የአንድ ሙያ ሰዎች የአንድ ቀን እረፍት

አንዳንድ የታሪክ አጋጣሚዎች መመሳሰል ያጋጥማቸዋል። ለምሳሌ በዚህ ሳምንት ሁለት አንጋፋ የሥነ ጽሑፍ ሰዎችን እናስታውሳለን። ልዩነቶች ቢኖሯቸውም ሁለቱም የሥነ ጽሑፍ ሰዎች ናቸው። በሥነ ጽሑፉ ዓለም ውስጥ ስማቸው ተደጋግሞ የሚጠሩ ናቸው። ሁለቱም በትርጉም ውስጥ ጉልህ እና ልዩ ድርሻ አላቸው። እነዚህ ጉምቱ የሥነ ጽሑፍ ሰዎች ብርሃኑ ዘሪሁን እና ደበበ ሰይፉ ናቸው። ሁለቱም ሕይወታቸው ያለፈው በዚህ ሳምንት ሚያዚያ 16 ቀን ሲሆን ዓመተ ምሕረቱ ግን የተለያየ ነው። በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን እነዚህን ሁለት አንጋፋ የሥነ ጽሑፍ ሰዎች እናስታውሳለን።

መምህር፣ ተርጓሚ፣ ጋዜጠኛ እና ደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁን

ከልጅነቱ ጀምሮ ጎበዝ ተማሪ ነበር። በ1948 ዓ.ም ከተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት ሲመረቅ አንደኛ በመውጣት የከፍተኛ ማዕረግ ተሸላሚ ሆኖ ነው። የከፍተኛ ውጤት ባለቤት በመሆኑ በዚያው በተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት መምህር ሆኖ ተቀጠረ። የተለያዩ የውጭ መጻሕፍትንም ያነብ ስለነበር አስተርጓሚ ሆኖም ሠርቷል። ለጋዜጠኝነት ሙያ ልዩ ፍቅር ስለነበረው በተለያዩ ጋዜጦች በጋዜጠኝነት ሠርቷል። የአንጋፋውና ዕለታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነበር። መምህር፣ ተርጓሚ፣ ጋዜጠኛ እና ደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁን!

ብርሃኑ ዘሪሁን በሥነ ጽሑፍ ሰዎች ዘንድ ካልሆነ በስተቀር በሙያዎቹ ልክ ያልተዘመረለት የብዙ ሙያ ባለቤት ነው። ይህን ሰው ያጣነው ከ37 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሚያዚያ 16 ቀን 1979 ዓ.ም ነው። እነሆ በዋና አዘጋጅነት ሲመራው የነበረው ጋዜጣ ሕይወቱንና ሥራዎቹን ያስታውሳል።

ብርሃኑ የተወለደው በ1925 ዓ.ም ነው። አባቱ መሪጌታ ዘሪሁን መርሻ የቤተ ክህነት ሊቅ ስለነበሩ ለልጃቸው ትምህርት የሚጨነቁ ነበሩ። እናም ልጃቸው በቤት ውስጥ በእርሳቸው የሚሰጠውን ጨምሮ የቤተ ክህነት ትምህርት እንዲማር አድርገዋል።

የኢትዮጵያን ባሕላዊ፣ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን በቤተ ክህነት ትምህርት ከተከታተለ በኋላ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ገባ። ዘመናዊ ትምህርት ቤት ከገባ በኋላም ለንባብ ያለው ልዩ ፍቅርና የጽሑፍ ችሎታው መገለጥ ጀመረ። ብርሃኑ ከልጅነቱ ጀምሮ ልዩ የማንበብ ፍቅር እንደነበረው የሚያውቁት ሁሉ ይመሰክሩለታል። መጽሐፍትን የሚያነብ ብቻ ሳይሆን እንደ ምግብም የሚጠቀምባቸው ዓይነት ሰው ነበር ይባላል።

