የሙዚቃው አጥቢያ ኮከብ

መሽቶ ሲነጋጋ፤ ጀንበር ጠልቆ ጀንበር ሲወጣ፤ የአጥቢያ ኮከብ ከአዲስ ሰማይ ላይ አዲስ ቀንን ከአዲስ ብርሃን ጋር ይዞ ከተፍ ይላል። የአጥቢያው ኮከብ፤ ለሚገፈፈው ጨለማ፤ ለምትመጣዋ ፀሐይ ማብሰሪያ ነው። የውበቱ ግርማ የቀኑን ብሩህነት ይነግረናል። እይታችን ሲጠነክር ከአንዱ ቦታ እየተወረወረ፤ ከሌላኛው ቦታ ላይ በኃይለኛ የብርሃን ምት ብው!“ ሲል እናያለን። ከዘመናት በአንዱ ዘመን፤ ጥበብም እንዲህ ያለውን ልጅ ወለደች። ልጁም፤ በሙዚቃ ቤት አድጎ፤ ሙዚቃን ከልቡ ኖሮ ከልቡ ሠራት። የሙዚቃው የአጥቢያ ኮከብ፤ ኮሎኔል ሣሕሌ ደጋጎ … ከስንት አንዱ እንደሚወረወሩቱ እንደ አጥቢያ ኮከቦቹ ሁሉ፤ እሱም ከስንት አንዴ ከሚፈጠሩ የጥበብ ክዋክብት መሐከል አንደኛው ነው።

ኮሎኔል ብሎ የጦር ሜዳ ጀግና እንጂ፤ የጥበብ አውድማ ልሂቅ አለ ለማለት ምናልባትም ለምናብ የሚከብድ ነው። ኮሎኔሉ ግን ጠመንጃን ፈቶ የመገጣጠም ያህል ሙዚቃንም እየፈቱ በልበ ሙሉነት ገጣጥመው ተዓምሩን ለማሳየት ችለዋል። ከጦር ሜዳው ጀብዱ ይልቅ፤ ከሙዚቃው መዋደዱ ልባቸውን እየፈነቀለ፤ “ላልከዳህ! ላልከዳሽ!” ተባብለው፤ በጥበብ ፊት ከሙዚቃ ጋር የቃለ መሐላውን የእምነት ማኅተብ አስረዋልና የቱ ጀግና፤ ማንስ ብርቱ ሊለያያቸው … ለጥበብ መሰጠት ካሉ አይቀር እንዲህ ነው እንጂ።

እንደ ጥበብ አንቺ፤ እንደ ኪነ ጥበቡም አንተ፤ ስንል በፍቅር እንጂ ለአጥቢያ ኮከቡ የሚሆን ክብር ጠፍቶ አይደለም። ሥራው እንኳንስ እሱንና አንድ ፍሬ ጨቅላውንም “አንቱ” የሚያሰኝ ቢሆንም፤ የሙያ ልጆቹ ሁሉ “ጋሼ” ብለው አንተ፤ እንደሚሉት የአባት ፍቅር እጣን እንዲጤስ ነው። ኮሎኔል ጠመንጃ አቀባባይ፤ ዋሻ ሰርሳሪ ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ፤ ሙዚቃ ቀማሪ ሆኖ ቁጭ አለው። እሱ ሙዚቃን የወደዳትን ያህል፤ ጥበብም ከልጇ ሙዚቃ ጋር በፍቅር ወድቃለታለች። ጠላትን መማረክ ብቻም ሳይሆን፤ ጥበብንም በፍቅር፤ “ልብ ወደ ላይ!” ለማለት የቻለ ድንቅ የግጥምና ዜማ ደራሲ፤ የሙዚቃ መሣሪያዎች ተጫዋች ነበር።

ነጆ፤ ምዕራብ ወለጋ ይህን የዘመን ክስተት የሆነ የአጥቢያ ኮከብ አብቅላ ተመለከተች። ከተከበረው የባላንባራስ ደጋጎ ቤት ውስጥ ሣሕሌ ደጋጎ የተባለው ተዓምረኛ ልጅ ይወለድ ዘንድም ከላይ ተፈረደበት። ደጓ እናት ደጊቱ ፈይሳና ንጉሣዊው ባላንባራስ ደጋጎ አለቤ፤ በ1923ዓ.ም ሣሕሌ ደጋጎን፣ ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ ዱብ አደረጉ። ይሰማኛል፤ የዚያን ዕለት…ከጎረቤታቸው ወይዘሮ ሱመያና ጋዲሴ፤ እንዲሁም ከአመለወርቅና ኤራዬ በላይ፤ የጥበብ የእልልታ ድምፅ እንዴት ሰፈሩን በአንድ እግሩ አቁሞ እንደነበረ።

