ሴቶችን በይበልጥ ወደ ፋይናንስ ዘርፉ በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ይገባል

አዲስ አበባ፡- ሴቶችን በይበልጥ ወደፋይናንስ ዘርፉ በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገለጸ።

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን አስመልክቶ “በሴቶች ላይ ኢንቨስት በማድረግ እድገትን ማፋጠን” በሚል መሪ ሃሳብ ዩኤን ውመን ከገንዘብ ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ትናንት የፓናል ውይይት አካሂዷል ።

በወቅቱ በገንዘብ ሚኒስቴር የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዘርፍ ተወካይ ራሔል መለሰ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ በርካታ ሴቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን ያልቻሉና ከእጅ ወደ አፍ የሚባል ኑሮ ላይ ናቸው፡፡

በመሆኑም ሴቶችን በይበልጥ ወደፋይናንስ ዘርፉ በማቅረብ ተጠቃሚነታቸው ማረጋገጥ እንዲሁም የፋይናስን አካታችነትን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።

ሴቶች ላይ ኢንቨስት በማድረግ በፆታ ልዩነት ሳቢያ የሚመጣን የኢኮኖሚ ክፍተት በመሙላት ዕድገትን ማፋጠን ይቻላል ሲሉ አስረድተዋል።

ገንዘብ ሚኒስቴር በሥራዎቹ ላይ ሥርዓተ ፆታን በማካተት ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ተቋሙ ሴቶችን ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ የማይክሮ ኢኮኖሚና የፊሲካል ፖሊሲዎችን አዘጋጅቶ ለተቋማት በጀት በመመደብ የፆታ እኩልነት እንዲሰፍን እየሠራ መሆኑን አሳውቀዋል።

በዩኤን ውመን የኢትዮጵያ ተወካይ ወይዘሮ ሴሲሌ መኩሩቡጋ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የኢኮኖሚ ዕድገትንና የፆታ እኩልነት ለማሳካት ሴቶች ከፋይናንሻል ዘርፉ ይበልጥ የሚሠሩበትን ዕድል መፍጠር ያስፈልጋል፡፡

በፋይናንስ ዘርፉ ላይ ያሉ የሥርዓተ ፆታ ፖሊሲዎችና የሕግ ማዕቀፎች ሴቶችን ያካተቱ እንዲሆን በማድረግ እንስቶች እራሳቸውን የሚችሉበት እንዲሁም በሀገሪቱ በኢኮኖሚ ላይ አስተዋፅዖ የሚያበረክቱበት አማራጭ ማስፋት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የሥርዓተ ጾታ ፖሊሲዎች የሴቶችን የፋይናንስ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ በተጨማሪ ገንዘብ ነክ ያልሆኑ አገልግሎቶችን ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ዕድል መፍጠር ያስፈልጋል ሲሉ አስረድተዋል። ይህም የግል ድርጅቶችም ተግባራዊ በሚያደርጉት መልኩ መዘጋጀት እንደሚገባው አንስተዋል፡፡

የጾታ እኩልነት ሳይሰፍን ሀገር የምትፈልገውን የዕድገት ደረጃ ላይ መድረስ አይቻልም ያሉት ወይዘሮ ሴሲሌ፤ ባለፉት ዓመታት ሴቶችን በፋይናንስ ዘርፉ በማሳተፍ ረገድ የተወሰኑ መሻሽሎች ቢኖሩም አሁንም ብዙ ክፍተቶች መኖራቸውን አመላክተዋል።

እንደሀገር በዘርፉ የአመለካከት ለውጥ በማምጣት ሴቶችን በኢኮኖሚ፣ በማኀበራዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች በይበልጥ ማሳተፍ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You