‹‹የቀላል ምግቦች አዘገጃጀት››

በብዙ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ስለምግብ አዘገጃጀት የሚሠሩ ፕሮግራሞችን አያለሁ። አንዳንዶቹ ቋሚ የምግብ አዘገጃጀት ፕሮግራም ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ ለሌላ ፕሮግራም ማድመቂያ የሚዘጋጁ ናቸው። መቼም የምግብ ነገር በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ያለ ነውና ምግብ ነክ ነገር መኖሩ ‹‹ለምን ይሆን?›› አያሰኝም። በተለይም እንግዳ የሚጋበዝባቸው አንዳንድ ፕሮግራሞች (በተለይም የመዝናኛ ፕሮግራሞች) ምግብ ሲዘጋጅ አያለሁ።

በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን አንድ የሚገርመኝ ነገር የሚዘጋጁት ምግቦች ናቸው። አብዛኞቹ ኢትዮጵያ ውስጥ የማውቃቸው አይነት አይደሉም። በብዙ ሰው ቤት ውስጥ የሚገኙ አይደሉም። ይህንን ስል ከራሴ ኑሮ ጋር አነፃፅሬ አይደለም። ከእኔ የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ባሉት ሰዎች ቤት ውስጥ ከማየው ጋር አነፃፅሬ ነው። በቴሌቪዥን ሲዘጋጁ የሚታዩ ምግቦች በብዛት በውጪው ዓለም የሚሠሩ እና በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች የሚኮረጁ ናቸው።

እዚህ ላይ ግን አንድ የማደንቀው ነገር አለ። ቋሚ የምግብ አዘገጃጀት ከሆኑት ፕሮግራሞች ይልቅ በተጋባዥ እንግዳ ፕሮግራሞች ላይ የሚታዩ የእግረ መንገድ የምግብ አዘገጃጀቶች ሀገርኛ ይዘት አላቸው። የሚታወቁ ምግቦች ናቸው። ከዚያ ውጭ ያሉት ግን ተጠቀሙ እያሉ የሚናገሯቸው ግብዓቶች ራሱ በብዙው ኢትዮጵያዊ ዘንድ የማይታወቁ ናቸው።

‹‹ቀላል የምግብ አዘገጃጀት››ተብለው የሚነገሩ አዘገጃጀቶች ቀላል የተባለው ምናቸው እንደሆነ አይገባኝም። የሚወስዱት ጊዜ ወይስ የሚጠቀሙት ግብዓት? ‹‹ማንኛውም ሰው በቤቱ የሚያገኛቸው…›› እያሉ ይናገራሉ፤ ኧረ ተዉ አንዳንድ ግብዓቶችን ማንኛውም ሰው ሊያገኛቸው አይችልም። እንዲያውም መባል የነበረበት ‹‹ሀብታም የሆነ ብቻ ሊያዘጋጀው የሚችል እና ድሃ ደግሞ በቴሌቪዥን እያየ ምራቁን የሚውጥበት የምግብ አዘገጃጀት›› ነው መባል ያለበት። እና ታዲያ ያ ምግብ በማንኛውም ሰው ቤት የሚዘጋጅ ነው?

የሆቴል ምግብ አዘገጃጀት የሚማሩ ተማሪዎች ላይ የሰማሁት አንድ ነገር አለ። የሚማሩት ትምህርት በውጭው ሥርዓተ ትምህርት የተቀረጸ ነው። የሀገር ውስጥ ምግቦች ራሱ መጠሪያቸው በውጭ ቋንቋ ነው። በዚያ ላይ የሀገራችን የባሕል ምግቦች በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ያላቸው ድርሻ በጣም ውስን ነው። እንደ ቂጣ፣ ጨጨብሳ፣ ፍርፍር ያሉ ምግቦች ዓለም አቀፍ ሆቴሎቻችን ውስጥ የሉም፤ ቢኖሩም እንደ ሌሎች የውጭ ምግቦች ታስቦባቸው የተሠሩ አይደሉም።

ምክንያታቸው ግልጽ ነው። የሚያዘጋጁት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለሆነ ነው። እንግዳ ማለት ግን የውጭ ሀገር ሰው ብቻ አይደለም፤ የሀገር ውስጥ ሰውም ዓለም አቀፍ ሆቴሎቻችን ውስጥ ያርፋል። ሲቀጥል ለውጭ አገር ሰዎች የሀገራችንን የባሕል ምግቦች ማስተዋወቅ ያለብን በእንዲህ አይነት ሆቴሎች ነው። ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ የመጣ እንግዳ የሀገሩን ምግብ ብቻ አይቶ የሚሄድ ከሆነ ምኑን ጎበኘው? እንዲያውም እዚህ ላይ አንድ የሰማሁት ገጠመኝ ነበር።

አንድ ፈረንጅ ነው አሉ። አንድ ምግብ ቤት ውስጥ ገባ። አስተናጋጇ መጥታ ‹‹ምን ልታዘዝ›› ስትለው ምን ምን እንዳለ ጠየቃት። እሷም በፈረንጅ አፍ የሚገቡትን ብቻ ዘረዘረች። ከዚያማ ፈረንጁ ስሙን ጠርቶ ‹‹ሽሮ የለም?›› አላት አሉ። ምናልባት ይሄ ፈረንጅ ሽሮ መብላት አስቦ ቢሆንስ የገባ? ባይሆን የፈረንጁንም የሐበሻውንም ዝርዝር ተናግሮ ምርጫውን ለእሱ መተው አይሻልም ነበር? እሷ ንቃ ያልጠራችውን ሽሮ ፈረንጁ ፈለገው ማለት ነው።

