በመዲናዋ ደንብ በሚተላለፉ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ደንብ በሚተላለፉ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

ባለስልጣኑ ከሁሉም ክፍለ ከተማ ከተወጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ባለፉት ዘጠኝ ወራት ባከናወናቸው ሥራዎች ዙሪያ በትናትናው ዕለት ውይይት አካሂዷል።

የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ በወቅቱ እንደገለጹት፤ መዲናዋ ለነዋሪዎቿ ምቹና ውብ እንዳትሆን ደንብ በሚተላለፉ አካላት ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

በቀጣይ በከተማዋ ከተፈቀዱ ቦታዎች ውጪ በዋናና የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ላይ የጉልት ንግድ በሚያካሂዱ፣ ተንጠላጣይ የደላላ ማስታወቂያዎችን በሚሰቅሉና ጫማ በሚጠርጉ አካላት ላይ የተጠናከረ እርምጃ እንደሚወሰድ ሻለቃ ዘሪሁን ገልጸዋል፡፡

በሕዝብ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች የግንባታ ዕቃ በሚያስቀምጡ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

እንደ ሻለቃ ዘሪሁን ገለጻ፤ በተለይ በከተማዋ በሚገኙ አደባባዮችና መንገዶች ላይ የሚደረጉ ሕገ ወጥ ንግዶች፣ ሕገ ወጥ የቤት ግንባታና መሬት ወረራ ላይ ከሕዝብ ጋር በመተባበር መሥራት በመቻሉ የመዲናዋን ውበት መጠበቅ ተችሏል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሁሉም ከፍለ ከተሞች ላይ በተሠራው ሥራ ከ15 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ጤንነቱ ያልተረጋገጠ ስጋ ለሕዝብ ሊቀርብ ሲል መያዙንም ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም መሬት በሕገ ወጥ መንገድ በግለሰቦች እንዳይወረር በተሰራው ሥራ ከ10 ሚሊዮን ካሬ ሜትር በላይ መሬት ወደ ባንክ መግባቱን አስረድተዋል፡፡

የደንብ ማስከበር አባልት የሕዝብን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ባለስልጣኑ ተከታታይ የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠቱን ጠቁመዋል፡፡

ሕገ ወጥ የጎዳና ላይ ንግድ ኅብረተሰቡን ለዝርፊያና ለትራፊክ አደጋ እያጋለጠ መሆኑን አውስተው፤ ኅብረተሰብን ያሳተፈ ሥራ በመሠራቱ ጎዳናዎች ነጸ ሆነው እግረኞች በነጻነት እየተንቀሳቀሱ ናቸው ብለዋል፡፡

ሻለቃ ዘሪሁን አክለውም ደንብ መተላለፍን ለመቀነስ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ያሉ ሲሆን፤ የመከላከል ሥራው ውጤታማ መሆኑን አመላክተዋል።

ከደንብ ማስከበር ጋር በተገናኘ ከኅብረተሰቡ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የስነ ምግባር ጥሰት በፈጸሙ ደንብ አስከባሪዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።

ደንብ መተላለፍን የሚጸየፍ ኅብረተሰብ ለመፍጠር ባለስልጣኑ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠቱን ጠቁመው፤ ሁሉም አካላት ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ ሻለቃ ዘሪሁን ጥሪ አቅርበዋል።

አማን ረሺድ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You