የፍቅር፣ የሥነጥበብ፣ የፋሽን፣… ከተማዋ ፓሪስ ከስፖርትም ጋር በእጅጉ የተወዳጀች ነች፡፡ በአውሮፓ ስመጥርና በጎብኚዎች ዘንድ ተዘውታሪ ከሆኑ ከተሞች መካከል አንዷ የሆነችው ፓሪስ፤ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ በጉጉት የሚጠበቁ ታላላቅ ስፖርታዊ ውድድሮችን በማስተናገድም የተመሰከረላት ናት። የስፖርቱ ዓለም ቁጥር አንድ የሆነውን ስፖርታዊ ውድድር ኦሊምፒክንም በታሪኳ ለሦስተኛ ጊዜ ለማሰናዳት 95 ቀናት ብቻ ቀርተዋታል፡፡
በርካታ ታላላቅ ስፖርታዊ ውድድሮችን ለማሰናዳት ተመራጭ ከሆኑ እንዲሁም ለልዩ ልዩ ስፖርት ዓይነቶች ምቹ የሆኑ ማዕከላት ካሏቸው ቀዳሚ 10 ከተሞች መካከል አንዷ የፈረንሳዊያን ኩራት የሆነችው ፓሪስ ናት፡፡ ከተማዋ ብቻም ሳትሆን እንደአጠቃላይ ፈረንሳይ ታላላቅና እጅግ ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን መገንባትና ውድድሮችንም መሳብ የቻለች ከተማ ናት። የዓለም ሻምፒዮናው የእግር ኳስ ቡድኗ እንዲሁም የእግር ካስ ሊጓ በአውሮፓ ታዋቂ ከሆኑት መካከል የሚመደብ እንደመሆኑ ከስፖርቱ ጋር ጠንካራ ቁርኝት አላት፡፡ ከአትሌቲክስ ስፖርት ጋርም ስሟ በስፋት የሚያያዘው ከተማዋ ዓመታዊው ፓሪስ ማራቶን ከመለያዎቿ መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡ ዝነኛ አትሌቶችን ጨምሮ በርካቶችን የሚያሳትፈው ይህ የጎዳና ላይ ሩጫ ከኒው ዮርክ ማራቶን ቀጥሎ ሁለተኛው የዓለም ትልቁ ሩጫ ነው፡፡
ታላቁን የብስክሌት ውድድር ቱር ደ ፍራንስን ጨምሮ የኦሊምፒክ ደረጃን የሚያሟሉ በርካታ የዋና ገንዳዎቿ፣ የሜዳ ቴኒስ፣ የፈረስ ግልቢያ፣ የራግቢ እና ሌሎች ስፖርታዊ ውድድሮች በፓሪስ አፈር ላይ ከ‹‹ኤፍል›› ማማ ስር የሚከወኑ ታላላቅ ሁነቶች ናቸው። አሁን ደግሞ ኦሊምፒክን ለማስተናገድ ሽር ጉዷን እያጠናቀቀች ትገኛለች፡፡ በእርግጥም ፈረንሳይና ፓሪስ ስፖርታዊ ሁነቶችን በማካሄድ ብቻም ሳይሆን ለዓለም የስፖርት ታሪክ ስማቸው ለዘመናት ሲወሳ የሚኖር ታላቅ ባለሙያዎችንም አፍርታለች፡፡ በተለይ የዘመናዊው ኦሊምፒክ ምስረታ ሲታሰብ የጥንስሱ ባለቤት የሆኑት የስፖርት እና የሥነጥበብ ሰው እንዲሁም መምህሩ ፒየር ደ ኩበርቲን አብረው ይነሳሉ። ጥንታዊው የአቴናውያን ልማድና የአምልኮ ሥርዓት የሆነው ኦሊምፒክ ከዘመናት በኋላ በዘመናዊ መልክ ተቃኝቶ የዓለምን ሕዝብ የሚያስተሳስርና ሠላምን የሚሰብክ እንዲሆን ያደረጉት ፈረንሳዊው የስፖርት አባት ናቸው፡፡
እአአ በ1896 የኦሊምፒክ ትውልድ ሃገር የሆነችው ግሪክ የመጀመሪያውን ዘመናዊ ኦሊምፒክ አቴንስ አስተናገደች፡፡ ከአራት ዓመት በኋላ ተራው የፓሪስ በመሆኑ ከተማዋ ከግሪክ ውጪ ኦሊምፒክን ያስተናገደች የዓለም ቀዳማዊቷ ከተማ በመሆን በማኅደሯ ሌላኛውን ታሪኳን ልትመዘግብ ችላለች፡፡ የከተማዋ ቀጣዩን ኦሊምፒክ ለማስተናገድ 24 ዓመታትን ብቻ የጠበቀች ሲሆን፤ አንደኛው የዓለም ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ የተካሄደ ሁለተኛው ኦሊምፒክ መሆኑንም ታሪክ ያወሳል፡፡ በወቅቱ የዘመናዊው ኦሊምፒክ መሥራችና የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት የሆኑት ፒየር ደ ኩበርቲን የመጨረሻው ቆይታ በመሆኑም ታሪካዊ ያደርገዋል፡፡
ኦሊምፒኩ ከ44 ሃገራት የተወጣጡ 3ሺ የሚሆኑ ስፖርተኞች ተሳታፊ የነበሩበት ሲሆን፤ የመክፈቻ እና መዝጊያ መርሐ ግብሮቹን በኮሎምበስ ስታዲየም በማድረግ ነበር የተካሄደው፡፡ ወቅቱ ፓሪስ የመጀመሪያውን የኦሊምፒክ የዋና ገንዳ፣ የኦሊምፒክን መንደር ያስተዋወቀችበት እንዲሁም ጥቂት ስፖርቶች ላይ ለውጥ የታየበትም ነበር፡፡ በጥንታዊ ነገር ግን አስደናቂ በሆኑ ኪነ ሕንጻዎቿ የምትታወቀው ተወዳጇ ከተማ ፓሪስ ሦስተኛውን ኦሊምፒክ ለማካሄድ 100 ዓመታትን ጠብቃለች፡፡ ይህም ታሪካዊ ሊባል የሚችል ጉዳይ ሲሆን፤ ይህንን ተከትሎም በኦሊምፒክ ባሕል መሠረት ከተለመደው ውጪ የመክፈቻ እና የመዝጊያ መርሐ ግብሮቹ በስታዲየም ውስጥ አይደረጉም፡፡
ይህ ኦሊምፒክ ታሪካዊ ሊያስብለው የቻለው ፓሪስ ለአዘጋጅነቷ አንድ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረችበት ብቻም ሳይሆን ከሴቶች ተሳትፎ ጋር በተያያዘም ነው፡ እአአ በ1924 ፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ ከተካፈሉ 3ሺ አትሌቶች መካከል የሴቶቹ ቁጥር 100 ብቻ ነበር። በኦሊምፒክ ኮሚቴው በኩል ተሳትፎው በየጊዜው እያደገ ነው ይባል እንጂ የሚፈለገውን ግብ ሳይመታ ዘመናትን ማስቆጠሩ አልቀረም፡፡ ከሦስት ወራት በኋላ በሚደረገው 33ኛው የፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ ግን እኩል የተሳትፎ ታሪክ እንደሚመዘገብ ከወዲሁ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም