ሚኒስቴሩ የኢኖቬሽን ማዕከላትን ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ ነው

አዲስ አበባ:- ወጣቶች በሀሳብ የያዟቸውን የፈጠራ ሥራዎች ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያገለግሉ የኢኖቬሽን ማዕከላትን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ከደቡብ ኮሪያው ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ ኮይካ ጋር በትብብር ያስገነባውን «ኢኖቪዝ- ኬ ኢትዮጵያ» የኢኖቬሽን ማዕከል ባስመረቀበት ወቅት ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ሠላምይሁን አደፍርስ እንደተናገሩት፤ ፈጠራን የሚያዳብር፣ ምርምርንና ልማትን የሚያበረታታ የፈጠራ ጅምሮች እና ኢንተርፕራይዞችን እድገት የሚደግፍ ምቹ አካባቢ ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል። በአይ ሲ ቲ ማዕከል የተገነባው ማዕከልም ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው።

“ኢንኖቪዝ-ኬ” ኢትዮጵያ በጋራ የሚሠራበት፤ የሥልጠና እና የማምረቻ ቦታና ቁሳቁስ እንዲሁም ሌሎች የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ክፍሎችን ያካተተ ነው። ለጀማሪዎች አካላዊ መሠረተ ልማቶችን እና ግብዓቶችን ብቻ እንዲሁም የእውቀት መጋራት እና የአቅም ግንባታ ሆኖ የሚያገለግል ነው። ማዕከሉ የጀማሪዎቻችንን የሥራ ፈጠራ ችሎታ ለማሳደግ ወርክሾፖችን፣ ሴሚናሮችንና የስልጠና ፕሮግራሞችን የሚዘጋጁበት ይሆናል” ብለዋል።

በተጨማሪም ሀሳብ ላላቸው ወጣቶች የተቀናጀ ድጋፍ የሚቀርብበትና እርስ በአርስ የሚደጋገፉበት ሲሆን ዩኒቨርሲቲዎች፤ ባለሀብቶች፣ አማካሪዎችና ኢንዱስትሪዎችም የሚሳተፉበት እድል አለ፤ ማዕከሉ ወጣት ኢትዮጵያውያንን በመደገፍ አዳዲስ ምርቶችን እና አገልግሎቶችን እንዲያሳድጉ እና ጀማሪ ኩባንያዎች እንዲፈጠሩ የሚረዳም ነው ብለዋል።

ይህም ፈጠራን በማጎልበት፣ ጅምሮችን በማብቃት እና የኢኮኖሚ እድገትን በማፋጠን ረገድ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል። ነገር ግን እንደ ሀገር ከሚጠበቀው ተደራሽነት አንጻር በርካታ ስራዎች ይቀራሉ። በመሆኑም እንደዚህ አይነት ማዕከላት በአዲስ አበባ በአንድ ማእከል ብቻ መቀመጡ ተደራሽ ሊሆን አያስችለውም ሲሉም ተናግረዋል።

እንደ ሀገር በዩኒቨርስቲዎችና በክልሎችም ማስፋፋት የሚጠበቅ በመሆኑ ከኢንኖቢዝ-ኬ ኢትዮጵያ ልምድ በመውሰድ በሌሎች ቦታዎችም የኢኖቬሽን ማዕከላትን ለመገንባት የሚሠራ ይሆናል ብለዋል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You