ሣሕሌ ደጋጎ፤ አደገ ተመነደገ። ድክ ድክ ከማለት፤ ዱብ ዱብ ወደ ማለት ተሸጋገረ። አሁን ወሳኙ ነገር፤ ፊደል ቆጥሮ የቀለም ቀንድ ማብቀል ነበር። ይህን ቀንድ ፍለጋ ከነጆ ወደ ነቀምት አመራ። በዚያም የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ፤ ከሚንስትሪ ኩባያ ላይ የነበረችውን ጥያቄ ጭልጥ ቢያደርግም፤ በአንድ በኩል ብቻ ያለ ቀንድ ውበትንም ይገድፋልና ለሁለተኛው ቀንድ፤ አዲስ አበባ በመዝለቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ቀጠለ። ወደፊት ስሟን የሚያስጠራውን ጀግና የማስተማር ዕድሉን ለማሳለፍ አልፈቀደችምና፤ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት፤ እጇን ዘርግታ ተቀበለችው።

ልጅ በልጅነቱ የተመለከተውን ነገር፤ ቢረሳውም ልቡ ግን ፈጽሞ አይረሳውም። ገና ሕጻን ሳለ በባላንባራሱ፤ በአባቱ ዙሪያ ይመለከተው የነበረው፤ ጠመንጃና የወታደርነት መንፈስ፤ ደርሶ አሁን ልቡን ፈንቀል እያደረገ ይተነኩሰው ጀመር። ተማሪው ሣሕሌ ወታደር መሆን አማረው። ጠመንጃ ማንገብ፤ ለሀገር ቆሞ ለሀገር መዋደቅ፤ ልቡን ሰልቦ ምርኮኛ አደረገው። እናም፤ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በቀጥታ ወደ አንደኛ ክፍለ ጦር አመራ። እዚህስ ቢሆን ማንስ እጁን አጣመረበትና … ደግሞ ከአንደኛ ክፍለ ጦር በ1942ዓ.ም ወደ ማዕከላዊ ዕዝ ተሸጋገረ፤ ወደ አንጋፋው የክቡር ዘበኛ ጦር ማለት ነው። ብቻ ይገርማል፤ ከነበረው ወታደራዊ ቅልጥፍናና ታዛዥነት የተነሳ፤ ከተራ ወታደርነት በአንድ ጊዜ የሃምሳ አለቅነት ማዕረግ፤ ከሳሪያን ኮቱ ላይ ተለጠፈለት። ሃምሳ አለቃ ሣሕሌ ደጋጎ።

ጥበብ ግን ይህንን ተመልክታም አልማረችውም። እጆችህ የሙዚቃ መሣሪያ እንጂ የጠመንጃ አይደሉም አለች። ጣቶችህም ለፒያኖና ክላርኔት እንጂ ለቃታ አይደሉምና ∙ ∙ ∙ በማለት፤ ምን ቀረ ሳትል፤ ይሄን የሙዚቃ መሣሪያ ባይነት ባይነቱ አስታቀፈችው። መሣሪያዎቹን በነካ ቁጥርም የሚፈሰው ግጥምና ዜማ ሆነ። ከሣሕሌ ጋር ትውውቅ ያደረገችው የመጀመሪያው የሙዚቃ መሣሪያ ክላርኔት ነበረች። አስቀድሞ በእግረኛ ባንድ ውስጥ ሳለ አሳምሮ ተጫውቷታል። እሷም ከእጁ ላይ ሆና ስትሽኮረመምና ትንፋሹ ከውስጧ ሲደባለቅ፤ አቤት! የምትሰጠው ድምፅ… በሣሕሌ ደቀመዝሙርነት ውስጥ፤ የሙሴ ኒኮ መምህርነት የሚረሳ አይደለም። ሙሴ ኒኮ፤ ፈረንሳዊ ምርጥ የሙዚቃ አስተማሪው ነው። ምናልባትም ከልጅነቱ የዳከረባቸውን ሁለቱን የእውቀት ቀንዶች፤ በክብር ያጠለቀለት ሰው ነው። የወይን ጣፋጭነት በፍሬው፤ እንዲሉ የሣሕሌ ጣፋጭነት በተነሳ ቁጥር፤ የዚህ ፈረንሳዊ ግንድነት አብሮ ይወሳል።

