ፓርኩ በዘጠኝ ወራት 18 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ተኪ ምርት አምርቷል

አዲስ አበባ፦ በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት 18 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ተኪ ምርት ማምረቱን የደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ አስታወቀ።

የደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ የሺጥላ ሙሉጌታ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በፓርኩ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ባለሀብቶች በአልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ፣ በብቅል እንዲሁም በሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች ተሰማርተው ተኪ ምርቶች እያመረቱ ይገኛሉ።

ፓርኩ በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት 18 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ተኪ ምርት አምርቷል ያሉት አቶ የሺጥላ፤ በዚህም አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የገበያ ትስስሮች ተፈጥሯል። ይህም በዋናነት የቢራ ገብስ አምርቶ ለኩባንያዎች በማቅረብ የተፈጠረ ነው ብለዋል።

ፓርኩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ወደ ውጭ ከላካቸው ምርቶች ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት ችሏል ያሉት አቶ የሺጥላ፤ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በውጭ ምንዛሪ ግኝት፣ ተኪ ምርት በማምረትና በገበያ ትስስር ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል። በዚህም ለ335 የሚሆኑ ዜጎች የእውቀት ሽግግር መፈጠሩን ገልጸዋል።

ፓርኩ ከሁለት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል ተጠቃሚ አድርጓል። ከዚህም ባለፈ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በየወሩ ከ400 ሺህ ብር በላይ ለአካባቢው ማህበረሰብ ወጪ ያደርጋል ያሉት አቶ የሺጥላ፤ ይህም ድጋፍም ለአካባቢው አረንጓዴ ልማት እና ሥራ እድል ፈጠራ የሚውል መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ አቶ የሺጥላ ገለፃ፤ አማራ ክልል ከሚገኙ የኢንዱስትሪ ልማት ፓርኮች መካከል ደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ አንዱ ነው። ከአዲስ አበባ በ130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን በ100 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባ ነው። በዚህም ስምንት ዋና ዋና የፋብሪካ ሼዶችን ይዟል። የማምረቻ ሼዶቹ አምስት ሺህ 500 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው ናቸው።

ለኢንዱስትሪ ፓርኩ የውሃ፣ የመብራት፣ የቴሌኮም አገልግሎትና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመርና አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች ተሟልተዋል ያሉት አቶ የሺጥላ፤ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ወደ ሥራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን በማቃለል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በፓርኩ ውስጥ የጉምሩክ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በአንድ ማዕከል አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። ይህም ለባለሀብቶች መልካም የሥራ ከባቢን ፈጥሯል ብለዋል።

ኢንዱስትሪ ፓርኩ በ2015 በጀት ዓመት ለሦስት ሺህ 568 ዜጎች አዳዲስ የሥራ እድል ፈጥሯል። በፓርኩ ውስጥ የሚሠሩ ኩባንያዎችም ከ100 ሺ በላይ ከሚሆኑ የአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር ከአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር መፍጠራቸው ተመልክቷል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You