የአዲስ አበባን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ማጽናትና ማጠናከር የሁልጊዜ ተግባር ሊሆን ይገባል

አዲስ አበባ፡– የአዲስ አበባን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ማጽናትና ማጠናከር የሁልጊዜ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ አስታወቁ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 37ኛው የአፍሪካ ኅብረት መደበኛ የመሪዎች ጉባኤና 44ኛው የአፍሪካ ኅብረት ሥራ አስፈጻሚዎች ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማትና አካላት በሚያዝያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም የምስጋናና የእውቅና መርሀ ግብር አካሂዷል፡፡

በመርሀ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ እንደገለጹት፤ ለ37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤው በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን በሚገባ መወጣታቸውን በመግለጽ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

አዲስ አበባ የላቀች የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ማጽናትና ማጠናከር የሁልጊዜ ተግባር ሊሆን ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ፤ አፍሪካ ኅብረት ጉባኤን ከዓመት ወደ ዓመት በተሻለ መስተንግዶ እንግዶች ተቀብሎ የመሸኘት ልምዱ እየዳበረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ስብሰባዎችን በስኬት በማስተናገድ የዳበረው ባህል ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመልክተው፤ የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ መስተንግዶ በስኬት በማዘጋጀት ያዳበርነውን ልምድ ማጠናከር ብቻ ሳይሆን፤ አዲስ አበባ የላቀች የዲፕሎማሲ ማዕከል ሆና እንድትቀጥል የአባቶቻችንን አደራ መወጣት የሁልጊዜ ተግባራችን ሊሆን ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ትላልቅ ስብሰባዎችን ማስተናገድ አድካሚ ቢሆንም በሀገር ወዳድ ዜጎችና ተቋማት በስኬት ማጠናቀቅ ተችሏል ያሉት ሚኒስትሩ፤ 37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የኢትዮጵያን ገጽታ መገንባት ያስቻለ ነበር፡፡ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫነት ኢትዮጵያ ለጥቁር ሕዝቦች ነጻነትና የቅኝ ግዛትን በመታገል ላበረከተችው አስተዋጽኦ የተሰጣት መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ጉባኤው ኢትዮጵያ የዓለም የስህበት ማዕከል መሆኗን ያሳየ መሆኑን ገልጸው፤በቀጣይ መሰል ስብሰባዎችን በስኬት በማስተናገድ አዲስ አበባ የስህበት ማዕከልነቷን ማስቀጠል እንደሚገባት ገልጸዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታና የብሔራዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በመርሀ ግብሩ የተሠሩ ሥራዎችን አስመልክቶ ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት፤ በጉባኤው የተሳተፉ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ እንግዶችን በተሳካ መልኩ ተቀብሎ በማስተናገድና በመሸኘት የተሟላ አገልግሎት ለሰጡ ተቋማት ምስጋና አቅርበዋል።

ከእንግዳ አቀባበል እስከ አሸኛኘት ድረስ ከየትኛውም ዓመት የተለየ መስተንግዶ መደረጉን በመግለጽ፤ ለቀጣይ ዓመት የበለጠ የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ለጉባኤው መሳካት ብሔራዊ ኮሚቴ ተዋቅሮ በቅንጅትና በመናበብ መሥራት በመቻሉ ውጤታማ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡

እንደ አምባሳደሯ ማብራሪያ፣ አስፈላጊውን የጸጥታ ሥራ የተሠራ በመሆኑ ያለምንም ችግር ከ8ሺህ በላይ እንግዶች በሰላም ማስተናገድ ተችሏል፡፡

በሁሉም ዘርፍ ለተመዘገበው ውጤት የአዲስ አበባና የሸገር ከተማ ነዋሪዎች ያደረጉት ትብብር ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ አመስግነዋል፡፡ በጉባኤው መሳካት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላደረጉ ለተቋማትና ግለሰቦች በተለያዩ ደረጃዎች ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ሞገስ ጸጋዬ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You