ወታደር ቤትና ሣሕሌ ደጋጎ፤ ማለትም አሁን ኮሎኔል እያልን ብንጠራው ይሻላልና ኮሎኔል ሣሕሌ ደጋጎ፤ እንደ እጅና ጓንት ልክክ አሉ። የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ባንድ ለእርሱ፤ እርሱም ለባንዱ ትክክለኛው ቦታና ምርጫ ነበሩ። ከነ ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ፣ ሻለቃ ግርማ፣ ባሻ ገብረአብ ተፈሪና ኮሎኔል ሣሕሌ በቤቱ ውስጥ የነበራቸው ጥምረት፤ የክቡር ዘበኛን ከማማው ላይ ሰቀለው። እዚህ ቤት ውስጥ ኮሎኔል ሣሕሌ ሙዚቀኛ ብቻ አልነበረም። እንደየቦታና አስፈላጊነቱ ረዥምና አጫጫር ድራማዎችንም እየጻፈ፤ ቤቱን በሁሉም አቅጣጫ ቀስቶ የያዘ ሁለገብ ቅስት ሆነ።

እሱ ማለት፤ ታሪካዊ ሥራዎቹን ከታሪክ ጋር ያዋሐደ፤ የጀግንነት መጠሪያው የማይበቃው ጀግና ቢሆንም፤ ሳይነገርለት የኖረና አንዳንዴም አሳዛኝ ነው። በወቅቱ ከነበሩትና ዛሬም ድረስ በልባችን ካዘልናቸው ድንቅ ድምፃዊያን፤ የኮሎኔሉን የግጥምና የዜማ ድርሰቶች እየጠረጠረ ያልበላ፤ እያዜመ ያላንቆረቆረ አለ ለማለት አይቻልም። ክቡር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ፤ ቀዳሚው ተጠቃሽ ነው። በትንሹ ሰባት ያህል የሙዚቃ ሥራዎች ላይ አብረው ማዕድ ቆርሰዋል። “ዋይ ዋይ ሲሉ” ልብን የሚሰብር፤ አሳዛኙ ገጽ ነው። ጊዜው በኢትዮጵያ ምድር፤ በኢትዮጵያ አድባር ላይ፤ ረሀብ ጸንቶ ዋይታና ሲቃው የበረታበት ጊዜ ነበር። ከዕለታት በአንዱ ቀን፤ የሙዚቃ ቡድን ኦርኬስትራው አባላትና ሌሎችም ለሥራ ወደ አሰብ በመሄድ ላይ ነበሩ።

በመኪናው መስታወት ወደ ውጭ የሚታየው ሁሉ ልብን ኩምሽሽ የሚያደርግና በኀዘን የሚደፍቅ ነበር። ከደረሱ በኋላ ወደ አንደኛው ወረዳ ጎራ ሲሉ፤ በዚያ ደግሞ ከብቱ ሁሉ አልቋል። ወንድ ልጅ የለም። ያለውም በረሀብ የፊጥኝ ታስሮና ተክዞ በሞት መስታወት ውስጥ እራሱን በመመልከት ላይ ነው። እጆቿ ቢቆረጡ በአፏ የምታጎርሰው እናት፤ ልጆቿን ከጅብና አሞራ ለማትረፍ አንዱን በጀርባዋ አዝላ፤ ሌላውን በቀኝና ግራ አቅፋ፤ በደረቷም ተሸክማ፤ ከሞት ሽሽት ትድሃለች። በስፍራው የተገኙትን አባላት የተመለከቱ ሕጻናት ልጆችም፤ ድንገት ሲሮጡ መጥተው ከዙሪያቸው ተኮለኮሉ።