ጋዜጠኛና ጸሐፊ ጥበቡ በለጠ ስለብርሃኑ ዘሪሁን በሰንደቅ ጋዜጣ በፃፉት ጽሑፋቸው እንዳብራሩት፤ የብርሃኑን ቀልብ ከሳቡት ድርሳናት መካከል ዋነኞቹ ስለኢትዮጵያ ታሪክ የተፃፉት መጻሕፍት ናቸው። ከነዚህም መካከል አለቃ ዘነብ የፃፏቸው ታሪኮች ተጠቃሽ ናቸው። አለቃ ዘነብ በዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ቤተ መንግሥት ውስጥ የነበሩ የዘመኑ ሊቅ ነበሩ። እርሳቸው የፃፉትና በዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ታሪክ ላይ ያተኮረው መጽሐፍ በብርሃኑ የሚወደድ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ብርሃኑ ‹‹መጽሐፈ ጨዋታ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ›› የተሰኘችውን፣ ሃይማኖት ላይ መሠረት አድርጋ የተዘጋጀችውንና ከኢትዮጵያ የፍልስፍና ጽሑፎች መካከል አንዷ ተደርጋ የምትቆጠረውን የአለቃ ዘነብን መጽሐፍ በተደጋጋሚ አንብቧታል። የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ፣ የክብር ዶክተር ከበደ ሚካኤል እና የነጋድራስ አፈወርቅ ገብረኢየሱስ መጻሕፍትም ለብርሃኑ የንባብ ፍቅርና እውቀት መሠረት እንደሆኑት ታሪኩ ያስረዳል።

ብርሃኑ በ1945 ዓ.ም ከተወለደባትና ብዙ እውቀትን ከገበየባት ጎንደር ከተማ ወደ አዲስ አበባ መጣ። በአዲስ አበባ ቆይታውም ተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት ገብቶ የሬዲዮ ቴክኒሻንነት ሙያ በመማር በ1948 ዓ.ም ላይ በዲፕሎማ ተመረቀ። የተመረቀውም በትምህርቱ ከፍተኛውን ውጤት አስመዝግቦና አንደኛ ደረጃን በመያዝ ተሸላሚ ሆኖ ነው።

ብርሃኑ የተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት ተማሪ በነበረበት ወቅት የታላላቅ የዓለማችንን ደራሲያን ሥራዎችን ለማንበብ ዕድሉን አገኘ፡ የዊሊያም ሼክስፒርን፣ የአሌክሳንደር ዱማስ ፔሬን፣ የቻርልስ ዲከንስን፣ የአሌክሳንደር ፑሽኪንን እና የሌሎችን ስመጥር ደራሲያን መጻሕፍትን አነበበ። በዚህም የንባብ ልምዱን እያጎለበተና እውቀቱንም እያሳደገ መጣ። በዚህ ጊዜ ነበር የማንበብ ብቻ ሳይሆን የመፃፍም ችሎታ ያለው ብርሃኑ በንባብ የተከማቸውን እውቀቱን በጽሑፍ ማውጣት የጀመረው። እዚያው ተግባረ-ዕድ ትምህርት ቤት ሲማር የትምህርት ቤቱ ልሳን የነበረችውና ‹‹ቴክኒ ኤኮ›› የተሰኘችው መጽሔት አዘጋጅ ሆኖ ሠርቷል።

ብርሃኑ ከተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት ሲመረቅ ውጤቱ ከፍተኛ ስለነበር እዚያው በመምህርነት ተቀጠረ። ከማስተማር ሥራው ባሻገር ለተለያዩ ጋዜጦች መጻፍ ጀመረ። ከተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት በመልቀቅ በወቅቱ አጠራር የጦር ሚኒስቴር (የአሁኑ መከላከያ ሚኒስቴር) በሚባለው መሥሪያ ቤት በአስተርጓሚነት ተቀጥሮ መሥራት ጀመረ። እዚያም ብዙ ሳይቆይ በ1952 ዓ.ም ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ተዘዋወረ።

በማስታወቂያ ሚኒስቴርም ‹‹የኢትዮጵያ ድምፅ›› ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆነ። በወቅቱም ጋዜጣዋን ታዋቂ ከማድረጉም በላይ በብዙዎች ዘንድ የሚነበቡ መጣጥፎችንና ታሪኮችን በመፃፍ ዝነኛ እየሆነ መጣ። በመቀጠልም የ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆነ። ከዚህ በኋላ የብርሃኑ ስምና ዝና እየገነነ መጣ፤ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ልብም ውስጥ ገባ።

በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ቦታ ሊሰጣቸው የሚገቡ ሥራዎችን ካበረከቱ ደራሲያን አንዱ የሆነው ደራሲ፣ ጸሐፌ ተውኔት እና ጋዜጠኛ ብርሃኑ ዘሪሁን ከ1952 ዓ.ም ጀምሮ ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለየበት 1979 ዓ.ም ድረስ 11 ልብ ወለድ ድርሰቶችንና ሦስት ተውኔቶችን ለተደራሲያኑ ያበረከተ ብዕረኛ ነው።

