ባንኩ ያለአግባብ ከተወሰደበት ገንዘብ 78 በመቶውን አስመልሷል

– 9 ሺህ 281 ግለሰቦች ያለአግባብ የወሰዱትን ገንዘብ በፈቃደኝነት መልሰዋል

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም ሌሊት ከሲስተም ማሻሻያ ሥራ ጋር በተገናኘ በተፈጠረ ችግር ምክንያት ያለአግባብ ከተወሰደበት 801 ሚሊዮን 417 ሺህ ብር ውስጥ እስከትናንት ድረስ 622 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ብሩን (78 በመቶውን) ማስመለስ እንደቻለ አሳወቀ፡፡ ዘጠኝ ሺህ 281 ግለሰቦች ያለአግባብ የወሰዱትን ገንዘብ በፈቃደኝነት ለባንኩ መልሰዋል።

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳመላከቱት፤ ባንኩ ያጋጠመውን የዲጂታል ሥርዓት አሠራር ችግር ተከትሎ መንስኤዎችን ለማወቅና አስፈላጊውን የእርምት ርምጃ ለመውሰድ በርከት ያሉ ሥራዎችን አከናውኗል፤ አሁንም እየሠራ ይገኛል፡፡ ባንኩ ያለአግባብ ከተወሰደበት 801 ሚሊዮን 417 ሺህ 747 ብር ውስጥ 622 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ብሩን ማስመለስ እንደቻለ ተናግረዋል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ ችግሩን በተመለከተ ከባንኩ ባለሙያዎች የተውጣጡና ጉዳዩን የሚያጠኑ ቡድኖች ተቋቁመው ወደ ሥራ ገብተዋል፤ እንዲሁም የባለድርሻ አካላትን ያቀፉ አጥኚ ቡድኖችም በሥራ ላይ ናቸው፡፡

በጉዳዩ ተሳትፎ የነበራቸው ዘጠኝ ሺህ 281 ግለሰቦች የወሰዱትን ከ223 ሚሊዮን 475 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ በፈቃደኝነት የመለሱ መሆናቸውን የገለፁት አቶ አቤ፣ 5 ሺህ 160 ደንበኞች ደግሞ በከፊል ማለትም ከ149 ሚሊዮን 21 ሺህ ብር በላይ መመለሳቸውን አሳውቀዋል፡፡

አላግባብ ከወሰዱት ብር ዘጠኝ ሚሊዮን 838 ሺህ ብር በላይ እስካሁን ምንም ያልመለሱ 567 ግለሰቦች መኖራቸውንም አቶ አቤ አመላክተዋል።

ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ በሂደቱ ውስጥ የተሳተፉ ግለሰቦችን ሒሳብ ልየታ ተከናውኗል፤ በዚህም 15 ሺህ ስምንት የሒሳብ ቁጥሮች ተገኝተዋል፡፡

ችግሩ በታወቀበት ወቅትም የሚመለከታቸው የሀገራችን የፀጥታና ፍትሕ አካላት ጉዳዩን እንዲያውቁት ስለመደረጉ ያመላከቱት አቶ አቤ፤ አስፈላጊውን መረጃ በመስጠትም በትብብር እየሠራን እንገኛለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የባንኩን የዲጂታል ክፍያ አገልግሎቶች ተጠቅመው ገንዘብ ያንቀሳቀሱና ወጪ ያደረጉ ግለሰቦች ያለአግባብ የወሰዱትን ገንዘብ በአቅራቢያቸው በሚገኙ ቅርንጫፎች ተመላሽ እንዲያደርጉ ለማስቻል በርከት ያሉ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል ብለዋል፡፡

በፕሬዚዳንቱ ንግግር መሠረት፤ ችግሮቹ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ግለሰቦች ያለአግባብ የወሰዱትን ገንዘብ ተመላሽ እንዲያደርጉ ተሠርቷል፡፡ ዩኒቨርስቲዎች በማስታወቂያና በተለያዩ መንገዶች ጥሪ አድርገዋልም ነው ያሉት፡፡

ባንኩ ባከናወናቸው ተግባራት አብዛኛውን ገንዘብ በግለሰቦች ፈቃደኝነት ተመላሽ ማድረግ ችለናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ለዚህ ውጤትም በየአካባቢው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት እና የባንካችን ሠራተኞች ላደረጉት ጥረት ከፍ ያለ ምስጋና እናቀርባለን ብለዋል፡፡

በተሰጧቸው ዕድሎች ተጠቅመው ተመላሽ በማያደርጉት ላይ ያለአግባብ የተወሰደውን ገንዘብ ለማስመለስ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ይዘው እንደሚሄዱም አንስተዋል፡፡

በቀጣይም ጉዳዩ የተሳተፉ ግለሰቦችን ማንነት የሚገልጹ መታወቂያዎችን እንዲሁም የፎቶ ግራፍ መገለጫዎችን ባንኩ በመረጣቸው የብዙኃን መገናኛ ዘዴዎች በመጠቀም የሚገልጽ ይሆናል ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዘመናዊና ዓለም የደረሰበትን የባንክ አገልግሎት ለደንበኞቹ ለማቅረብ የሚያደርገውን ጥረት አሁንም ቢሆን ይቀጥላልም ያሉት ፕሬዚዳንቱ የተፈጠረው ክስተት ዳግም እንዳይፈጠርም ጠንክሮ ይሠራል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በባንኩ በጉዳዩ ዙሪያ የሚኖሩ መረጃዎችን በየጊዜው ለኅብረተሰቡ የሚያሳውቅ መሆኑንም የባንኩ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ አሳውቀዋል።

ዳግማዊት ግርማ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You