“ዕድሎችን ተጠቅሞ በጋራ ለማደግ በፈጠራ ሃሳብ ብቃት ያላቸው ዜጎች በብዛት ያስፈልጉናል”- ሙፈሪሃት ካሚል የሥራና ክህሎት ሚኒስትር

አዲስ አበባ:– ዕድሎችን ተጠቅሞ በጋራ ለማደግ በፈጠራ ሃሳብ ብቃት ያላቸው ዜጎች በብዛት ያስፈልጉናል ሲሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ተናገሩ።

በሳይንስ ሙዚየም ሲካሄድ የቆየውና 16 ሺህ ሰዎች የጎበኙት የስታርትአፕ ኢትዮጵያ ኤግዚቢሽን ትናንት ተጠናቋል::

በማጠናቀቂያ መርሀ ግብሩ ንግግር ያደረጉት ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል እንደገለጹት፤ በፈጠራ ሃሳቦች ላይ ተመርኩዘው ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በስፋት የሚያፈልቁ ዜጎችን ማፍራት ይገባል።

በአሁኑ ጊዜ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለቤቶች ያገኙትን ዕድል ተጠቅመው ለሀገር የሚበጅ ሰፊ ሥራ ማከናወን እንዳለባቸው አመላክተው፤ በስታርትአፕ ኤግዚቢሽኑ ላይ የተሳተፉና ዕውቅና ያገኙ ወጣቶች ያገኙትን ዕድል ተጠቅመው ሌሎችን የማብቃት ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

በተለያዩ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ የቴክኖሎጂና ችግር ፈቺ ፈጠራ ባለቤቶች የሚያከናውኗቸውን ሥራዎች በማጠናከር በቀጣይ አቅማቸውን ለማጎልበት ሊሠሩ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የስታርትአፕ ኢትዮጵያ ኤግዚቢሽን እንዲካሄድና ዘርፉ እንዲነቃቃ አቅጣጫ በመስጠት ልዩ አስተዋጽኦ ላደረጉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ ሲሉ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ኤግዚቢሽኑ እንዲሳካ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማትና ግለሰቦች ምስጋና አቅርበው በስታርትአፕ ውድድር አሸናፊ ለሆኑ የፈጠራ ሃሳብ ባለቤቶች የዕውቅና ሽልማት አበርክተዋል።

ላለፋት አራት ሳምንታት ሲካሄድ በቆየው ኤግዚቢሽን 300 ስታርትአፖች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ማቅረባቸውን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታውቋል:: በተዘጋጀው የአዕምሯዊ ንብረት የፈጠራ ባለቤትነት ውድድር በግብርና ሙያ የአንበጣ መከላከል ሥራ ላይ ትኩረቱን ያደረገው የርጭት መሳሪያ ቴክኖሎጂ ያቀረቡት አቶ ኪዳኔ ገብረስላሴ አንደኛ በመውጣት ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል።

በተመሳሳይ በቴክኖሎጂ ፈጠራ ውድድሮች አሸናፊ የሆኑ ቡድኖች ከአንድ ሺህ አምስት መቶ ዶላር ጀምሮ የተለያዩ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል።

በመድረኩ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ወልዱ ይመስል እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል::

ጌትነት ተስፋማርያም

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You