በ1952 ዓ.ም ‹‹የእንባ ደብዳቤዎች›› በተባለ ድርሰቱ ጉዞውን የጀመረው ብርሃኑ፤ ‹‹ድል ከሞት በኋላ››፣ ‹‹አማኑኤል ደርሶ መልስ››፣ ‹‹የበደል ፍጻሜ››፣ ‹‹ጨረቃ ስትወጣ›› እና ‹‹ብር አምባር ሰበረልዎ›› የተባሉትን ድርሰቶቹን አበርክቷል። በተጨማሪም ‹‹የቴዎድሮስ እንባ›› እና ‹‹የታንጉት ምስጢር›› የተባሉ ሁለት ታሪካዊ ልብ ወለዶችንና በወሎ ክፍለ ሀገር ተከስቶ የነበረውን ድርቅና የመንግሥትን ቢሮክራሲ ሕያው አድርጎ የከተበባቸውን ‹‹ማዕበል የአብዮት ዋዜማ››፣ ‹‹ማዕበል የአብዮት መባቻ›› እና ‹‹ማዕበል የአብዮት ማግስት›› የተባሉ ሦስት ልብወለዶችን አስነብቧል። እነዚህ የማዕበል ድርሰቶቹ በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሦስት ተከታታይ የሆኑ መፃሐፍትን በማሳተም ረገድ ብርሃኑ ዘሪሁን በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ፈር ቀዳጅ ሆኖ እንዲጠቀስ አስችለውታል። ‹‹ጣጠኛው ተዋናይ›› እና ‹‹ባልቻ አባ ነፍሶ›› የተሰኙ ተውኔቶችንም ጽፎ ለመድረክ አብቅቷል።

በ1958 ዓ.ም ያሳተመው ‹‹የቴዎድሮስ እንባ›› የተሰኘው መጽሐፉ የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስን አነሳስና ለኢትዮጵያ የነበራቸውን ራዕይ ብሎም የሕይወታቸውን ፍፃሜ የሚያሳይ ነበር። ብርሃኑ ይህን መጽሐፍ ከመፃፉ አስቀድሞ በነበሩት ጊዜያት ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በይበልጥ የሚታወቁት በኃይለኛነታቸውና በጭካኔያቸው ስለነበር ውስጣዊ ስብዕናቸውና ሌሎች ባሕርዮቻቸው ጎልተው አይነገሩም ነበር። እናም ብርሃኑ ዘሪሁን ያልተነገሩትን የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ባሕርያት ወደ አደባባይ በማውጣት ንጉሠ ነገሥቱ ብሔራዊ ጀግና መሆናቸውን የሚገልፅ ድርሰት ጽፎ በማቅረቡ የበርካቶችን ቀልብ መሳብ ቻለ። ይህ ‹‹የቴዎድሮስ እንባ›› የተሰኘው ታሪክ በኋላ ወደ መድረክ ሥራ ተቀይሮ ከታላላቅ ትያትሮች ተርታ መሰለፍ ችሏል።

‹‹ድል ከሞት በኋላ›› የተሰኘው ሥራው የሌሎች ሕዝቦችን ታሪክ መተረኩ ከብርሃኑ ሥራዎችም ሆነ ከሌሎች በዘመኑና ከእሱም ቀድመው ከታተሙ ልብወለድ ድርሰቶች ልዩ እንደሆነ ይነገርለታል።

ሦስቱ ማዕበሎች እና ‹‹የታንጉት ምስጢር›› መጻሕፍቱ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ተተርከው ለሕዝብ በመቅረባቸው በበርካታ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ አሉ።

የኢትዮጵያን ደራሲዎች ታሪክ ‹‹Black Lions The Creative Lives of Modern Ethiopia’s Literary Gi­ants and Pioneers›› በሚል ርዕስ የፃፉት ኖርዌያዊው ሩዶልፍ ሞልቬር፤ ብርሃኑ ዘሪሁንን ከኢትዮጵያ ታላላቅ ደራሲያን ተርታ አስቀምጠውታዋል።

ሀገርን እና ትውልድን በብዕሩ ቀለማት ሲዘክር የኖረው ደራሲና ጋዜጠኛ ብርሃኑ ዘሪሁን ሚያዚያ 16 ቀን 1979 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት ተለይቶ ሥርዓተ ቀብሩ በባለወልድ ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል።