“አባባ… ዋይ! ዋይ!…ግደሉን… ሞትን” በማለት ጠግቦ ባልተናገረው አንደበታቸው የሲቃ ድምጻቸውን በተማፅኖ ለማሰማት ሞከሩ። ኮሎኔል ሣሕሌ ሲያስታውሰውም፤ “ፍራንክ ብንሰጣቸውም ለልጆቹ ምንም አይጠቅማቸውም። እናም አሰብ ገባንና ሁለት ቀን ካደርን በኋላ፤ በሦስት ኩንታል ሞልተን ዳቦ ገዛንና ተመልሰን ወደ እዚያው ሄድን። ትንሽ እንኳን ሕይወት እንዲተርፍ በማሰብ፤ ለእያንዳንዱ አንዳንድ ድፎ ዳቦ ስናድል ዋልን።” ይላል፤ መጥፎውን አጋጣሚ ተንተርሶ የሠራትን ሙዚቃ፤ መነሻዋን ሲገልጽ። በሰዓቱ ጥበብ የከፈተችው የሣሕሌ የልብ በር ገርበብ እንኳን ለማለት አልቻለም ነበር። በመኪናው ውስጥ ሳሉም፤ በልጆቹ ዋይታ በልቡ እያነባ፤ ”ዋይ ዋይ ሲሉ” የምትለዋን የሙዚቃ ግጥም በመጻፍ ላይ ነበር። “ዋይ እማማ፤ ዋይ አበባ ሲሉ፤ ሆዴ ባባ!” ይላል። አባላቱ ከአሰብ ተነስተው አዲስ አበባ ገቡ። እንዲህቹ ሲታገላት የደረሰው ይህ ሙዚቃም፤ ሁሉም ወደዱትና መሠራት አለበት በማለት ግፊት አደረጉ። “እንባው ከየት እንደመጣለት ባላውቅም፤ ጥላሁን ከልቡ እያለቀሰ ነበር የሠራው” አለ ኮሎኔል ሣሕሌ፤ በወቅቱ በድምፁ ያንቆረቆረውን የጥላሁን ገሠሠን ሁኔታ በማስታወስ።

ዋይ ዋይ ዋይ ሲሉ፤

የረሀብን ጉንፋን ሲስሉ፤

እያዘንኩኝ ባይኔ አይቼ፤”

ምን ላድርግ፤ አለፍኳቸው ትቼ …

አሳዛኙን ሀገራዊ ክስተት፤ ልብን ስንጥቅ በሚያደርጉ የግጥም ስንኞች፤ አንጀትን በሚበሉ የዜማ ፏፏቴዎች፤ አጥቦና ከሽኖ በድምፁ ቅላጼና ስርቅርቅታ መላ አካላትን ለሚቀሰቅሰው፤ ለሙዚቃው ንጉሥ ለጥላሁን ገሠሠ ሰጠው። ጥላሁንም፤ እንባውን ከአይኑ እያረገፈ፤ አድማጭ ተመልካቹን ሁሉ ከእንባ ዥረት እየቀዳ እንዲጠጣ አደረገው። የሁለቱ፤ በአንድ የሙዚቃ ማዕድ ዙሪያ ተቀምጦ መጎራረስ ተጀመረ እንጂ አላከተመም። “ስቆ መኖር” በሚለው ሥራቸው፤ ያለቀሰው ሁሉ ስቆበታል። ኮሎኔል ሣሕሌ በግጥምና ዜማው፤ ክቡር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ በድምፁ “እውነት ማሪኝ” አሉና ደግሞ እንደገና “ውሸት ለመናገር” በማለት “ልብሽን ለአፈርሰው”ን ደገሙት። ቢሆንም ግን “ይህቺ ጉብልማ መቅረት የለባትም ብለው በማሰብ፤ “ኮቱሜ” ሲሉ ትመጣ ዘንድ ጠሯት። የሁለቱ ጥምረትና ውሕደት ግን የሚጠገብ አልነበረም። አምጡት በላይ ላዩ፤ ስሩት በስር ስሩ … የሚያስብልም ነበር። የሰሙበት ጆሮ እያጣጣመ ድገሙልኝ በማለት፤ ልብም ቅቤውን ጠጥቶ አልጠገብኩም ሲል እሰይ! እያለ አንጀትም ይርሳል።

