የትግራይ ክልልን ፖሊስ አቅም ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፡- የትግራይ ክልል ፖሊስ እና አመራሮችን አቅም በማሳደግና የኅብረተሰቡን የአገልግሎት ተደራሽነት ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማኅበር ጋር በመተባበር ‹‹በውጤታማ የፖሊስ አገልግሎት የአመራሩ ሚና›› በሚል መሪ ሐሳብ ለትግራይ ፖሊስ አመራሮች በተዘጋጀ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መርሐ ግብር ጀምሯል። ሥልጠናው ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ድረስ ያሉ የሥራ ኃላፊዎች የአመራር አቅም ማጎልበትና ፖሊስ ለኅብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ማቀላጠፍ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር እና ሥራ አመራር ኮሌጅ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ፈቃዱ ጌታቸው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ የፕሪቶሪያው ሥምምነት ከተፈረመበት ጊዜ ጀምሮ የፌደራል ተቋማት ለትግራይ ክልል በተለያዩ ዘርፎች ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን አስታውሰው፤ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲም በበኩሉ የሚቻለውን ሁሉ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

ከሰሜኑ ጦርነት ማግስት በፖሊስ አገልግሎት ዘርፍ የተፈጠሩ ክፍተቶችን ለማስተካከል ሲባል ዩኒቨርሲቲው በልዩ ትኩረት ለትግራይ ክልል ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡ የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሌጅን በሥልጠና በመደገፍና ለኮሌጁ በግብዓት የሚያገለግሉ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ድጋፍ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ኮማንደሩ ከሆነ፤ በአሁኑ ወቅት የሚሰጠው ሥልጠና የትግራይ ክልል ፖሊስ አመራር አቅምን የበለጠ ለማጎልበትና በጦርነቱ ሳቢያ የተፈጠሩ ክፍተቶችን ለማሟላት ያለመ ነው።

በተለይም ዘመናዊ የፖሊስ አመራር ብቃትና የመፈፀም አቅምን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትኩረት ያደረገ ሥልጠና መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አመራሮችም ሥልጠናዎችን በየደረጃው ለሚገኙ አባላት በማስተላለፍና በማሠልጠን የክልሉን ፖሊስ አቅም የበለጠ ለማጎልበት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የፖሊስ አገልግሎትን ተደራሽነትን በፍጥነትና ጥራት ለማከናወን ዓይነተኛ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመው፤ በቀጣይም መሰል ሥልጠናዎች እንደሚጠናከሩ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ድጋፍም እንደሚጎለብት ኮማንደር ፈቃዱ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቱ ዘመናዊ ፖሊስ ማደራጀት ከተጀመረ አራት ዓመት በኋላ ከ1939 ዓ.ም አባዲና ፖሊስ ኮሌጅ በሚል ስያሜ የተቋቋመ አንጋፋ ተቋም መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You