ሠላም፣ ጤና እና መልካም ነገሮችን ሁሉ የምንመኝላችሁ ውድ ልጆቻችን እንዴት ናችሁ? ሳምንቱ እንዴት አለፈ? እንደሚጠበቀው በጥናት እና በትምህርት በሚገባ አሳልፋችኋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ልጆችዬ ወላጆቻችሁ ወይም መምህራን ‹‹አባባ ተስፋዬ›› ሲሉ ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? በእርግጥ ዛሬ በሕይወት ባይኖሩም ብዙዎች ‹‹ልጆች የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች›› በሚል ንግግራቸው እንዲሁም በኢትዮጵያ ቴሊቪዥን ‹‹የልጆች ክፍለ ጊዜ›› በተሰኘው ፕሮግራም ለልጆች በሚያቀርቡት ታሪክ ያስታውሷቸዋል።
‹‹አባባ ተስፋዬ›› ሙሉ ስማቸው ተስፋዬ ሣሕሉ ይባላሉ። በ1978 ዓ.ም ‹‹ከአባቶች ለልጆች›› የተሰኘ ሦስተኛ መጽሐፋቸውን አሳትመው ነበር። በዚህ የተረት መጽሐፍ ‹አንበሳና አይጥ› በሚል ርዕስ የቀረበውን አንድ አስተማሪ ታሪክ እናቀርብላችኋለን። ታሪኩ እንዲህ ይጀምራል፤
አንድ ጊዜ አንበሳ ምግቡን ለማግኘት አጋዘን ሲያባርር ውሎ ከያዛት በኋላ ምግቡን በልቶ የቀረበውን በአንድ ስፍራ አስቀምጦ ተመልሶ በጣም ስለደከመው ጋደም ብሎ ተኝቶ ነበር።
ግን እንቅልፍ አልወሰደውም። በዚህ መሐል አንድ አይጥ ምግቧን ፍለጋ ከወዲያ ወዲህ ስትራወጥ ሳለ አንበሳ ከተኛበት ስፍራ ትደርስና ዙሪያውን ትዞራለች። አይንቀሳቀስም። አሁንም በሰውነቱ ላይ ታልፋለች አይንቀሳቀስም። አሁን በመዝናናት ቀስ ብላ እራሱ ላይ ትወጣና ከጆሮው ግድም ለመብላት ስትሞክር ጆሮውን ነቅነቅ ያደርጋል። በዚህ ጊዜ ዘላ ትወርድና መንቃነቁን ስላልደገመ ወደ አፍንጫው ተጠግታ መተንፈሱን አዳመጠች፤ እሱ ግን አፉን ከፍቶ ልክ እንደሞተ ሆኖ ተኝቶ ስለነበር አንዴ ባፉ ውስጥ አለፈችና ሁለተኛ ስትገባ ጥርሱን ግጥም አድርጎ ያዛትና ‹‹ለምን መኝታ ከለከልሽኝ፤ አሁን ዋጥ ላድርግሽ?›› ቢላት ደንግጣ ‹‹አያ አንበሳ አትዋጠኝ። የዛሬን ማረኝ። ዛሬ ብትምረኝ እኔ ደግሞ ላንተ አንድ ቀን ውለታ እመልሳለሁና ማረኝ?›› አለችው።
አንበሳው ከት ብሎ ሳቀና ‹‹የሚያስቀሳፍትሽ (የሚያስቀባጥርሽ) የነፍስ ሲቃ ይዞሽ ነው እንጂ አንቺ ለእኔ ብድር መላሽ ልትሆኚ አትችይም፤ ይልቅ ማረኝ በይና ልልቀቅሽ?›› አላትና ለቀቃት።
አይጥ ግን ስለለቀቅኸኝ ‹‹በጣም አመሰግንሀለሁ። ብድርህን ለመመለስ ያብቃኝ›› ብላው ሄደች።