የኮሎኔሉን አጥቢያ ኮከብነት፤ ጅምሩን እንጂ ፍጻሜው ድረስ ቆሞ አንድ ባንድ ለመመልከት ያዳግታል። ቃታውን እየሳበና ዒላማው ላይ እያነጣጠረ የሚያረግፈውን የሙዚቃ እንኮይ፤ እስኪጠግቡ ይበሉት ይሆናል እንጂ ቅርጫት ሞልቶ ለመሸከም የማይቻል ነው። እጅግ ግሩም በሆነ መልኩ፤ ይህ ድንቅ ኮሎኔል አራት መቶ (400) ያህል የሙዚቃ እንኮይ በማርገፍ፤ የሙዚቃ አድማጩን ረሀብ ወደ ጥጋብ ለውጦታል። ምን ይሄ ብቻ፤ አንድ መቶ ያህል የኦሮምኛ ሙዚቃዎችንም በመሥራት፤ ሁለገብነቱን ብቻም ሳይሆን ሁሉ አዋቂነቱንም አስመስክሯል። አዋቂ ክፉ አይወጣውምና “አይወጣኝም ክፉ ነገር” ሲል በብዙነሽ በቀለ ሙዚቃ ውስጥ ነገረን። “ከንቱ ሥጋ”፤ “አታሳየኝ ጭንቁን”፤ “የፍቅር ወጋገን”፤ “ቃልኪዳን”፤ “ፍቅርህ ቀሰቀሰኝ” እና ሌሎችንም ግጥምና ዜማዎችን በመሥራት፤ ለብዙነሽ በቀለ ሰጥቷል። ድምፃዊቷ መንበረ በየነ “እንዴት ከረማችሁ” ስትል፤ ግጥምና ዜማው በኮሎኔሉ ነው።

የኮሎኔል ሣሕሌ ደጋጎ ሌላኛው ምትሐታዊ ብቃት፤ ግጥምና ዜማ ከመሥራትና የሙዚቃ መሣሪያዎቹን እንዳሻው ከማናዘዝ ያለፈ ነው። በአንድ ሙዚቃ ሙሉዕነት ውስጥ የቀረው ነገር ግጥምና ዜማውን አዋዶ ሙዚቃ ማቀናበር ነበር፤ ጥበብ እሱንም አንስታ ሰጠችው። የጥበብ ለጋስነት፤ የእርሱም የታማኝነት ልክ ምትሐት ነው። ጥበብ ፍሬዋን የዘራችው፤ ከትክክለኛው ለም መሬት ላይ ነበርና፤ አንዱ ሃምሳና ስድሳ … መቶና አራት መቶ፤ አልፎም አምስት መቶ አፈራ። ታዲያ ይህ ምትሐት አይደለምን?

ወደ መጣሁበት ምድር፣

እስክመለስባት በክብር፤

ሰውን ከማስደሰት በቀር፣

አይወጣኝም ክፉ ነገር።

ቀደም ሲል ያነሳነውን “አይወጣኝም ክፉ ነገር” የተሰኘውን፣ ይህን የብዙነሽ በቀለን ጥዑም ዜማ፤ በፍቅር እስክንወድቅበት ድረስ አሳምሮ ያቀናበረው ይሄው ኮሎኔል ሣሕሌ ነው። “ፍላጎቴ”፤ “ምን ነበር”፤ “ምንድን ነው ትዝታህ” የሚሉት ሥራዎቿንም እንዲሁ በቅንብር ያዋሓዳቸው እርሱ ነው። “ይህ ነው ጌትነት” እና “የምድር ፈተና” የተሰኙትን ጨምሮ በ1966 ዓ.ም፤ በውብሻው ስለሺ የተዜሙትን ተወዳጅ ሥራዎች አቀናብሮ ለክብር አብቅቷቸዋል። የተፈራ ካሣን “የከተማው”፤ “ሥራ ፈቶ ሲያይሽ”፤ እንዲሁም፣ “መጠን አትለፉ” የሚሉ ጣፋጭ ሙዚቃዎችን ስናደምጥ፤ ኮሎኔል ሣሕሌም ከጀርባ አለበት።

በመጠጥ ደስታ ይገኛል ብላችሁ፤

መጠን አትለፉ ትቃጠላላችሁ፤

ስንቱ በማንኪያ የማይሞላለትን፤ እርሱ በጭልፋ ከዛቀው፤ ስንቱን ጨልፈን እንደምንችለው ግራ ነውና እነኚህን ሥራዎቹን እንጨምር። “በመጠጥ ደስታ”፤ “አላዝንም ለራሴ”፤ “አሸብርቆ ደምቆ” “ከረሜላ ነህ” እና በሌሎችም የልዩ ልዩ ድምፃውያን ሥራ ላይ ከግጥምና ዜማ እስከ ቅንብር ተሳትፎባቸዋል። በሙዚቃው አድማስ፤ ከግጥምና ዜማው እስከ ቅንብር ውሕደቱ ድረስ፤ ከማሕሙድ አሕመድ አንስቶ ጥሶ ያልገባበት የግዛት ድንበር የለም። የአጥቢያ ኮከብ ነውና ደምቆ በብርሃን ሊታይበት የማይችልበት ወሰን የለም።

