታውሰዋል።በ2020 መንግሥት በዘርፉ ሰፋፊ ሥራዎችን ማለትም የሰው ኃይልና መሰረተ ልማትን በማሟላት እንዲሁም የአሰራር ስርዓታቸውን በማሻሻል በተለይም የአገልግሎት ወሰናቸውን በማስፋት ከዚህ ቀደም ሲሰጡ የነበረውን አገልግሎት በአይነትም በመጠንም በማሻሻል ተቋማቱ ከነበሩበት ደረጃ ከፍ ማለት ችለዋል ብለዋል፡፡

እኤአ በ2014፣ በ2017 እና በ2020 ኢትዮጵያ የብሔራዊ ጥራት መሰረተ ልማት ተቋም ከገነቡ አራት አገራት ተርታ መሰለፍ አልቻለችም ነበር ሲሉ ጠቅሰው፣ ይሁንና በ2023 ኢትዮጵያ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ችላለች ሲሉ አቶ እንዳለው ተናግረዋል። በመንግሥት ቁርጠኝነት ከስድስት የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ መሆን እንደቻለች ገልጸው፤ ይህም በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እየተከናወነ ያለውን የመሰረተ ልማት ማስፋፋት ተግበር ሳያካትት የተገኘ ውጤት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ ሀገሪቱ በጥራት መሰረተ ልማት ያሳየችው ለውጥ የሀገሪቱ የጥራት መሰረተ ልማት በአጠቃላይ በጣም በፍጥነት እያደገ መሆኑን እንደሚያሳይ የጠቀሱት አቶ እንዳለው፤ ደረጃ አራት ላይ ለመድረስ በቀጣይ የሚሠሩ ሥራዎች ስለመኖራቸውም ገልጸዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ማስፋፊያ እየተደረገባቸው ከሚገኙ ሰፋፊ መሰረተ ልማቶች መካከል ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ጠብቀው በቅርቡ የሚመረቁ 13 የላቦራቶሪ አገልግሎት የሚሰጡ ህንጻዎች ይገኛሉ።ይህም ስራ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ተመድቦለት በፍጥነት እየተሠራ ሲሆን፣ ግንባታዎቹ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቁ ተቋማቱ የሚጠቀሟቸው ይሆናል።በመሆኑም በቀጣይ በሚኖረው ግምገማ ኢትዮጵያ ቀዳሚ በመሆን በአፍሪካ አቅም የገነቡ የብሔራዊ ጥራት መሰረተ ልማት ተቋማት ካላቸው አገራት ተርታ የሚያሰልፋት ይሆናል በማለት ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።

እንዲህ ያለ ትልቅ አቅም በኢትዮጵያና በዙሪያዋ በሚገኙ ጎረቤት አገራትና በቀጠናው ጭምር ባለመኖሩ ኢትጵያን ጨምሮ አፍሪካ አገራት አብዛኞቹን የፍተሻ አገልግሎቶች የሚያገኙት ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም አውሮፓ (ጀርመን) ድረስ በመላክ እንደነበር ያጠቀሱት አቶ እንዳለው፤ በአሁኑ ወቅት ግን ወደ ውጭ ተልከው የሚሰሩ በርካታ ሥራዎች በራስ አቅም እየተሠሩ እንደሆነ ተናግረዋል።ይህም ለማምረቻ ተቋማት ትልቅ ዕድል የሚፈጥርና ተቋማት ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉ ትልቅ አበርክቶ ያለው መሆኑንም አያይዘው ገልጸዋል።ይህም መንግሥት በወሰደው ጠንካራ የተቋማት ሪፎርም ሥራ የተገኘ ውጤት ነው ብለዋል።

አቶ እንዳለው እንዳብራሩት፤ የጥራት መሠረተ ልማት እውን መሆን እንደ ሀገር የሚያስገኘው ጥቅም ዘርፈ ብዙ ነው።ተቋማትንና ሀገርን ተወዳዳሪ በማድረግ ጠንካራ ኢኮኖሚን መገንባት ይቻላል።በተለይም ከደረጃ በታች የሆነ ምርት ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ በማድረግ የዜጎችን ጤና ይታደጋል።

የምርት ጥራት ጉዳይ በሰዎች የሕይወት እንቅስቃሴ ውስጥ ወሳኝ ነው።ሰዎች ከምግብና መጠጥ ጀምሮ የሚጓጓዙባቸው ተሽከርካሪዎችና የሚሰሩባቸው አካባቢዎችና ህንጻዎች እንዲሁም የሚወጡባቸውና የሚወርዱባቸው የትኛዎቹም መሰረተ ልማቶች ሙሉ ለሙሉ ከጥራትና ደረጃ ጋር የተገናኙ ናቸው።ስለዚህ ጥራት ላይ በአግባቡ መሥራት ኢኮኖሚን ከማሳደግ ባለፈ የሰዎችን ደህንነት መጠበቅ ያስችላል፤ የአካባቢን ደህንነት ከማረጋገጥ አኳያም እንዲሁ የማይተካ ሚና ይኖረዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የጥራት መሠረተ ልማት አቅም ናሙና ልኮ በአንድ ጊዜ ውጤቱን ለማግኘት፤ ለሌሎች ሀገራት የባለሙያ ሥልጠና ለመስጠት፤ ለሀገሪቱ አምራቾች፣ ላኪና አስመጪዎችም ትልቅ እድል የሚፈጥር ነው። ከዚያም አልፎ ለጎረቤት ሀገራት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ሁኔታ ያመቻቻል። በተለይም በደረጃ ከኢትዮጵያ ያነሱ ሀገራትን ለመሳብና ተጠቃሚነትን ለማስፋት ትልቅ አቅም በመፍጠር መፍትሔ መስጠት የሚችል ነው፡፡

ኢትዮጵያ ብሔራዊ የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማትን ገንብታ በአፍሪካ መስፈርቱን ካሟሉ ስድስት አገራት መካከል አንዷ መሆን መቻሏ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆንም እያደረገች ያለችውን ጉዞ የሚያፋጥን እንደሆነም ገልጸዋል።ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ምርት የትኛውም የአፍሪካ መዳረሻ ላይ ተመራጭ እንዲሆንና እንዲላክም ጥሩ መደላደልን የሚፈጥር ነው።

ይሁንና ኢትዮጵያ አሁን የደረሰችበትን ደረጃ የበለጠ ከፍ ለማድረግና ደረጃ አራት ላይ ለመድረስ ጠንካራ ሥራ መሥራት ያስፈልጋታል ያሉት አቶ እንዳለው፤ በተለይም ከሕጋዊ ሥነ-ልክ አኳያ ከኢትዮጵያ የሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ጋር ተያይዞ የታዩና የተነገሩ ግብረመልሶች ላይ ትኩረት በማድረግ መሥራት ተገቢ ነው ብለዋል።

አሁን የተጀመሩ የማስፋፊያ ሥራዎችም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበው፣ በዚህ ዓመት ለማጠናቀቅ በእቅድ የተያዙ ሰፋፊ መሠረተ ልማቶች እንዳሉም ጠቅሰዋል።ይህም ኢትዮጵያ በቀጣዩ ግምገማ አሁን ካለችበት ደራጃ ከፍ ማለት እንድትችል ፋይዳ እንዳለው ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል፡፡

መረጃዎች እንዳስታወቁት፡ የውድድሩ ተሳታፊ 55 የአፍሪካ አገራት ሲሆኑ ከእነዚህ መካካልም 10 የሚደርሱ አገራት የጥራት መሰረተ ልማት ተቋም የላቸውም በሚባል ደረጃ በጣም ጥቂት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ናቸው።13ቱ በጣም ውስንነት ያለበት አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆኑ፣ በከፊል አገልግሎት ያላቸውና የተሟላ መሰረተ ልማት የሌላቸው አገራትም እንዲሁ 13 መሆናቸው ተጠቁሟል። ተቀባይነት ያለውና አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሰረተ ልማት ያሟሉና ጥሩ ተቋማት ያላቸው 13 ብቻ ናቸው።በደንብ የለሙና ብሔራዊ የጥራት መሠረተ ልማት ተቋም በመገንባት የተሟላ አገልግሎት መስጠት የቻሉት አገራት ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ ስድስት አፍሪካ አገራት ናቸው።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You