ደበበ ሰይፉ

ገጣሚ፣ ፀሐፊ ተውኔት፣ ደራሲ፣ ሃያሲ፣ ተርጓሚ፣ መምህር እና የሥነ ጽሑፍ ተመራማሪ ደበበ ሰይፉ ያረፈው በዚሁ ሳምንት ከ24 ዓመታት በፊት ሚያዚያ 16 ቀን 1992 ዓ.ም ነው።

ደበበ ሰይፉ ሥራዎቹ በተደጋጋሚ የሚጠቀሱና በብዙ የሥነ ጽሑፍ ወዳጆች የተመሰከረለት ገጣሚ ነው። የግጥም ትሩፋቶቹ በአንድ ላይ ተሰባስበው ‹‹የብርሃን ፍቅር›› በሚል ርዕስ ታትመዋል። በ1992 ዓ.ም ደግሞ በሜጋ አሳታሚ ድርጅት አማካኝነት ‹‹ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ›› በሚል ርዕስ ሁለተኛዋ የሥነ ግጥም መፅሐፉ ታትማ ለንባብ በቅታለች።

ደበበ ሰይፉ ከገጣሚነቱ ባሻገር ሐያሲም ነበር። ያለፈውን ከአሁኑ ጋር እያነፃፀረ የሚያስረዳና የሚተነትን ባለሙያ ነው። የሂስ ጥበብን ከታደሉትና በኢትዮጵያ የዘመናዊ ሂስ ጥበብ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት ሰዎች መካከል ደበበ ሰይፉ አንዱ ነበር።

ደበበ የትያትር ጥበብ መምህር ከመሆኑም በላይ በዘርፉ ውስጥ ግዙፍ የሚባል አስተዋፅዖ አበርክቶ አልፏል። ደበበ በመድረክ ላይ የሚሠሩ ቴአትሮችንና የቴአትር ጽሑፎችን የያዟቸውን ሐሳቦች በመተንተንና ሒስ በመስጠት ለዘርፉ ዕድገት የበኩሉን ሚና ተጫውቷል።

ደበበ የቃላት ፈጣሪም ነው ይባልለታል። ለአብነት ያህል በትያትርና በሥነ ጽሑፍ ዘርፎች ውስጥ በእንግሊዝኛ ቋንቋ መጠሪያ የሆኑ ሙያዊ ቃላትን ወደ አማርኛ በማምጣት አቻ የሆነ የአማርኛ ትርጉም በመስጠት ይታወቃል። በኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ክፍለ ትምህርት ውስጥ እስከ አሁን ድረስ መጠሪያ የሆኑትንና ‹‹ገፀ ባህርይ››፣ ‹‹ሴራ››፣ ‹‹መቼት››፣ ‹‹ቃለ ተውኔት›› … እየተባሉ የሚገለፁትን መጠሪያዎች የፈጠረው ደበበ ሰይፉ ነው።

ደበበ ለትያትር ትምህርት ዘርፍ ካበረከታቸው አስተዋፅዖዎች መካከል ለትምህርቱ መጐልበት ይረዳ ዘንድ በ1973 ዓ.ም ‹‹የቴአትር ጥበብ ከጸሐፌ ተውኔቱ አንፃር›› የሚል ርዕስ ያላት መጽሐፍ ማሳተሙ የሚጠቀስ ነው።

ደበበ ጸሐፌ ተውኔትም ነው። በርካታ ተውኔቶችን ጽፎ ለመድረክ አብቅቷል። አንዳንዶቹ ደግሞ ለበርካታ ጊዜያት ያህል በቴሌቪዥን ታይተውለታል። ደበበ ከጻፋቸውና ከተረጐማቸው ተውኔቶች መካከል ‹‹ከባሕር የወጣ ዓሣ››፣ ‹‹እናትና ልጆቹ››፣ ‹‹እነሱ እነሷ››፣ ‹‹ሳይቋጠር ሲተረተር››፣ ‹‹የሕፃን ሽማግሌ››፣ ‹‹ማክቤዝ››፣ ‹‹ክፍተት››፣ ‹‹እድምተኞቹ›› እና ‹‹ጋሊሊዮ ጋሊሊ›› ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ በነበረባቸው ዓመታት በርካታ የምርምር ሥራዎችን አከናውኗል፤ ብዙ መጽሐፍትንም ጽፏል። በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎች ተቋም የጥናት መጽሔት አሳታሚ ኮሚቴ እና በኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ውስጥ ዋነኛ ተሳታፊ በመሆን ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ መስፋፋት ሰፊ እገዛ አድርጓል። እነሆ በሥራዎቹም ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You