ኮሎኔል ሣሕሌ ደጋጎንማ ጥበብ እራሷ በሰማይ ውለታውን ከፍላ ታስተሰርየን እንጂ፤ እንደኛማ ውለታ መላሽነት … ቀና ብለን በሁለት ዓይን ለማየት አያስደፍረንም። ኮሎኔሉ በእድሜ ዘመኑ “ተበርክቶለታል” ተብሎ የሚነገርለት ይህ ነው። በአንድ ወቅት የክብር ሜዳሊያና የ20ሺህ ብር የገንዘብ ስጦታ፤ በረዥም ዓመታት ውስጥ፤ በ10፣ በ20 እና 30 ዓመት ለእያንዳንዱ ከወርቅ እስከ ነሐስ ተበርክቶለታል። በ1991 ዓ.ም ደግሞ የሕይወት ዘመን ሽልማት አግኝቷል። ለተዋጊ ወታደርነቱ ደግሞ የደረት ላይ ዓርማ የሆነውን ኒሻን ተሸልሟል።

በአንድ ወቅት፣ የሙዚቃ ቀማሪው፤ የግጥምና ዜማው ጌታው ኮሎኔል ሣሕሌ ደጋጎ በጠና ታመመ። ለስንቱ ደርሶ ስንቱን እንዳልሠራ፤ የዚህን ጊዜ ግን ሕክምናውን እንኳን በቅጡ ለመከታተል ሳይችል ቀረ። እጅግ አዝኖና ተክዞ የሞትን የጥሪ ድምፅ መጠባበቅ ጀመረ። የእርሱን ሕይወት ለእናት ሀገሩና ለጥበብ ሰጥቶ የኖረው ሰው፤ “እንዴትስ የሚያሳክመኝ ልጣ? ብሎ፤ ማንንስ ይውቀስ? የነበረው አማራጭ በኀዘን እየተብሰለሰሉ ዝም ማለት ነበር። ይህን የሰማችው እውቋ ጋዜጠኛ ስንዱ አበበም ልታወጋው ስትገሰግስ ከቤቱ ደረሰች። እሱ ግን በመታመምና በመከፋት ጥምልምል ብሎ፤ በተስፋ መቁረጥ ተሸብቦ ነበር የደረሰችው። እናም፣ በጨዋታቸው መሐል፣ “እኔ ለአለቤ ሾው አንሳለሁ?” የሚል፤ ብስጭት አዘል የብሶት ጥያቄ ጠየቃት። “አለቤ ሾው” በወቅቱ ሕዝቡ ሁሉ በፍቅር የተማረከለት የቴሌቪዥን ዝግጅት ነበርና ወዲህ ጎራ ብሎ ችግሩን መናዘዝ ለቻለ፤ ጧሪ ደጋፊው ብዙ ነው።

የተሸከመውን ቀንበር ለመቋቋም የተሳነው ኮሎኔል ሣሕሌም፣ በዚህ ቀርቤ ችግሬን ለኖርኩለት ሕዝቤ ላጋራ በማለት፤ የአዘጋጁን የአለባቸው ተካን ደጅ ጠንቶ፣ አለቤ ግን ለካስ በጊዜው ሳይደርስለት ኖሯል፣ “እኔ ለአለቤ ሾው አንሳለሁ?” ብሎ ንድድ ማለቱ ለዚሁ ነበር። ይህ ለዛሬው ሚዲያዎቻችንም ጭምር የሚሆን ጥያቄና የሕሊና እዳ ነው። አለቤ በመጨረሻም ቢሆን፤ ደርሶ ክሶታል። ያማረ ቆይታ በማድረግም ሕክምናውን እንዲያገኝ አደረገው። ሞት ግን መካሪ የለውምና ቋምጦ እንደተመኘውም፣ መጋቢት 6 ቀን 2002 ዓ.ም ላይ አገኘውና ይዞት ከነፈ። ተላላው ሞት፤ ኮሎኔል ሣሕሌን ያህል ሰው ይሞት መስሎሃል … ይህ አይነቱ የአጥቢያ ኮከብነት፤ ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም!!!

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን  ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You