የምግብ አዘገጃጀት ፕሮግራሞች በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ያለውን የአሠራር መመሪያ ተከትለው ነው የሚናገሩት። ይህ ግን ከአብዛኛው የኢትዮጵያ ባሕላዊ የምግብ አዘገጃጀት ጋር አይሄድም። ምክንያቱም የኢትዮጵያ የባሕል ምግቦች በዘመናዊው ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ የሉም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን የሚያውቀው የራሱ ሀገር በቀል አሠራር እና ጣዕም የሆኑትን የባሕል ምግቦች ነው። ስለዚህ በቴሌቪዥን የሚነገሩ አሠራሮች ለፈረንጆቹ ይሆን? ከሐበሻ ተምረው ምግብ እንዲያዘጋጁ? በአማርኛ የሚተላለፈውን ፕሮግራም ወደ እንግሊዘኛ አስተርጉመው እንዲጠቀሙበት?

የፈረንጅ የምግብ አሠራሮች አይታወቁ ማለት አይደለም፤ ሐበሻ ሆኖ የፈረንጅ ምግብ የሚመገብ ይኖራል። ዳሩ ግን ለሀገር ውስጥ ማኅበረሰብ ከሆነ፣ የሀገር ውስጡን ማስቀደም አይሻልም ወይ? ቢያንስ እኩል ቢሄዱ።

እዚህ ላይ አንድ ነገር ይባል ይሆናል። የሐበሻ የምግብ አዘገጃጀት እንዴት ለራሱ ለሐበሻ ይነገረዋል? የሚል ጥያቄ ይነሳል። ዳሩ ግን የሰሜኑ ለደቡቡ፣ የምዕራቡ ለሥሥራቁ፣ የገጠሩ ለከተማው…. የተለያዩ ናቸው። ለምሳሌ ከሰሜን ወደ ደቡብ ወይም ከደቡብ ወደ ሰሜን የሄደ ሰው ‹‹እንዲህ የሚባል የበላሁት ምግብ…›› ብሎ ሊደነቅ ይችላል። ይህ ሰው በእንግድነት በሄደባቸው ቀናት የዚያን ምግብ አሠራር ሊያውቅ አይችልም። ስለዚህ በቴሌቪዥን ቢከታተል ሊያዘጋጀው ይችላል ማለት ነው።

ከከተማ ወደ ገጠር የሄዱ ሰዎች የገጠር ምግቦችን ቀምሰው ሊጣፍጣቸው ይችላል። ያንን ምግብ ማዘጋጀት ይፈልጋሉ። ስለዚህ በቴሌቪዥን ቢያገኙት ጥሩ ነበር ማለት ነው። እንዴት የገጠር ምግብ አዘገጃጀት የቴሌቪዥን ፕሮግራም ይሆናል? ይባል ይሆናል። ምግቡ ከተወደደ እና ሰዎች ከፈለጉት ምን ችግር አለው? ራሳቸው ያዘጋጁትን ሰዎች ሲያዘጋጁ በመቅረጽ ወይም የምግብ ባለሙያ የሆነ ሰው ሄዶ በመልመድ ቢያስተዋውቀው ምን ችግር አለው? የምግብ አዘገጃጀቱስ ከጤና አንፃር ቢጠና ምን ችግር አለው?

በነገራችን ላይ ዘመናዊ የተባሉትም ከልማድ ያደጉ ናቸው። ምናልባትም ዘመናዊ የተባሉት ለሐበሻ ሊሆን ይችላል። ለፈረንጆች ምናልባትም እንደ ኢትዮጵያ የባሕል ምግቦች የዕለት ከዕለት መደበኛ ምግብ ነው።

በዚህ በኩል ከዋናዎቹ የመገናኛ ብዙኃን ይልቅ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሳይሻሉ አልቀሩም። የየአካባቢውን ባሕላዊ ነገር ያሳያሉ። ስለአንድ ነገር አሠራር ለማወቅ ቴሌቪዥን ከመክፈት ይልቅ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ መክፈት የተሻለ ይሆናል ማለት ነው። በመሰረቱ ግን አገራዊ ነገሮች ላይ ማተኮር እና ማስተዋወቅ የነበረባቸው ከማኅበራዊ ገጾች ይልቅ ቴሌቪዥኖች መሆን ነበረባቸው።

አገር በቀል ነገሮችን ማስተዋወቅ ያለብን ለባሕል ምግቦች ብቻ አይደለም፤ ለሌሎችም ነገሮች ነው። ለምሳሌ፤ ግብርናን በተመለከተ የአርሶ አደሩ ልማዳዊ ዘዴዎች መጠናት አለባቸው። አዋጪ የሆነውን በመጠቀም፣ ስህተት የሆነውን ደግሞ ለማረም ያመቻል።

ሲጠቃለል፤ የምግብ አዘገጃጀት ፕሮግራሞቻችን ባሕላዊ የሆኑትን አገር በቀል አሠራሮችንም ቢያስተዋውቁ ተመልካች ያገኛሉ!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You