በዚህ ሁኔታ ከቆዩ በኋላ አዳኞች ወጥመድ አጥምደው ኖሮ አንበሳ እዛ ወጥመድ ውስጥ ገብቶ ለመውጣት ሲታገል አይጥ ምግቧን ፈልጋ በዛ ስታልፍ ድንገት አንበሳ ተይዞ ታየውና ‹‹አያ አንበሶ ምን ሆነህ ነው በዚህ ግድም የተገኘኸው?› ብላ ጠየቀችው።
አንበሳም ‹‹ይሔው እንደምታይኝ እዚህ ወጥመድ ውስጥ ገብቼ እጨነቃለሁ።›› አላት። አይጧም ‹‹ወጥመድን ያጠመዱ ሰዎች ድንኳናቸው ውስጥ ምሳቸውን ሲበሉ ነበር። ከመምጣታቸው በፊት እንዳወጣህ ስለምፈልግ አይዞህ! ጓደኞቼን ይዤ ልምጣ?›› ብላ ካጠገቡ ፈትለክ በማለት እየሮጠች ሄደች።
አንበሳም ‹‹አይ አትልፊ አሁን ያንቺን ጉልበትና የጓደኞችሽን ጉልበት እኔን ከዚህ ውስጥ ሊያወጣኝ ነው? ይልቅ ተይው ፤ አልኩ ለማለት እንደሆነ ሃሳብሽ ይበቃል።›› አላት።
አይጥ ግን ‹‹ግዴለም›› ብላ ጓደኞቿን አንድ አይጥ ሳይቀር ይዛ ከተፍ አለችና ያ ወጥመድ የታሰረበትን ጠፍርና ገመዱን ብጥስጥሱን ካወጡት በኋላ ‹‹በል አሁን በኃይል ተወራጭ በዛን ጊዜ ግንዱ ሁሉ ይንከባለላል።›› አለችና ነገረችው።
አንበሳም ‹‹አይ አይጢት ስንቴ ሞክሬው ያልሆነውን?›› ብሎ በትከሻው ገፋ ቢያደርገው ያ ግንድ ሁሉ ተንከባለለ። አንበሳ ከወጥመዱ ውስጥ ወጣ።
አይጢት ‹‹በል ሂድ እኔም ቃሌን ፈጽሜያለሁ። አንድ ቀን ብድር እመልሳለሁ ብዬ ነበር ያው አንተ ስለማርከኝ ብድሬን መልሻለሁ። አንተ ግን ትንሽ ነች ብለህ ንቀኸኝ ነበር።›› ካለችው በኋላ ‹‹ሳይመጡብህ አምልጥ።››ብላ እሷም ከነጓደኞቿ ወደ ጉድጓዷ ገባች ይባላል።
‹‹ልጆች ሰውንም ሆነ እንስሳን ትንሽ ነው ብለው መናቅ አይገባም። ሰውም ለጭንቅ ቀን ይገኛል። ትንሽ አውሬም ሰውን ያበላሻልና።›› በማለት አባባ ተስፋዬ መልካሙን ምክራቸውን በመጽሓፋቸው ላይ አቅርበዋል።
ልጆችዬ ከአይጢቷ እና ከአያ አንበሳ ታሪክ ቃል ማክበር እንደሚገባ፣ አጉል ድፍረት እንደማያስፈልግ ፣ትንሽ ናት ወይም ነው ብሎ ማንንም መናቅ እንደማይገባ፣ በመተባበር እና በመረዳዳት እንዴት ከችግር መውጣት እንደሚቻል ከዚህ ታሪክ እንደተማራችሁ ምንም ጥርጥር የለኝም። በተረፈ ደግሞ እናንተ የተማራችሁትን እንዲሁም ያገኛችሁትን እውቀት ለታናናሾቻችሁ እና ለጓደኞቻችሁ በማካፈል መልካም ነገር እንዲማሩ ለማድረግ እንደምትጥሩ ተስፋ አደርጋለሁ። ልጆችዬ ለዛሬ በዚሁ እናብቃ ሳምንት በሠላም ለመገናኘት ያብቃን።
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም