ባለሥልጣኑ በጤና ባለሙያዎች የሕክምና ስህተት ላይ ልዩ ቁጥጥር ሊያደርግ ነው

አዲስ አበባ፦ የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን በጤና ባለሙያዎች የሕክምና ስህተትና ሥነ ምግባር ላይ ልዩ የቁጥጥር ሥርዓት ሊያደርግ መሆኑን አስታወቀ።

ባለሥልጣኑ አዲስ መጠሪያ እና ሎጎ ባለድርሻ አካላት እና የሚመለከታቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች በተገኙበት ትናንት ይፋ አድርጓል። ከሎጎው ምርቃት በተጨማሪ በሕክምና ስህተት የሚመጡ አቤቱታዎች ላይ የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት አድርጓል።

የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሙሉ እመቤት ታደሰ በወቅቱ እንደተናገሩት፤በመንግሥትና በግል የጤና ተቋማት ላይ የሚፈጠሩ የሕክምና ስህተቶች ሕጋዊ መፍትሔ እንዲያገኙ በርካታ ሥራዎች ሲሠራ ቆይቷል፡፡ አሁን ባለሥልጣኑ በሚያደርገው የሪፎርም ሥራ ጉዳዩ በልዩ ትኩረት እንዲሠራ አቅጣጫ ተሰጥቷል። በዚህም በጤና ባለሙያዎች የሕክምና ስህተትና ሥነ ምግባር ላይ ልዩ የቁጥጥር ሥርዓት ሊደረግ ነው፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎች ከሕክምና ስህተቶችና ከባለሙያ ሥነ ምግባር ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ሲያጋጥሟቸው በነፃ የስልክ መስመር ቁጥር 8864 ላይ ጥቆማ ሊሰጡ ይገባል ያሉት ወይዘሮ ሙሉ እመቤት፤ ይህንን መብት ነዋሪዎች በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል ብለዋል።

በሌላ በኩል የሎጎና የስያሜ ለውጡ ስማርት ሲቲን የሚመጥን የምግብና መድኃኒት ደኅንነት ለማረጋገጥ ዓላማ ያለው የሪፎርም ሥራ ነው ያሉት ወይዘሮ ሙሉ እመቤት፤ ይህም የሕግ፣ የአደረጃጀት እና የዲጂታል ማሻሻያዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

ስማርት ሲቲን የሚመጥን የምግብ ደኅንነት ተቋም ማቅረብ የሚችል ባለሥልጣን ለመገንባት እየሠራ እንደሆነም ገልጸዋል።

የባለሥልጣኑን አዲስ ሎጎ በሚመለከት ማብራሪያ የሰጡት በባለሥልጣኑ የአገልግሎት አሰጣጥ ክትትል ድጋፍና ምዘና ዳይሬክተር አቶ መብራቱ ጣዕመ በበኩላቸው፤ የአዲሱ ሎጎው ይዘት፣ እሳቤና ፍልስፍና የዓለም አቀፍ ጤና ድርጅት መሠረታዊ ሰማያዊ ቀለም በመውሰድ የባለሥልጣኑ ተልዕኮና ስምሪት እንዲሁም መርሕ ከዓለም አቀፍ ጤና መርሆዎችና ደረጃዎች ላይ የተመሠረተ ነው ብለዋል።

ሎጎው ከኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴርና ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶች የተቆራኘ የኅብረቀለም ይዘት እንዲኖረው ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑን አመልክተው፤ ባለሥልጣኑ ተቆጣጣሪና እርምጃ የመውሰድ ሥልጣን ያለው መሆኑና የራሱ መለያ እንዲኖረው በማሰብ ደግሞ በቀጭኑ ቀይ ቀለም እንዲኖረው ተደርጎ ተዘጋጅቷል ነው ያሉት።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You